ጅምላ ጨራሹ ኮቪድ19 እና የተፈጥሮ ሀብት!

Views: 349

ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ከወራት ቀደም ብሎ ምድርን ከተቀላቀለ ጀምሮ ለሰው ልጅ እረፍትና ሰላም ነስቶ ይገኛል። ቫይረሱ በቻይና ዉሃን ግዛት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው ከእንስሳ ወደ ሰው ልጅ ተላልፎ ነው የሚል ዘገባ ሲሰማ የቆየ ሲሆን፣ ፕሮፌሰር መንግሥቱ ውቤ (ዶ/ር) እንደውም የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ባለመጠቀምና ደንን በመጨፍጨፍ፣ እንስሳቱንም ከመኖሪያቸው በማፈናቀል የተከሰተ ነው ሲሉ ይሞግታሉ። ባሳለፍነው ታኅሳስ ወር ላይ ‹‹የሕይወቴ ስንክሳር›› የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ ያበቁት መንግሥቱ፣ ከዛም በላይ የሰው ልጅ ግጭትና መጎዳዳት፣ አንዱ በአንዱ ላይ በመነሳቱም ለከፋ ጉዳት ዳርጎናል ሲሉ ጠቅሰዋል።

ኮሮና ቫይረስ (Coronavirus/COVID-19) በዉሀን (Wuhan) ግዛት ቻይና ከተከሰተ ወዲህ ኁልቆ መሳፍርት የሆነ ሀብት ለማካበት ስንል የተፈጥሮ ሀብታችንን እያወደምንና የሰው ልጆች እርስ በእርስ እየተጎዳዳን የምንገኘ ሁሉ ዘር፣ ቀለም፣ ሀይማኖት የማይለየው፣ ሀብታም ደሀ፣ ጉልበታም ደካማ፣ ገዥና ተገዥ፣ አፈናቃይ ተፈናቃይ የማይለው ኮሮና ቫይረስ (COVID 19) የጅምላ ጨራሽ መሣሪያ ታጥቆ መግቢያና መዉጫ በማሳጣት እያስጨነቀን ይገኛል።

ይህ ቫይረስ የትና እንዴትስ ተፈጠረ፣ ስርጭቱስ ምን ይመስላል? ከዚህ ጭንቀት ተምረን የባሰ ጅምላ ጨራሽ በሽታ እንዳይፈጠር ምን ማድረግ አለብን? የተለያዩ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ከሆነ ቫይረሱን የተሸከሙት እንስሳቶች ከዉሀን ነዋሪዎች ጋር በመገናኘታቸዉ በሽታውን አስተላፈውታል። ችግሩም በዚህ ቦታ ሳይገታ በፍጥነት ወደተለያዩ የቻይና ግዛቶችና ወደሌላው የዓለም ክፍል በፍጥነት ሊዛመት ችሏል።

የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማም ከአሁን ቀደም ያልተፈጠረ ችግር አሁን እንዴት ተከሠተ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ነው። ለዚህም ከተለያዩ የጥናት ውጤቶች ያገኘሁትንና በአገራችን ላይ ያደረኩትን ተመሳሳይ ዘገባ መሠረት በማድረግ ነው።

በዚህ ርዕስ ላይ በቅርቡ በተደረገ ጥናት፣ የተፈጥሮ ሀብት ውድመት ካስከተለው የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ከዚህ ቫይረስ መፈጠርና መስፋፋት ጋር ግንኙነት እንዳለው ያስረዳል። እንደነዚህ አጥኚዎች አባባል ከመቶ ሰባ የሚሆኑት አዳዲሰ በሽታዎች ከእንስሳት ንክኪና መመገብ ጋር የተያያዘ ነው ሲሉም ያትታሉ።
ሉይስ እና ሌሎች ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ዉሀን (Wuhan) ግዛት በጫካ ያሸበረቀች በአራዊት ሀብቷ ደግሞ የታደለች ነበረች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የተፈጥሮ ልብሷን በመቀማቷ የዱር አራዊቶቿ ለብዙ ሺሕ ዓመታት ቫይረሱን ተሸክመው ከሌሎች እንስሳቶች ጋር ተቻችለዉና ተዛምደዉ (Coexistence) የኖሩበትን ቦታ ሳይወዱ በግድ እየለቀቁ ነው። ለቅቀውም ሰዉ ወደሚኖርበት አካባቢ (ወደ ከተማ ጭምር) በመምጣታቸው ለእነርሱ አዲስ ያልሆነ ወይም የማይጎዳ ለሰዉ ልጅ ግን ሰምቶትና ዐይቶት የማያውቀውን ገዳይ በሸታ ማስተላለፍ ችለዋል።

እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ2003 ‹ሳርስ› የሚባል አዲስና ከኮሮና ቫይረስ ጋር ዝምድና ያለው በሽታ በቻይና ተከስቶ ብዙ ሰዎችን መፍጀቱ አንዱ አሳማኝ ምስክር ነው ይላሉ። አኔም የእነዚህን ሰዎች የምርምር ዉጤት በመጋራት፣ በመጀመሪያ የተፈጥሮ ሀብት መዉደም ያስከተለዉ የአየር ንብረት ለውጥ መሠረታዊ ምክንያት እንደሆነ በአጭሩ አስረዳለሁ።

የአየር ንብረት ለውጥ ክስተት በኹለት መንገድ ሊታይ ይችላል፤ አንደኛዉ በተፈጥሮ የነበረ፣ ያለና የሚኖር ነው። ማለትም መሬትን የሸፈኑ ቅርፊት መሰል አካላት ንቅናቄ (Lithosphere)፣ የመሬት መንቀጥቀጥና የእሳተ ገሞራ መከሰት (Seismicity & Volcanic Activity)፣ የካርቦንና የናይትሮጅን ውህደትና በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ የሚገኘው ዉቅያኖስ ገፅ የሙቀት ለውጥ (El-Nino) የመሳሰለው ነው።

ከመቶ ዘጠና የሚይዘው ኹለተኛዉ ምክንያት ግን የተፈጥሮ ሀብት ዉድመት፣ ቁጥጥር የሌለው የሕዝብ ብዛት፣ የበረሀ መስፋፋት፣ የተፈጥሮ ሀብት ሕግን ያልተከተለ የመሬት አጠቃቀም ስርአት፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከእጨትና ከከሰል፣ ከደን ቃጠሎ፣ ከትራንስፖርትና ከጄኔሬተር የሚለቀቅ በካይ ጋዝ (N2O፣ SO2፣ CO2፣ CO,፣ Pb) እንዲሁም ከኮንስትራክሽን የሚወጣ ብናኝ ነገር እስከ 2.5 ማይክሮ ሜትር ፓርቲክል ነው።

ሰው ሠራሽ ምክንያቶች በተፈጥሮ የሚከሰተውን ችግር በማባባስ ለሰውና ለእንስሳት በሽታ፣ ለምግብ እጥረት፣ ለድህነት፣ ለፖለቲካ አለመረጋጋትና ለወንጀል መስፋፋት የሚዳርጉ ናቸው። ምንም እንኳ ጠለቅ ያለ ምርምር የሚያስፈልግ ቢሆንም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን እየተስፋፋ ያለው የአስም፣ የካንሰር፣ የኩላሊት ወዘተ በሽታዎች ከላይ ለተጠቀሱት እንደ አንድ ምክንያቶች ሊቆጠሩ ይችላሉ ብል ስህተት አይሆንብኝም።

በአጭሩ በተፈጥሮ ምክንያት የሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ከእኛ ቁጥጥር በላይ ስለሆነ የተፈጥሮ ክስተቱን ለመለማመድ እንድንችል የመሬት አጠቃቀም ስርአትና ለአካባቢ ጥበቃ ደኅንነት ስንል አስተሳሰባችንን ከለወጥን፣ ችግሩን መቋቋም እንችላለን እላለሁ።

የተፈጥሮ ሀብት አውዳሚ ቴክኖሎጂን (ጥበብን) በማንገብ ከልክ በላይ ሀብት ለማጋፈፍ ስንል ለምግብ፣ ለመድኃኒት፣ ለልብስ፣ ለመጠለያ፣ ወዘተ፣ የሚያገለግለንን የደን ሀብታችንን ስላወደምን፣ የኛ በጥበብ መራቀቅ ይህን አዲስና የጅምላ ጨራሽ በሽታ (COVID-19) መቋቋም አልቻለም። አቅማችን እስከዚህ ድረስ ዉሱን መሆኑን መገንዘብም ችለናል፤ ለወደፊቱም ማወቅ ይኖርብናል። የተፈጥሮ ሀብትን በማውደም፣ የሕዝብ ሀብትን በመዝረፍ እንዲያም ሲል ወገንን በመግደልና በማፈናቀል፣ ከልክ ባለፈ ሀብት በመንደላቀቅና የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም ጥምን ለማርካት የምናደርገውን ሩጫና መቅበዝበዝ ካላቆምን፣ ከዚህ የባሰ ችግር ፈጥረን መጠጊያና መሸሸጊያ እንዳናጣ ካሁኑ ቆም ብለን እንድናስብ አንገደዳለን።

ይህ ጅምላ ጭራሽ መሣሪያ የዘመኑ ጥበብ/ሳይንስ ሳያግደው በአጭር ጊዜ ዉስጥ የዓለምን ሕዝብ ማሽቆጥቆጡ የተፈጥሮን፣ የኅብረተሰብን፣ የአስተዳደርና የሀይማኖት ሕግና ሥርዐትን ባለማክበራችን የተፈረደብን ፍርጃ ይመስለኛል። በሽታን መከላከል እንድንችል ዕፅዋት ለምግብና ለመድኃኒት እንዲያገለግሉን፣ ለልብስና ለመጠለያ እንዲሆኑን ብቻ ሳይሆን ያላግባብ እንዳንጠቀምባቸዉና እንዳናጠፋቸዉ፣ ካጠፋናቸዉ ደግሞ ከፍ ያለ ቅጣት እንደሚከተለን ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከሳይንስ የምርምር ዉጤቶች መማር እንችላለን።

የአምላክንና የተፈጥሮ ሕግን በመጣስ የብዛ ሕይወት መገኛ የሆኑትንና የአየር ንብረት ለውጡን እንድንቋቋም የተፈጠሩልንን በአማዞን፣ በምዕራብ አፍሪካ፣ ሰሜንና ደቡብ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ማላይዥያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኢትዮጵያ፣ ወዘተ፣ የሚገኙትን የተፈጥሮ ሀብት በጭካኔ በመጨፍጨፋችን ለድርቅ፣ ለደን ቃጠሎ፣ ላልተጠበቀ ጎርፍና ማዕበል፣ ብሎም ለምግብ እጥረትና ለስደት ተዳርገናል። ይህ ሁኔታ ተፈጥሮአዊ የነበረውን የአየር ንብረት ለውጥ በማባባሱ ከተፈጥሮ ጋር የነበረንን መልካም ግንኙነት አናግቶታል። ስደቱም በሰው ዘር ብቻ ሳይወሰን የዱር አራዊትም ሆኑ ሌሎች ፍጥረታትን ለስደት እየተዳረጉ ናቸው።

ምንም እንኳ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ለጥናት በምዘዋወርበት ወቅት ከተፈጥሮ ሀብተ ጭፍጨፋ ጋር በተገናኘ ተመሳሳይ በሽታዎች መከሰታቸዉን የተመለከትኩ ብሆንም፣ ሰሜንና ምዕራብ ጎንደር በተለያዩ ቦታዎች የደረሰውን እንደምሳሌ ማንሳት እፈልጋለሁ። አንዱ ደምቢያ ወረዳ ሲሆን ሌላው ደግሞ ከጎንዳር ዙርያ ስድስት ቀበሌዎች ናቸዉ።

እነዚህ ቦታዎች ከልጅነት እድሜዬ ጀምሮ ሳውቃቸዉ ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈኑ፣ እንደ ደጋ (ሀይላንድ) ዉሀ የጠሩ ወንዞች የሚፈሱባቸውና የሚመነጩባቸው፣ ብርቅዬ የቤት እንስሳትና የዱር-አራዊቶች የሚፈነጩባቸው፣ ነዋሪዎችም ሰውነት-ገምቢ ምግቦችንና የእንስሳት ተዋፅዖ በበቂ ሁኔታ የሚያገኙባቸው፣ የሰውም ሆነ የእንስሳት በሽታ እምብዛም የማይታይባቸዉ አካባቢዎች ነበሩ።

በዚህ ወቅት ግን፣ የተፈጥሮን ሕግ ከሚፃረር የመሬት አጠቃቀምና ከሕዝብ ብዛት የተነሳ፣ እነዚህ ኹለት ቦታዎች አምላክ የለገሳቸውን ልብስ ተገፈዉ እርቃናቸውን ሲቀሩ፣ ቁጥር ስፍር የሌለው የዱር አራዊቶችም ተሰደዱ፣ ብዙዎቹም ሞቱ። ብዙ ሕዝብም በቢጫ ወባና በሌሎች አደገኛ በሽታዎች በመቀጣቱ፣ ቀባሪ እንኳ ለማግኘት አስቸጋሪ ጊዜ እንደነበር የቅርብ ትውስታዬ ነው። የዚህ ዓይነቱ በሽታ በእነዚህ አካባቢዎች ተከስቶ የማያውቅ መሆኑን ነዋሪዎች ያስረዳሉ።

በአሁኑ ወቅት የሕይወታችን መሠረት የሆነውን የተፈጥሮ ሀብት መጨፍጨፋችን አልበቃ ብሎ፣ የሥልጣን ጥማችን ለማርካት፣ ቂም በቀል ለመወጣትና ሀብት ለማግበስበስ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ወገናቻችን ተጨፍጭፈዋል። ቤታቸውና ንብረታቸው ተዘርፏል፣ ተቃጥሏል። ለዚህ ዓይነቱ ጨካኝ ድርጊታችን ይሆን COVID-19 የማይታየውንና የማይዳሰሰውን ጅምላ ጭራሽ በሽታ ታጥቆ፣ እንኳንስ ከአንዱ አኅጉር ወደ ሌላው አኅጉር መጓጓዝ ይቅርና፣ ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት፣ ወላጅ ከልጆቹ፣ ዘመድ ከዘመዱ እንዳይገናኝ፣ የእግዚአብሔር ሰላምታ እንኳ እንዳይለዋወጥ በማድረግ በየጓዳችን እንድንቆዝም፣ እንድንፈራና እንድንቀጠቀጥ እያደረገን ያለው ቅጣት ነው ወይስ ማስጠንቀቂያ?

ምንም እንኳ ይህ ወረርሽኝ ከምድረ ገፅ እንዲጠፋ የሁላችን ምኞት ቢሆንም፣ አስተማሪነቱንም ማንሳት ደግሞ ያስፈልጋል። ለዓለም ስጋት አየሆነ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ መጨመር፣ ከኢንዱስትሪ አብዮት በፊት ወደነበረበት ለመመለስ በጉዳዩ ላይ ብዙ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ቢደረጉም፣ ሥጋቱ የሚያስጨንቃቸው አገራትም ሆኑ የመስኩ ጠበብቶች ድምጻቸውን ቢያሰሙም ችግሩ እየባሰ መፍትሄ ሳይገኝለት ቆይቷል።

ከቀናት በፊት የተነሳው የሳተላይት ስዕል የዓለም የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ልቀት ቀንሶ በማሳየቱ ዓለምን አስደምሟል። ይህ የሆነበት ምክንያት ኢንዱስትሪዎች፣ የየብስ፣ የአየርና የባህር መገናኛዎች ሥራ ማቆምና፣ የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ሁሉ በዚህ ጅምላ ጨራሽ በሽታ ተገትቶ ፀጥ ረጭ በማለቱ ነው። በአገራችንም ዘርና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ያፈናቃይ ስብሰባ በዚህ ወረርሽን በመገታቱ፣ ለመፈናቀልና ለግድያ የተፈረደባቸው ወገኖቻችን ጊዜያዊ እፎይታን ያገኙ ይመስላል።

ያም ሆነ ይህ፣ እኛ የሰው ልጆች ከዚህ ተምረን በተፎጥሮ ሀብትና በወገኖቻችን ላይ የምናደርገውን ያልተገባ ጭፍጨፋና ማፈናቀል እንደምናቆም፣ የጋራ ጠላታችን የሆነውን ወረርሽኝ በሽታ እንድንገታና የውሀ ሀብታችን እንዳንጠቀም እያደደረጉን ያሉትን ኃይሎች በአምላክ ኃይል፣ በተግባርና በአንድነት ሆነን እንደምናሸንፋቸዉ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ።

ከዚህ በባሰ የጅምላ ጨራሽ መሣሪያ እንዳንቀጣ ከአሁኑ ምን ማድረግ አለብን? ስንል፤ አንደኛ እያንዳንዳችን በምናምነው አምላክ፣ በተፈጥሮ፣ በኅብረተሰብና በአካባቢ ጥበቃ ሕግ መመራት አለብን። የማንንም ብሔር፣ ዘር፣ ቀለም፣ ሀይማኖት ተከታይ አንግደል፣ አናፈናቅል፣ አንጥላ፣ የሕዝብን ሀብት አንስረቅ፣ ለሰላምና ለእድገት የሚጥሩትን ብሎም በተግባር የሚያሳዩ መሪዎችን በጥንቀቄ እንምረጥ፣ እናክብር፣ እንከባበር፣ ይቅርታም እንባባል።

ብቃት ያላቸውን የባህልና የዘመናዊ መድኃኒት አዋቂዎችንና ጠበብቶችን ወዘተ ፈጥነን በማገናኘት እናወያይ፣ መፍትሄም እንፍጠር። በመንግሥትና ኅብረተሰቡ ትብብር ለአደንዛዥ ሱስና ለሌላ ዓላማ ሲባል የተገነቡትን ግንቦች አሁኑኑ እናፍርስ። በአንጻሩ ወጣቱን ትውልድ ወደ ትክክለኛው ጎዳና ሊመልሱ የሚችሉ ተቋማትን ከእድር ቤት ጀምሮ እስከ ላይኛው ጣራ ድረስ የሚዋቀሩበትን መንገድ በፍጥነት እንፈልግ።

እያንዳንዳችን ኃላፊነታችንን እንወጣ። ተፈጥሮንና ወገናችን ለማጥፋት ከምንፈላሰፍ ይልቅ ለአዲስ አስተሳሰብ፣ ለአዲስ ጥበብ፣ ለሰውና ለተፈጥሮ ሀብት ደኅንነት፣ ለምግብ ዋስትና እንትጋ።

እንደ ማጠቃለያ ጽሑፌን ለመደምደም ያህል፣ ወባን፣ ቢጫ ወባን፣ ኢቦላን፣ ሳርስ፣ ሜርስ፣ ስዋይን ፍሉ፣ በርድ ፍሉ እና ሌሎችንም በሽታዎች ጭምር ለማጥፋት መድኃኒት እስክናገኝ አሁን ያለንን የመፍትሔ ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ አለብን። ማድረግ ካለብን ጥንቃቄ በተጨማሪ ሌላ አዳዲስ በሽታዎች እየተፈጠሩ ስለሆነ፣ ከዚህ ችግር ተምረን አስተሳሰባችንን ከአሁኑ በመለወጥ የአየር ጠባይ ለውጥ አባባሽ የሆነውን የተፈጥሮ ሀብት ጭፍጨፋና፣ በወገኖቻችን ላይ የምናደርሰውን ጭካኔ ማቆም ይኖርብናል። ካልሆነ በሌላ የጅምላ ጨራሽ በሽታ (በCOVID-20) እንዳንጠፋ እንጠንቀቅ።

ተባባሪ ፕሮፌሰር መንግሥቱ ውቤ (ዶ/ር) የአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ ባለሞያ፣ተሟጋችና ሕጋዊ አማካሪ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው E-mail: biofoodp@gmail.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com