-በኹለት ወር ተኩል ውስጥ መድረስ የሚችሉ ዝርያዎች ናቸው
የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በደብረ-ዘይት የእርሻ ምርምር ተቋም ውስጥ ከዓመታት በፊት ሲያደርገው በነበረው አዲስ ዘርን የማምረት ጥናትና ምርምር ሙከራ፣ ኢ. ኤም. ኤስ. የተሠኘ ኬሚካልን በመጠቀም አራት ዓይነት ምርጥ የጤፍ ዝርያዎች ማግኘቱን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ከተቋሙ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ፣ ከዚህ በፊት የኒኩሌር ጨረርን በመጠቀም የጤፍን ዘረመል በማሻሻል ከተለመደው የጤፍ ዘር ዓይነት የተሻሉ ምርጥ ዘሮችን ለማግኘት እየተሠራ የቆዬ ሲሆን፣ በምርምሩ መሠረትም አራት ምርጥ የጤፍ ዝርያዎች ተገኝተው ለአርሶ አደሮች መድረሳቸው ነው የተገለጸው።
የኢ. ኤም. ኤስ. ኬሚካልን በመጠቀም አራት የተሻሉ የጤፍ ምርጥ ዘር ዓይነቶች መገኘታቸውን ከተቋሙ ጋር በተመራማሪነት የሚሠሩት እና ሲውዘርላንድ ውስጥ በሚገኝው በርን ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ሳይንቲስትና ተመራማሪ የሆኑት ዘሪሁን ታደለ (ፕ/ር) ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
‹‹በአሁኑ ወቅት አራት ዓይነት የጤፍ ዝርያዎችን በደብረ ዘይት እርሻ ምርምር አውጥተናል›› ሲሉ ዘሪሁን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አዲስ የተገኙት የጤፍ ዝርያዎች ተስፋ፣ ኤባ፣ ቦራ እና ቦኒ የሚል ሥም እንደተሠጣቸው የገለጹት ዘሪሁን፣ የሥያሜያቸው መሠረትም “ቦኒ” እና “ቦራ” ድርቅን ከመቋቋም አንጻር ሲሆን፣ “ተስፋ” የተሠኘው የጤፍ ዘር ደግሞ ሥያሜውን ያገኘው በቢሾፍቱ ሙከራ እንዲያደርግበት ዘሩ ከተሰጠው አርሶ አደር ሥም በመነሳት ነው ብለዋል።
“ኤባ” የተሠኘው አዲስ የጤፍ ዘር ሥያሜ ደግሞ፣ የጤፍ ዝርያን በማግኘት በሚታወቀው ታደሰ ኤባ ሥም የተሠየም መሆኑን ተመራማሪው ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።
አዳዲስ ዝርያዎችን ማግኘት የተቻለው እንደ “ቆንጮ” እና “ኮራ”፣ እንዲሁም ሌሎች መሠል የጤፍ ዘሮችን በማዳቀል ሲሆን፣ ኢ.ኤም.ኤስ. የተሠኘው ኬሚካል ምርታቸው ከፍ ያለ፣ ቁመታቸው ያጠረ ወይም ረዥም ቢሆኑም እንዳይወድቁ ግንዳቸው የጠነከረ የጤፍ ዘሮችን ማግኘት አስችሏል ሲሉ ነው ተመራማሪው የገለጹት።
ዘሪሁን አያይዘውም፣ ነባሮቹ የጤፍ ዝርያዎች ቁመታቸው 30 ሳንቲ ሜትር ድረስ ሲሆኑ፣ በምርምር የተገኙት ግን ቁመታቸው ከ20 እስከ 25 ድረስ ነው። አዲሶቹ ዝርያዎች በቁመታቸው፣ በጥንካሬያቸውና ድርቅን መቋቋም በመቻላቸውም የተሻሉ ናቸውም ብለዋል።
አዲስ ከተገኙት ምርጥ የጤፍ ዘሮች መካከል “ቦራ” የተሠኘው ድርቅን የመቋቋም አቅም እንዳለው ተመራማሪው የገለጹ ሲሆን፣ ዝርያውም አለም ገና ውስጥ በሚገኘው የቦረና ወረዳ ሙከራ ተደርጎበታል ብለዋል።
በተያያዘም፣ “ቦኒ” ማለት ትርጓሜው የኮራ ማለት ሲሆን፣ ከቦራ በተመሳሳይ ድርቅን የመቋቋም አቅም እንዳለው እና በቢሸፍቱ አካባቢ ተዘርቶ እንደተሞከረም ዘሪሁን አክለው ተናግረዋል።
የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከዚህ በፊት አዲስ የጤፍ ዘርን ለማምረት ያቀደው የኒኩሌር ጨረርን በመጠቀም ሲሆን፣ አሁን ግን ከኑኩሌር ጨረሩ በተሻለ መልኩ በኬሚካሉ ምርጥ የጤፍ ዝርያን ማምረት እንደተቻለ ነው የተገለጸው።
ከኒኩሌር ጨረሩ በተሻለ መልኩ የጤፍ ዝርያን ማዳቀል ተችሏል የሚሉት ዘሪሁን፣ የጨረሩ ኃይል ዘሮቹ ላይ ጉዳት ያስከትላል ያሉ ሲሆን፣ ኬሚካሉ ግን ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት የለውም ነው ያሉት።
አርሶ አደሮች ገለባውን ስለሚፈልጉት ቁመታቸው ሊያጥሩ የሚችሉ ዘሮችን ብዙም ስላልወደዷቸው፣ ቁመታቸው ብዙም ሳያጥር ግንዳቸው ጠንካራ የሆኑ ዘሮችን ለማምረት በበርን ዩኒቨርስቲ ሮቦትን በመጠቀም ምርምር እያደረጉ መሆናቸውንም ተመራማሪው ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል፣ በአርሶ አደሩ እየተመረጠ ያለው ቶሎ የሚደርሱ የጤፍ ዝርያዎችን ነው ያሉት ዘሪሁን፣ የተለመዱት የጤፍ ዘሮች ለምርት የሚበቁት በሦስት ወር እንደሆነ ጠቁመው፣ አሁን ግን በኹለት ወር ተኩል ውስጥ መድረስ የሚችሉ ዘሮች ናቸው የተዳቀሉት ብለዋል።
የግብርና ኢንስቲትዩቱ ዘሮቹን በተለያዩ ቦታዎች ለአርሶ አደሩ እያከፋፈለ ነው የሚሉት ዘሪሁን፣ ለአብነትም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ተጉለትና ጅሩ፣ በምስራቅ ሸዋ ምንጃርና ሸንኮራ፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች አሠራጭተናል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ከሌሎች ሠብሎች በበለጠ የጤፍ ዘር ሦስት ሚሊዮን ሔክታር በመሸፈን ከፍተኛውን ቦታ እንደሚይዝና፣ 4.7 ሚሊዮን አርሶ አደሮች እንደሚያበቅሉት ይነገራል።
ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014



