በሱማሌ ክልል በቦምባስ ከተማ በተፈጠረ ግጭት ሰዎች መሞታቸው ኢዜማ አስታወቀ

0
822

ሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መጋቢት 12/2014 በሱማሌ ክልል በቦምባስ ከተማ በተፈጠረው ግጭት የሰው ህይወት መጥፋቱንና በዜጎች ላይም የአካል ጉዳት ማጋጠሙን ታማኝ ከሆኑ ምንጮች መረጃ ደርሶኛል ሲል አስታውቋል፡፡

ፓርቲው በቦምባስ ከተማ ሊካሄድ በነበረው የአኪሾ የጎሳ መሪ ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት፤ የጸጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል በመጠቀማቸው የሰው ህይወት የጠፋ ሲሆን፤ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡

በክልሉ በተለያዩ ጊዜ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የጎሳ ምርጫ የሚደረግ ሲኾን፤ በቅርቡ ሊደረግ የነበረው የአኪሾ ጎሳ መሪ ምርጫ ድብቅ የፖለቲካ አላማ ያላቸው አካላት ፍላጎታቸውን ለማሳካት ባደረጉት ጥረት በጸጥታ አካላትና በሕዝቡ መሀከል ግጭት እንዲነሳ በዛም ደግሞ ንጹሃንን ተጎጂ ያደረገ ጉዳት ደርሷል፡፡

በሱማሌ ክልል በተለያየ ጊዜ የሰውና የመንግሥትን ንብረት ያወደመ፣ የሰውን ሕይወት የቀጠፈ ግጭት ከተፈጠረ በኋላ የግጭቱ መነሻ ምን እንደሆነ ሳይጣራ፣ አጥፊዎች ተለይተው ለህግ ሳይቀርቡ፣ የፍትህ ሥርዓቱ አስተማሪ የሆነ ቅጣት ሳያስተላልፍ፤ በመንግሥት ኃላፊዎች እገዛ ጭምር ግልፅ ያልሆነ የእርቅ ሂደት መከናወኑ ግጭቶች እንዲደጋገሙ መንገድ ከመክፈቱ በተጨማሪ የክልሉን ሰላም ከቀን ወደ ቀን አስተማማኝ እንዳይሆን እያደረገው ይገኛል ሲልም ኢዜማ ገልጿል፡፡

የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከዚህ ድርጊት በስተጀርባ እጃቸው ያለበትና የሚመለከታቸውን አካላት ማንነት በማጣራት አፋጣኝ ፍትህ እንዲሰጥ ያሳሰበው ፓርቲው፤ ግጭቱን ተከትሎ የቆሰሉ አካላት ተገቢ ሕክምና እንዲያገኙ፣ የሟች ቤተሰቦችም ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙ ጠይቋል፡፡
____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here