ወርቅነሽ ገበየሁ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናት። በየካ ክፍለ ከተማ በአስተዳደር ዘርፍ ውስጥ በቋሚነት ተቀጥራ እንደምትሠራ እና 3100 ብር የተጣራ የወር ደሞዝ እንደሚከፈላት የምትናገረው ወርቅነሽ፣ ከምታገኘው የወር ደሞዝ በላይ ወጪዋ ሠማይ መንካቱን በመግለጽ የኑሮ ውድነት እንዳማረራት ትናግራለች።
ለቤት ኪራይ ኹለት ሺሕ ብር፣ ለትራንስፖርት በትንሹ አምስት መቶ ብር የምታወጣው ወርቅነሽ፣ የበርበሬ፣ ዘይት እና ጤፍ ዋጋ በመወደዱ፣ አሁኑ ላይ ገቢዬ እና ወጪዬ የተመጣጠነ አይደለም ስትል በምሬት ትናገራለች።
የወር ደሞዜና ወጭዎቼ የሚቀራረቡ አይደሉም የምትለው ወርቅነሽ፣ የምታገኘው የወር ደሞዝ ብር ለመቆጠብ ሊያስችላት ቀርቶ፣ ከወር ወር እንደማያደርሳትና ሕይወቷን በተገቢው መንገድ ለመምራት እንደምትቸገር ጠቁማለች።
መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነትን በቶሎ መቋጨት የሚችል ከሆነ እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝን መቆጣጠር ከተቻለ፣ የኑሮ ውድነቱንም ማስተካከል ይቻላል ብላ ተስፋ ብትጥልም፣ ያ እስከሚሆን ድረስ ግን ኑሮ በጣም ፈታኝ እንደሆነባትና እንደከበዳት ትገልፃለች።
ወርቅነሽ አያይዛም፣ መንግሥት በከተማዋ ያለው የኑሮ ውድነት ተቀጥረው ለሚሠሩ ሠራተኞች ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ተረድቶ የደሞዝ ጫማሬ ቢያደርግ የተሻለ እንደሚሆን ትናግራለች። የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት በመንግሥት በኩል ትኩረት ሠጥቶ ቢሠራ የተሻለ ነው ትላለች።
ሌላው አስተያየት ሰጭ በአንድ የመንግሥት ተቋም በሹፌርነት ተቀጥሮ የሚያገለግለው ደረጀ አሊ ነው። ደረጀ በቋሚነት ተቀጥሮ በሚሠራበት የመንግሥት ተቋም ውስጥ ሦስት ሺሕ ብር አካባቢ የተጣራ ደሞዝ ይከፈለኛል ብላል።
ተቋሙ የሚከፍለው የወር ደሞዝና በአሁን ሰዓት በከተማዋ ያለው የኑሮ ውድነት ከአቅሙ በላይ እንደሆነበትና የኑሮ ጫናው እየከበደው መምጣቱን ይናገራል።
ደረጀ፣ ቅዳሜና ዕሁድ ባለው የዕረፍት ቀን ጭምር ታክሲ በማሽከርከር ተጨማሪ ሥራ እንደሚሠራ ተናግሯል።
ለቤት ኪራይ ኹለት ሽሕ አምስት መቶ ብር፣ ለዘይት፣ ለሽንኩርትና ሌሎች የቤት ወጪ ብዙ ብር እንደሚያወጣ የሚናገረው ደረጀ፣ በከተማዋ ያለው የኑሮ ውድነት ከቀን ወደ ቀን እያሻቀበ መሔዱን ተከትሎ፣ ኑሮ ለመምራትና ቤተሰብ ለማስተዳደር እየተቸገርኩ ነው ብላል።
የኑሮ ውድነቱ በዋናነት እየፈተነ ያለው ገበሬውንና ነጋዴውን ሳይሆን፣ በድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ እሱን መሠል የመንግሥት ሠራተኞችን፣ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የከተማ ነዋሪዎችን እንደሆነ ይገልፃል።
ደረጀ እንደሚለው፣ የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር የደሞዝ ጭማሬ ከማድረግ ባሻገር፣ የአገር ውስጥ ምርት መጠቀምን ማበረታታት እና ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን መቀነስ የሚያስችሉ የመፍትሔ ዕርምጃዎችን መንግሥት መውሠድ ይገባዋል ብሎ ያምናል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ የመንግሥት ተቋም ውስጥ በፅዳት ሠራተኛነት ተቀጥራ የምትሠራው ማርታ ለገሰ ናት። ማርታ ተቋሟ በወር ከሚከፍላት ኹለት ሽሕ አንድ መቶ ብር ውስጥ፣ አንድ ሽሕ ኹለት መቶ ብር ኦሮሚያ ልዩ ዞን ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ለተከራየችው ቤት ትከፈላለች። ከቤት ኪራይ የሚተርፋትን ዘጠኝ መቶ ብር አብቃቅታ ለቤት አሠቤዛ መሸመቻና ለትራንስፖርት እንደምታውለው ትናግራለች።
የወር ደሞዜና ወጪየ የተመጣጠነ አለመሆኑን ተከትሎ እያማረርኩ እንድኖር ተገድጃለሁ የምትለው ማርታ፣ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለመቅረፍና ለማረጋጋት የተለያዩ ዕቅዶችን አውጥቼ እየሠራሁ ነው ቢልም በሚባለው ልክ ለውጥ እንዳላመጣ ትናገራለች።
መንግሥት የደሞዝ ጭማሬ እያደረገ እና መደቦችን በየጊዜው እየገመገመ ከማሻሻል ጎን ለጎን፣ አምራችና ሸማቹን በማስተሳሰር የግብርና ምርቶች በተሸሻለ ዋጋ የሚገኙበትን መንገድ አጎልብቶ በማስቀጠል የኑሮ ውድነቱን ቢቀርፍ የተሻለ ነው ባይ ናት።
በከተማዋ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ የመንግሥት ባለሥልጣናት በምርምር እና በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ መረጃዎችን ይጠቀማሉ መባሉ ጥርጣሬን ይጭራል ትላለች። የሕዝቡን ኑሮ የማይቀርፉ ንግግሮች ዛሬ ላይ ለተደራረቡብን ችግሮች እንደዳረጉንም ገልፃለች።
መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራለሁ ከማለት ባለፈ፣ የዋጋ ንረቱ እንዲባባስ የሚያደርጉ ሕገ-ወጥ ነጋደዎች ላይ ጠንካራ ዕርምጃ እየወሠደ አለመሆኑን የምትናገረው ማርታ፣ በተደጋጋሚ ዕርምጃ እወሥዳለሁ ከማለት ባለፈ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በመንግሥት በኩል የሚሠራው ሥራ አናሳ ነው ብላለች።
አዲስ አበባ ውስጥ በመንግሥትና በግል ተቋማት ተቀጥረው የሚሠሩ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት፣ በተቋሞቻቸው በኩል የሚከፈላቸው ደሞዝና በከተማዋ ያለው የኑሮ ውድነት የማይመጣጠን መሆኑን ተከትሎ ኑሮን ለመግፋት መቸገራቸውን ነው።
ኢትዮጵያ በዘርፈ ብዙ ችግሮች ተተብትባ በምትገኝበት በዚህ ወቅት፣ ኢኮኖሚው በበርካታ ችግሮች እየተፈተነ ይገኛል። የኢኮኖሚው መፈተን የገጠሟትን ችግሮች ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት እንዳከበደባት የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።
ባለፉት ኹለት ዓመታት ክፍለ ኢኮኖሚው ካስተናገዳቸው ከፍተኛ ፈተናዎች መካከል የዋጋ ግሽበት አንዱ ነው። በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጣውን የዋጋ ግሽበት የሚያባብሱ ኹነቶች አሁን ላይ ገጥመውታል። በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት የዋጋ ግሽበቱ ያባባሰ እና የአብዛኛውን ማኅበረሠብ ክፍል ኑሮ እየፈተነ የሚገኝ ነው።
ጦርነት የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ የሚያደርግና የማኅበረሠቡን ኑሮ የሚፈታተን በመሆኑ፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለው ጦርነት በቶሎ መፍትሔ ካላገኘ የዋጋ ግሽበቱ እንዲባባስ ምክንያት እንደሚሆን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ በዘርፈ ብዙ ችግሮችን እያለፈች በምትገኝበት በዚህ ወቅት፣ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ዜጎችን በችግር አረንቋ እየዘፈቀ ይገኛል። የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ከፖለቲካው ጥገኝነት ያልተላቀቀ አለመሆኑን ተከትሎ፣ በየጊዜው በሚፈጠሩ ፖለቲካዊ ችግሮች ሳቢያ ዜጎች ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን እያስተናገዱ መሆናቸውን ብዙዎች ይስማማሉ።
የ2014 የታኅሣሥ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 35.1 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ የምግብ ነክ ግብዓቶች ግሽበት ደግሞ 41.6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል።
እንዲሁም፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት የታኅሣሥ ወር 2014 ካለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር 2013 ጋር ሲነጻጸርም የ26.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡
በአንድ ወር ውስጥ ብቻ የታየው የዋጋ ግሽበት ልዩነት በኅዳር ወር 2014 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ33.0 የነበረ ሲሆን፣ በአንድ ወር ልዩነት ወደ 35.1 በመቶ ከፍ ብሏል።
የምግብ ዋጋ ግሽበት የኅዳር ወር 2014 ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 38.9 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በአንድ ወር ውስጥ ወደ 41.6 በመቶ ከፍ ብሏል።
በተጨማሪ፣ የጥር ወር 2014 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ34.5 በመቶ ጭማሬ ማሳየቱን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ያወጣው መረጃ ያስረዳል። የምግብ ዋጋ ግሽበት የጥር ወር 2014 ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ39.9 በመቶ ጭማሬ ያሳየ ሲሆን፣ በያዝነው ወር በእህሎችና በአትክልቶች ላይ በአብዛኛው የዋጋ ቅናሽ ታይቷል ተብሏል። ይህም ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ሽምብራና ምስር በአብዛኛው የዋጋ ቅናሽ ማሳየታቸው ተገልጿል።
ይሁን እንጂ ሥጋ፣ ወተት፣ አይብና እንቁላል፣ ቅመማ ቅመም (በዋናነት ጨውና በርበሬ) ጫማሬ አሳይተዋል። የምግብ ዘይትና ቅቤ፣ ቡና፣ ለስላሳ መጠጦች ተከታታይ የዋጋ ጭማሬ አሳይተዋል ነው የተባለው።
ለዋጋ ግሽበት ዋነኛ ምክንያት ከሚባሉት መካከል የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን አንዱ ሲሆን፣ ከጦርነቱ መከሠት በኋላ በተፈጠሩ መስተጓጎሎች የተነሳ በተለያዩ ጊዜያት የምርት አቅርቦት ዕጥረት ሲያጋጥም ተስተውሏል።
በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለ ከፍተኛ አለመመጣጠን በተለይ ደግሞ የአገር ውስጥ ምርቶች ከፍላጎት ጋር በተመጣጠነ መልኩ አለማደጋቸውን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል።
በሌላ በኩል፣ ሕገ ወጥ ደላሎች በገበያ ውስጥ የሚፈጥሩት ጣልቃ ገብነት እና የጥሬ ገንዘብ ሥርጭት የዋጋ ግሽበትን ከማባባስ ባሻገር ለኑሮ ውድነት መጨመር ምክንያት ሁኗል።
ከ 1997 ጀምሮ ለበርካታ ዓመታት እየተስተዋለ የመጣውና የዜጎች ሮሮ የሚሠማበት የኑሮ ውድነት፣ እስካሁን ድረስ ተጨባጭና ዘላቂ መፍትሔ ሳይገኝለት፣ አሁን ላይ ይባስ ብሎ የንረት አዙሪቱን አስፋፍቷል።
አሁን ላይ፣ በተለይ በመዲናዋ 102 ሺሕ የሚጠጉ ዜጎች በቀን አንዴ እንኳን መመገብ የማይችሉበት ደረጃ እንደሚገኙ ከስድስት ወራት በፊት ይፋ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥናት ያስረዳል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ መንግሥት የደሞዝ ጭማሬ ከማድረግ በተጨማሪ፣ በየጊዜው ጭማሬ የሚያሳየውን የኑሮ ውድነት ማጥፋት ባይቻል እንኳን ባለበት ደረጃ ለማስቆም በትኩረት መሥራት እንዳለበት ጠይቀዋል።
ሕጉን አክብረው የሚሠሩ ነጋዴዎች እንዳሉ ኹሉ፣ አጭበርባሪና የኑሮ ውድነቱን የሚያንሩ ነጋዴዎችም እንደተበራከቱና እነዚህ አካላት በአገር ውስጥ ለሚመረቱ ምርቶች ተጠያቂ የሚሆኑበት ዕድል ሠፊ በመሆኑ መንግሥት ተከታትሎ ተገቢውን ዕርምጃ እንዲወስድ ጠቁመዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014



