አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አረፉ

0
1192

ብፁዕነታቸው በጎንደር ክፍለ አገር በደብረ ታቦር አውራጃ አለታ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ ማር ምድር በሚባል ቦታ በ1930 ከአባታቸው ከብላታ ፈንታ ተሰማ እና ከእናታቸው ለምለም ገሰሰ ተወለዱ።
እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ገዳማትና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውረው የቤተክርስቲያን ትምህርት ተምረዋል። በኋላም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተለያዩ መንፈሳዊ ትምህርቶችን በማስተማርና የልማት ሥራዎችን በማስተባበር ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል።
ብፁዕነታቸው በ1961 ምንኩስና እንዲሁም ማዕረገ ቅስናን ከተቀበሉ ከአስር ዓመት በኋላ፣ ባላቸው በቂ የቤተክርስቲያን ዕውቀትና ባሳዩትም መልካም የመንፈሳዊ አገልግሎት ጥር 13/1971 በቅዱስ ሲኖዶስ፣ በካህናትና በምዕመናን ከፍተኛ ድምጽ ተመርጠው የኦጋዴን አውራጃ ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ተሹመዋል።
እንዲሁም፣ ነሐሴ 29/1980 ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ 4ኛ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ፓትርያርክ ሆነው ሲሾሙ፣ በፓለቲካዊ ጫና አገራቸውን ለቀው እስከሚወጡ ነሐሴ 28/1983 ድረስ ለቤተክርስቲያን አመራር ሲሰጡ ቀይተዋል።
ከ26 ዓመታት ስደት በኋላ ሐምሌ 25/2010 በድጋሜ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ሲሆን፣ ከተሾሙበት ነሐሴ 29/1980 ጀምሮ ላለፉት 34 ዓመታት በፓትርያርክነት አገልግለዋል። ሆኖም ባደረባቸው ህመም ሆስፒታል ገብተው በህክምና ሲረዱ ቆይተው፣ አርብ የካቲት 25/2014 አዲስ አበባ ውስጥ እንዳሉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሥርዓተ ቀብራቸው እሁድ መጋቢት 4 2014 በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይከናወናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here