የሕዝቡን ችግር ተረዱለት!

0
818

የኢትዮጵያ ሕዝብ በኑሮ ውድነት እያደር ይበልጥ እየተፈተነ መምጣቱ ለማንም ግልፅ ነው። “ነፃ ገበያ” በሚል እንደ እኛ አገር ስግብግብ ነጋዴዎች በበዙበት፣ እንዲሁም ብቃትና አቅም ባጣ መንግሥት ሥር ሊሆን የማይችል ፍልስፍና እየተከተሉ ሕዝቡን በችግር እንዲማቅቅ ማድረግ ሊቆም ይገባል።

ሕዝብ መንግሥት አለልኝ ብሎ የኑሮ ውድነቱ እያደር ይሻሻላል ብሎ ቢጠብቅም፣ ተስፋው በራሱ በመንግሥት እየተሟጠጠበት የሚያደርገው ጠፍቶት ወደ ምሬት እያመራ እንደሆነ ያየውን ማስተዋል የሚችል ማንም ሰው የሚረዳው ነው። የሕዝብ ብሶት ገንፍሎ ሊመለስ የማይችልበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት መንግሥት ለተቸገረው ሲል ባይሆንም፣ ለራሱ ሲል በአፋጣኝ ነገሮችን ለማስተካከል መሥራት እንደሚኖርበት አዲስ ማለዳ ታምናለች።

የአጭር ጊዜ መፍትሔ በማምጣት የማያዛልቅና ችግሩን በዘላቂነት የማያስወግድ ሐሳብ ላይ ባለሥልጣናቱ ከመዘባረቅ፣ የኅብረተሰቡን የልብ ትርታ ተረድቶ አስቸኳይ የመፍትሔ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። አፈ ጮሌ ሊያስብል የሚችል፣ አልያም አንደበተ ርቱዕ አስብሎ ያስደንቀናል በሚሉት ንግግር ብቻ የሕዝብን ትኩሳት ማብረድ ይቻላል ብሎ ማመን፣ እሳት ላይ ራስን እንደመጨመር መሆኑን ተረድቶ መንግሥት አካሄዱን ማስተካከል የሚያስፈልግበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ይገኛል።

የምበላው አጣሁ ብሎ የተጨነቀን ሕዝብ አይቶት የማያውቀውን ቅጠል እያሳዩ ጨው ጨምሮ ይብላው ብሎ ምክር መስጠት፣ በቁስሉ ላይ እንጨት መስደድ ብቻ ሳይሆን ቁስሉ አመርቅዞ እንዳይድን፣ እንጨቱም ተመልሶ እንዳይወጣ ከመከላከል አይተናነስም። እንጀራ በወጥ ሁሌ መበላት የለበትም እየተባለ ሕዝቡ ዳቦ በሙዝ ብላ እየተባለ፣ የሚበላውን እንደ ሐኪም መንግሥት ሊያዝለት አይገባም።

ሕዝብ የሚፈልገውንና የሚጥመውን እራሱ እንደሚያውቅ መንግሥት በመጀመሪያ ደረጃ ሊረዳው ያስፈልጋል። የ”እኔ አውቅላችኋለሁ” ፖለቲካ ለበለጸጉት አገራትም ምንም እንዳልፈየደ አውቆ፣ መበልጸግን ርዕዩ አድርጎ ሕዝቡ እየተራበበት ያለው መንግሥት የኅብረተሰቡን ስሜትና ፍላጎት ተረድቶ ያንን ለማሟላት መንቀሳቀስ እንዳለበት አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።

ሥራ አጥነት፣ የምርት ዕጥረትና የኑሮ ውድነት እርስ በርስ የተሳሰሩ ችግሮች በመሆናቸው አንዱን ብቻ በማስተካከል ሌላውን ትቶ መፍትሔ ሊገኝ አይቻልም። ቅድሚያ የሚሰጠው የዜጎች በሠላም የመኖር መብት ቢሆንም፣ ማንም ሰው ሳይበላ እየተራበ በሠላም ሊኖር እንደማይችል ግምት ውስጥ መክተት ያስፈልጋል። ሕዝቡ ሠርቶ የሚበላበት መንገድን ከማመቻቸት በፊት በልፋቱ ባገኘው ገቢው ገዝቶ የሚበላው የምግብ አቅርቦት በበቂ ኹኔታ መዘጋጀት ይኖርበታል።

የሠው ልጅ ለመኖር የመጀመሪያ መሠረታዊ ፍላጎቱ እንደመሆኑ ለመኖር ግዴታ አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ኹኔታዎች ከኹሉም በፊት ትኩረት ተሠጥቶ ሊታሰብባቸው ይገባል። “ኹሉ ነገር ወደጦር ግንባር” እየተባለ ሕዝቧን በጥይት አረር ለዘመናት ያጣች አገር፣ ኹሉንም ጉልበት ሠርቶ ለመኖር ማዝመት እንዴት ያቅታታል!

ዶላር ለማግኘት እየተባለ፣ ለዓመታት ይታረሱ የነበሩ ማሳዎች ለባለ ሀብት ሲሰጡ እየተመለከትን በዝምታ ቆይተናል። እነዚያ የሚሊዮኖችን ጉሮሮ ሲሞሉ የነበሩ መሬቶች የማይበሉ አበባን የመሳሰሉ ምርቶችን ማስተናገድ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ሕዝቡ ለምግብነት ያውላቸው የነበሩ ከብቶችም ያለከልካይ በሕጋዊና በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ እየሔዱ የሌላውን ሆድ ቦርጭ ሲያሳክሉ፣ የኢትዮጵያውያን ግን ከጀርባቸው ተጣብቆ እንዲቀር እየተደረገ ነው።

ኢትዮጵያውያን ሕፃናት በተመጣጠነ ምግብ ዕጦት እየቀነጨሩ፣ ብዙዎችም በቂ ምግብ እያጡ ሲራቡ እየተመለከትን ምግብን አምርተው ወደ ውጭ የሚልኩ ባለሀብቶች ውፍረታቸውን ለመቀነስ ወጪ ሲወጣ መመልከት ተለምዷል። ለሕልውናው ሲል መንግሥት ቅድሚያ ዶላር ለማግኘት የማይልከው ነገር ባይኖርም፣ ላኪዎቹ የነጋዴ ማኅበረሰቦች ራሳቸውን እንደመንግሥት ተክተው በማሰብ ሕዝቡን ሊታደጉት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።

የሚያስብለት ያጣ ሕዝብ ለየራሱ በተናጥል ማሰብ የጀመረ ዕለት የችግሩ የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ መሣሪያ የጨበጠው ወገን ስለማይሆን፣ ሌሎቻችን ለራሳችንና ለወገናችን ስንል ከስግብግብነትም ሆነ ከማንአለብኝነት ተግባር ልንቆጠብ ይገባናል። የመግዛት አቅም የሌለውን ሕዝብ ይዘን ሸቀጥ እያመጣን ግዛን ብንል ውጤቱ ዜሮ ድምር መሆኑን ተረድተን የሀብት ምንጭም ሆነ መሠረት ለሆነው ገበሬውና ለፍቶ አዳሪው ማሰብ እንደሚገባን አዲስ ማለዳ ታስታውሳለች።

መንግሥትና ነጋዴው የድመትና አይጥ ግንኙነታቸውን ትተው ኹለቱም ተባብረው ለሕዝብ መሥራት እንዳለባቸው ሊያውቁት ይገባል። ያለው በሀብቱ የሌለው በጉልበቱ፣ መንግሥትም በሥርዓቱ ተጠቅሞ በመተጋገዝ ለውጥ ማምጣት ይቻላል እንጂ፣ ኹል ጊዜ በመወቃቀስና በመፈራረጅ የሚመጣ በጎ ነገር እንደማይኖር ኹሉም ሊረዳው ያስፈልጋል።

መንግሥት ሥልጣኑን ተጠቅሞ ካፒታል ላለው የኅብረተሰብ ክፍል ከለላም ሆነ ዕድልን ሊያመቻች፣ ከሕገ ወጥ ነጋዴም ሆነ ሥርዓት አልበኞች ሊጠብቅ፣ ነጋዴው ዕውቀቱንም ሆነ አቅሙን ተጠቅሞ ያለምንም ሰበብ ለኅብረተሰቡ እየጠቀመ ራሱን መጥቀም እንደሚቻለው ሊገነዘብ ግድ ይለዋል።

መንግሥት የፍጆታ ዕቃ አስመጪው የነጋዴው ማኅበረሰብ እንዴት እንደሚያስብ ሊረዳ ይገባዋል። ለጽድቅ እንደማይለፋ አውቆ ትርፍ ለማግኘት ሲል ምን ምን መንገዶችን እንደሚጠቀም ሊያጤነው ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል፣ ከመርካቶ ነጋዴ ምን ያህሉ በሕጋዊ መንገድ ምንም ሳያጭበረብር እንደሚሠራ መገመት ለማንም ግልፅ ነው። ዶላር ከመንግሥት በበቂ ስለማያገኝ ከጥቁር ገበያ የሚያገኘውን ደብቆ ይዞ እንደሚወጣ ይታወቃል።

ነጋዴው ‹ፕሮፎርማ› ዝቅ አድርጎ የሚያስገባበትን ዓላማ የሚያውቅ አካል፣ የጥቁር ገበያንም ሆነ የነጋዴው መንገድን በጊዜያዊነትም ቢሆን ምን ያህል እንደሚጠቅም ይረዳዋል። ይህን ለዓመታት የዘለቀ አካሔድ ግምት ውስጥ ሳያስገባ ጥቁር ገበያ ላይ ከልብ መዝመት፣ በብርበራ ወቅትም ያለልክ መበርበር ምን እንደሚያስከትል መንግሥት የተረዳው ነገር አልነበረም። አንድ ችግርን ለመቅረፍ ተብሎ በተናጥል ታስቦ የሚወሰን ዕርምጃ ሌላ የባሰ መዘዝ እንደሚያስከትል ከእንዲህ ዓይነቱ የንግድ ሥርዓቱን ካዛቡ ሒደቶች በመመልክት ማስተካከል እንደሚያስፈልግ አዲስ ማለዳ አጽንዖት ሠጥታ ትናገራለች።

ኹሉ ነገር በአደባባይ የሚነገርበት ጊዜ እንዳልሆነ ብንረዳም፣ ሠሞኑን ከዘይት መወደድ ጋር የተከሰተውን አሻጥር ለማስወገድ በሚል ዕውቀቱ በሌላቸውና አካሄዱን ባልተረዱ የደንብ አስከባሪዎችም ሆኑ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተወሰዱ የአሰሳና የመውረስ ሒደቶች የታሰበውን ውጤት በማስገኘት ፈንታ በተቃራኒው ጭራሹኑ የሸቀጡን መጥፋት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ መረዳት ያስፈልጋል።

የድሮ ነጋዴ የሚያተርፍበት መንገድ ቢጠብበትና ቁጥጥር ቢበዛበት ሳይነግድ ቁጭ ብሎ መኖርና ሕይወቱን በሌላ አማራጭ መግፋት ስለማይቻለው እንደተፈለገ ይደረግ ነበር። የዘመኑ ነጋዴ ግን አቅምና ካፒታሉ ከፍ ያለ ስለሆነ፣ እንዲህ ሥራ ተብሎ ቢገደድ እሺ ብሎ ከመሥራት ይልቅ ዝም ብሎ ለመጠበቅ አቅሙ አለው። ሌላ ዘርፍ መቀየርም ሆነ ታግሶ ነገሮች ወደነበሩበት እስኪመለሱ መጠበቅ ስለሚቻለው ማስገደዱ ውጤታማ መሆኑ አጠያያቂ ነው።

ይህ ሁሉ የንግድ ሥርዓት መዛባት የተከሠተው የንግዱ ማኅበረሰብ እየተፎካከረ ዋጋ እንዲቀንስ ሲያደርገው የነበረው የመለያየት አሠራር በቀደመው ሥርዓት እንዲቀር በመደረጉ ነው። የማይስማሙ የነበሩ አስመጪዎችንም ሆነ አከፋፋዮችን፣ እንዲሁም ቸርቻሪዎችን በማገናኘት፣ ተቀራርበው የውጭ አገር ነጋዴዎችን ተጋግዘው እንዲቋቋሙና በዓለም መድረክ ጫና ማሳደር እንዲችሉ የተመቻቸላቸው የመግባቢያ መድረክ ፍሬው ጎምዛዛ ሆኖ ነበር የተቆረጠው።

መንግሥት ባስቀየማቸው ወቅት ያቀራረባቸው አካል ላይ አንድ በመሆን ሕዝብ እንዲነሳበት በሚል ኅብረተሰቡን በማማረር ለውጥ ለማምጣት የበኩላቸውን መንገድ ሞክረው ነበር። በዚህ መሀል ከፍተኛ ትርፍ የለመዱ ቁጥጥር የጠሉ አካላት በዛው ተግባራቸው ቀጥለውበት፣ አሁን የተልፈሰፈሰ የመንግሥት አካል ሲያጋጥማቸው ጭራሹኑ ለሕዝብ ማሰባቸውን ትተው ለራስ ብቻ ማለታቸው እየታየ ይገኛል።

“በቅሎ ገመዷን በጠሰች በራሷ አሳጠረች” እንደሚባለው፣ ሕዝብ ላይ አሲረው እንዲማረር የሚያደርጉም ሆኑ፣ አቅሙ እያላቸው ምንም የማያከናውኑ በዚህ ድርጊታቸው ሊዘልቁ እንደማይችሉ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።
እንደሱማሌዎች ተረት በማጭበርበር የተገኘ ሀብትንም ሆነ ሥልጣንን ጎርፉ ይዞት የሚሔድበት የክረምት ወቅት መምጣቱ ስለማይቀር፣ ኑሮ እንዲወደድ እጃችን ያለበት ኹሉ ከወዲሁ ልናስብበት ይገባል።


ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here