ፍርድ ቤቱ የትግራይ ህዝብ ሀብት የሆኑት ድርጅቶችን የውርስ ትዛዝ ለማሰጠት ታስቦ በሚደረግ ሂደት ላይ ክርክር ሳይደረግ በሌሉበት የሚል ትዛዝ እንዳይሰጥ ተጠየቀ

0
1449
ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎች የትግራይ ህዝብ ሀብት የሆኑት ድርጅቶችን የውርስ ትዛዝ ለማሰጠት ታስቦ በሚደረግ ሂደት ላይ ክርክር ሳይደረግ በሌሉበት የሚል ትዛዝ እንዳይሰጥ ተጠየቀ።
በዛሬው ዕለት በእነ ዶ/ር ደብረጺሆን ገ/ሚካኤል የክስ መዝገብ የተካተቱ ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ፣ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ዶ/ር አብርሐም ተከስተ፣ ዶ/ር ረዳይ በርሔ እና ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔን ጨምሮ በማረሚያ ቤት የሚገኙች 20 ተከሳሾች በችሎት ተገኝተዋል።
በባለፈው ቀጠሮ ችሎቱ ላልቀረቡት ለዶ/ደብረጺኦን ገ/ሚካኤል እና ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ለሌሎችም ተከሳሽ ግለሰቦች እና አራት ድርጅቶች በተመለከተ ፖሊስ መጥሪያ እንዲያደርስ የሰጠውን ትዛዝ ውጤት ለመጠባበቅ ዕረፋድ 4:06 ላይ ተሰይሟል።
ከሳሽ ዓቃቢህግ በሰዓቱ ችሎት ባለመገኘቱ ምክንያት ዳኞቹ በቢሮ በመቀመጥ መጠበቃቸውን በመጥቀስ ዓቃቢህግ በቀጣይ በሰዓቱ ችሎት እንዲገኝ አሳስበዋል።
የፌደራል ፖሊስ ጉዳይ አስፈጻሚ ዋና ሳጅን ጌታቸው ውብሸት የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉዳይ እያስፈጸሙ መሆኑን እና የሰው ሀይል ዕጥረት እንዳለ ጠቅሰው ዘግይተው ችሎት የተገኙበትን ምክንያት ያብራሩ ቢሆንም ችሎቱ ሥራውን አቋርጦ መጠባበቅ እንደሌለበት አስተያየት ሰቷቸዋል።
ይሁን እና ተከሳሽ ግለሰቦችም ሆነ ለድርጅቶቹ መጥሪያ እንዲያደርስ የታዘዘው ፌደራል ፖሊስ የድርጅቶቹን የመኖሪያ አድራሻ ባለመጻፉ አድራሻቸውን ማግኘት አለመቻሉን በመጥቀስ ብቻ የግለሰቦችን የመጥሪያ ውጤት ሳያካትት በጽሁፍ ምላሽ ሰቷል።
የተከሳሽ ጠበቆች ዘራይ ወልደሰንበት እና ሀፍቶም ተከስተ በበኩላቸው ከሳሽ ዓቃቢህግ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ የትራንዝ ኢትዮጲያ፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል እና ሱር ኮንስትራክሽን ድርጅቶችን የሚያስተዳደር አካል ለማሾም አመልክቶ፤ ኮሜርሻል ኖሚስ በበላይነት እያስተዳደረው እንደሚገኝና የሰራተኞች ደሞዝን በጠቅላይ ዓቃቢህግ ማመልከቻ እንደሚከፈላቸው አብራርተዋል።
ይህ በሆነበት እና አድራሻቸው አዲስ አበባ መሆኑ እየታወቀ አድራሻ አላውቅም መባሉ በራሱ ፖሊስ ትኩረት ሰጥቶ ሥራውን አለመስራቱን የሚያሳይ ነው ሲሉ ጠበቃ ዘራይ አስተያየት ሰተዋል።
በተጨማሪም በፍታብሔርም ሆነ በወንጀል ሥነ ሥርዓት ህጉ መጥሪያ የሚያደርስ አካልን የሚመርጠው ፍርድ ቤቱ በመሆኑ፤ ከተፈቀደልን መጥሪያውን እኛ በቀጥታ ማድረስ እንችላለን ሲሉ ጠበቃ ዘራይ ወ/ሰንበት መጥሪያውን ለማድረስ ፍቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህ መልኩ የትግራይ ህዝብ ሀብት የሆኑት ድርጅቶች የውርስ ትዛዝ ለማሰጠት ታስቦ ነው ይህ የሚደረገው ክርክር ሳይደረግበት በሌሉበት የሚል ትዛዝ ሊሰጥ እንደማይገባ ጠበቃ ሀፍቶም ጠይቀዋል።
ከሳሽ ዓቃቢህግም በበኩሉ የድርጅቶቹን አድራሻ አናውቅም ጠበቆቹ በትብብር ስልካቸውን ወይም አድራሻቸውን ከሰጡን አፈላልገን መጥሪያውን እናደርሳለን ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱ የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ሀላፊ ችሎት ቀርበው የድርጅቶቹን አድራሻ ማግኘት ያልቻሉበትን እና ለግለሰብ ተከሳሾች መጥሪያ ውጤትን ያላቀረቡበትን ምክንያት እንዲያብራሩ ለመጋቢት 1 ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች።
በባለፈው ቀጠሮ የተከሳሽ ጠበቆች ባቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያና ህገመንግስትዊ ትርጉም የሚየስፈልጉ ጥያቄዎች ላይ ቀጠሮ እስኪሰጠው ድረስ ዓቃቢህግ መልስ እንዲያዘጋጅ ታዟል።
በሌላ በኩል 4 ተከሳሾች ከዚህ ቀደም በጊዜ ቀጠሮ የተፈቀደላቸውና በቀዳሚ ምርመራ መዝገብ የታገደባቸው የዋስትና ብር እንዲመለስላቸው ዛሬ በጽሁፍ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ በቀጣይ ቀጠሮ ትዛዝ እንደሚሰጥ ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here