የሰሜኑ ጦርነትና ሰብዓዊ አቅርቦት መስተጓጎል

0
1027

የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት መነሻውን ትግራይ ክልል አድርጎ ከተቀሰቀሰበት ከጥቅምት 24/2013 ጀምሮ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ አንድ ዓመት ከአምስት ወር በላይ ማስቆጠሩን ተከትሎ፣ ጦርነቱ በተካሄደባቸው በትግራይ፣ በአፋርና በአማራ ክልል ያሉ ንጹኃን ዜጎችን ለሰብዓዊ ችግር ተጋልጠው ቆይተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በምህጻረ ቃሉ ዩኤንኦቻ(UNOCHA) መጋቢት 9/2014 ባወጣው ሳምንታዊ ሪፖርት በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልል 9.4 ሚሊዮን ዜጎች በጦርነቱ ምክንያት ለመሰረታዊ ፍጆታ አቅርቦት ችግር ተጋልጠዋል። በተለይ በትግራይ ክልል በነዳጅ፣ በጥሬ ገንዘብና በአቅርቦት ችግር የሰብዓዊ ድጋፎች በከፍተኛ ኹኔታ መቀነሱን የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ በአፋር ክልል በቀጠለው ጦርነት የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሆኑና ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ አቅርቦት እንዳይጓጓዝ የትራንስፖርት መስተጓጎል እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን ያመላክታል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በበኩሉ፣ ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያጓጉዙ ተሸከርካሪዎች መንግድ ላይ ችግር እየገጠማቸው እየተመለሱ መሆንን መግለጹ የሚታወስ ነው። በትግራይ ክልል የምግብ፣ የመድኃኒት፣ የጥሬ ገንዘብና የነዳጅ ዕጥረት ማጋጠሙን ተከትሎ የክልሉ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች ክልሎች እየተፈናቀሉ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ገልጿል።

በትግራይ ክልል አዋሳኝ በሆኑ የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች ጦርነቱ አለመቆሙን ተከትሎ፣ በእነዚህ አካባቢ ለሚገኙ ዜጎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስ አለመቻሉን የኦቻ ሪፖርት ያመላክታል። በአማራ እና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ንብረታቸውን ያጡና የተፈናቀሉ ዜጎችን በቂ የሰብዓዊ አቅርቦት እያገኙ አለመሆኑ እየተገለጸ ነው።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን የሰብዓዊ አቅርቦት ችግር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ጦርነት እንዲቆምና ሰብዓዊ አቅርቦት በአግባቡ ተደራሽ እንዲሆን እየወተወቱ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መጋቢት 15/2014 ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት “ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት የማቆም ውሳኔ አሳልፏል” ብሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት የግጭት ማቆም ውሳኔውን የወሰነው በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ እና የዜጎችን እንግልት ለመቀነስ መሆኑን አስታውቋል። የውሳኔው ዓላማ አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ በነጻነት እንዲጓጓዝና ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች መድረስ እንዲችል ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰነው ለሰብዓዊነት የግጭት ማቆም ውሳኔ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሰብዓዊ ኹኔታ እንደሚያሻሽልና በቀጣይ “ያለተጨማሪ ደም መፋሰስ” ለጦርነቱ መፍትሔ ሊያመጣ እንደሚችል ገልጿል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት የተሳለጠ እንዲሆን፣ የአየርና የየብስ ትራንስፖርት አማራጮችን ለዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ማመቻቸቱን አስታውሷል። ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍለጋ ወደ አጎራባች ክልሎች እየተጓዙ መሆኑን አረጋግጧል።

ጦርነቱ ከትግራይ ክልል ወደ አማራና አፋር ክልሎች መሸጋገሩን ተከትሎ በኹለቱ ክልሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው በመፈናቀላቸው ዕለታዊ የሰብዓዊ ድጋፍ ጠባቂ ሆነዋል። በኹለቱ ክልሎችና በትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ጦርነቱ አለመቆሙን ተከትሎ አሁንም ዜጎች እየተፈናቀሉ ነው።

ሕወሓት ወደ ትግራይ ክልል ከተመለሰ በኋላ ዳግም ባገረሸው ጦርነት በአፋር ክልል ከ700 ሺሕ በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል። በአፋር ክልል አሁንም በቀጠለው ጦርነት ምክንያት ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች በጸጥታ ችግር ድጋፍ ማድረስ እንዳልተቻለ የኦቻ ሪፖርት ያመላክታል።

የአፋር ክልል መንግሥት ባወጣው መረጃ መሠረት እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሆኑንና መጠለያ፣ ውኃና በቂ ምግብ ማቅረብ አለመቻሉን መግለጹ የሚታወስ ነው።

ኦቻ መጋቢት 14/2014 ባወጣው የሰብዓዊ ክንውን ሳምንታዊ ሪፖርት ላይ በአፋርና በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢ እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት በትንሹ 600 ሺሕ የአፋር ክልል ዜጎች መፈናቀላቸውን ጠቁሟል። በአካባቢው በቀጠለው ጦርነት በአፋር ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎችና ሰብዓዊ ድጋፍ በአግባቡ ማቅረብ አለመቻሉን የገለጸው ኦቻ፣ የሰመራ-አባላ-መቀሌ መስመር በጸጥታ ችግር ምክንያት በመዘጋቱ ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ አቅርቦት ለማጓጓዝ አለመቻሉን ገልጿል።

ኦቻ ባወጣው ሳምንታዊ ሪፖርቱ ከትግራይና ከኦሮሚያ ክልል በግጭቶችና በደረሰባቸው ችግር የተፈናቀሉ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአማራ ክልል እንደሚገኙ ጠቁሟል። የአማራ ክልል መንግሥት ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው መረጃ በክልሉ ከ11 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ዕለታዊ የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቋል።

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን ወደ ሌላ በታ ማዘዋወር እንደሚያስፈልግ ገልጿል። በተለይ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በቆቦና ሰቆጣ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች መጠለያ የመቀየር ሥራ እየተሠራ ነው ተብሏል። ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው ወደ ራያ ቆቦ ያቀኑ ተፈናቃዮች ከ60 ሺሕ በላይ ሲሆኑ፣ 10 ሺሕ የሚደርሱ ተፈናቃዮችን ከጃራ ወደ ዲሬ ሮቃ የማዘዋወር ሥራ እስከ መጋቢት 13/2014 ድረስ መሠራቱን የኦቻ ሪፖርት ያመላክታል።

ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩ ተፈናቃዮችን መሠረታዊ የመጠለያ እና ዕለታዊ ፍጆታ ማድረስ እንደሚያስፈልግ የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳምንት በፊት ከ14 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮችን ከዋግ ኽምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ በስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ወሌህ ወደ ተባለ መጠለያ ማዘዋወራቸውን ይጠቁማል።

በዋግ ኽምራ አካባቢ ቀደም ሲል በጦርነት የተፈናቀሉና ንብረታቸውን ያጡ ዜጎችን ጨምሮ፣ በአካባቢው እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎች ለከፍተኛ የሰብዓዊ ችግር መጋለጣቸውን ዞኑ እየገለጸ ነው። በአካባቢው ከ60 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ዕለታዊ የምግብ፣ የመጠጥና የሕክምና አገልግሎት እንደሚሹ ተገልጿል።

በየአቅጣጫው ወደ ሰቆጣ ከተማ የሚገባው የተፈናቃይ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የዞኑ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ከትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚፈናቀሉ ዜጎች ወደ ሰቆጣ ከተማ እየገቡ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን፣ ተፈናቃይ ግን ተገቢውን መጠለያ እያገኙ አይደለም ተብሏል።

በአካባቢው ከሚገኙት 61 ሺሕ 668 ተፈናቃዮች በመጠለያ ያሉት 18 ሺሕ 748 ያክሉ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ በየዘመድ ቤትና በየበረንዳው እየኖሩ መሆኑን የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። በችግር ላይ ከሚገኙት ተፈናቃዮች መካከል 2 ሺሕ 521 አጥቢ እናቶች፣ 882 የሚሆኑት ነፍሰ ጡር እናቶች፣ 1 ሺሕ 273 ከአምስት ዓመት በታች ሕጻናት፣ 371 የአካል ጉዳተኞች፣ 1 ሺሕ 163 የሚሆኑት አረጋውያን መሆናቸውን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ደስታዬ ጌታሁን ተናግረዋል።

ከተፈናቃዮች መካከል 882 ነፍሰ ጡር እናቶች ችግር ላይ መሆናቸውን የሚገልጸው ጽሕፈት ቤቱ፣ ለነፍሰ ጡሮች የተለዬ ዕገዛ ያስፈልጋቸዋል ብሏል። በአካባቢው የተዘጋጀው መጠለያ እና የተፈናቃዮች ቁጥር የተጣጣመ አለመሆኑን ተከትሎ ተፈናቃይ ዜጎች በመጠለያ ችግር ሜዳ ላይ ወድቀዋል ተብሏል።

የተዘጋጀው መጠለያ እና የሰው ቁጥሩ አለመጣጣሙን ተከትሎ አጥቢ እናቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያንና ነፍሰ ጡሮች አፈር ላይ እየተኙ ነው ተብሏል። የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ካቀረባቸው ድንኳኖች እና ከተወሰኑ ገንዘብ ረጂዎች ውጭ ድጋፍ እየተገኘ አይደለም ተብሏል።

የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መረጃ መሰረት፣ የተፈናቃዮች ቁጥር 61 ሺሕ 668 ቢሆንም፣ በወለህ መጠለያ ጣቢያ የተዘጋጀው መጠለያ ግን ከ2 ሺሕ ሰው በላይ መያዝ እንደማይችል ነው።
አሁንም ድረስ በዋግ ኽምራ ያለው የምግብ ዕርዳታም ሆነ የመጠለያ ድንኳን በየጊዜው ከሚጨምረው ተፈናቃይ ጋር ስላልተመጣጠነ፣ ማንም ሰው የሆነ ኹሉ ተፈናቃዮችን እንዲደግፍ ከሰሞኑ በተለያዩ መንገዶች ጥሪ እየቀረበ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here