በሚቀጥለው አንድ ወር ድርቅ ባለባቸው አካባቢዎች መደበኛ ዝናብ እንደሚኖር ይጠበቃል

0
753

በሚቀጥለው አንድ ወር ድርቅ ባለባቸው በኦሮሚያ እና በአፋር ክልሎች መደበኛ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አህመድን አብዲከሪብ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ በአሁን ወቅት ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ያለው እርጥበታማ አየር እየጨመረ መጥቷል። በዚህም የተነሳ ከሚቀጥለው ሳምንት ማለትም ከመጋቢት 11/2014 ጀምሮ በቀጣይ አንድ ወር በሰሜን ምሥራቅ፣ በመካከለኛው እና በደቡብ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከመደበኛ ወቅት ጋር የተቀራረበ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የአየር ትንበያ መረጃዎች አሳይተዋል ብለዋል።

ባለፈው የካቲት ወር እና ያለፈውን አንድ ሳምንት ጨምሮ ለዝናብ መፈጠር ምክንያት የሆኑ ምልክቶች እየተጠናከሩ ሊሔዱ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ እንደሚሆን የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ትንበያ መስጠቱ አይዘነጋም።

በአንጻሩ ባለፈው ወር የሰሜን ምሥራቅ፣ የመካከለኛውና የደቡብ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከመደበኛ ወቅት ጋር የተቀራረበ ዝናብ ሊያገኙ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ የነበረ ቢሆንም፣ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የነበረው እርጥበታማ አየር መቀነሱን ተከትሎ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ደረቃማ ወራት ሆነው ሊያልፉ እንደቻሉ ተጠቁሟል።

አህመዲን አክለውም፣ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ከላይ ከተጠቀሱት ቦታዎች ጎን ለጎን በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን፣ ኢሉ አባቡር፣ ምዕራብ እና ምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ በአርሲ እና በባሌ ዞን፣ በቦረና ዞን፣ በጉጂ ዞን፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በአብዛኛው አካባቢዎቻቸው ላይ መጠነኛ የሆነ እርጥበት የሚያገኙበት ወቅት እንደሚሆን አመልክተዋል።

ከዚህ ባሻገር ከአፋር ክልል ዞን ሦስት እና አምስት፣ ከአማራ ክልል ሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ እና ምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ደቡብ ጎንደር፣ የባህር ዳር ከተማ እና ዙሪያዋ፣ ከትግራይ ክልል የመካከለኛው ምሥራቅ እና የደቡብ ትግራይ ዞኖች፣ ደቡብ በሁሉም ዞኖች ለማለት በሚያስችል ሁኔታ፣ እንዲሁም የጋምቤላ ክልል ጨምሮ አብዛኛው ቦታዎች ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ እና በጥቂት አካባቢዎቻቸው ደግሞ ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ እንደሚያገኙ ተገልጿል።

የተቀሩት የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ እንዲሁ ደረቃማ እና ፀሐያማ የአየር ጸባይ ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል የትንበያ ዘገባዎች እንደሚያሳዩ ኃላፊው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ድርቅ በተከሰተባቸው ቦታዎች ማለትም በኦሮሚያ ክልል ባሌና ቦረና ዞን፣ በአፋር ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተወሰነ መልኩ እርጥበት እንደሚያገኙ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም ለከብቶች መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ለግጦሽ መሬት ጉልህ ጥቅም እንደሚኖረው ይታመናል።

ኃላፊው አያይዘው በተያዘው ወር በሱማሌ ክልል እርጥበት የሚገኝበት እድል ጠባብ ሊሆን ስለሚችል ኅብረተሰቡ ጥንቃቄዎችን እንዲያደርግ እና መንግሥትም እንደሚያደርገው የተለመዱ ሥራዎችን ሊያስቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ የበልግ ወቅት ትንበያን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፣ የዘንድሮው የበልግ ወቅት ሊዘገይ እንደሚችል እና መደበኛና ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ እንደሚጠበቅ ቀድሞ አሳውቋል። ኅብረተሰቡ ዘግይቶም ቢሆን የሚገኘውን እርጥበት፣ ውኃን በአግባቡ ለሚፈለገው ዓላማ እንዲጠቀም፤ በተለይም በኃይል ማመንጫ ግድቦች ላይ የሚገኘው ውኃ ከሚጠናከረው ከፍተኛ ሙቀት ጋር ተያይዞ የመትነን ዕድል ስለሚኖረው በአግባቡ ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውል ማሳሰቡ ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here