በቦሌ አየር ማረፊያ የሚደረገው የኮቪድ19 ምርመራ አወዛጋቢ ሆኖ ቀጥሏል

Views: 3997

በቦሌ ዓለም ዐቀፍ አየር ማረፊያ ለኮሮና ቫይረስ የሚደረገው ምርመራ አጥጋቢ አለመሆኑን በአየር መንገዱ አገልግሎት የሚያገኙ ተጓዦች ገለፁ።
ሥማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ ከቀናት በፊት የመጡ ተጓዦች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በአየር መንገዱ የሙቀት ምርመራ ለማከናወን ረዥም ሰልፍ ሲጠባበቁ ከቆዩ በኋላ በአየር መንገድ የቫይረሱን ምርመራ የሚያከናውኑ ባለሙያዎች የተሰለፉትን ሰዎች የመጡበትን አገር እየጠየቁ እንዲያለፉ ሲያደረጉ ተመልክተዋል።

አክለውም ቫይረሱ በወቅቱ ከደቡብ አፍሪካም ጭምር መስፋፋት የጀመረበት ወቅት እንደነበር የጠቆሙ ሲሆን፣ በባለሙያዎቹ ድርጊት መደናገጥ ውስጥ ገብተው እንደነበር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ምርመራው በትኩረት ሲሰጥ የነበረው ከ8 አገራት ለሚመጡ ተጓዦች ብቻ እንደነበር የሚገልፁት የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮና ቫይረስ ቅድመ ዝግጅት እና ምላሽ አስተባባሪ ዘውዱ አሰፋ ናቸው።

ከቫይረሱ በቻይና መከሰት በኋላም ቻይና ጨምሮ ቫይረሱ ከተስፋፋባቻው ጣሊያን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ኢራን፣ ጃፓን ጀርመን እና ዱባይ የሚመጡ ተጓዦች ላይ ትኩረት ተደርጎ ምርመራ ሲደረግ እንደነበር ዘውዱ ገልፀዋል።

ከእነዚህ አገራት የሚመጡ ተጓዦችን ፓስፖርት በመመልከት ልዩ ትኩረት ተደርጎባቸው የሰውነት ሙቀት ምርመራ ሲደረግባቸው ቆይቷል ያሉት ዘውዱ፣ ከሌሎች አገራት የሚመጡ ተጓዦችን ግን በጅምላ ማስተር ቴርሞ ስካነር በተሰኘ መሣሪያ የሙቀት ልየታ ሲደረግባቸው ቆይቷል ብለዋል።

የቫይረሱ መከሰት ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ ከ300 ሺሕ በላይ ሰዎች የሙቀት ልየታ የተደረገባቸው ሲሆን፣ ዘጠኝ ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ተመዝግበው የመጡበት አገር ፓስፖርት ታይቶ ፎርም እንዲሞሉ እና የይለፍ ፍቃድ እንዲሰጣቸው መደረጉን ዘውዱ ተናግረዋል።

ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ ከሁሉም አገራት የሚመጡ ተጓዦች ላይ ጥብቅ ምርመራ እየተደረገ ይገኛል ሲሉ ጠቅሰዋል። አሁን የሚነሱት ጥያቄዎች ተጓዦች ማስተር ቴርሞ ስካነር የሚደረገውን የሰውነት ሙቀት ልየታ ልብ ባለማለታቸው የመጣ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በቫይረሱ የመዛመት ባህሪ ምክንያት በኢትዮጵያ በበሽታው የተለከፉ ሰዎች ቁጥር አሁን ካለበትም ከፍ ሊል እንደሚችል የጠቆሙት ዘውዱ፣ ኢንስቲትዩቱ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች የቫይረሱን ምልክት ሊያሳዩ ስለሚችሉ በለይቶ ማቆያ ክትትል ማድረጉን ይቀጥላል ብለዋል።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባባር በቦሌ ዓለም ዐቀፍ አየር ማረፊያ እና በክልሎች በሚስተናገዱ ተጓዦች ላይ ጥብቅ ክትትል እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሔኖክ ሲራክ በበኩላቸው፣ አየር መንገዱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በዓለም ዓቀፉ የጤና ድርጅት መመዘኛ መሰረት በተለያዩ መንገዶች ጥብቅ ምርመራ በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

አየር መንገዱ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትንም ሆነ አዲስ አበባን እንደ መተላለፊያ የሚጠቀሙ የሌሎች አገራት ዜጎች የቫይረሱን ምርመራ ለማድረግ በተቀናጀ መልኩ እየተሠራ ይገኛል ሲሉ ቅሬታውን አስተባብለዋል።

መንግሥት ከፍተኛ የሰዎች እንቅስቃሴ የሚስተዋልባቸውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች፣ ስብሰባዎች ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆሙ ያደረገ ሲሆን፣ ትምህርት ቤቶች ለኹለት ተከታታይ ሳምንታት ዝግ ሆነው እንዲቆዩ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር እየሠራ ይገኛል።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com