አልን ተባልን አስባልን ይባላል

0
1186

ዓለም በብዙ ለውጦች ውስጥ አልፋለች። በድሉ አበበ በአፍሪካ እንዲሁም በተለያዩ አገራት የተፈጠሩ ለውጦችንና ለለውጦቹም መነሻ የነበሩ ማዕበል ያሏቸውን አመጽና ትግሎች በምልሰት አንስተዋል። ‹መነሻ ሐሳቡ የወሰድኩት ከደራሲ አብረሃም ረታ ዓለሙ (ነፍሰ ኄር) “አልን፤ ተባልን፤ አስባልን ይባላልና ሌሎችም” መጽሐፍ ነው ብለው፤ ወደኋ መልሰው የቀደሙ የለውጥ ትግልና ሂደቶችን አስቃኝተዋል።

የዚህ ዓለም አንድ አካል ነንና፤ ለውጥም፣ ማዕበልም፣ አብዮትም የዕጣ ፈንታችን አንድ አካል ነው። በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ደግሞ ይህ ሁኔታ የሚገጥመውና የማይገጥመው ትውልድ አለ። በሌላም መልኩ ይሄን ሁኔታ ወደ መልካም አጋጣሚ በመለወጥ ለተሻለ ነገና ትውልድ ለሚጠቅም ያዋሉ እንዳሉ ሁሉ፤ ልዩነታችንን ለማስፋት የሚጠቀምበት ሞልቷል። ልዩነት ደግሞ ለዘላለም ይኑር! ውበት ነውና። ኢትዮጵያም እንደጊዜው በየትውልዱ አንድ አብዮት አልያም የለውጥ ማዕበል ያናጋታል። ሰሜን ከደቡብ፤ ሐሳብ ከሐሳብ፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ሕዝብ ከሕዝብ የሚመስል ተቃርኖ፤ የትርክት ንትርክ፤ ዋልታ ረግጥ አመለካከት፣ የእኔ እበልጥ ባይነት ሙግትና ለአንድ የሳር ቤት ክዳን የማይመስል የሳር ሽሚያ ታይቶብናል።

በዚህ የኃያላን ፍልሚያ መሃል ዜጋ ይገደላል፤ ሰው ይሰደዳል፤ የአገርና የግለሰቦች ሀብት ይወድማል። የአገር ዕዳም በአንድ ዲጂት ይጨምራል። እኛም ያንን ለመክፈል ትውልድ አንሰዋለን። ጊዜም በግራ ዐይኑ እየጠቀሰ ያፏጭብናል። እኛም ባላየ እያለፍን ከዛሬ ደርስን። እስቲ እኛም በጊዜያችን ስለኖርነው አንድ የለውጥ እጥፋት በጨረፍታ ምን እያልን፤ እየተባልን፤ እያስባልን እዚህ እንደደረስን እናነባለን።

ኢትዮጵያ እንደማንኛውም አገር በእኛም ዘመን፤ በ1990ዎች መጨረሻና 2000 መጀመሪያ ለለውጥ ታጥቃ ተነስታ ነበር። የቱኒዚያው የሞሃመድ ቦአዚዝ ተምሮ ሥራ ማጣት፤ መንገድ ዳር የሚነግድባትን ኩርማን መንጠቅ ፕሬዝደንቱን ማደሪያ ያሳጣል ብሎ የገመተ አልነበረም። በአንድ ወጣት ቁጣ የተጀመረ አመጽ የአንድ አገር ፕሬዝደንት በሕዝብ ማእበል አሽቀነጠረ። በዚያውም የፕሬዝደንቱ ባለቤት የዱባይ ቅንጡ ግብይትም ላይመለስ ተሸኘ። ቀጥሎም ግብጽ ለምን አልሞክርም ብላ ታህሪር አደባባይ ውላ አደረች። የካይሮ የጸጥታ ኃይሎች ሊያስቆሙት አልቻሉም። ‹The Facebook Revolution› አንድ መሪ ቀይራ፤ ለሌላው ተሞክሮ አካፈለች። መንበሩ ወዲያው አልረጋም። የሙስሊም ወንድማማቾቹ ፕሬዝደንት ዶ/ር ሙርሲ በታህሪር አደባባይ አመጽ ወደ ሥልጣን እንደመጣ በታህሪር አደባባይ አመጽ ተሸኘ። ፕሬዝደንት አልሲሲ የሰነበቱ ይመስላል።

የመን ልሞክረው ብላ እንደገባችበት የፖለቲካ ወንዝ ዋናው ረዘመባት። ሶሪያ አልተነሳችም፤ ታሪካዊቷ ቁስጥንጥንያንና ታሪካዊቷ አሌፖ ዓለም እያለቀሰላቸው ጥልቅ እንቅልፋቸውን ይለጥጣሉ። አልጄሪያ የማእድን አልማዟ፤ የአፍሪካ የማዕድን ቋቷ ማዕከላዊ ዴሞክራሲያዊት ኮንጎ ዛሬም በአንጃ ተከፋፍላ ትታኮሳለች። ጎረቤታችን ሱዳን እስቲ ልሞክረው ብላ ጥርሰ ወርቁን ከዙፋን ገፍታ፤ ወደ ሽግግር ዘው ብላ ገብታ ነበር፤ የሽማግሌ ብዛት ከቀውሱ ባይታደጋትም ቅሉ። ልዩነትን መፍታት የተሳናችው ባለሥልጣናት ፍትጊያ የደቡብ ሱዳን ሕጻናትና ሴቶች ከኻያ ዓመታት በላይ በድህነት ማቅና በንጹህ ውሃ እጦት ይማቅቃሉ።

የኔ ትውልድ ዕጣ ፈንታም ከለውጥ ሙከራ አላመለጠም። የ1960ዎችን ዕርጅናና ፍረጃን ተጭኖ፤ የ1970ዎችን ጀብድ፤ ትዝታና ፀፀትን ታዝሎ፤ የ1980ዎችን የተጋጋለ ተቃርኖን ታቅፎ፤ የ1990ዎችን ኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ውሎን ታክኮ፤ ለተሻለ ምርጫ ተስፋና ቀቢፀ ተስፋ ተብሰልስሎ፤ በሚሊኒየም ብልጭልጭታ ከለላ የታለፈ የመሰለው የፖለቲካ ትኩሳት በ“ደፈጣ” ውስጥ ለውስጥ እየተብላላ ነበር። ስንጀምረው ውጥናችን ላይ ብዙም ልዩነት አልነበረንም። ከአገር ውስጥም ከአገር ውጭም፤ የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም፤ ፕሮፌሰር ብርሀኑም ጃዋር መሐመድም፤ አንዳርጋቸው ጽጌም ልደቱም፤ ፕሮፌሰር መረራም፣ ሌንጮ ባቲም ታግለው ያታግሉ ነበር። ለአንድ ዓላማ። እደግመዋለሁ ለአንድ አላማ። ኢሕአዴግን ለመገርሰስ፤ ‹ኢህአዴግ ቁጥር አንድን› ለመገርሰስ ። ‹The end justifies the means› በሚለው መርህ እየማሉ፤ እየተገዘቱ፤ ቀን ቀን በአውደ ውይይትና አውደ ጥናት ማታ ማታ በኢሳት ቴሌቪዥን ይቀሰቅሱን ነበር። ‹The means gauge the end› ስላላሉን እኛም ሳንጠይቅ፤ ጊዜ አልነበረንምና ሕይወትም ሰልፏ ከብዶን ሰለነበር በስሜትም በስሌትም ተከተልናቸው።

በወቅቱ መንግሥትም ጣራ ላይ የመውጣት ስፖርት ቀን በቀን ይሠራም ያሰራም ነበር። የግንብ አጥር ነሽ፤ የእንጨት አጥር ነሽ፤ ቪላ ነሽ የደሳሳ ጎጆ፤ የኮንዶሚኒየም ሕንጻ አልቀረ ዲሽ ለማውረድ ቤት ለቤት ይርመሰመስ ነበር። ዲሽ ለመንቀል በጀት ይመደባል። ጎረቤት ጎርቤቱን ምን ሚዲያ እንደሚከታትል፤ ማንን እንደሚወድና እንደሚሰማ፤ ምን እንደሚወድ ምን እንደሚጠላ በእጅ አዙር ይከታተላል። ለሚመለከተው ሪፖርት ያቀርባል፤ የ40 ሚሊዮን ሕዝብ የቴሌቪዥንና ሪሞቱን ለመቆጣጠር!።

ጊዜው የመረጃ ነው የሚለው አባባል የኢትዮጵያን አየር ሞልቶት ነበር። መንግሥት በጊዜው ጆሮ ዳባ ልበስ ቢልም። ዲሽ አውራጆች ሲወርዱ፤ ከኋላ ኪሱ በማውጣት በአምስት ደቂቃ ውስጥ ቻናል የሚቀይርልን ደፋር ወጣት እዛው ቆሞ ቶሎ ፈተው አይሄዱም እንዴ እያለ ዐይኑን ያሻሽ ነበር። በኋላማ ልጆቹን ማሰር ሰለቻቸው መሰል ዲሹንም መውሰድ ጀምረው ነበር አሉ።

አገር ስንት ተሰሚ ድምጽ ያስፈልጋታል፤ የብዙ ሕዝብ አገር የበዛ ድምጽ አያስፈልጋትምን? ድምጽ ሳጥን ያለው ሁሉ ማውራት ቢኖርበትም ለአገር ሲሆን ግን የተመረጡ ድምጾች አየሩን ቢመሉት አይሻልምን? በወቅቱ ግን አንድ ጉምቱ ድምጽ አየሩን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮት ነበር ብንል ማጋነን አይሆንም። ተፈጥሮም በትዝብት ትመለከት ነበር። አንድ ድምጽ ስንት ዘመን ብቻውን ዐየሩን ሊሞላው ይችላል? ይሄ በራሱ ለሕዝብ የለውጥ ናፍቆት በቂ እርሾ ነበር።
በዘመናችን ብዙ ፖለቲከኞቻችንም ልዩነታቸውን ላለማቻቻልና ከሚመጣው ማዕበል ለመጠቀም ስለሚቋምጡ ከማርገብ ይልቅ ሲያጋግሉት ይታያል።

ጥቅምት 28/1998 በ “ረጅሙ የታሰረች ዶሮ የተፈታች ይመሰላታል“ ብሎ ሰብስቦ ያሰረው ኢሕአዴግ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ውሳኔ፤ “ሳስበው ሳስበው ደከመኝ” ተረትና በ ”fiscal economy” ተረባ፤ በ”አገርና ሴት መድፈር” ንጽጽር፤ በዶ/ር መረራ የፓርላማ ወግ፤ በአቶ ቡልቻ “ልጄ ነህ ስማኝ” ተማጽኖ ሚሊኒየሙ ካልገባሁ እያለ ይታገል ነበር።

ዶክተሮቹ፣ ኢንጅነሮቹ፣ ፕሮፌሰሮቹ ታስረው የተፈቱ የቅንጅት ፓርቲ አባላት በይቅርታ ጉዳይ ላይ በአደባባይ በሚዲያ የየራሳቸውን እውነት ለተከዳው ሕዝብ ይገልጹ ነበር። እውነት አንድም ብዙም ናትና ሕዝቡም በመገረም ቤቱ ውስጥ ሆኖ ይሰማ ነበር። ከዕስር ቤት መልስም በየፊናችው የራሳቸውን መጽሐፍ በመጻፍ የዘመኑን አየር ተቆጣጥረውታል። በአዲስ ነገር ጋዜጣ ጋዜጠኞች ስደት፤ በቃሊቲ ምስጢሮች ጉጉት፤ በአገቱኒ ተምረን ወጣን ትምህርት፤ በ‹የነጻነት ጎህ ሲቀድ› ተስፋ፤ በዞን ዘጠኝ ጦማር፤ በእንጉርጉሮ ግጥምና ዜማ፤ በቃሌ ቃል ቅትት፤ በነጋሶ መንገድ ቁዘማ፤ በልደቱ አያሌው መድሎት፤ 200ዎች መጣሁ ገባሁ እያለን ነበር፤ ሌላ ምርጫ አለበታ!

ለምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎች ከአገር ውስጥም ከአገር ውጭ ሆነው፤ አንድም ብዙም፤ ብዙም አንድም ሆነው፤ ሥልጠና የሰጡም ያሰጡም፤ በምርጫው የተሳተፉም ፓርቲዎች አንድ ካሉሺያን በፓርላማ ወክለው አረፉት። ኢሕአዴግ ሙሉ በሙሉ አሸነፈ ተባለ። ይህም የ2002 ምርጫን ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ በ99.6% አሸንፎ መመረጡን “ምርጫ ቦርድ” አበሰረ። ሕዝቡም፡-
“ባርሳ የሚያሸንፈው አምስት ለዜሮ ነው፤
ማንቼ የሚረታው ሁለት ለዜሮ ነው፤
የዘንድሮ ነገር መቶ በመቶ ነው።” ብሎ በአዝማሪ አፍ ትዝብቱን ዘፈነ።

ሕይወት ቀጠለ። መንግሥትም ተመርጫለሁ፤ የሕዝብ ይሁንታ አግኝቻለሁ ብሎ ወደ ቀድሞ ግብሩ ተመለሰ። ነገሮች ለጊዜውም ቢሆን የተረጋጉ መሰሉ። አዋጅ በአዋጅ ላይ ማውጣቱን ቀጠለ፤ 2003 ብዙ አዋጆች የወጡበት ዓመት ሳይሆን ይቀራል? የሕዝቡ ልብ ግን አሁንም እንደኮበለለ ነበር። ሲጠሩት ይሰበሰባል፤ የሚሉትን ይሰማል፤ ወደ ቤቱ ይመለሳል። ቤቱ ከገባ በኋላ ግን ቡና ላይ የልብ የልቡን መንግሥትን ሲያማ ይውል ነበር። ደራሲውም በብዕሩ፡-
“ንብ ኑሮ ለውጣ ኑሮዋን ቀየረች፤
አበባ መቅሰምን ኋላቀር ነው አለች።
ዛሬ ተሻሽላ ሥራን መናቅ ትታ፤
በየጉራንጉሯ ከሕዝብ ተጋፍታ።
ጣፋጭ ወለላዋን ማመንጨቷን ትታ፤
ስኳር ትልሳለች ብርጭቆ ውስጥ ገብታ።”

የተመረጠው መንግሥት አንድ ዓመት እንኳን ሳይሞላው የሕዝብ ተቃውሞ ገጠመው። የዘመኑ መንፈስ የራሱ ልዩ ቀለም ነበረው። ጊዜው የጥልቅ ዝምታ ወቅትም ነበር። ጥልቅ ዝምታም፤ ጥልቅ ፍርሀት ውስጥ አገሩን ከቶት ነበር። የረዘመ ዝምታ መጨረሻው ጩኸት ነውና፤ የውስጥ ጥልቅ ዝምታ፤ ፍርሃትና ጩኸት ወደ አደባባይ ጩኸት ለመለወጥ እንደ ፍም እሳት ውስጥ ለውስጥ እየተቀጣጠለ ነበር።

ተጀመረ። ዘመኑን የሞገቱ ተከታታይ ድምፆች እንደ እሩምታ እዛም እዚህም ይተኮሱ ነበር። ወቅቱ የድምጻችን ይሰማ ድምጾች ይሰሙ የጀመረበት ወቅትም ነበር። በየሳምንቱ አርብ ጁምዓ ላይ ፌዴራል ፖሊስ በቆመበት፤ እጅግ ጥበቃ በበዛበት ሁኔታ አምልኮቱ ቀጠለ። መስጂድና መድራሳዎች ከወትሮው በተለየ ሞልተው ፈሰሱ። ምድራዊው መንግሥት ስላልስማ፤ አላህ መልስ አንዲሰጥ በፌዴራል ፖሊስ ታጅቦ ዱዓው በየለቱ አርብ ቀጠለ። ይሄ ሁኔታ ከኹለት ዓመታት ያህል በላይ ዘለቀ። የክርስትና እምነት ተከታዮችም የሙስሊም ወንድሞቻችን ጥያቄ መልስ ይሰጠው ብለው ተቃውሞውን ተቀላቀሉ። አየሩ በሙሉ ለመንግሥት ሳንባ የተስማማ አልነበረም። አብዛኛው ሰው በየቤቱ ያጉረመርም ነበር። እንዲያውም በውስጡ የጠፋበትን አንድ ነገር፤ የጠፋበትን ከተማ እያሰሰ ነበር። መንግሥት ትንፋሽ ሊያጥረው እንደሚችል ምልክቶች እዚህም እዚያም ይታዩ ነበር።

መንግሥትም መልስ እንደመስጠት አስተባባሪ ኮሚቴውን አሰረ። ይሄ ደግሞ ተቃውሞውን የበለጠ አቀጣጠለው። ከመንግሥት ጋራ ሌባና ፖሊስ ጨዋታው ደራ። መብታችን ይከበር፤ ለጥያቄያችን መልስ ይሰጥ ሲል ሁሉም አጉረመረመ። አንዋር መስጂድ እጅግ በደመቀ፤ ኮሽታና ችግር ሳይፈጠር በሚያስደንቅ የሃይማኖት ድባብ ሺዎች በአደባባይ ሰግደው መግባት የሁልጊዜ ተግባር ሆነ። ረባሽና ተረባሽ ቦታ ተቀያየሩ። ሕግ አስከባሪና ሕግ አክባሪ ጉዟቸው ለየቅል ሆነ። የአገር ውስጥ ሚዲያም፤ ዓለምም እየተደነቀ ዜናውን ተቀባበለ። በይሆናል ተስፋ የሚመጣውን መናፈቅ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ሆነ። ገጣሚው በብዕሩ ዘመንን እየታዘበ፡

“…ቤልማ
በምሥራቅ ነፋስ ተባብረሽ የተሰወርሽው ከተማ።
የሰይፋችን ሰገባ ነሽ የወጋችን ማሳረጊያ
የተስፋችን መዳረሻ የውርደታችን ማብቂያ፤
ካንቺ መምጣት ካንቺ መፍካት
ምን ውርስ አለን?
ትርፍ ምኞት? ሌላ መሻት?
ቤልማ።” ይል ነበር።

ዞን ዘጠኝ የተባለ የዘጠኝ የወጣቶች ስብስብ ‹ክበብ› ጥያቄውንም መልሱንም በግልና በማኅበራዊ ድረ ገፅ ጦመረ። መንግሥትም አባሮሽና እስሩን አስቀጠለ። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሰልፍ ጠሩ። አደባባዩም በየፊናው ጥያቄውን አስተጋባ። ምሁራንም የመድረክ ተዋስዖውን በገደብም ቢሆን ጀመሩት። ከ‹አደገኛ ቦዘኔነት› የተረፈው ወጣት፤ ልቡ ለመንግሥት የሚተኛ አልነበረም። ሥራ አጥነቱ በዚያ ላይ ቤንዚን ሆኖ ያቀጣጥል ነበር። አድሎአዊነቱ ዐይን ያወጣ ነበር። የጦርነትና የምርጫ አንጎቨር ያልወጣለት ሕዝብ በየጥጋጥጉ ያጉረመርም ነበር። የምሁሩ ‹አገሬ ገመናሽ› እዚህም እዚያም፤ በጋዜጣም፤ በመጽሐፍም፤ በስስ ቅጂም ተስተጋብቷል።

በድሉ አበበ በጅማ ዩኒቨርሲቲ በኅብረተሰብ ጤና የሦስተኛ ዲግሪ (PhD) ተማሪ ናቸው። በአድራሻቸው [email protected] ላይ ይገኛሉ፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here