ሐሙስ መጋቢት 1 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ)የንግድ ህጉን በመተላለፍ 39 በርሜል ነዳጅ በህገ ወጥ መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ ከተማ ለማጓጓዝ የሞከሩ ግለሰቦች በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ።
የካቲት 27 ቀን 2014 ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ገርጂ ማርያም አካባቢ ከሚገኝ ኖክ ፈጣን ነዳጅ ማደያ በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 A 10734 አ/አ በሆነ ኤፍ ኤስ አር ተሽከርካሪ 39 በርሜል ነዳጅ በመቅዳት ጭነው ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ ከተማ ሲያጓጉዙ የተገኙ ኹለት ግለሰቦችና ሁለት የማደያው ሰራተኞች ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ተይዘዋል፡፡
ፖሊስ ከህብረተሰቡ የደረሰውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ በተወሰደ እርምጃ 50 በርሜል ተዘጋጅቶ ሰላሳ ዘጠኝ በርሜል ናፍጣ ተቀድቶ የተያዘ ሲሆን፤ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን እና የተያዘው ነዳጅ 7 ሺህ 800 ሊትር መሆኑን ተረግጧል፡፡
ግለሰቦቹ መመሪያ ቁጥር 12/2011 አንቀፅ 14 ንዑስ አንቀፅ 16 ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ምንም አይነት ህጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው ነዳጁን ለማጓጓዝ ሲሞክሩ መያዛቸውን ነው ፖሊስ ያስታወቀው።
ህገወጦቹ በህብረተሰቡ ጥቆማ መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልፆ፤ መሰል ድርጊቶች ሲያጋጥሙ ጥቆማ የመስጠት ልምዱን አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ከአገር ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም የሚንቀሳቀሱ አካላት እና በህጋዊ የንግድ ፍቃድ ሽፋን ህገወጥ ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ከህገወጥ ተግባራቸው ሊታቀቡ እንዲሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል።
_________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n






