መነሻ ገጽዜናየእለት ዜናከሦስት ዓመት በላይ የታሰሩት ኢሳያስ ዳኘው፣ አብዱልሀፊዝ አህመድ እና ማስረሻ ጥላሁን ከተከሰሱበት...

ከሦስት ዓመት በላይ የታሰሩት ኢሳያስ ዳኘው፣ አብዱልሀፊዝ አህመድ እና ማስረሻ ጥላሁን ከተከሰሱበት የሙስና ክስ ነፃ ተባሉ

አርብ መጋቢት 23 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ከሦስት ዓመት በላይ የታሰሩት ኢሳያስ ዳኘው፣ አብዱልሀፊዝ አህመድ እና ማስረሻ ጥላሁን ከተከሰሱበት የሙስና ክስ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነፃ ተባሉ፡፡

ፍርድቤቱ የቀድሞ የኢትዮ ቴሎኮም የቀድሞ አፕሊኬሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩት የሜ/ጀ ክንፈ ወንድም ኢሳያስ ዳኘው፣ የኔትወርክ ኢንፍራስትራክቸር ፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩት አብዱልሀፊዝ አህመድ እና የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ፕሮጀክት ዳይሬክተር የነበሩት ማስረሻ ጥላሁን ከተከሰሱበት የሙስና ክስ በነጻ እንዲሰናበቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ተከሻሾቹ በሱማሌ ክልል ከ1999 እስከ 2003ባሉት ጊዜያት በተከናወነ የ9 የቴሌኮም የሃይል ማስፋፊያ ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ በተከሰሱበት ሙስና ክስ በተገቢው መንገድ ተከላክለዋል ሲል ው ፍርድ ቤቱ በነፃ ያሰናበታቸው፡፡

ተከሳሾቹ ላይ ክስ ከቀረበ በኋላ ዓቃቢህግ ማስረጃ ማሰማቱን ተከትሎ፤ እንዲከላከሉ ፍርድቤቱ ብይን መስጠቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ተከሳሾቹም መከላከያ ምስክር አቅርበው አሰምተው ነበር፡፡

በዚህም መከላከያ ምስክር አሰማም፤ በፕሮጀክቱ ማስፋፊያ ሥራ በወቅቱ በሱማሌ ክልል በአልሸባብና በሌሎች የሽብር ቡድኖች የጸጥታ ችግር መኖሩን ተከትሎ፤ የግል ኮንትራክተሮች መሳተፍ ባለመቻላቸው በመከላከያ ኢንዱስትሪ በኩል ሥራው እንዲሰራ መደረጉን እንዲሁም በቴሌኮም ግብአት አቅርቦት ችግር ተቋራጩ ላዘገየው ፕሮጀክት ጉዳት ቅጣት አለመጣሉን ጠቅሰው፤ የቴሌኮም ሲቪክ ሥራዎች አስተባባሪ ተስፋዬ ታዬ እና የጂጂጋ ፕሮጀክት አስተባባሪ የነበሩት አለምሸት ለማ በመከላከያ ምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተው ነበር፡፡

በተለይም በአካባቢው የሰላም እጦት መኖሩን እና በየቦታው በሥራ ላይ በነበሩ ዜጎች ግድያዎች መፈጸሙን እንዲሁም በክልሉ በነዳጅ ፍለጋ ላይ የነበሩ ቻይናውያንና ኢትዮጵያውያን በጸረ ሰላም ኃይሎች መገደላቸው እንደ አንድ ማሳያ ጠቅሰው፤ የቀድሞ የጠቅላይ ኢታማዡር ሹም ጀነራል ሳሞራ የኑስና የቀድሞ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሃመድ ኡመር መከላከያ ምስክርነት መሰማቱም ይታወሳል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በዓቃቢ ህግ የቀረቡ የሰውና ሰነድ ማስረጃ መርምሮ እንዲከላከሉ የሰጠውን ብይን ተከትሎ፤ ተከሳሾቹ ያቀረቡትን መከላከያ ምስክር መርምሮ በዛሬው ቀጠሮ ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው ማስረጃ አልቀረበም ክሱንም በተገቢው ተከላክለዋል ሲል ሦስቱንም ግለሰቦች ነጻ ብሏል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ በሌላ ክስ የማይፈለጉ ከሆነ ከዛሬ ጀምሮ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ነገር ግን ኢሳያስ ዳኜ ያልተጠናቀቀ ሌላ የሙስና የክስ መዝገብ ያለባቸው ሲሆን፤ ቀሪ በዚህ መዝገብ ጥፋተኛ ተብለው በሌሉበት ጉዳያቸው እየታዩ ያሉ 5 ተከሳሾች የቅጣት አስተያየት ዓቃቢህግ እንዲያቀርብ ቀጠሮ መሰጠቱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች፡፡

ተከሳሾቹ በ1996 የወጣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ) እና 407 (1ሀ እና ለ) እና (3) ላይ ተደነገገውን የኢትዮ ቴሌኮም የግዥ ፖሊሲና መመርያ በመተላለፍ፤ የዕቃና አገልግሎት ግዥ ሲፈጸም በውድድር መሆን ሲገባው፣ ያለ ውድድር በቀጥታ ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ብቻ እንዲሆን በማድረግ፣ ለራሳቸው ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘትና ለኮርፖሬሽኑ ለማስገኘት በማሰብ ድርጊቱን እንደፈጸሙ አድርገዋል ብሎ ዐቃቢህግ ክስ መስርቶ ነበር፡፡

በዚህ ቀርቦባቸው በነበረው ክስ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩትን አማረ አምሳሉ፣ የኤንጂፒኦ ሥራ አስፈጻሚ ወልደ ጊዮርጊስ ወልዱ፣ የኢንተርፕራይዝ ማኔጅመንት ዳይሬክተር የነበሩት ሰይፈ ኃይለ ሥላሴ፤ በተጨማሪም የኦፕሬሽን ሰፖርት ኦፊሰር የነበሩት ፀጋዬ መኮንን፣ የኤንጂፒኦ ምክትል ፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩት አይተንፍሱ ወርቁ፣ የሲቪል ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ጌታሁን ያሲን እና የኤንጂፒኦ ሞባይል ፕሮግራም ኃላፊ የነበሩት ሳሙኤል ፈጠነም በክሱ ተካተው ነበር፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች