በተፈጥሮ ለታደልናቸው አምስት የስሜት ሕዋሳት የምንሠጠው ትኩረት እንደሚለያይ ይታወቃል። እንደስራው ባህሪ ከሠው ሠው የበለጠ ጥቅም የሚሠጥ አካል ቢኖርም፣ ኹሉም ግን አስፈላጊና ጠቃሚ መሆናቸውን የሚክድ የለም። ያለምክንያት የተፈጠረ ነገር ስለሌለ የጤና ምርመራ በማድረግም ሆነ በመንከባከብ ሠውነታችንን መጠበቅ እንዳለብን የሕክምና እና የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች ሲናገሩ እንሠማለን።
ከሠውነት አካላችን ውስጥ ዐይን እንደብሌኔ እየተባለ ከኹሉም በላይ የሚሳሳለትን ያህል፣ ሌሎቹ ትኩረት ተደርጎላቸው እንክብካቤ ሲያገኙ አይታይም። አፍንጫ በተለያየ ምክንያት መተንፈስም ሆነ ማሽተት በሚሳነን ወቅት ጥቅሙን የምንረዳው ቢሆንም፣ ያን ያህል ክትትልና ትኩረት አያገኝም። “አፍንጫ ሲመታ ዐይን ያለቅሳል” እየተባለ ተያያዥነታቸው ቢገለጽም፣ እኩል እንደማታይ ግን መገመት ይቻላል። ምላስም ቢሆን ጥቅሙ ትልቅ የሆነ፣ የምንነጋገርበትና የምንቀምስበት ቢሆንም፣ ያን ያህል በጉዳት ስለማናጣው እንክብካቤ አናደርግለትም። ትኩስ ነገር ጠጥተን ከምንጎዳው ወይም ነክሰን ከምናቆስለው ሌላ ዕድሜልካችንን ከማገልገል ስለማይቦዝን የዓይንን ያህል ትኩረት ባንሠጠው ላይገርም ይችላል።
ስለእጅና ሌላው አካላችን ጥቅም ያን ያህል መነጋገር ባያስፈልግም፣ አጠቃላይ የጤናችንን ኹኔታ ለማወቅ ሳንታመም ሔደን የመመርመር አቅሙም ሆነ ልማዱ ስለሌለንና እስኪጎዳ ስለምንጠብቅ፣ ችግር ላይ ከወደቅን በኋላ ዘግይተን ወደሕክምና ተቋማት ልናመራ እንችላለን። ለምሳሌ፣ የጡት ካንሠርን በተመለከተ ሴቶች እራሳቸውን በየጊዜው እየፈተሹ ሥር ከመሥደዱና ለሕክምና ከማስቸገሩ በፊት ዕጢው ካለባቸው ወደሕክምና ተቋማት በቶሎ እንዲሔዱ ይመከራሉ።
በአገራችን ባለው የሕክምና አለመዘመን ወይም የአስተሳሰባችን አለመዳበር የተነሳ ለምርመራ ሆስፒታል የምንሔደው ሲያመን ብቻ መሆኑን ማንም የሚያውቀው ነው። በዚህ ምክንያት በቀላሉ ሊድኑ የሚችሉ በሽታዎች ተዘንግተው ሥር እየሠደዱ በጊዜ ባለመታወቃቸው ማኅበረሠቡን ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጋቸው ይነገራል።
ምንም እንደማይጎዳ በማሠብ ያለእንክብካቤ በየቀኑ ከምንጠቀምበት የአካላችን ክፍሎች መካከል ጆሯችን አንዱ ነው። ጆሮን ለማፅጃ በከተማ የእስኪርቢቶ ክዳን ጥቅም ላይ ከመዋሉ ውጭ በዘመናዊ መልክ የሚያሳጥብም ሆነ የሚያጸዳው እጅግ በጣም ትንሽ ቁጥር ያለው ሠው ነው። በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ግን፣ ከከተሜው በተሻለ ለጆሮ ማፅጃ የሚውል ማንኪያ የመሰለች አነስተኛ መጎርጎሪያ ስትሸጥ ይታያል። የጆሮ ታምቡርን የመጉዳቱ ኹኔታ በምርምር የታወቀ ባይሆንም፣ ከተሜው በተለምዶ ከሚጠቀምበት የእስኪርቢቶ ክዳን የተሻለ እንደሚሆን በኹለቱም ተጠቅሞ የሚያውቅ መናገር ይችላል።
ይህን ያህል ስለጆሮ ያነሳንላችሁ አብዛኞቻችን ካላመመን ወይም ውኃ ገብቶብን ለማፅዳት ካልፈለግን በስተቀር ምንም አይነት ትኩረት ስለማንሰጠው ስለጆሯችን የተሰራ ጥናት ይፋ መደረጉን ተከትሎ ነው። ከዕድሜ ጋር በተገናኘ ዐይንና ጆሮ እንደሚደክሙ ቢታወቅም፣ የዐይን ድካም ወዲያው ስለሚታወቅ አቅሙ ካለ ለመታከምም ሆነ ትኩረት አግኝቶ ለመንከባከብ ጊዜ እንደማይፈጅ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። ጆሮ ግን ቀስ በቀስ እየቀነሰ ድንገት የመስማት ዕድልን ስለሚያሳጣ የሚገባውን ትኩረት ሊነፈገው አይገባም።
በኒውዚላንድ በተካሄደ ጥናት ከዓለማችን ሰዎች ሩብ የሚሆኑት ከ30 ዓመት በኋላ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የመስማት አቅማቸው እንደሚቀንስ ለመገመት ተችሏል። ከእነሱም አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ምንም ዓይነት ሕክምናም ሆነ ቴክኖሎጂን ሳይጠቀሙ መስማት ሳይችሉ እንደሚቀሩ ተገምቷል።
የዓለም የመስማት ቀን “ተጠንቅቃችሁ ዕድሜ ልክ አድምጡ” የሚል ይዘት ባለው መሪ ቃል ባሳለፍነው ዕሮብ የካቲት 24 ታስቦ መዋሉን ተንተርሶ ተመራማሪዎቹ ይፋ ያደረጉት የጥናት ውጤት እንደሚያሳየው፣ ዕድሜ ልክ እያዳመጡ ደስተኛ ሆኖ ለመኖር ለጆሮ ከተለመደው በላይ እንክብካቤ እንደሚያስፈልግ ነው።
የጥናቱ ተሳታፊ ከነበሩ መስማት ከተሳናቸው የኒውዚላንድ ዜጎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት መስማት የሚያስችላቸው መሣሪያን አግኝተው ድጋሚ ማዳመጥ በመቻላቸው በሕይወታቸው መልሰው ደስተኛ ለመሆን ችለዋል። ሲሶ የሚሆኑት መስማት ባለመቻላቸው ምክንያት ተበላሽቶ የነበረው ማኅበራዊ ሕይወታቸው ከተናጋበት ሊመለስ መቻሉንም አሳውቀዋል።
ለናሙና ተመርጠው ጥያቄ ከቀረበላቸው መስማት ከሚችሉ ሰዎች ደግሞ 53 በመቶ የሚሆኑት የማድመጥ ችሎታቸው እንደቀነሰ ቢያምኑም ለምርመራ ወደጤና ተቋማት አምርተው አያውቁም። ለወደፊቱም ሔደው ያለበትን ደረጃ ለማወቅም ምንም ዕቅድ እንደሌላቸው ታውቋል። ሩብ የሚሆኑት ብቻ ሔደው ለመመርመር እንደሚያስቡ አመላክተዋል።
“ጆሯችሁን ውደዱ” በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርምር አድርገው ውጤቱን ይፋ ያደረጉት ተመራማሪዎች እንደተናገሩት፣ ጥሩ ሕይወትን ለመምራት ሠዎች በየጊዜው ጆሯቸውን እያስመረመሩ እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባቸው ነው።
በተለያዩ 14 አገራት የሚገኙ መስማት የተሳናቸውን ግለሰቦች ያካተተ ዓለም አቀፍ ጥናት የሚያመላክተው፣ መስማት ሳይችሉ ቀርተው በዘመናዊ ማዳመጫ ቴክኖሎጂ ማድመጥን መልሰው የቻሉ ጥቂቶች ብቻ እንደሆኑ ነው። እነዚህ ሕክምናን ተጠቅመው ወደማዳመጡ የተመለሱ ሠዎች ምንም መስማት ሳይችሉ ከቀሩት በላይ በሕይወታቸው በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ከሚናገሩት በላይ በኹኔታቸው መለየት እንደሚቻል ታውቋል።
የማዳመጫ መሣሪያን በጊዜ ተመርምረው እንዲጠቀሙ ከተደረጉት መካከል 41 በመቶ የሚሆኑት አስቀድሞ ከነበራቸው ሕይወት በተሻለ ኑሯቸውን እየመሩ እንደሆነ ተናግረዋል። ከእነሱ መካከል አንድ አራተኛ የሚሆኑት ሕይወታቸውን ሥር-ነቀል በሚባል መልኩ በከፍተኛ መጠን እንደቀየረላቸው ይመሰክራሉ።
ዕድሜ በገፋ ቁጥር ሠውን ከሚያሳስበው የማየትና የማስታወስ ችግር በተጨማሪ የመስማት ችግርም ብዙዎችን እንደሚያጠቃ ማወቅ ተችሏል። የማስታወስ ችግር ከሸመገሉ ሰዎች በ53 በመቶዎች ላይ እንደሚከሠት ጥናቶች የሚያመላክቱ ሲሆን፣ የመስማት ችግር ደግሞ በ45 በመቶዎቹ ላይ እንደሚከሰት ይገመታል። ይህ በኒውዚላድ ዜጎች ላይ የተመዘገበው አኃዝ ከዓለም አቀፉ መጠን ከፍተኛ ነው የተባለ ሲሆን፣ በዓለም ደረጃ 35 በመቶ አዛውንቶች ናቸው የመስማት ችሎታቸው ዕድሜያቸው በገፋ ቁጥር የሚቀንስባቸው።
ዕድሜያቸው ከገፋ ሰዎች የጆሮ ምርመራ ለማድረግ በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ የሚያቅዱት 25 በመቶ ያህሉ ሲሆኑ፣ የዐይን ምርመራ ለማድረግ በዚሁ ጊዜ ውስጥ የሚያስቡት ግን 39 በመቶ መሆናቸው ታውቋል።
ከኒውዚላን አዛውንቶች ማስታወስ የሚቸግራቸው 63 በመቶዎቹ ሲሆኑ፣ ከሽማግሌዎቹ 82 በመቶ የሚሆኑት የመርሳት በሽታ ከመስማት እክል ጋር ስላለው ቁርኝት ጭራሹኑ ምንም የማያውቁ ናቸው። ‹ዘ ላንሰንት› ላይ ከኹለት ዓመት በፊት የወጣ ሪፖርት እንዳመላከተው አንድ ሠው የመስማት ችግር ሲያጋጥመው የማስታወስ ብቃቱም እንደሚቀንስ ነው።
መስማት የተሳናቸው ሠዎች ኹልጊዜ በዕድሜያቸው መጨመር ብቻ ችግሩ የማይከሰትባቸው ሲሆን፣ በየጊዜው የሕክምና ተቋማት እየሄዱ በመመርመር ያለጊዜ የሚከሰተውን እክል ለማስቀረት ያግዛቸዋል። ችግሩ መከሰቱ የማይቀር ቢሆንም እንኳን፣ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የመስማት ችሎታን ወዲያው ለመመለስ መጣር ያስፈልጋል። በተለይ ከቤተሰብ ጋር ያለ ግንኙነት ከመሻከሩ በፊት ዕድሜያቸው የገፋ ሠዎች በአፋጣኝ የሕክምና ክትትል አድርገው ለችግሩ ዕልባት እንዲሠጡት ተመክረዋል።
ከመስማት ጋር በተገናኘ የሚፈጠር ዕክል በእርጅና ብቻ የሚከሰት እንዳልሆነ የጠቆሙት ተመራማሪዎች፣ ከልጅነት ጀምሮ ለጆሯችን እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ ይጠቁማሉ። ዐይናችንንም ሆነ ሌላ አካላችንን የምናፀዳውን ያህል፣ ጆሯችንንም ሹል ባልሆነ ነገር በየተወሰነ ጊዜው እንደሚያስፈልገው መጠን ማፅዳት እንዳለብንም ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪ፣ የጆሮ ማዳመጫ ኢር ፎንን ስንጠቀም ድምፁን ማጮህ እንደሌለብን እና የጆሮ ታንቡራችንን አላግባብ ማድከምና መጉዳት እንደሌለብን ምክራቸውን ይለግሳሉ።
በአጠቃላይ፣ ለጆሮ የምንሠጠው እንክብካቤ አናሳ ስለሆነ ጥንቃቄ ከማድረግ ጀምሮ ትኩረት በመስጠት ረገድ ከዐይናችን ለይተን ማየት የለብንም። አውዲካ (Audika) የተሠኘ የመስማት ቀንን ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር የሚያከብር ተቋም፣ 5 ደቂቃ የሚፈጅ የኦንላይን የጆሮ ምርመራ እንደሚያደርግ ይፋ ማድረጉንም ‹ስኩፕ› ድረገጽ ዘግቧል።
ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014



