”የሸገር ዳቦ ከነገ ጀምሮ ዳግም ለገበያ ይቀርባል”:-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

0
1457

በከተማዋ ከ2 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት እየተሰራጨ እንደሚገኝም ተናግረዋል

ዕረቡ የካቲት 30 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የሸገር ዳቦ ምርት ከነገ ጀምሮም ዳግም ወደ ገበያ የሚወጣ በመሆኑ ህብረተሰቡ ዳቦው በሚሰራጭባቸው ማዕከላት ማግኘት እንደሚችል የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

በዋጋ ጭማሪና በኑሮ ውድነት ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ የምግብ ፍጆታዎች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን ሲሉም ገልፀዋል።

በተለይም በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ በመንግስት ድጎማ እየተሰራጨ ያለውን የምግብ ዘይትና ዳቦ በተመለከተ ልዩ ትኩረት ሰጥተናል ነው ያሉት ከንቲባዋ።

የምግብ ዘይት በህገወጥ ክምችት የተገኘውንም ጨምሮ በተለያዩ አቅራቢዎችም እንዲቀርብ በማድረግ ለጊዜው ከ2 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት እየተሰራጨ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የከተማዋ ነዋሪ በተለይም በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ግለሰቦች በየአካባቢያቸው ወደሚገኙ የሸማች ሱቆች በመሄድ ምርቶቹን ማግኘት እንደሚችሉም አስታውቀዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሸገር ዳቦን በተመለከተ ፋብሪካው በእድሳትና በወቅቱ የስንዴ ዋጋ ንረት ምክንያት ለጊዜው ማምረት አቁሞ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ለሸገር ዳቦ 613 ሚሊዮን ብር ድጎማ በማድረግ፣ እንዲሁም በ198 ሚሊዮን ብር ለስንዴ አቅርቦት በድምሩ 812 ሚሊዮን ብር በመመደብ የዳቦ ምርት ማስጀመር መቻሉንም ገልፀዋል፡፡

ከነገ ጀምሮም ምርቱ ወደ ገበያ የሚወጣ በመሆኑ ህብረተሰቡ የሸገር ዳቦ በሚሰራጭባቸው ማዕከላት ዳቦ ማግኘት እንደሚችልም አስታውቀዋል።

ነገር ግን እነዚህ ምርቶች ዝቅተኛውንና በተለይም ቅድሚያ ወደሚሰጠው ህዝብ በሚፈለገው ደረጃ መድረስ ላይ እጥረቶች እንዳሉ ይታወቃል ያሉት ከንቲባዋ፤ ይህንንም ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ የጀመረው ቁጥጥር ቢኖርም ነገር ግን ህዝቡ በተለይም የዳቦ በመንግስት ከፍተኛ ድጎማ እየቀረበ ሳለ የተሻለ ገቢ ያላቸው የንግድ ድርጅቶችና ባለሃብቶች ምርቱን ወስደው የሚያተርፉበት ሁኔታ እንዳለ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ገልፀዋል፡፡

ህብረተሰቡ ይህንን ሁኔታ በመጠቆምም፣ በማጋለጥም፣ በመቆጣጠርም በኩል ድርሻውን እንዲወጣ ከንቲባ አዳነች ጥሪ አቅርበዋል።

የከተማችን የንግዱ ማህበረሰብም በመተሳሰብ ለጊዜው ትርፋችሁን ቀንሳችሁ ህዝባችሁን ታተርፋ ዘንድ በአክብሮት ጥሪ እናቀርብላቹሃለን ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here