አገራት ሕዝባቸውን ወደ እድገት ጎዳና ለመውሰድ በየተወሰኑ ዓመታት የሚከለስና ተግባራዊ የሚደረግ ዕቅድን አውጥተው ያስፈጽማሉ፤ መከናወኑንም እየገመገሙ ተግባራዊ ያስደርጋሉ። ኢትዮጵያም ተመሳሳይ መንገድን እየተከተለች፣ የሕዝብን ፍላጎት የሚያሟላ የሚባሉ ዕቅዶችን የተለያዩ መንግሥታት ይፋ ሲያደርጉ ኖረዋል። በቅርቡም ‹የዐስር ዓመት ዕቅድ› የሚባል ተሠርቶ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ወደሥራ እንደተገባ ቢነገርም፣ ያለዕቅድ የተከሰተው ጦርነት ብዙውን እንዳመሰቃቀለው ይነገራል። የዕቅዱን አንኳር ጉዳዮች እያነሱ ከወቅታዊውኹኔታ ጋር በማገናዘብ መከለስ አለበት የሚሉት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ቶፊቅ ተማም ምልከታቸውን እንዲህ አስፍረዋል።
መንግሥት ባለፉት ዓመታት በልማት ዕቅድ ትግበራ የታዩ ክፍተቶችን እንዲሁም የተመዘገቡ ጠንካራ ጎኖች ከግምት ውስጥ በማስገባት በቀጣይ ዐስር ዓመት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማሳለጥ የሚረዳ ‹‹አፍሪካዊ የብልጽግና ተምሳሌት›› አገራዊ የዐስር ዓመት የልማት ዕቅድ አዘጋጅቷል። የልማት ዕቅድ የኢትዮጵያን ነባራዊ ኹኔታን ያገናዘበ ገበያ መር የኢኮኖሚ ሥርዓት (Pragmatic Economic system) በመከተል፣ የግል ዘርፉን ጉልህ ሚናና ተሳትፎ በማሳደግ፣ የበለጸገች አገር መገንባት፣ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ኹኔታን መፍጠር፣ ፈጣንና ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ ምርታማነት፣ ጥራትና ተወዳዳሪነት በማጎልበት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ (Structural Economic Transformation) ማረጋገጥ፣ የማኅበራዊ አካታችነት ማረጋገጥ፣ ዜጎች የልማቱ ባለቤትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ብቁ ገለልተኛ ነፃ የሕዝብ አገልግሎት ሥርዓት በመገንባት የመንግሥትን የመፈጸም ብቃት ማጎልበትና መልካም አስተዳደርን በማስፈን የዜጎችን ዕርካታ ማሳደግ እና ሠላምና ፍትሕን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ሥርዓት በመገንባት የሕግ የበላይነትንና ሰብዓዊ መብትን በማስከበር የዜጎችን ደኅንነት ማረጋገጥ፣ የልማት ዕቅድ ዋና ዓላማ ነው።
በተጨማሪም፣ የልማት ዕቅድ ለሀገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ቀጣይ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችና ዓላማዎችን በማስቀመጥ የአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገትና ልማትን በረጅም ጊዜ ዕቅድ በመምራት፣ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር የማምጣት ዓላማን ለማሳካት፣ ብሎም ኃላፊነትና ተጠያቂነት በግልፅ በማስቀመጥ ውጤታማ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እና የጋራ ብልጽግና ለማስፈን የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።
መንግሥት ይህንን የዐስር ዓመት የልማት ዕቅድ አዘጋጅቶ ለመተግበር ያሳየው ቁርጠኝነት ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም፣ በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት ከሕወሓት ጋር በተደረገው ጦርነት ሳቢያ ይህን የልማት ዕቅድ በአግባቡ ለማሳካት የነበረው ውጥን ላይ ቀላል የማይባል አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። የዚህ ጽሑፍ ዓላማም በልማት ዕቅዱ የመጀመሪያ ዓመት (2013- 2014) በጦርነቱ ሳቢያ ዕቅዱ በተቀመጠለት መልኩ እንዳይሳካ አሉታዊ ተጽዕኖ የደረሰባቸውን የልማት ዕቅዱን ዘርፎች በጥቂቱ በማየት የተሻለ የማካካሻ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ተግባር ይገባ ዘንድ በተለይ በዝግጅትና አተገባበር፣ በክትትልና ግምገማ ላይ የተሻለ አቅም ያላቸው አካላት ትኩረት ይሰጡት ዘንድ፣ ብሎም የሚጠበቅባቸውን በያገባኛል ስሜት ያበረክቱ ዘንድ ለመጠቆም ነው።
የ“ፊስካል ፖሊሲ”
ፊስካል ፖሊሲ ዋና ዓላማ የወጪ በጀትን በዋናነት በአገር ውስጥ ገቢ በመሸፈንና የበጀት ጉድለት ዝቅተኛ እንዲሆን በማድረግ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ምቹ የማክሮ ኢኮኖሚ ኹኔታን ማስፈን ነው። ከዚህ በተጨማሪም፣ የአገር ውስጥ ገቢን በተለይም የታክስ ገቢን ማሳደግና በአገር በቀል የፖሊሲ ማሻሻያዎች ላይ በመመስረት ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ መልኩ አገሪቱ ቅድሚያ የሰጠቻቸው የልማት ፕሮግራሞችን ፋይናንስ ለማድረግ ቁልፍ ሚና አለው›› (ገፅ 8) በማለት የሚያስቀምጠው የልማት ዕቅዱ፣ የመንግሥት ገቢና ወጪን ጤናማና ዘላቂ ለማድረግ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ገቢን የሚያሳድጉና በአንፃሩ የአገራችን የዕዳ ጫናን ለመቀነስና በዘላቂነት ጤናማ የብድር ኹኔታ እንዲኖር ለማድረግ አቅጣጫ ተቀምጧል።
የአገር ውስጥ ገቢን በተለይም የታክስ ገቢን በማሳደግ የልማት አጀንዳዎችን ለማስፈፀም የሚያስፈልገውን ፋይናንስ አስተማማኝና ዘላቂ በሆነ መልኩ በማሰባሰብ የውጭ ዕርዳታና ብድር ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ የመንግስት ጠቅላላ ገቢ በተለይ የታክስ ገቢን ማሳደግ የሚያስችል ቢሆንም፣ ባለፈው ዓመት ብቻ በተለይ በአማራና በአፋር ክልል በነበረው የጸጥታ መደፍረስ ሳቢያ፣ በርካታ ቢሊየን ብሮች አለመሰብሰባቸው በራሱ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ጫና ያሳድራል። መንግሥት በልማት ዕቅዱ አሳካዋለሁ ብሎ ካስቀመጠው ከታክስ የሚገኝ ገቢን ማሳደግ፣ ብሎም ከታክስ የሚገኝ ገቢ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የሚኖረውን ድርሻ ከ9.2 በመቶ ወደ 18.2 ለማድረስ የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካት ተግዳሮት እንደሚሆን ይጠበቃል።
በቀጣይ ይህን ለማካካስ ሠላማዊ በሆኑ ቅርንጫፎች የቆዩ ዕዳዎችን መሰብሰብ፣ አዳዲስ ወደ ታክስ መረቡ የሚገቡ ታክስ ከፋዮችን ቁጥር መጨመር፣ የግብር ማሸሽና ስወራ / Tax Evasion / መከላከል፣ ከዚህ ባለፈም ዘመናዊ የሀብት አሰባሰብን ተግባራዊ በማድረግ በጦርነቱ የታጣውን ኢኮኖሚ ለማካካስ ጥረት ማድረግ ያሻል። ቁጠባን መሠረት ያደረገ እጅግ በርካታ የበጀት አጠቃቀምን መከተል ግድ የሚል ሲሆን፣ የተሻለ የገቢ አሰባሰብ ስትራቴጂ ተቀርፆ ወደ ተግባር መግባት ብሎም ሌሎች የማካከሻ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል። አገሪቱ ካሳለፈችው ፈታኝ ጊዜ አንፃር የማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ጉልህ ድርሻ ያለው የወጪ ንግድ ገቢ በአንፃሩ የተሻለ አፈፃፀም አሳይቷል።
ባህልና ቱሪዝም ልማት
የባህልና ቱሪዝምን ልማት በተመለከተ፣ የልማት ዕቅዱ የትኩረት አቅጣጫዎች ብሎ ካስቀመጣቸው ነጥቦች መካከል ‹‹የአገሪቱን የቱሪዝም አለኝታዎች በአግባቡ መለየትና ማልማት፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መሠረተ ልማት ማጠናከርና ተጨማሪ አዳዲስ የቱሪዝም መስህቦችን በማልማትና ነባር መዳረሻዎችን በማጎልበት፣ ብሎም የቱሪዝም ምርቶችን ዓይነትና መጠን በማስፋፋት ተወዳዳሪነት ማሳደግ፣ ውጤታማ የገበያ ትስስር፣ ብራንዲንግና ፕሮሞሽን ሥራዎችን መሥራት፣ አዳዲስ የቱሪዝም ገበያዎችን መፍጠርና የገበያ ድርሻን ማሳደግ፣ ዘርፉን በቴክኖሎጂ፣ በጥናትና ምርምር በመደገፍ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ከፍ ማድረግ ትኩረት ይሰጣቸዋል።››(ገፅ 131) ይሁን እንጂ አገሪቱ ውስጥ በነበረው ጦርነት፣ እንዲሁም በኮቪድ ወረርሽኝ ሳቢያ አገሪቱ ከቱሪዝም ዘርፍ ወደ አንድ ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ገደማ የሚጠጋ ገቢ ማጣቷ ተገልጿል። ለዚህም ምክንያቱ በአሜሪካና አውሮፓ የጉዞ ክልከላዎች መደረጋቸው እና የቱሪዝም መዳረሻዎች የትራንስፖርትና የሆቴል አገልግሎቶች መቋረጣቸው፣ በአገሪቱ የሚደረጉ ዓለም ዐቀፍ ስብሰባዎች ወደ ኦንላይን መቀየራቸው፣ ይህም ከኹነት ቱሪዝም ( MICE Tourism) የሚገኝ ገቢ ክፉኛ እንዲያሽቆለቁል አድርጓል።
ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል አንድ አንድ የቱሪስት መዳረሻዎች የጦርነት ቀጠና ከመሆናቸው በተጨማሪም፣ በፀጥታው ችግር ሳቢያ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር መቀነሱ በቱሪዝም ልማት ላይ የታቀደውን ግብ ለማሳካት ተግዳሮት ይሆናል። ከዚሁ ጎን ለጎን አስጎብኚ ድርጅቶች ለባለ ሆቴሎች፣ ሎጅዎች፣ የትራንስፖርት አከራዮች እና ሌሎች የዘርፉ አካለት የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ተቋርጠው እንደነበር የሚታወስ ነው። ይህም በልማት ዕቅዱ መጨረሻ ዘመን 2022 በቱሪዝም ዘርፍ የሚፈጠር የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች ቁጥር 5.2 ሚሊየን ለማድረስ የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካት የሚፈታተን ይሆናል።
በእርግጥ በአሁኑ ሰዓት ምቹ ኹኔታዎች በመፈጠራቸው የቱሪዝም ዘርፉ፣ በተለይ የእናት አገርን ጥሪ ተቀብለው በመጡ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አማካይነት በደንብ መነቃቃት የጀመረ ሲሆን፣ በቅርቡ የተከበሩት የገና እና ጥምቀት በዓላት ለአብነት ሲጠቀሱ፣ ተዘግተው የነበሩ ብሔራዊ ፓርኮች (ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ) መከፈታቸው የራሱ የሆነ አዎንታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል። በቀጣይ ጉዳት የደረሰባቸውን የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ታሪካዊ መስኅብ የሆኑ ቅርሶች በመጠገን ወደ አገልግሎት መመለስ፣ አዳዲስ የቱሪስት መስኅብ ስፍራዎችን ማስተዋወቅ፣ የኹነት ቱሪዝም (MICE Tourism) በማሳደግ፣ እንዲሁም የጎብኚዎች ዕርካታ በመጨመር ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ጎብኚዎች ቁጥር ለማሳደግ ሠፊ የማስተዋወቅ ሥራዎች አጠናክሮ መቀጠል ይገባል።
የከተማ ልማት
“በአገሪቱ የሚታየው የማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ ልማትና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አንዱ የከተሞች ልማት ገፅታ ነው። ከዚህ አኳያ ከተሞች የኢኮኖሚ ልማትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ምንጭ እንዲሆኑ በከተሞች የማኑፋክቸሪንግ፣ ለከተማ ግብርና ለማዕድን ቱሪዝም ልማት ትኩረት ይሰጣል” ( ገፅ 12) በማለት የልማት ዕቅዱ ያስቀምጣል። የከተማ ልማትን የትኩረት አቅጣጫዎች በተመለከተ በልማት ዕቅዱ የተቀመጠ ሲሆን፣ በከተሞች ለ15 ሚሊየን ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የሥራ አጥነት ምጣኔን ከነበረበት 18.7 በመቶ በየዓመቱ በአማካይ በ 1 በመቶ በመቀነስ ወደ 9 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ታቅዷል።
ይህን ዕቅድ ለማሳካት ተግዳሮት የሚሆነው በነበረው የፀጥታ መደፍረስ በከተሞች ላይ በማኑፋክቸሪንግ ተቋማት ማለትም በብረታ ብረት ፣ ኬሚካልና ኮንስትራክሽን፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ ተቋማት እና ሌሎች ኢንደስትሪ ላይ በደረሰው የመሠረተ ልማት ውድመት ሳቢያ በልማት ዕቅዱ በትኩረት አቅጣጫ የተቀመጠው የነባር ኢንደስትሪዎች ምርትና ምርታማነት የማሳደግ ዕቅድ ወደ ኋላ ይጎትታል። በዚህ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት ሳቢያ የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር የጨመረ ሲሆን፣ ተጨማሪም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት / Foreign Direct Investment / በመሳብ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ምንጭ የሆኑት ኢንደስትሪ ፓርኮች ላይ የደረሰው ውድመት እና ዘረፋ፣ በዘርፉ የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች እጅጉን እንዲቀንሱ አድርጓል። ይህም ከተሞችን የኢኮኖሚና ልማት የሥራ ፈጠራ ምንጭ ለማድረግ የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካት ተግዳሮት ይሆናል።
በተጨማሪም፣ የከተሞችን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ የራሳቸውን ገቢ መጠቀም የሚችሉበት ኹኔታ በልማት ዕቅዱ የተመላከተ ቢሆንም፣ በጦርነቱ በከተሞች ላይ በደረሰው የከፋ ጉዳት ምክንያት ከተሞቹ የራሳቸውን ገቢ ሰብስበው የፋይናንስ አቅማቸውን ከማሳደግ አንፃር አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥርባቸዋል። ሌላው በልማት ዕቅዱ ገፅ 130 ላይ ከተሞችን የኢኮኖሚና ልማት ሥራ ፈጠራ ምንጭ እንዲሆኑ ለማድረግ በ972 ከተሞች አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሥራ ፈጠራ ማጎልበቻ ማዕከላት ለማቋቋም እንደታቀደ ያስቀምጣል። በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የወደሙ የሥራ ፈጠራ ማዕከላት ኢንተርፕራይዞች ተገቢውን ጥገና አድርጎና ወደ ሥራ ማስገባት የሚጠይቅ ሲሆን፣ ይህም በራሱ ከላይ የታቀደውን ዕቅድ በማሳካት ረገድ የራሱ የሆነ ጫና ስለሚኖረው ይህን በጦርነቱ ምክንያት በከተማ ልማት ላይ የደረሱ ጉዳቶችን ወደ ቀድሞ ለመመለስ የመልሶ ማገገሚያ ዕቅድ (Recovery Plan) ማዘጋጀት እና መተግበር ያስፈልጋል።
የትምህርትና ሥልጠና ልማት
ፍትሐዊ ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ ጥራትና ተገቢነትን ማረጋገጥ፣ መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ ብሔራዊ አንድነት፣ ብዝኀነትን የሚያረጋግጥ የትምህርት ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ የልማት ዕቅዱ የትምህርትና ሥልጠና ልማት የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው። የቀጣይ ዐስር ዓመት የትምህርትና ስልጠና ልማት ዓላማዎች ውስጥ፣ ‹‹ጥቅል የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት በ 2011 በጀት ዓመት ከነበረበት 41.8 በመቶ በ 2022 በኹለቱም ፆታዎች ወደ 100 በመቶ ፤ ከ 1ኛ- 6ኛ ክፍል ንጥር የትምህርት ተሳትፎ ወደ 100 በመቶ ፤7ኛ -8ኛ ክፍል ንጥር የትምህርት ተደራሽነት ወደ 100 በመቶ ፤ከ9ኛ -12ኛ ክፍል ንጥር ተሳትፎ ወደ 75 በመቶ ለማድረስ ግብ ተጥሏል››(ገፅ 151) በማለት የሚያስቀምጠው የልማት ዕቅዱ፣ ባለፈው አንድ ዓመት በትምህርት ዘርፉ በደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት፣ ብሎም በተከሰተው ማኅበራዊ ቀውስ ምክንያት ከኹለት ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው መክረማቸው በትምህርትና ሥልጠና የትኩረት አቅጣጫዎች የሆኑት ፍትሐዊ ተደራሽነትን፣ ጥራትና ተገቢነትን ከማረጋገጥ አንፃር የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳረፈ ነው።
በዕቅዱ የተቀመጠው የትምህርት ውስጣዊ ብቃትን / Internal efficiency / ከማሳደግ አንፃር መጠነ ማቋረጥ ምጣኔ በተለያዩ የክፍል ደረጃዎች ለመቀነስ ቢታቀድም፣ በፀጥታ መደፍረስ ሳቢያ ት/ቤቶች መውደማቸው የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ እጅግ ከፍ እንዲል አድርጓል። ይህም የዕቅዱ ተፋጻሚነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። ከዚሁ ጎን ለጎን መካካለኛ ደረጃ ባለሙያዎችን የሚያፈሩ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በተከሠተው የፀጥታ መደፍረስ ሳቢያ ከፍተኛ ለሆነ ውድመት እና ዝርፊያ በመዳረጋቸው በልማት ዕቅዱ ገፅ 154 የተመላከተውን ‹‹ የቴክኒክ ሙያ ሠልጣኞች ዓመታዊ መደበኛ መርሀ ግብር ቅበላ ዕድገት ከ 46 በመቶ ወደ 80 በመቶ፣ የቴክኒክ ሙያ አጠናቃቂዎች የመቀጠር ምጣኔ ከ 78 ወደ 96 በመቶ ›› ለማሳደግ የተጣለውን ግብ ለማሳካት ተግዳሮት እንደሚሆን ይጠበቃል። በተያያዘ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ልማት ስንመለከትም፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማ የደረሰው እጀግ የከፋ ውድመት፣ የወሎ ዩኒቨርሲቲን ብቻ ብንወስድ የወደመው ንብረት በገንዘብ ሲሳላ ወደ 10 ቢሊየን ገደማ ሲሆን፣ ዩኒቨርሲቲውን እንደገና ወደ ሥራ ለማስገባት ኹለት ዓመት እንደሚፈጅ ተነግሯል። ይህም ለማሳካት በታሰበው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ልማት ዕቅድ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም።
የጤና ልማት
‹‹ጤና ማበልጸግና በሽታ መከላከል ላይ ያተኮረ የማይበገር የጤና ሥርዓት በመገንባት የሕብረተሰቡን ጤና ማሻሻል እና ለኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋፅኦ ለማበርከት ኹሉን ዐቀፍ የጤና ሽፋንን በማረጋገጥ፣ ዜጎች በጤና ችግር ምክንያት ለኢኮኖሚ ቀውስ ሳይዳረጉ የጤና አገልግሎቶች ማረጋገጥ፣ መከላከል በሚችሉ ምክንያቶች የሚደርሱ የእናቶችና ሕፃናት ሞት መግታት›› የሚሉት የልማት ዕቅዱ የጤና ዘርፍ ዋና ዋና ዓለማዎች ናቸው። የእናቶች ሞት ምጣኔን፣ ከ አምስት ዓመታት በታች ያሉ ሕፃናትን ሞት፤ ከአምስት ዓመት ዕድሜ በታች ያሉ ሕፃናትን የመቀንጨርና የመቀጨጭ ምጣኔ ለመቀነስ፣ ኹሉንም ዓይነት የክትባት ዓይነቶች የወሰዱ ከ 1 አመት በታች ያሉ ሕፃናት ቁጥር በዕጥፍ ለመጨመር ቢታቀድም፣ በጦርነቱ ምክንያት በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ ውድመት እና ዘረፋ በመካሄዱ፣ ብሎም በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት እጅጉን የከፋ የጤናና ማኅበራዊ ጉዳቶች ተከስተዋል። በተለይ ሕፃናት ለከፍተኛ የምግብ ዕጥረት / Malnutrition / ሲጋለጡ፣ ሴቶች ለከፍተኛ የፆታ እና ሥነልቦናዊ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል። በዚህም ሳቢያ በጤናው ዘርፍ የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት እጅግ ከፍተኛ ርብርብ ይጠይቃል። በጤናው ዘርፍ የተከሰቱ የመሠረተ ልማት ጉዳቶችን ጠግኖ ወደ ነበሩበት ለመመለስ በአገር ውስጥ ባሉ የጤና ተቋማት የሚደረገው ድጋፍ እጅግ ሲበረታታ፣ ወደ አገር በገቡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እየተደረገ ያለው ድጋፍ የደረሰው ከፍተኛ ውድመት በመጠኑም ቢሆን የሚክስ ነው። በዐስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የጤና ልማቱን ለማሳካት የተቀመጡ የማስፈፀሚያ ስልቶችን ማለትም የጤና አገልግሎቶች አቅርቦት፣ ቅንጅታዊ አሠራር ማጠናከር፣ የጤናውን ሥርዓት ዕቅድ አፈፃፀም ከባለድርሻ አካላት ጋር መሥራት፣ የመንግሥትና የግል አጋርነት በጤናው ዘርፍ ለማስፋት ልዩ ትኩረት ሠጥቶ መረባረብ ከተቻለ በልማት ዕቅዱ የተጣለውን ግብ ማሳካት የሚቻልበት ዕድል ይኖራል።
ለማጠቃለል ያህል ባለፈው አንድ ዓመት በነበረው የፀጥታ መደፍረስ ሳቢያ በልማት ዕቅዱ የተካተቱት ዘርፎች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጫና ያድርባቸዋል። ከነዚህ ውስጥም የግብርና ልማት ሲጠቀስ፣ በተለይ በጦርነቱ ሳቢያ የወደሙ ሰብሎች፣ በዓመቱ መታረስ የነበረበት መሬት አለመታረሱ፣ የአርሶ አደር መፈናቀል እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እንደ ተግዳሮት ሲጠቀሱ፤ የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ እና ተጠያቂነት በተመለከተም በፀጥታው ችግር ምክንያት ብዙ የአገልግሎት ሰጪ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት በደረሰባቸው ጉዳት ከአገልግሎት ውጪ ሆነው ከርመዋል። በፍትህ ልማት ዘርፍ ስንመለከት በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት በፍርድ ቤቶች ላይ የደረሱ ውድመቶች፣ በተለይ መዛግብት ላይ የደረሰው ውድመት በገንዘብ ሊተመን የማይችል ሲሆን፣ በዕቅዱ እንደተመላከተው ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ ላይ እና ጠንካራ የፍትሕ አገልግሎት ለማስፈን ተግዳሮት ይሆናል።
በአጠቃላይ መንግሥት መሪ የልማት ዕቅድ አቅዶ በመተግበር የተሻለ አገር ለመፍጠር ያደረገው ጥረት ጥሩ ጅማሮ ቢሆንም፣ ከኹሉም በፊት ሠላም የሚቀድም በመሆኑ መንግሥት የአገር ሠላም ማስጠበቅ ላይ የበለጠ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል። ያለ ዘላቂ ሠላምና ልማት የዐስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ግቡን የማይመታ በመሆኑ ፈጣሪ አገራችን ሠላም ያድርግልን ዘንድ፣ እንዲሁም ዕቅዱ ግቡን ይመታ ዘንድ እየተመኘሁ በዚሁ ላብቃ። ሠላም!
የጽሑፉን አዘጋጅ ቶፊቅ ተማምን በ tofick1970@gmail.com አድራሻቸው ያገኙዋቸዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014