ከ100 በላይ ቤቶች በ12 ቀናት ውስጥ መቃጠላቸው ተገለጸ

0
382
የአባሙሳ ከተማ ነዋሪዎች ሙሉ ለሙሉ ተሰደዋል

ከመጋቢት አንድ እስከ 12/2014 ባሉት ቀናት ውስጥ በምሥራቅ ወለጋ ሊሙ ወረዳ ሥር የሚገኙ ከ100 በላይ ቤቶች በታጣቂዎች መቃጠላቸውን አስተማማኝ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ሥሜ እንይጠቀስ ያሉ የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ ከመጋቢት አንድ እስከ 12/2014 ባሉት ቀናት ብቻ ከ100 በላይ የሚሆኑ ቤቶች በታጣቂዎች ተቃጥለዋል ሲሉ ነው ገለጹት።

የአዲስ ማለዳ ምንጭ አስከትለውም፣ “የነዋሪዎቹን ቤት የሚያቃጥሉት ጁንታና ሸኔ ናቸው” ብለዋል። የሕወሓት አባሎች በአካባቢው ይኖሩ እንደነበር የገለጹት የመረጃ ምንጩ “መታወቂያቸው እየተቀየረላቸው ወደ አዲስ አበባ እየገቡ ነው” ሲሉም ጠቁመዋል።
የሕወሓት ታጣቂዎችም ከሊሙ ወረዳ ወጣ ብለው ክልል ስድስት ድንበር ላይ በዴሳ እና መንደር ስምንት በሚባለው አካባቢ እንደሚገኙም ነው ግለሰቡ ያመላከቱት።

ከብትና ንብረት ቀድሞ ተዘርፎ ስለላለቀ በቃጠሎው የወደመው ቤት ብቻ እንደሆነም ማወቅ ተችሏል። የተቃጠለው ባዶ ቤት ብቻ ነው የሚሉት የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ በሊሙ ወረዳ መንደር ስድስት ብቻ ታጣቂዎቹ ለኹለት ዙር ባደረጉት ዘረፋ በመጀመሪያው ዙር 300፣ በኹለተኛው ዙር 650 የአካባቢው ነዋሪ ከብቶች ቀድመው ተወስደዋል ነው ያሉት።

በዚሁ መንድር ብቻ 800 አባውራዎች ይኖሩ ነበር ያሉት የመረጃ ምንጭ፤ ነዋሪዎቹ ተፈናቅለው ወደ አንገር ጉትን ከተማ መሔዳቸውን ጠቁመዋል። አስከትለውም፣ በሊሙ ወረዳ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ተለቅመው መጥተዋል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል፣ በጊዳና ሊሙ ወረዳ ደንበር አባሙሳ ተብሎ በሚጠራው መንደር 10 የነበሩ ነዋሪዎች በሕወሓት ታጣቂዎች እየተፈናቀሉ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ሌላኛው የሊሙ ወረዳ ነዋሪ በበኩላቸው፣ በዚህ ሳምንት ውስጥ ደግሞ አንድ ሰፈር ፈርሶ ነዋሪዎቹ ወደ አንግር ጉትን ከተማ ተሰደዋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ጸቡ የተፈጠረው ከትግራይ ተወላጅ ጋር ነው ያሉት የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ ይህን ተከትሎም ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ነዋሪዎቹ ሙሉ ለሙሉ ወደ ጉትን ከተማ እንደተፈናቀሉና ቤት ንብረታቸው እየተቃጠለ ጠቁመዋል።

የአዲስ ማለዳ የመረጃ ምንጭ አክለውም፣ በአባውራ ደረጃ ከ200 በላይ ለቆ ወጥቷል ሲሉ ገልጸው፣ በተሠነዘረው ጥቃት አምስት የአባሙሳ ነዋሪዎች ሕይወታቸው አልፏልም ብለዋል። አስከትለውም “አሁን እያስወጧቸው ያሉት ጁንታዎች ናቸው” ያሉ ሲሆን፣ ሦሰት ቤቶች እንደተቃጠሉና ይህ ዘገባ እየተዘጋጀበት በነበረበት ወቅት (መጋቢት 15/2014) ሌሎች ቤቶችም በመቃጠል ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቀድመው ያላሸሹ ቤታቸው ብቻ ሳይሆን ንብረታቸውም እየተቃጠለ ነው ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል። የአባሙሳ ከተማ ነዋሪዎች አንዳንድ ሰዎች ዕቃቸውን ይዘው ሌላኛዎቹ ደግም ልጆቻቸውን ብቻ አስከትለው ወደ ጉትን ከተማ ጠቅልለው እየገቡ መሆናቸውን ከምንጮች መረዳት ተችሏል።

የአዲስ ማለዳ ምንጭ በመጨረሻም አንድ የአባሙሳ ወረዳ ነዋሪ፣ ታጣቂዎች ዛፍ ላይ በገመድ አንጠልጥለውት ሕይወቱ ሳያልፍ ተገኝቷል ብለዋል። አስከትለውም መንገድ ተዘግቶብናል መፍትሔ አልተሰጠንም ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም ዕትሟ በሊሙ ወረዳ 24 ቤቶች መቃጠላቸውን መዘገቧ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here