42 ኪሎ ግራም ኮኬይን የተሰኘው አደንዛዥ ዕፅ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋለ

0
981

በአጠቃላይ በኹለት ሳምንት ውስጥ ከ63 ኪሎ ግራም በላይ ኮኬይን መያዙም ተገልጿል

ማክሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ኮኬይን የተሰኘ አደንዛዥ ዕፅ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ትናንት ማለትም መጋቢት 12 ቀን 2014 ከምሸቱ 2፡30 ላይ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የኢትዮጰያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።

ሦስት የናይጄሪያ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች መነሻቸውን ብራዝል-ሳኦፖሎ በማድረግ በኢትዮጵያ በኩል ወደተለያዩ አገራት 1 ሺህ 895 ጥቅል ፍሬ (42 ኪሎ ግራም) የሚመዝን ኮኬይን በቦርሳ ይዘው ለማለፍ ሲሞክሩ የኢትዮጰያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት ባደረጉት ፍተሻ በቁጥጥር ሥር መዋላችውን የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ አደጋኛ ዕፅ ቁጥጥር ማስተባበሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር አዲሱ ባለኒ ገልፀዋል፡፡

ኢንስፔክተሩ አያይዘውም ግለሰቦቹ በአየር መንገዱ ጣቢያ ውስጥ ግርግር በመፍጠር እና ከሰራተኞች ጋር በመጋጨት ለማምለጥ ሙከራ ቢያደርጉም በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ መነሻዋን ብራዝል ሳኦፖሎ መዳረሻዋን ደግሞ በኢትዮጵያ በኩል ዱባይ ለማድረግ 1 ሺህ 49 ጥቅል ፍሬ (21 ኪሎ ግራም ከ380 ግራም) የሚመዝን ኮኬይን ይዛ የተገኘች ብራዝላዊት የኢትዮጰያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት ባደረጉት ፍተሻ የካቲት 24 ቀን 2014 በቁጥጥር ሥር መዋል መቻሏን ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ 15 ቀን ውስጥ 2044 ጥቅል ፍሬ (63 ኪሎ ግራም ከ380 ግራም) ኮኬይን መያዙን ጠቁመዋል፡፡

የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ተይዘው ወደ ፍርድ ቤት ቀርበው ውሳኔ ሳያገኙ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው ከእስር ከወጡ በኋላ በቀጠሮ ቀን ተመልሰዉ ሳይቀርቡ ስለሚቀሩ እና አደንዛዥ ዕፁን ይዘው ለሚገኙ ሰዎች የሚሰጥ ውሳኔ አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት ዝውውሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ኢንስፔክተር አዲሱ ገልፀዋል፡፡

የአዘዋዋሪዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ በመምጣቱም ህጉ መሻሻል አለበት ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዝውውሩን ለመከላከል በአየር መንገዱ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝና የተጠርጣሪዎቹ ጉዳይም በወንጀል ምርመራ ቢሮ እየተጣራ መሆኑን መግለፃቸውን ከኢትዮጰያ ፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here