ባለፈው አንድ ወር ብቻ 20 ሺሕ 337 ቶን ቡና ለተለያዩ አገራት ኤክስፖርት መላክ እንደተቻለ እና 101.7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ በላከው ሪፖርት ባለፈው የካቲት ወር 19 ሺሕ 954 ቶን ቡና ወደተለያዩ አገሮች ለመላክ እቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን፣ 20 ሺሕ 337 ቶን ቡና እንደተላከ እና በወሩ ይገኛል ተብሎ ከተጠበቀው 75 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማሳደግ 101.7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ተብሏል።
ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ኢትዮጵያ 15 ሺሕ 690 ቶን ቡና ወደ ውጭ አገሮች መላክ የቻለች ሲሆን፣ 59.5 ሚሊዮን ዶላር እንዳገኘች እና በተያዘው ዓመት እንዲሁ በየካቲት ወር ብቻ የተገኘው ገቢ በ42 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳሳየ ተጠቁሟል።
ባለሥልጣኑ በተያዘው ዓመት ከቡና ኤክስፖርት ለማግኘት ካቀደው አንፃር ሲፈተሽ የአንድ ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ገቢ ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል ቁመና አለው ተብሏል። ባለሥልጣኑ አክሎም በቀሪዎቹ አራት ወራት ውስጥ ከኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ ከማሳደግ ባለፈ ከዕቅዱ በላይ አፈጻጸም የሚያስመዘግብበት እድል እንዳለ ገልጿል።
ባለሥልጣኑ ኹለት ስትራቴጂዎችን ይዞ እየሠራ እንደሚገኝ እና የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ ገበያዎች ላይ በተወዳዳሪነት መቆየት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ አዳዲስ የቡና ገበያ መዳረሻ አገሮችን ማፈላለግ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተጠቁሟል።
አዳዲስ የቡና መዳረሻ አገሮች ከሆኑት ውስጥ ሩሲያ፣ ቻይና እና ታይዋን ተጠቃሾች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ከፍተኛ የኢትዮጵያ የቡና ገዥ አገሮች ምድብ ውስጥ እየገቡ ካሉ አገሮች ጋር ያለውን ገበያ ይበልጥ ለማጠናከር ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
የቡና ዋጋ በዓለም ዐቀፍ ገበያ እየጨመረ መምጣቱ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ለመጨመሩ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው እና ከዚህም ባለፈ በተለያዩ አገሮች በሚደረጉ ዓለም ዐቀፍ ኤግዚቢሽኖች ላይ ምርቱን ለማስተዋወቅ የሚደረጉ ጥረቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተመላክታል።
የኢትዮጵያን ቡና ከገዙት አገሮች መካከል ጀርመን በቀዳሚነት ስትቀመጥ፣ ሳዑድ ዓረቢያና ጃፓን ኹለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተጠቁማል።
ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014


