መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበአማራ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ዕጥረት አጋጥሟል ተባለ

በአማራ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ዕጥረት አጋጥሟል ተባለ

በደብረ ብርሃን 20 ሺሕ ተፈናቃዮች ለሦስት ወር ድጋፍ አላገኙም

በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢ በነበረው ጦርነት ለተፈናቀሉ እና ከሌሎች ክልሎች ተፈናቀለው በክልሉ ለሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማዳረስ ዕጥረት እንዳጋጠመው የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢያሱ መስፍን፣ በደብረ ብርሃን፣ በሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች፣ በባህር ዳር ከተማ፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የዕርዳታ አቅርቦት ችግር ማጋጠሙን አምነው፣ የክልሉ መንግሥት የሰብዓዊ ድጋፉን በየወሩ እያቀረበ ባለመሆኑ ዜጎች ችግር ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አክለውም፣ ለተፈናቃይ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ በወቅቱ ማድረስ ያልተቻለው የፌዴራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በትራንስፖርት ችግር የዕርዳታ እህል በወቅቱ መላክ ባለመቻሉ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ከፌዴራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝ እና ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ዕርዳታዎችን ወደ ክልሉ በማስገባት ለተፈናቃዮች የማድረስ ሥራ እንደሚሠራ ኃላፊው አክለው ገልጸዋል።

በአማራ ክልል የሕወሓት ቡድን ወሯቸው በነበሩና አሁን ላይ ነጻ በወጡ አካባቢዎች ከ9.3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው የሚገኙ 2.3 ሚሊዮን፤ በጠቅላላው ከ11 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ኃላፊው ጠቁመዋል።

አዲስ ማለዳ ስለ ጉዳዩ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ ለፌዴራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ያደረገችው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ አልተሳካም።

ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ ዞን እንዲሁም ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በታጣቂ ኃይሎች በሚፈጸም ግድያና ጥቃት የተፈናቀሉ፣ እንዲሁም በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ከሰሜን ወሎ ዞን እና ከሌሎች ቦታዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረብርሃን ከተማ በአምስት የመጠለያ ጣቢያ ተጠልለው የሚገኙ ከ20 ሺሕ በላይ ዜጎች የሦስት ወር የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳልቀረበላቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እነዚህ ተፈናቃይ ዜጎች በተያዘው ዓመት በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ሆነው ከመስከረም ወር ጀምሮ በየወሩ ለአንድ ሰው 15 ኪሎ ስንዴ ድጋፍ ይደረግላቸው የነበረ ቢሆንም፣ የአማራ ክልል መንግሥት፣ ከኢትዮጵያና ከዓለም ዐቀፍ የተራድዖ ድርጅቶች ጋር ተባብሮ የሚያደርገውን የሰብዓዊ ድጋፍ በማቋረጡ፣ የታኅሣሥ፣ የካቲት እና መጋቢት ወራት ዕርዳታ ለተፈናቃዮቹ አልተደረገም ተብሏል።

በመጠለያ ጣቢያው ከሦስት ሺሕ ያላነሱ ሕፃናት፣ ነፍሰ-ጡር ሴቶችና ወላድ እናቶች ቢኖሩም፣ በጣቢያው ላሉ የጤና ባለሙያዎች የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ እየቀረበ ባለመሆኑ የሕክምና አገልግሎት እያገኙ አለመሆኑን ነው ተፈናቃዮች ለአዲስ ማለዳ ያስረዱት።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም፣ በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተደጋጋሚ በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ የሚገኙ ከ300 ሺሕ ያላነሱ ተፈናቃይ ዜጎች በምግብ እና መጠለያ ችግር እየተሰቃዩ መሆናቸው ተገልጿል።


ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች