ኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆነውን የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶች ፍላጎቷን በአገር ውስጥ አምራቾች እንደምትሸፍን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
“ንግድዎን በመቅረዝ ላይ ያኑሩ” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የፊንቴክስ 3ኛ ዙር የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶች፣ አገልግሎቶች እና ቴክኖሎጂዎች ዓለም ዐቀፍ አውደ ርዕይና ኮንፈረንስ ባሳለፍነው ሐሙስ በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል በይፋ ተከፍቷል፡፡
በአውደ ርዕይና ኮንፍረንሱ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፣ በአሁኑ ወቅት 70 በመቶ የሚሆነው የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶች በአገር ውስጥ አምራቾች የሚመረቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቢሆንም ግን፣ አሁንም አገሪቷ 30 በመቶ የሚሆነውን ምርት እና ጥሬ ዕቃዎች ከተለያዩ አገራት እንደምታስገባና በዚህም በዓመት ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆነ ወጪን እንደምታወጣ የገለፁት ሚኒስትሩ፣ ባለፈው አምስት ዓመትም 78 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶችን ከውጪ አገራት ማስገባቷን ተናግረዋል።
እነዚህን ከውጭ የሚገቡ የፈርኒቸር ምርቶች ለማስቀረትና በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት መንግሥት የፖሊሲ ጣልቃ ገብነት ለማድረግ ዕቅድ እንዳለውም ሚኒስትሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶች ዘርፍ በአገራችን ሠፊ የማደግ ዕድል ያለው ነው ያሉት መላኩ፣ ነገር ግን የሰው ኃይል ሥልጠና ማነስ፣ የግብዓት አቅርቦት ችግሮች፣ የኬሚካል እና የመለዋወጫ ዕጥረት፣ የገበያ ትስስር ችግር እና የፖሊሲ ማሻሻያዎች አለመደረግ በዘርፉ ላይ እንደተግዳሮት የሚጠቀሱ ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
እነዚህንም ተግዳሮቶች ለመፍታት መንግሥት ከሚያደርገው የፖሊሲ ጣልቃ ገብነት በተጨማሪ፣ የአገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታት ኤክስፖርትን መቀነስ እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በማሳደግ ለዘርፉ ጉልህ ሚና እንዲጫወት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
‹ፕራና ኤቨንትስ› እና ‹አፍሪካን ትሬድ ፓርትነርስ› በጋራ በመሆን ባዘጋጁትና በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል በተባለው የፊንቴክስ 3ኛ ዙር የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶች ዓለም ዐቀፍ አውደ ርዕይና ኮንፈረንስ ላይ ከ40 በላይ ኩባንያዎች፣ ከአገር ውስጥ፣ ከኬኒያ፣ ከፖላንድ፣ ከጣሊያን፣ ከቱርክ፣ ከጀርመን እና ከቻይና የተሳተፉበት ሲሆን፣ ከ400 በላይ ገዥዎች፣ ከ4 ሺሕ በላይ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትና ጎብኚዎች እንደተስተናገዱበት አዘጋጆቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014


