ከአዲሷ የኮቪድ19 ማእከል ጣሊያን፤ ዓለም እንዲማርበት

Views: 629

 

ኮቪድ19 ዓለምን ማስጨነቅ ከጀመረ የወራት እድሜን አስቆጥሯል። በዚህ ጊዜ ውስጥም የዓለም አገራት ቫይረሱን መለየትና የሰዎችን እንቅስቃሴ መገደብ ቀድመው ተፈጻሚ ሊሆኑ እንደሚገባ ተረድተዋል። ይህም በአግባቡ ጥርት ባለ መንገድ ሊተገበር የሚገባ ነው።

እርምጃዎች በተገቢው መንገድና በትኩረት ተግባራዊ አለመደረጋቸው፣ የሕዝብ እንዲሁም የመንግሥት ዝንጋኤ፣ ጣልያን ቫይሱን እንዳትቆጣጠር ምክንያት ሆኗታል። ኢትዮጵያ ያለጥርጥር ከዚህ የጣልያን ልምድ የምትቀስመው ተሞክሮ ይኖራል በሚል ሽመልስ አርአያ ገዳ የኒው ዮርክ ታይምስን ዘገባ ተርጉመውታል።

 

በጣሊያን በኮቪድ19 ተጠቂዎች ከ400 በላይ በሆኑበትና እና በኹለት አሃዝ የሚቆጠሩ ዜጎቿ በሞቱበት ሰሞን፣ የገዥው ዴሞክራቲክ ፓርቲ መሪ የመጠጥ ብርጭቆ እያጋጩ፣ ‹‹ቺርስ›› እየተባባሉ የሚያሳይ ፎቶግራፍ ስር ለሕዝቡ ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹ተለምዷዊ እንቅስቃሴያችን በምንም ሁኔታ መቀየር የለብንም›› አሉ።

ይህን ካሉ ዐስር ቀናት በኋላ 5 ሺሕ በላይ የጣልያን ዜጎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ 233 ሰዎች ሕይወታቸው አለፈ። ይሄኔ የፓርቲው ሊቀመንበር ኒኮላ ዚንጋሬቲ አዲስ ቪዲዮ አወጡ፣ በዚህ ቪድዮ ግን እሳቸውም የቫይረሱ ተሸካሚ መሆናቸውን ለጣልያን ሕዝብ አረዱ።

በጣሊያን በአሁኑ ጊዜ ከ63 ሺሕ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ ከ6 ሺሕ በላይ ሞተዋል። ይህም ኒውዮርክ ታይምስ ዘገባውን ካወጣበ በኋላ፣ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሺሕ በላይ ጨምሯል። ባለፈው ቅዳሜ በአንድ ቀን ውስጥ 793 ሰዎች ሕይወታቸው ያፈ ሲሆን፣ ይህም እስከ አሁን በአንድ ቀን የተመዘገበ ትልቁ ቁጥር ነው።

ቫይረሱ ከተነሳባት ቻይና ይልቅ ጣልያንን የቫይረሱ ዋነኛ ማእከል እንድትሆን ያደረጋት።

በጣልያን በዋናነት የስርጭቱ ማእከል በሆነችውና የሟቾች አስክሬን በአብያተ ክርስትያናት በተከማቸባት የሰሜናዊው ሎምባርዲ ክልል፣ የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመገደብ መንግሥት የጦር ሠራዊት አሰማርቷል። አሁን በጣልያን ባለሥልጣናት በአገሪቱ አጠቃላይ ቁጥጥሩን አጠናክረዋል፣ ፓርኮች ተዘግተዋል፣ ከቤት ውጭ ርቆ መጓዝን ወይም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ ተጠናክረው ተከልክለዋል።

ቅዳሜ ምሽት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ እጅግ ከባድ ቀውስ አገራቸው እንደገጠማት አስታውቀዋል። በዚህም ‹‹የቫይረሱን ስርጭት በሚገባ ለመቆጣጠር ጣሊያን ፋብሪካዎች ከመዝጋት አልፋ ሁሉንም ኢኮኖሚያዊ መስዋእትነት ለመክፈል ትገደዳለች›› አሉ።

ይህ በጣልያን የታየው ክስተት ቫይረሱ በእኩል ፍጥነት እየተዛመተባቸው ላሉት ለአውሮፓ ጎረቤቶቿ እና ለአሜሪካ ከባድ ማስጠንቀቂያ ነበር። የጣሊያን ልምድ የሚያሳየው በስርጭቱ የተጎዱ አካባቢዎችን በሚገባ መለየት እና በፍጥነት የሕዝቡም እንቅስቃሴ መገደብ እንዳለበት ነው። እነኚህም እርምጃዎች ፍጹም ግልጽነት ባለው ሁኔታ ከዚያም በጥብቅ ክትትል እንዲፈፀሙ ማድረግ።

ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ በዓለም ሁሉ የሰዎች እንቅስቃሴ ቁጥጥር ቢደረግበትም፣ የጣሊያን ባለሥልጣናት መሰረታዊ የሲቪል ነጻነቶችን እና ኢኮኖሚያቸውን ለመጠበቅ በመፈለጋቸው የተነሳ የቫይረሱ ስርጭት እጅግ አስጊ እየሆነ መጥቷል። ቢመጣም ቁጥጥሩን በማላላታቸው ቫይረሱን ለመቆጣጠር በእጃቸው የነበረውን እድል አሳልፈዋል። ጣልያን ታደርገው የነበረው የቁጥጥር ስርዓት መጀመሪያ ከተማ ከዚያም ክልል በመቀጠል አገሪቱ በሞላ ከቫይረሱ የስርጭት ፍጥነት አንፃር እጅግ ወደኋላ የቀረ ነበር።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዋና ፀሐፊ ሳንድራ ዛምፓ ሲናገሩ ‹‹አሁን እሱን [ቫይረሱን] እየተከተልን ነው። ጣሊያን መረጃውን እንዳገኘች የምትችለውን ሁሉ አድርጋለች›› ብለዋል። ‹‹አጠቃላይ አውሮፓ እንዳደረገው ቀስ በቀስ ዘግተን ነበር። ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ጀርመን፣ አሜሪካ ተመሳሳይ ነገር እያደረጉ ነው። በየቀኑ ትንሽ በሚዘጉበት ጊዜ በሕዝቡ መደበኛ ኑሮ ላይ ብዙ ያሳጣል። ቫይረሱ ደግሞ መደበኛ የኑሮ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ አይፈቅድም።››

በአንፃሩ አንዳንድ ባለሥልጣናት በፍጥነት ውሳኔዎችን ከማድረግ ይልቅ አስማታዊ አስተሳሰብ ያራምዱ ነበር። ቫይረሱም ይህን ቸልተኝነት በሚገባ ተጠቅሞበታል። ይባሱኑ ከጣሊያን ተሞክሮ ባለመውሰድ መንግሥታት የተለመዱ ስህተቶችን በመድገም ተመሳሳይ ጥፋት ፈጽመዋል።

የጣሊያን ባለሥልጣናት በበኩላቸው አደጋው በዘመናችን ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን በመግለጽ ምላሽ በመስጠት ተከላክለዋል። መንግሥት በፍጥነት ምላሽ እንደሰጠ፣ በሳይንቲስቶች ምክር መነሻነት ወዲያውኑ እርምጃ በመውሰድ ከአውሮፓ አቻዎቻቸው ይልቅ ፈጣን እርምጃዎችን ወስደናል ብለው ሞግተዋል።

ነገር ግን የድርጊታቸውን ቅደም ተከተል እንደሚጠቁመው፣ ያመለጡ እድሎችና የተሳሳቱ የውሳኔ አካሄዶችን የነበሩ መሆናቸውን ያሳያል።

አንደኛው ደግሞ የመረጃ ጉዳይ ነው። ወረርሽኙ በተከሰተ የመጀመሪያ ቀናት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ኮንቴ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት አደጋው በማሳነስ ቫይረሱ እንዲሰራጭ እድል የሚፈጥር፣ ግራ አጋቢ እና የተሳሳቱ መረጃዎችን ይሰጡ ነበር።

የአገሪቱ መንግሥት ቫይረሱን ለማሸነፍ አጠቃላይ እንቅስቃሴ መገደብ አስፈላጊ መሆኑን ቢገነዘብም፣ ጣሊያናውያን ባለሙያዎች ያስተላለፉትን የጥንቃቄ ሕጎች እንዲያከብሩ በኃይል ለማስፈፀም አልቻለም።

የዓለም ጤና ድርጅት የቦርድ አባልና የጤና ጥበቃ አማካሪ ዋልተር ሪቺያርዲ ‹‹የጣሊያን መንግሥት ሳይንሳዊ መረጃ ላይ በመመስረት ተገቢውን እርምጃ ወስዷል›› ሲሉ ተከራክረዋል። በመቀጠልም ‹‹የግለሰብ ዴሞክራሲ በሰፈነበት አገር ውስጥ ይሄን ማድረግ በራሱ ቀላል አይደለም›› ብለዋል። አያይዘውም የጣሊያን መንግሥት ከአውሮፓ ጎረቤቶች ወይም ከአሜሪካ ይልቅ እጅግ ፍጥነት ባለው አኳኋን እንደተንቀሳቀሰ እና አደጋውን ይበልጥ በትኩረት እንደያዘው ተናግረዋል።

አሁንም የጤና ሚኒስትሩ የመንግሥት የሥራ ባልደረቦቹን በበለጠ ፍጥነት እንዲንቀሳቀሱ ለማሳመን ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፣ በማእከላዊ መንግሥቱና በክልሎች መካከል ካለው የሥልጣን ክፍፍል የተነሳ የተዘበራረቀ የትእዛዝ ሰንሰለትና ወጥነት የሚጎድላቸው መልዕክቶች ልውውጥ ክፍተት እንዳስከተለ አምነዋል። በመሆኑም የቁጥጥር ስርዓቱ በጊዜው ወጥነት ባለው መልኩ እንዳይደረግ እክል ፈጥሯል።

 

እዚህ በጭራሽ ሊከሰት አይችልም ነበር

ከወራት በፊት፣ በአውሮፓውያን አቆጣጠር ጥር 21 የጣሊያን ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር የጣሊያን-ቻይና ባህልና ቱሪዝም ትስስርን ለማክበር ባሰናዳው ክዋኔ፣ የቻይና ልዑካን ተገኝተው ነበር።

የቀድሞው ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊና ከቻይና ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖር አበክረው በመሥራት የሚታወቁት ሚሸል ገራቺ፣ በእለቱ ከሌሎች ፖለቲከኞች ጋር መጠጥ እየጠጡ ቢሆንም ምቾት የተሰማቸው አይመስልም ነበር።

‹‹እዚህ መሆናችን ግን ትክክል ነው?›› ሲሉም ደጋግመው ጠይቀዋል። በመድረኩ ላይ የነበሩ ፖለቲከኞች ስለ ኢኮኖሚው እና አገሪቱ ስለመመገብ ተጨንቀዋል። በቫይረሱ ፊት የታየውን አቅመ ቢስነታቸውን ግን መቀበልም ከባድ ሆኖባቸው ነበር።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ፀሐፊ ወ/ሮ ዛምፓ፣ ሁሉም ነገር ወዲያውኑ መዘጋት እንደነበረበት ተናግረዋል። ነገር ግን አሁን ባለው መጠን ነገሮች ግልጽ አልነበሩም ይላሉ።

ዛምፓ እንዳሉት ታድያ፣ ጣልያን በቻይና የሆነውን እንደ ምሳሌ ወስዳለች። ‹‹ነገር ግን እንደ ማስጠንቀቂያ ደወል ሳይሆን እንደ ሳይንስ ፊክሽን ፊልም፣ ከእኛ ጋር ግንኙነት እንደሌለው አድርገን ነው ስናየው የነበረው።›› ሚኒስትሯ ቀጠሉ፣ በኋላም ቫይረሱ ጣልያንን ሲወር አሉ፣ ‹‹የቀሩ የአውሮፓ አገራት እኛ ቻይናን ስናይ እንደነበረው፣ አሁን እኛን እንደዛ እየተመለከቱን ነው››

በጥር ውስጥ ቀኝ ዘመም የሆኑ አንዳንድ ባለሥልጣናት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀድሞ አጋሮቻቸው እና አሁን ደግሞ የፖለቲካ ባላንጣዎች ከቻይና ቆይታ በኋላ ወደሰሜን ክልሎች የተመለሱ ተማሪዎች ተለይተው እንዲቀመጡ ጥሪ አቅርበው ነበር። ይህም ትምህርት ቤቶችን ለመጠበቅ ታሳቢ ያደረገ ምክር ነበር። ከእነዚህ ልጆች መካከል ብዙዎቹ የቻይናውያን ስደተኛ ቤተሰቦች ነበሩ።

ብዙዎቹ የግለሰብ መብት አቀንቃኞች የቀረበውን ሐሳብ ጭካኔ የተሞላበት አድርገው አራገቡት። ጠቅላይ ሚኒስትር ኮንቴም ሐሳቡን ውድቅ አደረጉ። ነገር ግን ኮንቴ የቫይረሱ ስርጭት እጅጉኑ እንዳሳሰባቸው በመጠቆም፣ ጥር 30 ከቻይና ጋር የሚያገናኙ የአየር በረራዎችን አግደዋል። በመሆኑም ‹‹እንዲህ ዓይነቱን የጥንቃቄ እርምጃ በመውሰድ አውሮፓ ውስጥ የመጀመሪያ ነን›› ብለዋል።

 

 

የመጀመሪያው ታማሚ– ዋናው አሰራጭ

የ38 ዓመቱ ጎልማሳ የካቲት 18 ቀን ሎምባርዲ ክልል በሚገኝ ኮዶኞ በተባለ ሆስፒታል ለድንገተኛ ክትትል ያመለክታል። ታማሚው አደገኛ የጉንፋን ምልክት ቢኖረውም የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ጉዳዩን ቀለል አድርገው አነስተኛ የሕክምና እርዳታ አድርገው ወደ ቤቱ ይመልሱታል። ሕመሙ ሲጠናበት ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ተመልሶ ወደ ሆስፒታል በመምጣት አልጋ ይዞ ሕክምናውን መከታተል ይጀምራል። ቀጥሎም የካቲት 20 በቫይረሱ የተለከፈ መሆኑ ተረጋገጠ።

ይህ የመጀመሪያ ታማሚ እንደሆነ የሚጠረጠረው ግለሰብ በወሩ ውስጥ የተለያዩ ቦታዎች በመታደም ከብዙ ሰዎች ጋር ተገናኝቷል። ቢያንስ ሦስት የራት ግብዛዎች ላይ ተገኝቷል፣ እግር ኳስ ተጫውቷል፣ ከቡድን አጋሮቹ ጋር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲያደርግ ነበር። የሚገርመው ግን ይህ ሁሉ የሚሆነው ምንም አይነት የሕመም ምልክት እያሳየ ስላልነበረ ነው። ቫይረሱ ግን ከአንዱ ወደሌላው እየተላለፈ ነበር።

ሪቻርዲ ነገሩን ከእድለ ቢስነት ቆጥረውታል። ታማሚው ሕዝብ በሚበዛበት አካባቢ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ፣ አልፎም ከአንዴም ኹለት ጊዜ ሆስፒታል መሄዱና የሕክምና ባለሞያዎችን ጨምሮ በርካቶች ጋር ቫይረሱን በማዳረሱ ነው። ‹‹ግለሰቡ በማይታመን ሁኔታ ንቁና ጤነኛ ይመስል ነበር›› ብለዋል።

ሆኖም ግን ከቻይናውያን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አልነበረውም። ባለሙያዎች እንዳሉትም ግለሰቡ ቫይረሱን ከሌላ አውሮፓዊ አገር ዜጋ የተላለፈበት እንደሆነ ይገመታል።

በወቅቱ ቫይረሱ በጣሊያን ውስጥ ለሳምንታት በሚገባ ተሰራጭቶ ቆይቷል። በታማሚዎች ላይ የታዩት ምልክቶች ጉንፋን ናቸው በማለት በተሳሳተ መንገድ ታልፏል። የባህልና የንግድ ማእከል የሆነችው ሚላን ከተማ የሚገኝበትና ከቻይና ጋር የጠበቀ ግንኙነት ባለው ሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል፣ ቫይረሱ ሳይታወቅ ወደብዙዎች ተሰራጭቶ ነበር።

በመሆኑም የመጀመሪያ በሽተኛ የምንለው ግለሰብ ‹‹200ኛው በሽተኛ›› ሊሆንም ይችላል ሲሉ የጤና ባለሙያዎች በቁጭት ይገልፃሉ።

እሑድ የካቲት 23 ላይ የተመዘገበው የታማሚ ቁጥር ከ130 በላይ ሲሆን፣ ጣሊያን በ11 ከተሞቿ በፖሊስ እና በወታደር የታገዘ የተጠናከረ ፍተሻዎች ማድረግ ጀመረች። በየዓመቱ በድንቅ ሁኔታ የሚከበረው የመጨረሻዎቹ ቀናት የቬኒስ ከተማ የአደባባይ ላይ ትርዒት እንዲሰረዝ ተደረገ።

በነገራችን ላይ፤ የዚህ ጽሑፍ ተርጓሚ ከቤት ቤት የውሃ ትራንስፖርት ብቻ በመጥቀም እንቅስቃሴ የሚደረግባትን ጥንታዊቷን የቬኒስ ከተማን በ2017 ጎብኝቷል። በመሆኑም በዚያን ዓመት በዚህ ከተማ በተካሄደ የአደባባይ ትርዒት ላይ ተገኝቶ የቬንስን ጥንታዊነት የተላበሰ ግርማ ሞገሷ ተዘዋውሮ ከመጎብኘቱ በተጨማሪ በካርኒቫሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት ከተለያዩ የዓለም ሃገራት በዋናነትም ቻይናዎችን የሚስብ መሆኑን ታዝቧል።

የላምባርዲ ክልል ትምህርት ቤቶችን፣ ቤተ-መዘክሮቻቸውን እና የፊልምና ቴአትር ማሳያዎች ዘግቷል። ሚላናውያንም በድንጋጤ ሩጫቸውን ወደሱፐር ማርኬቶች ሲያደርጉ ተስተውለዋል።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ኮንቴ በሽታውን ለማቃለል ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በሎምባርዲ ክልል የሚደረገውን ጠንከር ያለ የጤና ምርመራ ነቅፈዋል። በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ‹‹እኛ በጣም ጠንካራና ትክክለኛ ቁጥጥር በማድረግ የመጀመሪያዎቹ ነን›› ሲሉም ተደመጡ። ሲቀጥሉም በቫይረሱ የሚጠቁት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የመጣው ‹‹ብዙ አላስፈላጊ ምርመራ ለማድረግ ስንል በሚፈጠር ስህተት ነው›› አሉ።

በሚቀጥለው ቀን የተጠቂዎች ቁጥር ከ200 በላይ ሲጨምር፣ ሰባት ሰዎች ሞቱ። ይህም ተከትሎ የአክሲዮን ገበያው ማሽቆልቆል ጀመረ። እንዲህም ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እውነታውን ለመጋፈጥ አልደፈሩም። ለቫይረሱ ስርጭት ግን ወቀሳቸውን በኮዶኞ ሆስፒታል ላይ ሰነዘሩ። በመቀጠልም ሎምባርዲኒና ቬንቶ የተሰኙት የሰሜን ክልሎች ከሚገባው በላይ አራግበውታል፣ ሰዎችን ይመረምሩ የነበረው ምንም ምልክት ሳያሳዩ ነበር በማለት ከሰሱ።

የሎምባርዲ ክልል ባለሥልጣናት የተጠቂዎች ቁጥር ወደ 309 በማሻቀቡና 11 ሟቾች በመመዝገቡ ተደናግጥው፣ የሆስፒታል አልጋዎችን ለማስለቀቅ ሲሯሯጡ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው፣ የካቲት 25 ላይ ‹‹ጣሊያን ደኅና የሆነች አገር ናት፣ ምናልባትም ከሌሎቹም ይበልጥ ደኅንነቷ የተጠበቀ ነው›› ሲሉ ተደመጡ። በየካቲት 28 ጽሕፈት ቤታው ጥያቄዎችን በጽሑፍ በመቀበል ምላሽ ሰጥቷል። በጥያቄው ከተካተቱት መካከል ግን፣ አስቀድሞ ስለተጠቀሙት ቃላቶቻቸው ማብራሪያ እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

 

የተደበላለቁ መልእክቶችና የዘሩት ግራ መጋባት

ከመሪዎቹ የሚቀርበው የተደበላለቀ መረጃ የጣሊያን ሕዝብ ግራ አጋብቶ ነበር።

የካቲት 27 ላይ የፓርቲው ሊቀመንበር ኒኮላ ዚንጋሬቲ የችርስ ፎቶውን አውጥተዋል። በዚያው ቀን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሉዊጂ ዲ ማዮ ሮም ውስጥ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ላይ ነበሩ። ‹‹በጣሊያን ወረርሽኙ ከሚያስከትለው አደጋ ወደ መሠረተ ቢስ ወሬ ተሸጋግረናል›› ያሉት ዲ ማዮ፣ አራግበውታል ያሏቸው የመገናኛ ብዙሃንን በመውቀስ፣ ‹‹0.089 በመቶ ብቻ የሆነው የጣሊያን ሕዝብ ተገልሎ እንዲቀመጥ ተደርጓል›› አሉ።

በሽታው ከተከሰተበት በጥቂት ማይሎች ርቅ የምትገኝው የሚላን ከተማ ከንቲባ ቤፔ ሳላ ደግሞ ‹‹ሚላን አታቆምም›› የሚል ዘመቻ በማስተጋባት በቫይረሱ ስርጭት የተነሳ ተዘግቶ የነበረው የከተማዋ ምልክትና ድንቅ የቱሪስት መስህብ የሆነው ዱሞ (Doumo) ካቴድራል ለቱሪስቶች እይታ በድጋሚ አስከፈቱ። የዚህ ጽሑፍ ተርጓሚ ይህን ድንቅ የሚላን ምልክት በ2017 የጎበኘ ሲሆን፣ እጅግ ለቁጥር የሚያታክት ከዓለም የጎረፈ የቱሪስት ማዕበል እየተጋፋ የሚጎበኘው ቦታ መሆኑን ታዝቧል። በዚህም በከንቲባው ውሳኔ ቤት ውስጥ በራሱ ተነሳሽነት ከእንቅስቃሴ ተገትቶ የነበረው የከተማው ሰው ግልብጥ ብሎ ወደከተማው ወጣ።

ነገር ግን ሚላን በሚገኘው የክልሉ መንግሥት ዋና መሥሪያ ቤት ስድስተኛ ፎቅ ላይ ሥራቸውን እያከናወኑ የነበሩት በቫይረሱ ለተጠቁት ሕክምና አቅርቦት አስተባባሪ የሆኑት ጊያኮሞ ግራሴሊ፣ በመላው ሎምባርዲ በቫይረሱ የተጠቃው ቁጥሩ እየጨመረ በመሄዱ አዳዲስ ተጠቂዎች እንዳይያዙ ቁጥጥር ካልተደረገ ሁሉንም በሽተኞች ማከም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ይደረሳልና፣ አደጋው ከባድ መሆኑን ተገንዝበዋል። የአልጋና የሕክምና አቅርቦት ከፈላጊው ቁጥር አንፃር ባይጣጣምም፣ የእርሳቸው ግብረ ኃይል በሽተኞቹን በአቅራቢያ በሚገኙ ሆስፒታሎች በሚችለው ሁሉ አገልግሎቱ ለመስጠት ጥረዋል።

ከ20 በማይበልጡት የጤና እና የፖለቲካ ባለሥልጣናት የዕለት ተዕለት ስብሰባ በአንዱ ስብሰባ ላይ ተገኝተውም፣ ለክልሉ ፕሬዝዳንት አቲሊዮ ፎንታና የተጠቂው ቁጥር እጅግ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። በመቀጠልም ‹‹የሆነ ነገር ማድረግ አለብን›› ሲሉ አሳሰቡ።

ማእከላዊውን መንግሥት ይበልጥ ከባድ እርምጃ እንዲወስድ ግፊት በማድረግ ላይ የነበሩት ፎንታናም ተስማሙ። ከሮማ የሚሰሙ የተቀላቀሉ መልእክቶችና የእንቅስቃሴ እገዳን መልሶ በማቃለል ጣልያናውያን ‹‹ሁሉም ነገር ቀልድ ነው ብለው እንደተለመደው ኑሮአቸውን መምራት ጀመሩ›› ሲሉም ተደመጡ።

ፕሬዝደንቱ በመቀጠልም ቅሬታቸው ሲያቀርቡ ‹‹በአገሪቱ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከሌሎች የክልል ፕሬዝዳንቶች ጋር በተደረገ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ላይ ጥሪ አቅርበናል። ጥያቄያችን ግን በተደጋጋሚ ውድቅ ተደርጓል። በመሆኑም ከአዳዲስ ተጠቂዎች ቁጥር የተነሳ በአገሪቱ ቅድሚያ ደረጃ ይዞ የነበረው የሰሜኑ ክፍል የጤና አቅርቦት እንዲዳከም ሆኗል›› አሉ።

ነገሩ እያየለ ሲመጣ መንግሥት የተወሰነ የኢኮኖሚ እርዳታ መስጠቱን የጀመረ ሲሆን፣ በኋላ ላይ 25 ቢሊዮን ዩሮ (28 ቢሊዮን ዶላር) መመደቡን አስታወቀ። ይሁንና ጣልያን ግን አደጋውን በተጋፈጡት ሰሜነኞቹ እና በማያውቁት መካከል ተከፋፍላ ነበር።

ወይዘሮ ዛምፓ፣ የቫይረሱ ዋና ማእከል በሆነችው ቬኔቶ ክልል የቫይረሱ ተጠቂዎች ከኮዶኞ ወረርሽኝ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ያልነበራቸው መሆኑን መንግሥት የተገነዘበው ዘግይቶ መሆኑን አመኑ። ፀሐፊዋ እንዳሉትም በዕለቱ የጤና ሚኒስትሩ ስፔራንዛ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኮንቴ፣ መረጃው እንደደረሳቸው አብዛኞቹን የሰሜን ግዛቶች ለመዝጋት መወሰኑን ተናግረዋል።

መጋቢት 8 በተሰጠ መግለጫ 7 ሺሕ በላይ ሰዎች ለኮሮና ቫይረስ በሽታ መዳረጋቸውና 366 ሰዎች መሞታቸው የተገለፀ ሲሆን፣ በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሞተር የሆነው የሰሜናዊ ክልሎች ውስጥ ከሚኖረው ሕዝብ አንድ አራተኛው እንቅስቃሴው እንዲገደብ እርምጃ እንዲወሰድ አዘዙ። በወቅቱም ‹‹አስቸኳይ ሁኔታ ተጋርጦብናል›› አሉ፣ ይህም ከብሔራዊ አደጋ ተቆጠረ።

ነገር ግን የዚህ የአዋጁ ረቂቅ ቅዳሜ ምሽት የጣሊያን መገናኛ ብዙኀን በሚስጢር አግኝተው መረጃውን ለሕዝብ አድርሰውት ስለነበር፣ ቁጥሩ እጅግ ብዙ የሆነ የሚላን ነዋሪ ክልሉን ለቅቆ ለመውጣት በሩጫ ወደ ባቡር ጣቢያው ነጎደ። በዚህም የቫይረሱ ቁጥጥር ለማድረግ በማያስችል ሁኔታ በዐስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ወደሌሎች ክልሎች እግሬ አውጭኝ አሉ።

በሚቀጥለው ቀን ግን አሁንም አብዛኛዎቹ ጣሊያኖች እገዳው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ግራ ተጋብተው ነበር። የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሥራ፣ ለጤንነት ወይም ለሌላ ‹‹ወሳኝ;አስፈላጊ›› ፍላጎቶች ሰዎች ለመጓጓዝ የሚያስችላቸው ‹‹ማረጋገጫ ሰርተፊኬት›› አወጣ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ የክልል አስተዳዳሪዎች አዲስ ከተከለለው አካባቢ ፈልሰው የሚመጡ ሰዎችን ተገልለው እንዲቀመጡ አዘዙ። ሌሎች ክልሎች ግን ይህንን አላደረጉም።

አሁንም በድጋሚ በሎምባርዲ ውስጥ ተደርጎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ ተነሳ። ከዋናው ወረርሽኝ ከተከሰተበት ኮዶኞና በሌሎችም ‹በቀይ መስመር› የተካተቱት ከተሞች ጨምሮ ማለት ነው። ፍተሻዎችም ተመልሰው ጠፉ። የአካባቢው ከንቲባዎች የከፈሉት መስዋዕትነት በከንቱ መቅረቱ አስቆጭቷቸው ቅሬታቸውን አሰሙ።

ከአንድ ቀን በኋላ፣ መጋቢት 9፣ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር ወደ 9 ሺሕ 172 ሲደርስና የሟቾች ቁጥር ወደ 463 ከፍ ሲል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንቅስቃሴ እገዳው በአጠቃላይ አገሪቱ እንዲሆን አሳወቁ።

ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ አንዳንድ ባለሙያዎች፣ እነኚህ እርምጃዎች ጊዜው ያለፈባቸው እንደሆኑና ፋይዳም እንደሌላቸው ይገልፁ ነበር።

 

የአገር ውስጥ ማሳያዎች

ጣሊያን አሁንም በሳይንቲስቶች እና በፖለቲከኞች ዘንድ በቀደሙት ቀናት በተላለፉ የተቀላቀሉ መልዕክቶችን ዋጋ እየከፈለች ነው። መጀመሪያ ሰሞን በቫይረሱ ሕይወታቸው ያለፈ በርካታ ዜጎች፣ በግራ መጋባቱ ጊዜ በቫይረሱ የተያዙ ናቸው።

አሁን ማእከላዊ መንግሥት ሕዝቡ የእንቅስቃሴ ገደቡን በብሔራዊ አንድነት መንፈስ ያከብር ዘንድ መወትወት ተያይዞታል። ነገር ግን ቅዳሜ ዕለት በጣም ከባድ ጉዳት ካደረሰባቸው አካባቢዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ከንቲባዎች ለማእከላዊ መንግሥት አሁንም እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች በጣም በቂ አይደሉም ሲሉ ገልፀዋል።

በሰሜን ያሉ አመራሮች ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሳ፣ መንግሥት ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወስድ አጥብቀው እየወተወቱ ይገኛሉ።

አርብ ዕለት፣ የሎምባርዲ ክልል ፕሬዝዳንት ፎንታና መንግሥት ያሰማራቸውን 114 ወታደሮች በቂ ስላልሆኑ ቢያንስ አንድ ሺሕ ያህል እንዲጨመር ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን፣ የሥራ ቦታዎችን እና የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች በሞላ እንዲዘጉ ታዘዘ።

ፕሬዝዳንዴቱ ‹‹በመጀመሪያ ሁሉንም ነገር ለኹለት ሳምንታት ዘግተን ቢሆን ኖሮ፣ ምናልባት አሁን ድልን እናከብር ነበር ማለት እችላለሁ” ብለዋል።

የፖለቲካ አጋራቸው የሆኑት የቬኔቶ ክልል ፕሬዝዳንት ለማእከላዊ መንግሥቱ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የበለጠ ‹ከባድ እገዳ› ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

አዳዲስ ተጠቂዎች በመላ አገሪቱ እየተስፋፉ ቢሆንም፣ እሳቸው በሚያስተዳድሩት ክልል ውስጥ የተጠቂዎች ቁጥር ደግሞ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ደርሶ ነበር። ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ተጠቅተው የነበሩት ከተሞች የቫይረሱን ስርጭት እንደበፊቱ እንዳይስፋፋ እየተቆጥጠሩት እንደሆነ ገልፀዋል።

የጣልያን ማእከላዊ መንግሥት የበሽታው ምልክት ሳይኖርባቸው ሰዎችን መመርመር በሀብት ላይ መቀለድ ነው በሚል ነቀፋ ቢያቀርብም፣ የዚህን ጥቅም አብራርተዋል። ይህም ‹‹በሽታ ያለባቸውንና የሌለባቸውን ሰዎች ለመለየት ስለሚያስችል ቢያንስ የቫይረሱ የስርጭት ፍጥነት ለመቀነስ ይረዳል›› ብለዋል።

‹‹የቫይረሱ ፍጥነት በመቀነስ ሆስፒታሎቹ እንዲተነፍሱ ማድረግ ይቻላል›› ሲሉም ልምዳቸውን አካፍለዋል። ካልሆነ ቁጥሩ ብዛት ያላቸው ሕመምተኞች አገልግሎት ፍለጋ ሲመጡ የጤና አጠባበቅ ስርዓቶችን ያፈናቅላሉ፣ እናም ብሔራዊ ጥፋት ያስከትላሉ። አሜሪካውያን እና ሌሎችም ‹‹ዝግጁ መሆን አለባቸው›› ብለው አሳስበዋል።

 

ኢትዮጵያ ከዚህ  ምን ትማራለች?

በጣልያንና በኢትዮጵያ መካከል ከኢኮኖሚ አቅማቸው ባሻገር የዴሞክራሲ ባህል ልዩነት እንዳላቸው ግልፅ ነው። ቻይና የቫይረሱ መገኛ ብትሆንም በሚገባ ቁጥጥር ስታደርግ፣ ለጣልያን ፈተና የሆነባትም የሰውን እንቅስቃሴ ለመገደብ ከምትከተለው የግለሰብ ነፃነት ጋር የሚጋጭ በመሆኑ እንደሆነ ተወስቷል። ለዚህም ነው ሌሎች የምዕራቡ ዓለም አገራት ከጣልያን መማር አለባቸው የሚባለው።

ኢትዮጵያም እንደዚሁ ብዙ መማር ያስፈልጋታል። አገራችን በኢኮኖሚ አቅሟ ድሃ ከሚባሉት ተርታ እንደመሆኗ በዚህ አደገኛ ቫይረስ ስርጭት የተነሳ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ከገባች፣ በቀላሉ ለማገገም የማያስችል አዘቅት ውስጥ እንዳትገባ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን አሁን ነው።

በዚህ አያያዛችን ከጥንቃቄ ጉድለታችን የተነሳ፣ ቫይረሱን ጎትተን ማስገባታችን አይቀርም። የበለፀጉት አገራት ተቆጣጥረው እኛም በተራችን ከቫይረሱ ጋር ግብግብ ውስጥ ስንገባ ከእኛ ጋር ማንኛውም አይነት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ማድረግ የሚፈልግ አገር አይኖርም። የተገለልን እንሆናለን። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ የትኛውም አገር እንዲበር አይፈቀድለትም። የማንም ሀገር ዜጋ ኢትዮጵያን ሊጎበኝ እግሩን አያነሳም።

የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ብዙ ሃብት (ማለትም ሆስፒታሎች፣ አልጋዎች፣ ባለሙያዎች) ይስፈልጋል። እንደ ድህነታችን ኤች.አይ.ቪ. ኤድስን ጨምሮ ብዙ አሳሳቢ የጤና ችግር የተጋፈጠች አገር ውስጥ ነን። የዐቢይ አሕመድ መንግሥት እንደጣልያን መንግሥት፣ ለአዲሱ ቫይረስ ተጋላጭ በሚያደርገን መልኩ መዳፈሩ ዋጋ እንዳያስከፍለን ያስፈራል።

በጣልያንም የተፈጠረው ከዚህ የተለየ ስህተት አይደለም። ከሌሎቹ የአውሮፓ ትላልቅ አገራት ሲነፃፀር የጣልያን ኢኮኖሚ በቱሪዝም ላይ የሙጥኝ ያለ ነው። ማእከላዊ መንግሥቱም ይህንን ክፍለ ኢኮኖሚ እንዳይጎዳበት በተቻለው መጠን በዜጎቹ ላይ የሚደርሰውን አደጋ እንዳላየ ሆኖ ሲያልፍ በዚህም ከክልል መስተዳድሮቹ አቤቱታ የሚጋጭ መግለጫ ይሰጥ እንደነበር፣ ባለፉት ወራ በጣልያን ከሆነው ታሪክ በሚገባ መረዳት ይቻላል።

ሁኔታው እያየለ ሲመጣ ግን የማእከላዊ መንግሥቱ ውሳኔ ሱሪ በአንገት ሆነ። ግን ምን ያደርጋል! እድሎቹ ቀድመው አልፈዋል። እድል ቆሞ አይጠብቅም። ልክ እንደዚሁ ለኢትዮጵያም የተከፈተ መምለጫ በርና የተሰጠ እድል ቆሞ አይጠብቀንም። እድሉ ካለፈን ተመልሶ እንደማይመጣ ከጣልያን መማር አለብን።

ሌላው በማእከላዊ መንግሥት እንዲሁም በክልል መስተዳደሮች እውቅና እየተካሄደ ያለው የፓርቲ ሥልጠናዎችና ስብሰባዎች በአስቸኳይ እንዲቋረጡና ኅብረተሰቡም እንደጣልያን ሕዝብ ብዥታና ግራ መጋባት ውስጥ እንዳይገባ ስለቫይረሱ ስርጭት ወጥነት ያለው እንደዚሁም በተግባር የሚታይ እርምጃ ይፈልጋል።

አለበለዚያ የመንግሥት አካላት የሚናገሩትና የሚያደርጉትን አልገጥም ሲል፣ ኅብረተሰቡም የተጋረጠውን ስጋት ከምንም ሳይቆይር የተለመደው እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ይቀጥላል። በዚህም መጨረሻው የጤና አቅርቦት ብቻ ሳይሆን አገርም ሊፈርስ ይችላል።

በመጨረሻም ከዚህ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዋጋ የሚያስከፍል ውሳኔ በተጨማሪ፣ ለሕዝቡ ምሳሌ ይሆናሉ የሚባሉት ባለሥልጣናት (የቫይረሱን ስርጭት እንዲቆጣጠሩ ሃላፊነት የተሰጣቸው የኮሚቴ አባላት ጭምር) ተጠጋግተው በመቀመጥ የሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫን ሲመለከት ሕዝቡ የቫይረሱን ስርጫት እንደቀልድ እንጂ እንደስጋት እንዳይቆጥረው በማድረግ ሌላ ግራ መጋባት ውስጥ ሊገባ ይችላል።

በዚህም ሕዝቡ ከመሪዎቹ በሚያየው አረአያነት የተነሳ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዳያደርግ የሚገፋፉ እንዳይሆን ያሰጋል። ማእከላዊው መንግሥት ከክልል መስተዳደሮች ጋር በሚገባ ተናብቦ ጠናካራ የሆነ ጥብቅ የእንቅስቃሴና ክልከላ ለማድረግ የዘገየ ቢሆንም፣ አሁንም እድሉ አለ። ያዝ ለቀቅ የሚመስሉ የዘመቻ ሥራ መሆኑ ቀርቶ፣ በተጠናከረ መልኩ ክልከላ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን።

ለማጠቃለል ለአንባቢዎች የማስተላልፈው መልዕክት፣ የታዘዙት የንፅህና አጠባበቅ መመሪያዎችን በሚገባ መከተል እንዳለብን ነው። በተጨማሪም ቫይረሱን ለመዋጋት የሰውነታችን በሽታ የመከላከል ስርዓታችንን ከፍ ለማድረግ በቪታሚን ሲ የበለፀጉ ምግቦችን መጠቀም ቫይረሱ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመግታትም ይመከራል።

እንዲሁም የቫይረሱ ተጠቂ ከሆንን ወይም አለብን ብለን ስጋት ከገባን፣ ወደ ሌሎች እንዳይተላለፍ የሚጠበቅብን የራሳችን ኃላፊነት መውሰድ አለብን። ሌላው ማኅበራዊ መራራቅን (Social distancing) ለጥንቃቄ መተግበር ቫይረሱን ለመዋጋት ቁልፍ በመሆኑ መመሪያውን እየተገበርን ለአረጋውያንና በቀላሉ ሊጎዱ የሚችሉ ሰዎች በዚህ ወቅት በሚገባ ልናስብ ይገባል።

ከመጣው መዓት ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን እንዲጠብቅልን በርትተን መፀለይም አለብን።

 

ሽመልስ በ Shimelis.A.Geda@agrar.uni-giessen.de ይገኛሉ፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com