ማክሰኞ መጋቢት 20 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ዘመን ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር በአገራችን የመጀመሪያ ነው ያለውን (ኤም ፒ ጂ ኤስ) የተሰኘ አዲስ የማስተር ካርድ የክፍያ ሥርዓት በዛሬው ዕለት አስተዋወቀ።
ባንኩ አዲስ ያስተዋወቀው ይህ የክፍያ ሥርዓት፤ በድረገፅ የሚደረጉ ክፍያዎችን ከማስተር ካርድ የክፍያ ዘዴዎች ጋር በማጣመር በዘመን ባንክ ፣ ማስተር ካርድ እና ቪዛ የካርድ ግብይት በዲጅታል መንገድ ክፍያ የሚያከናኑበት የክፍያ አማራጮ መሆኑ ተገልጿል።
የክፍያ አገልግሎቱ ተግባራዊ መሆኑ፤ ደንበኞች ከክፍያ ጋር በተያያዘ አለም ዓቀፍ ተደራሽነታቸው እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል ያሉት የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ደረጀ ዘነበ፤ አገልግሎቱ ደንበኞች ባሉበት ሆነው ክፍያ ሊፈጽሙ የሚችሉበት አሰራር እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
የባንኩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምክትል ፕሬዝዳንት አምሃ ታደሰ በበኩላቸው፤ በዚህ የማስተር ካርድ የክፍያ መስጫ ሥርዓት፤ ሆቴሎች፣ የንግድ ሱቆች፣ የጉዞና አስጎብኚ ድርጅቶች፣ የንግድ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች እና ሌሎችም የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
በተጨማሪም የአየር መንገድ ደንበኞች የ ኢ-ኮሜርስ አሰራርን በመጠቀም ቦታ እንዲይዙ እና የበረራ ቲኬቶችን በበይነ መረብ አማካኝነት እንዲከፍሉ አንደሚያስችላቸውም አምሃ ገልፀዋል።
አገልግሎቱ ክፍያዎችን በቪዛ እና ማስተር ካርድ በበይነመረብ ደብዳቤ-ትዕዛዝ፣ በስልክ ጥሪ ትዕዛዝ እንዲሁም በጥሪ ማዕከሎች ወይንም ሞባይል-ኮሜርስ በኩል መፈፀም እንደሚያስችልም ተነግሯል።
ባንኩ አዲሱን አገልግሎቱ ባስተዋወቀበት በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይም የማስተር ካርድ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የባንኩ የቦርድ አባላት እና ከፍተኛ የሥራ አመራሮች ተገኝተውበታል።
ዘመን ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር ባሳለፍነው ዓመት በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ከንክኪ ነፃ የተጓዦች ካርድ በማስተዋወቅ ደንበኞች በጉዟቸው ወቅት ክፍያቸውን ያለ ጥሬ ገንዘብ በዶላር እና በዩሮ እንዲፈፅሙ ማስቻሉ ይታወሳል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n








