ሰኞ መጋቢት 12 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ቅዳሜ መጋቢት 10/2014 በአዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ቡልቡላ ከተማ በተካሄደ የሚሊሻ ምርቃት ላይ በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ የ12 ዓመት ታዳጊን ጨምሮ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉን የወረዳው አስተዳዳሪ አስታወቁ።
ህይወታቸው ካለፈው ሰዎች መካከል ሦስቱ ለ20 ቀናት ሥልጠና ላይ ቆይተው በዕለቱ ይመረቁ የነበሩ የሚሊሻ አባላት መሆናቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ ሙሐመድ በሪሶ ገልፀዋል።
በዕለቱ በቡልቡላ ከተማ ስታዲየም በርካታ ነዋሪዎች በተገኙበት ከ200 በላይ የሚሊሻ አባላት መመረቃቸውን ተናግረዋል።
ይሁንና የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ተጠናቅቆ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከመድረኩ ከተሸኙ በኋላ፤ ሕዝቡና የሚሊሻ አባላት በደስታ እየጨፈሩ እያለ የቦንብ ፍንዳታው መድረሱን ተናግረዋል።
ከሞቱት ሰዎች ውጪም 35 የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸውን ባለሥልጣኑ ገልፀዋል።
ሙሐመድ አክለውም ፍንዳታውን በማድረስ የተጠረጠሩ ሦስት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ከምረቃ ፕሮግራሙ በፊት አነስተኛ ፕሮግራሞች እንደነበሩ ያስታወሱት ኃላፊው፣ ዋናው የምረቃ ፕሮግራም ከመጀመሩ በፊት ጥብቅ ፍተሻ እንደነበር በመግለጽ፣ የቦንብ ፍንዳታው የደረሰው ተቀብሮ ይሆን ተወርውሮ እየተጣራ ነው ብለዋል።
“ይህንን ቦንብ ያፈነዳው ጠላት” ነው ሲሉ የገለፁት ባለሥልጣኑ ፍንዳታውን ያደረሰው ማን እንደሆነ እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል። ለቦንብ ፍንዳታው እስካሁን ድረስ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም።
በዚህ ቦንብ ፍንዳታ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች በትናንትናው ዕለት የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው መፈፀሙን ተናግረዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




