“ኒያ ፋውንዴሽን” 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እና አለም አቀፉን የኦትዝም ወር በማስመልከት የተለያዩ መርሃ ግብሮች ማዘጋጀቱን አስታወቀ

0
1350

ዕረቡ መጋቢት 14 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኦትዝም እና ተዛማጅ ችግሮች ያለባቸውን ሰዎችን የመርዳት አላማ አንግቦ፤ በባለ ራዕይዋ ዘሚ የኑስ የተመሰረተው “ኒያ ፋውንዴሽን ጆይ ኦቲዝም ሴንተር” የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እንዲሁም አለም አቀፉን የኦትዝም ቀንና የግንዛቤ ወር በማስመልከት የተለያዩ መርሃግብሮችን ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

በአለም ዓቀፍ ደረጃ የሚያዚያ ወር የኦትዝም ወር እንዲሁም መጋቢት 24 (ኤፕሪል 2) ደግሞ ዓለም ዓቀፍ የኦቲዝም ቀን ተብሎ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ታስቦ ይከበራል።

የዚህም ዓመት የኦትዝም ቀን በኢትዮጵያ ለ20ኛ ጊዜ፣ በአለም ዓቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን፤ “ከኦትዝም ጋር የሚኖሩ ዜጎች በሥራ የመካተት እና የመሰማራት መብታቸው ይረጋገጥ፤ እድል እና ተግዳሮቶች ከወረርሽኝ ዘመን በሗላ” በሚል መሪ ቃል ይከበራል።

ይህንንም በማስመልከት “ኒያ ፋውንዴሽን” የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እና አለም አቀፉን የኦትዝም ቀንና የግንዛቤ ወር በማስመልከት የተለያዩ መርሃግብሮችን ማዘጋጀቱን በዛሬው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቋል።

በዚህም መሰረት መጋቢት 23 እና 24 ቀን 2014 ከብሄራዊ ደም ባንክ ጋር በመተባበር የሚደረግ የደም ልገሳ ፕሮግራም፣ ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ከ1 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የሚሳተፋበት ከሲኤምሲ አደባባይ እስከ ሳፋሪ የኦትዝም ልህቀት ማዕከል ግንባታ ፕሮክት የሚደረግ የእግር ጉዞ መዘጋጀቱን የፋውንዴሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ ሰሀራ ሀሰን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሚያዝያ 11 ቀን 2014 በኦትዝም ዙሪያ ያሉ በመሪ ቃሉ እና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥ አውደ ጥናት እንዲሁም ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 23 ቀን 2014 ድረስ የሚቆይ በአፍሪካ ብቸኛው ሁሉን ያሟላ የኦቲዝም የልህቀት ጣቢያ ግንባታ የሚደረግ የግንባታ ግብዓት ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች እንደሚከናወኑም ሰብሳቢዋ ገልፀዋል።

እንዲሁም ረጅም ዓመታትን ለኦትዝም እና ድምፅ አልባ የህብረተሰብ ክፍሎች ድምፅ በመሆን አገልግለው፤ ባሳለፍነው ዓመት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈው የኒያ ፋውንዴሽን መስራች ዘሚ የኑስ 1ኛ ዓመት የሚዘከርበት መርሀ ግብርም መዘጋጀቱንም የማዕከሉ ዳይሬክተር እሌኒ ዳምጠው ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

ኒያ ፋውንዴሽን ጆይ ኦቲዝም ሴንተር በተለይ ኦትዝም እና ተዛማጅ እክል ያለባቸውን ሰዎች በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው የሚያግዱ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን፤ በቅርቡም በማዕከሉ የሚገኙ 10 ተማሪዎች እንደሚመረቁም ተገልጿል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይም የኒያ ፋውንዴሽን የቦርድ አመራሮችና የፋውንዴሽኑ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ የተገኙበት ሲሆን፤ ፋውንዴሽኑን ለመደገፍ የተዘጋጀው የ 9616 አጭር የመልዕክት ፅሁፍ መላኪያም በመድረኩ ይፋ ተደርጓል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here