በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የዜጎች ሞትና መፈናቀል፣ ገዥው ፓርቲ ብልጽግና ማስቆም ባለመቻሉ ከተለያዩ አካላት ትችት እያስተናገደ ነው። ፓርቲው የመንግሥትነት ኃላፊነቱን አልተወጣም የሚለው ትችት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ቢሄድም፣ የዜጎችን ሞትና ማፈናቀል እስካሁን ማስቆም አልተቻለም።
ከኹለት ዐሥርት ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን የመራውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢሕአዴግ)፣ አፍርሶ ብልጽግና ፓርቲን የመሰረተው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ይሁን እንጂ ችግሮቹ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሱ መሄዳቸውን ተከትሎ “መንግሥት ለዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ዋስትና ከመስጠት ይልቅ፣ ቁሳዊ ልማት ላይ ተጠምዷል” የሚሉ ትችቶች ከተለያዩ ወገኖች ይቀርብበታል።
ብልጽግና ኢትዮጵያን መምራት ከጀመረ ኹለት ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም፣ በኢሕአዴግ የአስተዳደር ጊዜ የነበሩትን ችግሮች ማስቀረት እንደተሳነው ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ምሁራን እየገለጹ ነው። ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የብልጽግና መንገድ ከችግር የሚያወጣ አለመሆኑን የፖለቲካ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። የብልጽግና መንገድና መሬት ያለውን እውነታ የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ በማንሳትና የፖለቲካ ባለሙያዎችን በማነጋገር ጉዳዩን የሐተታ ርዕሰ ጉዳይ አድጎታል።
ኢትዮጵያን እየመራ የሚገኘው ብልጽግና ፓርቲ አገሪቱን ለ27 ዓመት ከመራው የኢትዮጰያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር(ኢሕአዴግ) መፍረስ በኋላ የተፈጠረ ነው። ፓርቲው ኢሕአዴግን የመሠረቱ የክልል ፓርቲዎች ፈርሰው የተመሠረተ ሲሆን፣ ተቆራርጦ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ አሸናፊ ሆኖ ባለፈው መስከረም መንግሥት መሥርቶ ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ነው።
ፓርቲው የክልል ፓርቲዎችንና ኢሕአዴግን አክስሞ የተመሠረተ ቢሆንም፣ በየክልሉ ያሉ ፓርቲዎች የብልጽግና ፓርቲ ተብለው እንደቀጠሉ ናቸው። እነዚህ የየክልሉ ብልጽግና ፓርቲዎች በተለያዩ ጊዜያት እርስ በርሳቸው የሚያደርጓቸው መወራረፎች “ብልጽግና የሥም እንጅ የተግባር አንድነት የለውም” የሚሉ ትችቶች ለማሰስተናገድ በር መክፈቱ የሚታወስ ነው።
ብልጽግና በምርጫ አሸንፎ ኢትዮጵያን መምራት የጀመረው ከመስከርም 2014 ወዲህ ይሁን እንጂ፣ ኢሕአዴግን አክስሞ ኢትዮጵያን መምራት ከጀመረ ከኹለት ዓመት በላይ አስቆጥሯል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጠንሳሽነት ኢሕአዴግን አክስሞ በምትኩ የተመሠረተው ብልጽግና “የኢትዮጵያን ብልጽግና አረጋግጣለሁ” እያለ ቢናገርም፣ “የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ቀርቶ፣ የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማስከበር አልቻልም” በሚል ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ትችት እየበረታበት ነው። በእርግጥም ብልጽግና የመሪነት መንበሩን ከኢሕአድግ ከተረከበበት ጊዜ በኋላ በኢትዮጵያ የሚታዩ ችግሮች መፍትሔ ያገኛሉ ተብሎ ቢታሰብም ተባብሰው ቀጥለዋል።
የኢሕአዴግን የመሪነት ጉዞ አምርሮ በመውቀስ የሚታወቀው የአሁኑ የብልጽግና መንግሥት፣ በቀደመው የመንግሥት ሥርዓት በተፈጠሩ ችግሮች ላይ የተፈጠረ መሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ። የጠቅላይ ሚኒስተሩ ብልጽግና ኢትዮጵያ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ በገባችበት ጊዜ ቢመጣም፣ ችግሮችን ማስቀረቱ ቀርቶ እንዳይባባሱ ማድረግ ነበረበት የሚሉ ትችቶች እንደቀጠሉ ናቸው።
አገርን እንደሚመራ ፓርቲ መሥራት ያለበትን ያክል መሥራት አልቻለም የሚል ትችት የበረታበት ብልጽግና፣ የመጀመሪያ ጉባኤውን “ከፈተና ወደ ልዕልና” በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት ኹለት እስከ መጋቢት 4/2014 እያካሄደ ነው። ፓርቲው ኢትዮጵያን የሚመራ መንግሥት እንደመሆኑ የሕዝቡን የሠላም ዕጦት፣ የኑሮ ውድነትና በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች ላይ የሚታዩ ብልሹ አሠራሮችን ማስቀረት አለመቻሉ በተደጋጋሚ እየተገለጸ ነው።
የብልጽግና ውልደት
የብልጽግና ፓርቲ ውልደቱ የተጠነሰሰው በወቅቱ ራሱን “የለውጥ ኃይል” ብሎ የሚጠራው በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ከኹለት አስር ዓመት በላይ በመራው ኢሕአዴግ ሥርዓት ላይ የቀጠለ ፓርቲ ነበር።
በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የሕዝብ ተቃውሞ ተከትሎ በፈቃዳቸው ሥልጣን የለቀቁትን የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝን ተከተው መጋቢት 24/2010 ወደ ሥልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ፣ ፓርቲውን የመሠረቱት የየክልሎቹን ፓርቲዎች በማዋኃድ ነበር።
የየክልሎቹን ፓርቲዎች አዋኅዶ አንድ ወጥ ፓርቲ የመመሥረት ሒደቱ፣ በወቅቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ጋር ቅራኔ ውስጥ ከገባው ከሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ሕወሓት) ውጭ የኹሉም ክልል ፓርቲዎች ተስማምተው ነበር።
በወቅቱ ኅዳር 6/2012 የኢሕአዴግ ሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ ተሰብስቦ ውኅደቱን በ27 አብላጫና በስድስት የተቃውሞ ድምፅ ነበር ያጸደቀው። ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው “ብልጽግና ፓርቲ” የሚለውን ሥያሜ ለኢሕአዴግ ምክር ቤት አቅርቦ፣ ኅዳር 11/2012 ምክር ቤት ውኅደቱን ከሕወሓት ውጭ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ።
የክልል ፓርቲዎች ተዋኅደው የተመሠረተው የወቅቱ አዲሱ ፓርቲ፣ “እህት” እና “አጋር” ተብለው ይጠሩ የነበሩ የክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች በይፋ ከስመው መዋኃዳቸውን ገልፆ ነበር። በወቅቱ የክልል ፓርቲዎች በይፋ ብልጽግና መሆናቸውን ሲገልጹ፣ ሕወሓት የኢሕአዴግን መክሰምና የብልጽግናን ውልደት አጥብቆ ሲቃወም ነበር።
“አጋር” እና “እህት” በመባል ይታወቁ የነበሩት የክልል ፓርቲዎች በየተራ ብልጽግና መሆናቸውን በይፋ መግለጫ ማረጋገጣቸውን ተከትሎ፣ ኅዳር 20/2012 ፓርቲውን የተቀላቀሉ ፓርቲዎች የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች በተገኙበት የብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ስብሰባ ተካሔደ።
ፓርቲውን የተቀላቀሉ ድርጅቶች ኅዳር 21/2012 ይፋዊ የስምምነት የፊርማ ሥነ-ሥርዓት አዲስ አበባ ላይ ካካሔዱ በኋላ፣ ብልጽግና ፓርቲ በይፋ ተመሠረተ። ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረበለትን የኢሕአዴግ ክስመትና የብልጽግና ፓርቲን ውልደት አጸደቀ።
ኢሕአዴግን አክስሞ ብልጽግናን የመመስረት ሒደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ “የለውጥ ኃይል” ነኝ የሚለው የዐቢይ አስተዳደር፣ ከሕወሓት ጋር የገባበት ዕሰጥ አገባ እየተባባሰ መምጣቱ የሚታወስ ነው። ቀድመው የተፈጠሩ ቅራኔዎች ከብልጽግና ውልደት ጋር ተዳምረው ሕወሓት እና ፌዴራል መንግሥት በጎሪጥ እየተያዩ ትካሻ መለካካታቸውን ቀጠሉ።
ኹለቱ ኃይሎች፣ ቅራኔያቸው እየተባባሰ ሔዶ ጦርነቱ እስከፈነዳበት ጥቅምት 24/2013 ድረስ፣ በከረረ የቃላት ጦርነት ውስጥ ቆይተዋል። የሰሜኑ ጦርነት ከፈነዳ በኋላ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የነበረው ጸብ በተለይ የትግራይ፣ የአማራና የአፋር ሕዝቦች የጦርነት ገፈት ቀማሽ እንዲሆኑ ምክንያት ሆኖ አሁንም እንደቀጠለ ነው።
የብልጽግና መንገድ
የብልጽግና መንገድ ከጅምሩ ቅጥ ያጣውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ መስመር ፈር ያስይዛል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። በወቅቱ ተስፋ እንዲጣልበት ያደረገው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር አዲስ የለውጥ መንገድ ለመከተል የሚያደርገው ሙከራ የኢትዮጵያ ችግር ያቃልላል ተብሎ የታምነበት በመሆኑ ነበር ።
ብልጽግና መጀመሪያ የተጓዘበት መንገድ በሐሳብ ደረጃ ጥሩ እንደነበረ ብዙዎች ያምናሉ። ይሁን እንጂ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የነበሩት ተስፋዎችና መልካም ጅማሮዎች እየከሠሙ ወደ ቀድሞው ሥርዓት የመመለስ ዝንባሌዎች እየታየ መምጣቱን ብዙዎች ይገልጻሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት በወቅቱ በየመድረኩ ይቀነቀን የነበረው የለውጥ ሐሳብ በተግባር አለመታየቱና የኢትዮጵያ ችግሮች ተባሰው መቀጠላቸውን ነው።
የገዥው ፓርቲ ብልጽግና አስተዳደር፣ የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር የሆነውን የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማረጋገጥ አለመቻሉን ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ሠብዓዊ መብት ተቋማት እያስተጋቡ ነው። በተለያዩ አካባቢዎች በየጊዜው የሚሞቱ ዜጎችን ሕይወት መታደግ ባለመቻሉ የበረታ ትችት የሚቀርብበት ብልጽግና አሁንም የዜጎችን ሞት ማስቀረት አልቻለም።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ(ኢሰመጉ)፣ መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማረጋገጥ አለመቻሉን በመጥቀስ ቀዳሚ ኃላፊነቱን እንዲወጣ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን ጨምሮ፣ ፓርቲዎች በየግላቸው የብልጽግናን መንገድ እየተቹ ነው። የፓርቲዎች የጋር ምክር ቤት መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማረጋገጥ አለመቻሉን በተደጋጋሚ መግለጹ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) እና እናት ፓርቲ በቅርቡ መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማረጋገጥ አለመቻሉን ባወጡት መግለጫ ማረጋገጣቸው የሚታወስ ነው። ኢዜማ ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጉዳይ ላይ በሠጠው መግለጫ፣ የብልጽግና መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብትና የአገርን ሠላም ማስከበር ተስኖታል ብሏል።
እናት ፓርቲ በበኩሉ፣ በዚሁ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ “መንግሥት ዕልቂቱን አስቁም ሲባል ዕልቂት እያለማመደን በመሆኑ ሕዝብ አማራጭ ለመፈለግ ይገደዳል” ማለቱ የሚታወስ ነው። ፓርቲው እስከአሁን መንግሥት የተሠጠውን ኃላፊነት በውል እንዲወጣ መወትወቱን የገለጸ ሲሆን፣ “መንግሥት የተጠለፉ ሕጻናትን ከማፈላለግ ዳተኝነት ጀምሮ፣ ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው የምዕራብ ኦሮሚያ ወረዳዎች በቁጥጥር ሲውሉ ዝምታን ነው የመረጠው” ብሏል።
መንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነቱን የሕዝብን ደኅንነት መጠበቅና ማስጠበቅ በአግባቡ ስላልተወጣ፣ ሕዝቡ ተደራጅቶ “የሚሞቱ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ለማዳን መንቀሳቀስ የሞራል ሆነ ኃይማኖታዊ ግዴታው ነው” ብሏል።
የእናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ጌትነት ወርቁ “የብልጽግና መንገድ በጎም መጥፎም ነገሮች የታዩበት ጉዞ ነው” ይላሉ። ከበጎ ብለው ከሚጠቅሱት መካከል ለተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሥልጣን ማጋራቱ፣ የልማት ፕሮጀክቶችን ማከናወኑና ሠዎችን ከዕስር መፍታቱ ነው።
በሌላ በኩል፣ የብልጽግና ዋናው ችግር ተቋም መሆን አለመቻሉ መሆኑን ይጠቅሳሉ። “አሁን ከሚታየው የብልጽግና መንገድ በጎ ነገር መፈለግ እንጅ ችግሩን መናገር ቀላል ነው” የሚሉት ጌትነት፣ ቢሮ ቀለም ከመቀባት በላይ የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማረጋገጥ ያልቻለ ነው ብለውታል።
ገዥው ፓርቲ የሚባለው ብልጽግና፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን ከባለሥልጣናት ግለሰባዊ ብልጽግና የዘለለ ነገር እንዳልታየበት ጠቁመዋል። “አገር በብልጽግና እጅ ላይ ናት” የሚሉት ጌትነት፣ ሕዝብ ላይ ያልተንጸባረቀ ብልጽግና በባለሥልጣናት ኪስና ቢሮ የተገደበ ነው ይላሉ።
የብልጽግና የልዕልና ዘመን ለብልጽግና ሠዎች እንጅ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና በየጊዜው ለሚፈናቀለው ዜጋ አይደለም የሚሉት ጌትነት፣ ዜጎች ቁም ስቅላቸውን የሚያዩበት ኹኔታ ላይ ነው የምንገኘው ብለዋል። ታጣቂ ኃይሎች ማኅበረሰቡን ግብር የሚያስከፍሉበት ኹኔታ የተፈጠረበት ወቅት መኖሩን የሚገልጹት ጌትነት፣ አሁን የሚታየው ኹኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን መንግሥት ከአንድ በላይ እያስመሰለው ነው ብለዋል። ድኅነቱን እንችለዋልን።
ባለፈው ሳምንት የአዲስ ማለዳ “አንደበት” እንግዳ የነበሩት የፖለቲካ ተንታኙ ዓለማየሁ አረዳ(ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር በቀውስ ውስጥ ነው ይላሉ። በወቅቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዛ ቀውስ ውስጥ እወጣለሁ አልወጣም በሚል ሥጋት ውስጥ በተንጠለጠለበት ሰዓት ላይ፣ የፓርቲ ሳይሆን ግለሰብ ድምጽ በአየር ላይ እንዳንሳፈፈው ያስታውሳሉ። “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዕምብረቱ የግለሰብ ተክለ ሰብዕና የተጫነው ነው” የሚሉት ዓለማየሁ፣ የብልጽግና ድርጅታዊ አቅም አሮጌ ነው ይላሉ።
በአሮጌው አስተሳሰብ ላይ የተገነባ ድርጅት ነው የሚሉት ተንታኙ፣ ብልጽግና የሚሠራው ድሮ ኢሕአዴግ በሠራው መንገድ መሆኑን ይጠቁማሉ። ዋነኛው የመንግሥት መሠረቱ ምንም አልተቀየረም እንዳለ ነው የሚሉት ዓለማየሁ፣ ፖለቲካ ኹልጊዜ የፖለቲካ አመራር ድርጅት ይፈልጋል ብለዋል። ድርጅትን የሚፈጥረው የፖለቲካ አስተሳሰብ መሆኑን የሚገልጹት ዓለማየሁ፣ ሐሳቡ አለ ነገር ግን የተደራጀ ድርጅት የለውም ይላሉ።
ድርጅት የሠዎች መሰብሰብ ማለት አለመሆኑን የሚገልጹት ዓለማየሁ፣ “ብልጽግና ሲመጣ ከዚህ በፊት በብሔር የነበሩ አደረጃጀቶች አንድ ላይ መሆን ይሻላል፣ በአንድ ድርጅት ተዋኅዶ የብሔር ነገር ይጠፋል ነበር የመሰለን፤ የሚታየውና መሬት ላይ ያለው ግን ሌላ ነው” ብለዋል። ፓርቲው አንድ ነኝ ቢልም የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የአፋር ብልጽግና እያሉ ተከፋፍለው እንደቀጠሉ መሆናቸው የሚገልጹት ዓለማየሁ፣ አንድ ነን ቢሉም የተግባር አንድነት አይታይባቸውም ብለዋል። የየክልሎቹ ብልጽግና ፓርቲዎች በየፊናቸው የተለያዩ ሐሳቦችንና መግለጫዎችን ሲሠጡ ይታያሉ የሚሉት ተንታኙ፣ እንደሚታየው በየክልሉ አሥራ አንድ ፓርቲ አለ ማለት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ይሻል?
ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በገባችበት ወቅት የተፈጠረው የብልጽግና አስተዳደር በተለይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩትን ሞትና መፈናቀሎች ያስቆማል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ይሁን እንጂ፣ በብልጽግና የአስተዳደር ዘመን የዜጎች ሞትና መፈናቀል መሻሻል ማሳየቱ ቀርቶ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሶ ቀጥሏል።
በሰሜኑ ጦርነት ለችግር ከተጋለጡት የትግራይ፣ የአማራና የአፋር ክልል ዜጎች በተጨማሪ፣ በተለይ በቤኒሻንጉል ጉምዝ እና በኦሮሚያ ክልል የታጠቁ ኃይሎች በዜጎች ላይ የሚደርሱት ሞትና መፈናቀል ቀድሞ ከነበረው ተባብሶ እንደቀጠለ ነው። መንግሥት የሰሜኑን ጦርነት ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ለዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆኑ የጸጥታ ችግሮችን እንዲያስቆም በተለያዩ አካላት ቢጎተጎትም ለውጥ ማምጣት አለመቻሉ በተደጋጋሚ እየተገለጸ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ላይ ከመንግሥት የሚፈልገው ነገር በመጀመሪያ ሞትን ማስቆምና የአገር ሠላም ማስጠበቅ መሆኑን ጌትነት ጠቁመዋል። “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞትን ማስቆም ከፈለገ ማስቆም ይችላል” የሚሉት ጌትነት፣ ሙሉ በሙሉ በአንድ ጊዜ ማስቆም ባይቻልም መቀነስ የሚቻልበት ኹኔታ መኖሩንም ጠቁመዋል።
ቀዳሚ የሆነውን የሠውን ሞት መቀነስ ከተቻለ፣ በየደረጃው እየተስፋፋ የመጣውን ሙስናን መታገል ቀጣይ ሥራ መሆኑን ጌትነት ጠቁመዋል። “የብልጽግና ሠዎች ብዙ የሙስና ወንጀሎችን ፈጽመዋል” የሚሉት ጌትነት፣ ብልጽግና እራሱን አጥርቶ የተሠጠውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ማድረግ አለበት ብለዋል።
ብልጽግና እንደ መንግሥት ለውጥ ላይ ነኝ ቢልም፣ በተግባር የታየ ለውጥ አለመኖሩን ብዙዎች እየገለጹ ነው። ጌትንት እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሠረታዊ ለውጥ ይፈልጋል። ይሁን እንጂ፣ የብልጽግና ለውጥ ጥገናዊ እንጂ የሕዝቡን ፍላጎት ያማከለ መሠረታዊ ለውጥ አይደለም ብለዋል።
የብልጽግና ሠዎች፣ “መናገር ብቻ ነው የሚችሉት፤ ሕዝብን መስማት አይችሉም” የሚሉት ጌትነት፣ “የተዘጋ አዳራሽ ውስጥ የራስህን ድምጽ እየሠማህ መደለቅ” ዓይነት ጸባይ በብልጽግና ውስጥ ይታያል ብለዋል። እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ማኅበረሰብ ውስጥ ሕዝብን አለማዳመጥ እንደማይቻልም ጠቁመዋል።
“አሁን ተፈጥሯዊ ሞት መሞት ብርቅ ሆኗል” የሚሉት ጌትነት፣ ከኢኮኖሚ ዕድገት እና ከብልጽግና በፊት መኖር ይቀድማል ይላሉ። ብልጽግና የተሠጠውን ዕድል መጠቀም ከቻለ፣ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ምሁራን ኢትዮጵያን ለማሻገር ድጋፋቸውን አሳይተውታል ብለዋል።
የብልጽግና ሠዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በቁሳዊ ልማት ላይ ትኩረት አድርገዋል፤ ቅድሚያ መሥጠት ላለባቸው ጉዳይ ትኩረት አልሰጡም በሚል በተደጋጋሚ ከተለያዩ አካላት ትችት ይቀርብባቸዋል። የእናት ፓርቲው ዋና ጸሐፊ ጌትነት “ቢሮ ቀለም መቀባት ገንዘብ መብያ ሆኗል” ይላሉ። ቁሳዊ ልማት የተጠላ ባይሆንም፣ የዜጎችን ሞትና ረሃብ ማስታገስ ከኹሉም በላይ ቅድሚያ ሊሠጠው እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014



