ኮቪድ19 – የሴቶችን የመብት ትግል ይፈትነው ይሆን?

Views: 621

ኮቪድ19 የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ የሰው ልጅን በቀለም፣ በዘር፣ ሃይማኖትና ብሔር ሳይለይ እያጠቃ ያለ ቫይረስ ነው። ወረርሽኝ እንደሆነና ዓለምን የሚያሰጋ ስለመሆኑ የዓለም የጤና ድርጅት ይፋ ካደረገ ጀምሮም፣ የሁሉም አጀንዳ ሆኗል፤ ቫይረሱ። ምንም እንኳ ያለምንም ልዩነት ሰውን ሁሉ ሲያጠቃ ቢታይም፣ የተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙኀን ወረርሽኙ ከወንዶች ይልቅ ሴቶችን ጎድቷል ሲሉ በገጾቻቸው ይዘው ወጥተዋል።

ዘ አትላንቲክ ይህን አስመልክቶ ባስነበበው ዘገባ፣ እንዲህ ያሉ ወረርሽኖች በሰዎች መካከል የጎደለውን እኩልነት አጉልቶ ማሳያ ናቸው ሲል አስቀምጧል። ምክንያቱም ከቤት አትውጡ ቢባል ቤታቸው ሆነው መሥራት የሚችሉ፣ ደሞዛቸው ሳይቋረጥ የሚሰጣቸውና ጥቅም የማይጎድልባቸው ሰዎች አሉ። በቅንጡ ቤት ውስጥ ሆኖ ራስን ማግለልና በጎስቋላ ቤት ውስጥ ታስሮ መዋልም ለየቅል ናቸው።

ከሁሉም በላይ ግን ይላል ዘገባው፣ ከሁሉም በላይ ግን የሴቶች ነጻነት ጉዳይ ጉዳት ከሚደርስባቸው መካከል ነው።
የምናውቀው እውነት አለ፤ የቫይረሱ ወረርሽኝ የሕዝብ ጤና አገልግሎትን አቃውሷል። የኢኮኖሚ አውድም መናጋትን አስተናግዷል፤ የባሰውንም ጠብቁ እያሉ ባለሞያዎች በየጊዜው እያሳሰቡ ነው። ትምህርት ቤቶችና የሕጻናት ማቆያዎች በመዘጋታቸውም ሰዎች ልጆቻቸውን ከፍለው ከማስጠበቅ፣ የማይከፈልበት እናት እንክብካቤ ላይ እንዲያሳርፉ አድርጓቸዋል።

ታድያ እንዲህ ያሉ በአገር ላይ መናጋትን የሚያስከትሉ ወረርሽኞች፣ በሥርዓተ ጾታ ላይ ጉዳት ያደርሳሉ፣ በበርካታ ምሁራን እይታ። ለዚህም የቀደሙትን ወረርሽኖች እንደማሳያ የሚያነሱ ሲሆን፣ ኢቦላ፣ ዚካ፣ ሳርስ፣ ስዋይን ፍሉ እና በርድ ፍሉን በመጥቀስ፣ ወረርሽኝ ዘለቂ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ ይፈጥራል ሲሉ ይሞግታሉ።
የጤና ፖሊሲ ተመራማሪ ጁሊያ ሲሞን ለኒውዮርክ ታይምስ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ምዕራብ አፍሪካ የተከሰተው ኢቦላ የሁሉም ሰው ገቢ ላይ ተጽእኖ ፈጥሮ ነበር። በኋላ ግን ሁኔታዎች ወደ ቀደመ ነገራቸው ሲመለሱ፣ ከሴቶች ይልቅ የወንዶች ገቢ ነው ወደነበረበት በፍጥነት የተመለሰው።›› ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በተመለደው የሥራ ክፍፍል፣ ወረርሽኝን ተከስቶ የሚፈጠሩ ሸክሞች በሴቶች ላይ የሚወድቁ ናቸው። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች፣ ራሳቸውን ያገለሉ አረጋውያንና አረጋውያት፣ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱና ቤት እንዲቆዩ የተደረጉ ልጆችና ሕጻናት፣ ሁሉም ተንከባካቢ ይሻሉ። ይህን እንክብካቤ ያለ ክፍያ የሚሰጡ ደግሞ በየቤቱ ያሉ ሴቶች ናቸው።

ይህን በሚመለከት የኢንግሊዝ መንግሥት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ 40 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች የትርፍ ሰዓት ሥራን ነው የሚሠሩት። በትዳር ውስጥ ያሉ ከሆኑም ብዙ ጊዜ የሴቶች ገቢ አነስተኛ ስለሆነ፣ አንዳች አገራዊም ይሁን ዓለማቀፋዊ ቀውስ ቢከሰት፣ የሴቶች ሥራና ገቢ መስዋዕት ለማድረግ ከባድ አይሆንም። ይህም ለሳምንት ሳይሆን ለወራት የሚዘልቅ ከመሆኑ ሌላ፣ በዛው ሥራቸውን አጥተው የሚቀሩ ሴቶች ጥቂት አይደሉም።

‹ዘ አትላንቲክ› በዘገባው እንዳካተተው፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ሥራ ያላቸው ይሁኑ የሌላቸው፣ ሴቶች ከወንዱ በበለጠ የቤት ውስጥ ሥራ የሚበዛባቸው ሲሆን፣ ለእረፍት የምትተርፋቸው ትንሽ ሰዓት ናት። ልጆቻቸውን ለብቻ የሚያሳድጉ እናቶች ደግሞ የበለጠ ፈተናው ይገጥማቸዋል። ገቢያቸው በየቀን በሚደረግ እንቅስቃሴና ሩጫ ላይ መሠረት ያደረገ ከሆነ ደግሞ፣ ልጆችን በመንከባከብ እና ሥራ በመሥራት መካከል ስለሚሆኑ፣ የትምህርት ቤቶች መዘጋት ሕይወታቸውን ከባድ ያደርገዋል።
ይህም ብቻ አይደለም፤ የጤና ስርዓት በጣም ይዛባል፣ ምክንያቱም ሁሉምና የሁሉም ትኩረት ወደ ወረርሽኙ ብቻ ስለሚሆን ነው። ባለሞያዎቹ ለዚህ ማሳያ የሚጠቅሱት በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሴራሊዮን የሆነውን ክስተት ነው። ሴራሊዮን በኢቦላ ክፉኛ በተጠቃችበት በ2013 እና 2016 መካከል፣ በወሊድ ችግር ምክንያት የሞቱት በቫይረሱ ከሞቱት ሴቶች የሚበልጥ ቁጥር ነበራቸው። ነገር ግን ወረርሽኙ የበለጠ ትኩረት ስቦ ስለነበር፣ በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ ሴቶችን ዞሮ የተመለከተ አልነበረም። የጤና አገልግሎቱም ትኩረቱን ከወረርሽኙ ላይ መንቀል አልሆነለትም፤ ገንዘቡም ግብዓቱም ወደ ወረርሽኙ በመደረጋቸው ነው።

ሴታዊት ከተሰኘችው የሴቶች ንቅናቄ መሥራች መካከል የሆኑት ስኂን ተረፋ (ፒኤችዲ)፣ የወረርሽኝ መከሰትና እንቅስቃሴዎች እንዲገደቡ መሆናቸው፣ ልጆቻቸውን ለብቻ ለሚያሳድጉ ሴቶች በጣም ጫና ይኖረዋል ሲሉ ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ አካፍለዋል።

ልጆቿን ለብቻዋ የምታሳድግ ሴት፣ በገንዘብ የሚደግፋት ሰው ወይም የልጆቿ አባት ከሌለ፣ የገንዘብ ምንጭ ከመድረቁ በተጓዳኝ በቤት ውስጥ ያለውም ጫና ስለሚበዛ፣ ቀኑን ሙሉ ልጆች መያዝ ከባድ እንደሚሆን ይጠቅሳሉ። ይህም ደግሞ ደሞዛቸው አነስተኛ የሆነና በቀን ሥራ ቤተሰብ ለሚያስተዳድሩት ክብደቱ የሚበረታ ነው፤ እንደ ስኂን አስተያየት።

ይህም ብቻ ሳይሆን የሴቶችን የመብትና የእኩልነት ጥያቄና ጉዞ ወደኋላ መጎተቱ ምንም ጥያቄ የለውም ባይ ናቸው። እንዲህ ባሉ የወረርሽኝ ጊዜያት ጾታዊ ጥቃት ይጨምራል። ሁሉም የአገራት ሀብትና ጉዳይ፣ አቅምና ጉልበት ወደ ወረርሽኙ ይወሰዳል። ትኩረትም በዛው ላይ ይሆናል። ለምሳሌም በሴራሊዮን የሆነውን የሚጠቅሱት ስኂን፣ ሕክምናው ቦታዎች ላይ ተጽእኖ እንደሚፈጥርና የሕክምና ግብዓት እጥረት ሊከሰት እንደሚችል ይጠቅሳሉ።

ወረርሽኝና ስርዓተ ጾታ
ዓለም አቀፍ የሠራተኛ ተቋም (ILO) ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ፣ ሴቶች ከጠቅላላ ሰዓት ውስጥ 76.2 በመቶ የሚሆነውን ክፍያ በማያስገኝ ሥራ ላይ ያሳልፉታል። ይህም ከወንዶች አንጻር ሲታይ በሦስት እጥፍ የሚልቅ ነው።

ይህ በአዘቦቱም ያለ የሥራ ክፍፍል እንዲሁም ቀስቃሽና ተናጋሪ የሚፈልገው የስርዓተ ጾታ ጉዳይ፣ ወረርሽኝ በነገሠበት ሰዓት ደግሞ ጭራሽ የተዘነጋ ነው። የስርዓተ ጾታ ባለሞያዎች እንደሚሉት ግን፣ እንዲህ ባለ የወረርሽ ሰዓት የስርዓተ ጾታን ጉዳይ እንደ ትንሽ አቅልሎ ማየት አግባብና ትክክል አይደለም። ይሁንና ‹‹መንግሥት/መንግሥታት መዘናጋት አመሉ/አመላቸው ነው።›› በባለሞያዎቹ አስተያየት።

ለዚህ ማሳያ ይሆናል ብለው የሚያቀርቡት፣ ኮቪድ19ን ነው። ቫይረሱ ገና ቻይና ሲጀምር ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ሲነገር ቢቆይም የተለያዩ አገራት መንግሥታት ግን ቸላ ብለው ነበር። ‹ቢደርስብን ምን እናደርጋለን› ብለውም እቅድ አልያዙም። ‹‹ይህን እያወቅን የሴቶችን ጉዳይ ጆሮ ሰጥተው ይሰማሉ ማለት እንዴት ይቻላል?›› የብዙዎቹ ጥያቄ ነው።

‹ቲንክ ግሎባል ኸልዝ› ላይ የሰፈረው ጽሑፍ እንደሚያስረዳው፣ ወረርሽኝን ለመግታትና ለመከላከል የሚሰጡ ግብረ መልሶች ስርዓተ ጾታን መሠረት ያደረጉ አይደሉም። ስርዓተ ጾታን መሠረት ለማድረግ ምን መደረግ አለበት ለሚለው፣ መጠየቅ ያለባቸው ጥያቄዎችና ሊሰጡ የሚገቡ መልሶች አሉ።

በተለይም ጥያቄዎቹ በሚከተሉት ላይ እንዲያተኩሩ የሚመከሩ ናቸው። እነዚህም መረጃዎች በጾታ ተለይተው ተቀምጠዋል ወይ? በቫይረሱ የመያዝ ሁኔታና ሞት በጾታ ልዩነት ያሳያል ወይ? ከሆነስ ምክንያቱ ምንድን ነው? በቤት ውስጥ እንዲሁም በተቋማት ውስጥ ያሉ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን እየተንከባከበ ያለው ማን ነው? እንክብካቤ እያደረጉ የሚገኙ (ብዙውን ጊዜ ሴቶች) ተገቢውን ክፍያና ድጋፍ እያገኙ ነው ወይ? ለወረርሽኙ መልስ የመስጠት ውሳኔዎችን እየወሰነ ያለው ማን ነው? ወዘተ።

ስኂን እንደሚሉት ደግሞ፣ ለስርዓተ ጾታ የሚሰጠው ትኩረት በደኅናውም ጊዜ ጤናማ አይደለም። ጉዳዩን ማንሳቱም እንደ ቅንጦት ነው የሚታየው፣ እንኳን እንዲህ በከፋው ጊዜ። ለዚህም ዋናው ነገር እይታ ነው ባይ ናቸው። በስርዓተ ጾታ ላይ የሰላ እይታና አመለካከት ያላቸው ጠንካራ ባለሥልጣናት ቢኖሩ፣ ስርዓተ ጾታን እንዲህ ባለው አስጨናቂ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በወትሮው የፖሊሲ አቅጣጫና ውሳኔ ላይም ማካተት አይከብድም ነበር።

እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱትም፣ ከአየር መንገድ የሚገቡ ሴቶች ቦሌ ትምህርት ቤት መቀመጣቸውን በማንሳት ሲሆን፣ ከነዛ ሴቶች መካከል የወር አበባ ላይ ያሉ ይኖራሉ። ውሃና አስፈላጊ ንጽሕና መጠበቂም ያስፈልጋቸዋል። ይህን ልብ ብሎ ማቅረብና መከታተል፣ አስቀድሞም በመዘጋጀት ውስጥ መታየት ያለበት ነው። ‹‹ሐሳባችን ውስጥ ሊኖር ይገባል [ሥርዓተ ጾታ]። መዘንጋት የለበትም። ጥያቄዎቹም የሚቀጥሉ ናቸው።›› ስኂን እንደተናገሩት።

ታድያ የስርዓተ ጾታ ጥያቄ ሲነሳ ትርፍ ነገር የተጠየቀ የሚመስላቸው መኖራቸውን አያይዘው አንስተዋል። ነገር ግን እንደዛ ባሉ ማቆያዎች ነፍሰ ጡር የሆነች ሴት ብትኖርና በድንገት ምጧ ቢመጣ፣ ምን ሊደረግ ይችላል የሚለው ቀድሞ መታሰብ ያለበት መሆኑ አከራካሪ አይደለም።

‹‹ችግሩ ካለፈ በኋላ ከመማር ከአሁኑ ያለውን ማስተካከል ያስፈልጋል። ጠቅላይ ሚስትሩን ጨምሮ አማካሪዎቻቸው ያ እይታ ቢኖራቸው፣ ከመጀመሪያው ሊስተካከል ይችላል። የእይታ ጉዳይ ነው።›› ብለዋል። አሁን በተከሰተው የኮቪድ19 ኮሮና ቫይረስ ቅድመ ዝግጅት ላይ ግን ይህን እይታ እስከ አሁን የለም። መገናኛ ብዙኀንም ትዝ አላላቸውም።

እንደውም ስኂን ‹‹ወደፊትም የምናየው አይመስለኝም።›› ብለዋል። ሐሳቡና እይታው የገባው ፖሊሲ አውጪና አመራር እስኪመጥ ድረስ፣ ነገሮች ካለፉ በኋላ መልሶ ለማስተካከል መሯሯጡም መቀጠሉ እንደማይቀር አሳስበዋል።

የኮቪድ19 ተጽእኖዎች – በሴቶች ላይ
ቢቢሲ በገጹ ባኖረው ጽሑፍ ኮሮና ቫይረስ በእስያ ያሉ ሴቶችን በምን መንገድ እንደጎዳ ያብራራል። ቫይረሱ እንደ ማኅበረሰብ ካደረሰው ተጽእኖ በተጓዳኝ፣ ሴቶች በብዛት ተጎድተዋልም ይላል።

በእስያና ፓስፊክ በተባበሩት መንግሥትታት የሴቶች ጉዳይ (UN Women) ሰብአዊና የአደጋ ጊዜ አማካሪ ማሪያ ሆልትስበርግ እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል፤ ‹‹ዓለማቀፋዊ ቀውሶች ሁልጊዜም የሥርዓተ ጾታ መበላለጥን ያብሳል›› ሲሉ ይገልጻሉ።

አሁን ላይ ዓለምን አስጨንቆ ያለው ኮቪድ19 የኮሮና ቫይረስም በሥርዓተ ጾታ ይልቁንም በሴቶች ላይ ከተለያየ አንጻር ጉዳት እያደረሰ ይገኛል። ይህም የተለያየ መነሻ ያለው ሲሆን፣ አንደኛው የትምህርት ቤት መዘጋት ነው።

ቢቢሲ ጋዜጠኛና የኹለት ልጆች እናት ከሆነችው ሱንግ ሶ ያንግ ጋር ቆይታ አድርጓል። ‹‹ላለፉት ሦስት ሳምንታት ቤት ውስጥ ከልጆቹ ጋር ነው ያሳለፍኩት›› ያለችውና ደቡብ ኮሪያ የምትኖረው ሱንግ፣ በአገሪቱ የትምህርት ቤቶች ለተጨማሪ ኹለት ሳምንታት ዝግ ሆነው ይቆያሉ መባሉ፣ ሥራዋን እንደፈተነው ሳትጠቅስ አልቀረችም። ‹‹ድብርት ላይ ነኝ›› ስትል ነበር ያለችበትን ሁኔታ የገለጸችው።

ቀጥላም አለች፤ ‹‹እውነት ለመናገር፣ ሐሳቤን ሰብስቤ ለመሥራት ከቤት ይልቅ ቢሮ መሄድ እፈልጋለሁ። ነገር ግን ባለቤቴ የቤቱን ከፍተኛ ወጪ ስለሚሸፍን ፈቃድ መውሰድ አይችልም›› በማለት ለቢቢሲ አስረድታለች። የ11 ዓመት እና የ5 ዓመት፣ ኹለት ልጆች ያሏት ሱንግ፣ ልጆቿ ሲተኙ ነው ወደ ሥራዋ ለማተኮር ጊዜ የምታገኘው።

እንደውም ሱንግ እንደገለጸችው ከሆነ፣ በአገሪቱ አንዳንድ ኩባንያዎች ሴቶች ልጆቻቸውን ለመጠበቅ ወደ ወደ ሥራ መግባት አለመቻላቸውን ተከትሎ፣ ደሞዛቸውን ተከልክለዋል። ‹‹ብዙ ድርጅቶች አውጥተው አይናገሩ እንጂ ሴቶችን ይልቁንም እናቶችን መቅጠራቸውን እንደ ሸክም ነው የሚቆጥሩት። በዛ ላይ ልጆች ከሌሉ፣ በተሻለ ቢሮ መግባት ይቻላል።›› ብላለች።

የቤት ውስጥ ጥቃት
ጾታዊና የቤት ውስጥ ጥቃት በተመሳሳይ እንዲህ እንደ አሁን ወረርሽኝ ሁሉም በየቤቱ እንዲቀመጥ ግድ በሚልበት ጊዜ ይበረታል። የውጭ መገናኛ ብዙኀን የሴቶች መብት ተሟጋቾችን አናግረን አገኘነው ባሉት መረጃ መሠረት፣ አሁንም የቤት ውስጥ ጥቃት እንደሚጨምር እየተጠበቀ ነው። የየግለሰብና የአባወራ ቤቶች በሮች በተዘጋጉበት ጊዜ፣ በቤቱ ውስጥ የሚፈጠረው ጭንቀት፣ የአልኮል መጠጥን መጠቀም እና የገንዘብ ችግር የቤት ውስጥ ጥቃትን ይቀሰቅሳልም ተብሏል።

እንዲህ ያሉ ክስተቶችን ፖሊሲ ሠሪዎች ልብ ስለማይሉ፣ ከቀደሙ ወረርሽኞች ልምድ ስላልተወሰደም ወረርሽኝን በተመለከተ የሚወጡ አዲስ መመሪያዎች ከስርዓተ ጾታ የተገለለ እይታ ያላቸው ናቸው። ለምሳሌ በዘገባው እንደተጠቀሰው ኮሮና ቫይረስ በነፍሰ ጡር ሴቶች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አልተጠናም። ልብ ያለውም ያለ አይመስልም።

የቤት ውስጥ ጥቃት ሲነሳ ታድያ፣ በቻይና ይህ ነገር መከሰቱን የመብት ተማጓቾች ሲገልጹ ተሰምቷል። ያውም ጥቃቱ ሲፈጸም ወዴት ሄዶ አቤት ማለት እንደሚቻልም አይታወቅም። ጥቃት ደረሰብን ያሉ ሴቶች ድምጻቸውን ቢያሰሙም፣ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ እንኳ የሚያስችል ሁኔታ የለም፤ በወረርሽኙ ምክንያት። በቻይናም ይህ የተስተዋለ ስለመሆኑ ቢቢሲ ከምንጮቼ ያገኘሁት ነው ብሎ አስነብቧል።

ታዮ ሊ የተባለች ቻይናዊት ከገጠማት ለቢቢሲ ስታካፍል፣ አንድ ዘመዷ በቀደመ ባሏ የደረሰባትን ጾታዊ ጥቃት ትጠቅሳለች። ይህቺ ሴት ለእርዳታ ብትጣራም የደረሰላት አልነበረም። በብዙ ጥረትና ውትወታ ግን ፖሊስ እንድትወጣ ፈቅዶ የታዮ ወንድም ቤቷ ድረስ በመሄድ ለእርሷና ለልጇ ሊደርስላቸው መቻሉን ታወሳለች።
በቻይናም ይህንና ሌሎች የተሰሙ ብዙ የቤት ውስጥ ጥቃቶች ላይ ተመሥርቶ፣ ሃሽታግ በማድረግ በወረርሽኑ ጊዜ የሚደረግ የቤት ውስጥ ጥቃት ተቃውሞ ድምጽ ሲሰማ ሰንብቷል።

በአገሪቱ ሥራ ላይ ያሉ ፖሊሶችም ‹ለወረርሽኙ ቅድሚያ እንሰጣለን› በሚል መንፈስ፤ የቤት ውስጥ ጥቃትን በቸልታ ሊያዩት አይገባም ሲሉ አሳስበዋል።
የቤት ውስጥ ጥቃት ማሳወቂያ የጥሪ ማእከል (ሆትላይን) ዋና ዳይሬክተር ኬቲ ሬይ ጆንስ፣ ‹‹ከባድ የሆኑ ንግግሮችን እያደረግን ነው›› ስትል አስተያየቷን ለኒውዮርክ ታይምስ ሰጥታለች።

ኬቲ ወደ እነርሱ ማእከል ከደረሰ ጥሪና ከተነገራቸውን ታሪክ መርጣ አንድ ጉዳይ አንስታለች። በዚህም አንዲት ሴት አጋሯ አንቆ ሊገድላት እንደነበርና የሕክምና እርዳታ እንደምትፈልግ ደውላ ገልጻ ነበር። ወደ ውጪ ወጥታ ወደ ሕክምና ማእከል እንዳትሄድ ደግሞ የቫይረሱ ስርጭትና ከቤት አትውጡ መባሉ አስፈርቷታል። እናም ድረሱልኝ ከማለት ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበራትም።

ሌላ ሴትም በተመሳሳይ ሥራዋን አልያም ቤቷን እንድትመርጥ ተገዳ ነበር። ‹‹ቤት ሆኜ የማልሠራ ከሆነ ከቤት እንደሚያስወጣኝ አስፈራራኝ። ቢያስለኝ (ሳል ቢኖረኝ) አውጥቶ መንገድ ላይ እንደሚተወኝና ሆስፒታልም ለብቻዬ እንደምሞት ነግሮኛል።›› ስትል ለጥሪ ማእከሉ በደወለች ሰዓት ተናግራለች።

እድሜዋ ከ13 እስከ 15 ዓመት የሚሆን ትንሽ ልጅም፣ እናቷ በባለቤቷ ጥቃት እንደደረሰባትና ይህም ወደ እርሷም ጭምር እንደተሻገረ ለጥሪ ማእከሉ ተቀባዮች ሪፖርት አድርጋለች። ትምህርት ቤት በመዘጋቱ ግን ትምህርት ቤት መሄድም ሆነ አማካሪ ጋር ለእርዳታ መጠጋት አማራጭ አልሆነላትም።

አሁንም በቤት ውስጥ ለመቀመጥ ከመገደድ፣ ከጭንቀትና አቅም ከማጣት ስሜት የተነሳ፣ ብዙ የቤት ውስጥ ጥቃቶች ይኖራሉ፣ እንደ ባለሞያዋ ገለጻ።
ታድያ ጭቅጭቅ እየጋለ ሲሄድና አለመስማማት ሲበረታ፣ መሸሻው ወዴት ነው ከተባለ፣ ባለሞያዎቹ የሚሉት፣ ‹‹ጭቅጭቃችሁን ከኩሽና እንዲሁም ከባኞ ቤት እንዲርቅ አድርጉ። እነዚህ አደጋ ያለባቸው ቦታዎች ናቸውና።››

ሴቶች በጤና ዘርፍ
ይህ ወረርሽኝ በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረው ጫና አሁን ባይሆንም እያደር የሚገለጥ እንደሆነ ኢኮኖሚስቶች ተገንዝበውታል፣ መንግሥታትም ተቀብለውታል። በለንደን ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ክርስቲና ማግስ እንደሚሉት፣ ቫይረሱ በሰዎች እንቅስቃሴ፣ ምርትና ተጠቃሚነት ላይ ወንድ ሴት ሳይል በሁሉም ላይ ተጽእኖ ፈጥሯል። ነገር ግን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሴቶች አገልግሎት ሰጪ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ በመሆኑ፣ በተጠቃሚ መቀነስ ከፍተኛ ተጎጂ የሚሆኑትም እነሱ ናቸው ባይ ናቸው።
የተባበሩት መንግሥታትም ይህን ጉዳይ ያጤናው ይመስላል። በድርጅቱ የዘርፉን የአኅጉራት ሂደት በመሪነት የሚከታተሉት መሐመድ ናክሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ሴቶችና የወንዶች በየራሳቸው ፍላጎቶች አሏቸው፣ በዚህም ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል። ወረርሽኙን በመከላከልና በመዋጋት ሴቶች እንደጤና ባለሞያ፣ እንደ ሳይንቲስትና ተመራመሪ፣ እንደ ቀስቃሽ፣ እንደ ሰላም ፈጣሪና ተንከባካቢ ድርሻቸውን እየተወጡ ነው። የሴቶች ድምጽ ሊሰማና እውቅና ሊሰጠው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ተመሳሳይ ይዘት ያለውን ዘገባ አስነብቧል። በአንድ ወገን የጤና አገልግሎት ሰጪዎች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑትና ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት ሴቶች ናቸው። ይህም አሃዝ በ104 አገራት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት የዓለም ጤና ድርጅት ደርሼበታለሁ ያለው ግኝት ነው። በዚህ መሠረት ታድያ የ2019ኙን ኮሮና ቫይረስ በመከላከልና በመዋጋት፣ በውጊያው ላይ ፊት ለፊት የሚገኙ ያደርጋቸዋል፤ ሴቶች።

ወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም የኮሮና ቫይረስ ጉዳትና ተጽእኖ ወንዶችም ሴቶችም እኩል ተሰምቷቸዋል ወይ በሚል ይጠይቃል። በቻይና የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያመላክተው፣ ቫይረሱ ከሴቶች ይልቅ ወንዶችን እያጠቃና ሕይወታቸውንም እየነጠቀ ይገኛል። ይህም በአሃዝ ሲቀመጥ፣ የወንዶች የመሞት መጠን 2.8 በመቶ ሲሆን የሴቶች 1.7 በመቶ ነው። (ለዚህም የአኗኗር ሁኔታ ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሎ ተገምቷል። አንደኛው ጥናቱ በተካሄደባት ቻይና ወንዶች ሲጋራ በማጤስ ከፍተኛውን ድርሻ ስለሚይዙ ነው፤ ለዚህ በሽታ ሊጋለጡና በቶሎ እጅ ሊሰጡ የቻሉት።)

በአንጻሩ ቫይረሱን ለመጣል በሚደረግ ትግል እንደተባለው ፊት ለፊት የሚገኙት ሴቶች፣ የቤት ውስጥ ሥራቸው ሳይቀንስና ሳይቀየር፣ ረጅም ሰዓት እንዲሠሩ ይገደዳሉ። በክፍያ ደረጃም ሴቶች ከወንዶች አንጻር 11 በመቶ የሚያንስ ክፍያን ያገኛሉ። ይህ እንግዲህ አገልግሎት ሰጪ የጤና ባለሞያዎች ላይ ያለው ጫና እና ተጽእኖ ነው።

እስኪያልፍ ማለፊያው…
ስኂን እንደ አገር ኮሮና ሳንዘጋጅ የደረሰብን ስለመሆኑ ከእይታቸው ያነሳሉ። ነገር ግን አሁንም ላይ እየተደረጉ ያሉ ቅድመ ዝግጅቶች ስርዓተ ጾታን ያማከሉ ሊሆኑ ይገባል ይላሉ። ‹‹አሁን የደም እጥረትም ሊኖር ይችላል። በተለይ ሴቶች በወሊድ ጊዜ ደም ያስፈልጋቸዋል።›› ሲሉም ያነሳሉ። እነዚህም ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ መሆኑን በማንሳት፣ በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ውስጥ ለነበሩና አሁን በቤተሰባቸው ላይ ለሆኑ ልጆችም፣ በመተጋገዝ መድረስ ይገባል ብለዋል።

በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ይሠሩ የነበሩና የሚሠሩበት ተቋም በወረርሽኑ ምክንያት እንዲዘጋባቸው የተደረጉ ሠራተኞች፣ ይልቁንም ሴቶች፣ ሥራቸው ቢዘጋም ደሞዛቸው ሊከፈል ይገባል። የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ዝም ብሎ ሠራተኛን ማባረር የለም። ነገር ግን በግልና በቤት ውስጥ ያ አይታይም።

ስኂን እንደጠቀሱት፣ ሠራተኛ ተመላላሽ ሲሆን በስጋት የተነሳ ሰዎች ማባረሩን ይመርጣሉ። ነገር ግን በዛች ሴት ሕይወት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ማሰብ ያስፈልጋል።

‹‹ያቺን ሴት የሚሸኙም ከሆነ ደሞዝ መስጠት ያስፈልጋል። ገቢያቸው እየታወቀ በምን እንዲኖሩ ይጠበቃል? ፋብሪካዎችና ሆቴሎች የሚያስገድዳቸው ባይኖርም የሞራል ጥያቄ ነው። አትምጡ ሲሉ በምን ይኖራሉ የሚለውን ማስብ ይጠበቅባቸዋል።›› የስኂን ምክረ ሐሳብ ነው።

እንደ ስኂን አስተያየት፣ መንግሥት በዚህ ላይ ትዕዛዝ መስጠት አለበት። አለበለዚህ የማንቋቋመው አዘቅት ውስጥ እንገባለን ይላሉ። ግንዛቤ መፍጠርም ላይ ከመንግሥት መምጣት አለበት ሲሉ ይሞግታሉ። መንግሥት የሃይማኖት ተቋማትና ሌሎች ጋር ውይይት እያደረገ ውሳኔዎችን እንደሚስተላልፍና ሐሳቦችን እንደሚሰጥ ሁሉ፣ የራሱን ተቀጣሪዎች ከቤት እንዲሠሩ እድል ከፈጠረ፣ ሌላውንም ማሰብ አለበት ባይ ናቸው።

‹‹ባለሀብቶች በራሳቸው አስበው ያንን ያደርጋሉ ብዬ አላስብም። ዝቅተኛ ገቢ ያለው ሥራ ላይ ያሉት አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው። እኩል ሥራ ላይም እንኳ ዝቅተኛ ነበር የሚከፈላቸው።›› ሲሉም ችግሩን ለማሳየት ሞክረዋል።

አዲስ ማለዳ ያጣቀሰቻቸው የተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙኀን ዘገባዎችም፣ ካናገሯቸው ባለሞያዎች ያገኟቸው ምክረ ሐሳቦች ከዚህ የተለዩ አይደሉም። ከምንም በላይ ግን አሁን በኮቪድ19 ምክንያት በሴቶች ላይ የሚከሰተው፣ የተሰማውም የማይሰማውም ጫና፣ ወደፊት ሊከሰት በሚችል ወረርሽኝ እንዳይደገም ለማድረግ ፖሊሲ አውጪዎችና የሚመለከታቸው ከወዲሁ ሊያስቡበት የሚገባ ነው።

በእርግጥ እንኳን የሴቶችን ጉዳይ ነገሬ ብለው ሊያስቡ፣ ሰርገኛ መጣ እንደሚባለው፣ እርምጃ ለመውሰድ ወረርሽኞች ጉዳት እስኪያደርሱ የሚጠብቁ መንግሥታት ጥቂት አይደሉም። በዚህ ሁሉ መካከል ግን በሽታዎችን ያርቅልን ከማለት ጎን ለጎን፣ ስርጭቱ ሴቶች ላይ የበለጠ ጫና እንዳይፈጥርና መከራቸውን እንዳያበዛው፣ ቀደም ብሎ ማሰብ ጠቃሚ መሆኑ አያጠራጥርም።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com