ምዕራፍ አንድ ሳይገባን!

0
1385

ምዕራፍ አንድ የሁሉ መሠረትና ትኩረት ያልተሰጠው ጉዳይ ነው የሚሉት በድሉ አበበ፣ በሁሉ ነገር መግቢያ የሆነውን የመጀመሪያ ክፍል የሚያስተውል ሰው ምን ያህል ትርፍ እንደሚያስገኝ ያብራራሉ። ልክ የሀይማኖት መጻሕፍትንና አስተምህሮን የመጀመሪያ ክፍል እንደማወቅና እንደመረዳት ነው። ይህም ፍቅር ነው። ምዕራፍ አንድ ሲገባን ፍቅርና ሰላምን ማስቀደም ይሆንልናል ሲሉ ተከታዩን ሐሳብ አካፍለዋል።

ሕይወት ፈርጀ ብዙ መልክ አላት፤ ገጠመኟም ስፍር ቁጥር የለውም። በእድሜና በዕውቀት፤ በዚህ ዘመንና ሁኔታ እዚህ ለመደረስ የሕይወት ምዕራፎችን ወድቀናል፤ ብዙዎቹንም ቀና ብለን አልፈናቸዋል። በዚህ የሕይወት ጎዳና መካከል ፈተናና ድል አልፈዋል። የግራውን እየጣልን የቀኙን አንስተናል። የሕይወት ምዕራፍ ክፍልፋዮች አሉት። እኛም የሚገርሙም፣ የሚያስደስቱም፣ የሚያሳዝኑም ብዙ ዓይነት ገጠመኞች አሉን። በበኩሌ ለምሳሌ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከብዙ ዓይነት ሰዎች ጋራ ውያለሁ። ከብዙዎች ጋራ አድጌያለሁ፤ ተምሬያለሁ ደግሞም ጥቂትም አገልግያለሁ፤ በዓለማዊውም በመንፈሳዊውም። ከአንዳንዶቹማ ጋር ከመከራከር በላይ ተፋልጫለሁ ብል ይቀላል። ከሚስቁት ጋራ የሳቅሁትን ያህል ከሚያነቡትም ጋራ አንብቻለሁ።

አገሬን ለናቁ ቁና የሚያስተነፍስ የሕይወት ዘመን የውይይትና ክርክር ልምድና ንባቤን መንዝሬያለሁ። የማይደፈሩትን ደፍሬያለሁ። ማንነትን፣ ክብርን፣ ሉዓላዊንትን ላለማስደፈር በመሰለኝ ልክ በሚያስገርሙ ዐይኖች ሥር በመዋል ተከራክሬያለሁ። ከተከራካሪዎቼ የተቀበልኩትን ያህል፤ እኔም የአቅሜን ሰጥቻለሁ። ተማምረናል፤ ተከራክረናል፤ ተጣልተናል ታርቀናል። እንደ ሰይጣን ቆጥረው የጠሉኝ እንዳሉ ሁሉ፤ ከፍ ያደረጉኝም አልጠፉም። በመልካምነት ሸልመው፤ በሕይወት የጋረዱኝም ጥቂት አይደሉም። እኔ በእርግጥ በብዙ መልካም ሰዎች የተከበብኩኝ ነኝ ብል አላፍርም።

ድህነትና አለማወቅ ይዞን እንጂ ኢትዮጵያዊያን በአጠቃላይ ጥሩዎች ነን። እኔ በአራቱም አቅጣጫ ይሄን በዐይኔ በብረቱ ዐይቻለሁ። አብረን ሳናድግ ቅንነትንና ወንድምነትን፤ በብዙ ነገር ብንለያይም ወንድማዊ መስዋዕትነትን አጭጃለሁ። በዚህ ሁሉ መካከል፣ ማሰቢያችንን ያልነፈገ ፈጣሪ ይመስገንና፤ ዘወትር ባሰብኩት ቁጥር የሚገርመኝ ግን ብዙዎቻችን በተለይም ፊደል ቆጥረናል የምንል ሰዎች በሕይወት ምዕራፎች ጉዞ ላይ ምዕራፍ አንድ ያልገባን መሆኑን ነው። ለመሆኑ ምዕራፍ አንድ ምንድን ነው?

ምዕራፍ አንድ?
ለኔ ምዕራፍ አንድ የሁሉ ነገር መሠረት ነው። መግባቢያ ነው። የጋራ ቋንቋ ነው። ምዕራፍ አንድ ጥልቅ ትርጉም ነው። ምዕራፍ አንድ መርኅ ነው። ምዕራፍ አንድ አገር ነው። ምዕራፍ አንድ ሰውነት ነው። ምዕራፍ አንድ ክብር ነው። ምዕራፍ አንድ በስንት ይከፈላል ነው። ምዕራፍ አንድ የሚጥም ፍልስፍና ነው። ምዕራፍ አንድ እውነት ነው። ምዕራፍ አንድ ክብርና መከባበርም ነው። ምዕራፍ አንድ ሕይወት ነው የሚሳሱለት፤ ደስታም ነው የሚኖሩለት፤ እምነትም ነው የሚሰዉለት። ፈጽሞ ልዩነት አልነበረም፤ አይደለምም። ምዕራፍ አንድ የቀጣዮቹ ምዕራፍ ምሰሶ ነው።

ይሄ ሳይገባን ቀጣዩን መረዳት፤ ተረድቶም ማስረዳት ዳገት ነው። ስለፍቅር እየሰበከ መለያየትን ማንገሥ ነው። ለማስታረቅ ሽምግልና ተቀምጦ ጥላቻን ማስፋት ነው። ምዕራፍ አንድ ምስጢርም ነውና፤ የመጨረሻው ምዕራፍ ካለሱ አይገለጥልንም።

በሕይወት ገጠመኝ ውስጥ ምዕራፍ አንድ የገባቸውና ያልገባቸው ኹለት ዓይነት ሰዎች እናገኛለን፤ ከቅርብም ከሩቅም። የገባቸው ራሳቸውንም ቤተሰባቸውንም፤ ማኅበረሰብንም፣ አገርንም ሲረብሹ አይታዩም። ምዕራፍ አንድ የገባቸው የሰላም ደመና ሆነው ለዓለም በረከት ያዘንባሉ። እነሱ መና ሆነው ረሀብን፤ ውሃ ሆነው ጥምን ይቆርጣሉ። ታላቅ ሆነው መከታ፤ አባትና አናት ሆነው መጠጊያ፤ ወንድም ሆነው ጋሻ ይሆናሉ እንጂ የውድቀት ምክንያት ሲሆኑ አናይም። ዝቅ ብለውም ቢሆን ሲያነሱ አንጂ ሲጥሉ አይታዩም። ሲያፈርሱ ሳይሆን ሲገነቡ ይታያሉ። ተስፋን አይገድሉም፤ ይዘራሉ። ዘርተውም ያበቅላሉ። አብቅለው ያሳድጉታል፤ ለወግ ማዕረግም ያበቁታል። የመጨረሻ ምዕራፍ ያደርሱታል ማለት ነው።

የኅብረተሰብ ተግበቦት ባለሞያ በላይ ናቸው፤ እንደ ድልድይ ሆነው በማኅበረሰብ መካከል የተፈጠረን ሰባራ ድልድይ የሚጠግኑ ናቸው። ጥንካሬ ሲኖር የሚያበሩትን ያህል፤ ክፍተት ቢኖር ለማረም ወደ ኋላ አይሉም። በአጠቃላይ ስናይ የሕይወት ጣፋጭ ቅመም ናቸው፤ ረጅም ዘመን እንዲኖሩልን የምንመኛቸው። ምዕራፍ አንድ የገባው የሚጸጸትበትን ሐሳብ አይናገረውም። የሚናገረውንም ይመርጣል። ድርጊቱንም እንዲሁ። ሳይጀምር አይጨርስም። አወቅክ አወቅክ ሲባል፣ እንደ ቄሱ ሚስት መጽሐፍ አያጥብም። ከመካከል ወደ ኋላ፤ ከመጨረሻም ወደ መጀመርያው ምዕራፍ መምጣት ይቸግረዋል።

ለምሳሌ አሁን ባለው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ላይ ክርክር ተነሳ እንበል። በመጀመርያ ስለምንም ነገር ለመወያየት ልባቸው የሌላውን የተለየ ሐሳብ ለመስማት ክፍት፤ አንደበታቸውም ለመናገር የታረመ ነው። እየቆረቆራቸውም፣ እየተሰማቸውና ልባቸው እየተሰበረም ችግር የለባቸውም፤ ይሰሙሃል። አይወስኑም ማለት አይደለም፤ ይሰሙሃል ይታገሱሃል ማለት እንጂ። ልትሰድባቸው ትችላለህ፤ አዎ ማውራት መብትህ ነው ተናገር ሊሉህ ይችላሉ። እንዲያውም ይሄ ሰው የሚሰማው ስላጣ ባልሰማው ሌላ ሰው ላይ ሌላ ቦታ ችግር ከሚፈጥር የአገሬን ሰው እዚሁ እኔው ልቻለው ብለው ትክሻቸውን ያጠነክራሉ። ባይስማማቸውም፤ እውነታቸውም እምነታቸውም ባይሆን እንኳ ከመስማት አይቦዝኑም።

እንዲያ ያሉ ሰዎች፤ እንዲያ ያለ ሰው ከሰማህ በኋላ፤ ከልብ ስለሰማህ ለማስረዳት ሲነሳ ትንፋሽ ሊያጥርህ ይችላል። መስማት ከመናገር በኋላ እንደ ማር ይጣፍጣል። ያልገባው ለማውራት የሚፈጥነውን ያህል፤ ተፈጥሮውም ቢሆን፤ የገባው ጫወታውን ፈርጅ ፈርጅ ያስይዘዋል። ያኔ መከራከር ቀላል፤ መወየያትም ለምክክር ቦታውን ይለቃል። ለልዩነት መቼም አንመካከርም አይደል? ይመስለኛል። የሐሳብ ልዩነት ቢኖር የመለያየት ምክንያት አይሆንም። ማሰብ፣ ማውራት፣ መከራከር፣ በገባው ልክ አቋም መያዝ ትክክል ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ለተሻለው ሐሳብ፣ መረጃ ወይም ማስረጃ፤ ለተሻለና ለትልቁ ዓላማ መንበርከክ ግዴታ ነው።

ትልቁ ዓላማ እኔንም እናንተንም እንደ ሰው፤ እንደ ማኅበረሰብ እንደ ሃገር የሚጠቅም መሆን አለበት። ወይም ያ የተለየውንና የማያኗኑረውን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያመዝን መተው ያስፈልጋል። ጠቃሚ ሐሳቦች እንዲሰራጩ መፈቀድ ያለበትን ያህል የማያኗኑሩቱ ቢገቱ ይሻላል። ሁሌም ለማሸነፍ መዘጋጀት አስፈላጊ አይደለም። ተሸንፎ ማሸነፍ የሚባልም ትልቅ ፍልስፍና አለ። ምዕራፍ አንድ ገብቶታላ!

እዚህ ጋራ ግን በሐሳብ መሸነፍ ማለት ክፉ ነው እያልኩኝ አይደለም፤ በክርክር ከተረቱ ዝቅ ማለት ያሻል ለማለት እንጂ። ላለመሸነፍ ደሞ ስንቅና በጉዳዩ ላይ የጠለቀ እውቀት ያስፈልጋል። ድል የተደረገ ተከራካሪም ሁሉን ይቀበላል ማለት አይደለም። በሐሳቦች ዝርዝር ውስጥ የሚሸነፍባቸው እንዳሉ ሁሉ የሚሸነፍላቸውም አሉ ማለቴ ነው። ምዕራፍ አንድ የገባው ሰው የሰው ውጋት አይሆንም። እረፍት በመሆን ሕመም ያሽራል። ምዕራፍ አንድ የገባው የኅብረት፣ የአንድነት፣ የወል፣ የጋራ ትልቅ ርዕይና ዓላማ አለው። ትንሹን ጉዳይ ብትነግረው ትልቁን ጉዳይ ከውስጥ ፈልቅቆ ያወጣዋል። ከትልቁ ጉዳይ ብዙ ትንንሽ ጠቃሚ ዝርዝር ጉዳዮችን ያገኛል። ከመከራ ደስታ፤ ከስቃይም ጤናን ያዋልዳል። እንዲህ ይልሃል፡-

‹‹አዎ! አገራችን ውስጥ ልዩ ልዩ ችግሮች አሉ። እነዚህ ችግሮች አሜሪካማ፣ ሩሲያም፣ ቻይናም አሉ። የኛዎቹ ችግሮች መጠናቸው፣ ሁኔታቸው፣ አፈጣጠራቸው፣ ጥልቀታቸው፣ መልካቸው፣ አኳኋናቸው የተለየ ሆኖ ነው። እነሱ ችግራቸውን በፈቱበት መንገድ ለመፍታት መነሳትም ሁኔታን አለማንበብ ይሆናል። የራሳችን ዘመናትን የተሻገረ፤ በባህል የዳበረ ከራስ የመነጨ መፍትሄ አይጠፋም።››

በተጨማሪም ምዕራፍ አንድ ያልገባው ትርጉሙ ሳይገባው መተርጉም ይሆንብሃል። አስተማሪ ማስተማር ጀምሮ አዳልጦት ከተማሪው ያንሳል። እንደማሳያ የግል ልምዴን ላውሳ፤ በሥራ አጋጣሚ የዲሲፐሊን ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆኜ ሠርቼ አውቃለሁ። የሚያስገርመኝና የምናደደው ተማሪን አስተማሪ ከሶ ሲመጣ ነው። እዚህ ጋራ የተማሪ ጥፋት ጥልቀት መታየት ቢኖርብትም እኔን የሚገባኝ ግን መምህሩ ‹ከተማሪው በታች› መሆኑ ነው። ይሄ መምህር የትምህርት ክፍል ውስጥ ያለውን ‹ማኔጅ› የማድረግ ኃላፊነት አልችልም ብሎ በስሜትም፣ በእድሜም፣ በእውቀትም ወርዶ ስታይ፤ በተቋሙ አልያም ከውጪ በመጣ የዲሲፐሊን ኮሚቴ አደባባይ ስታቆመው ማኔጅመንትም ማኔጅመንት ግራ የሚገባው ይመስለኛል።
ምዕራፍ አንድን ሳያውቅ የመጨረሻውን ምዕራፍ ሊያስረዳህ ይቃትታል። አይሆንለትም፤ ይንሸራተታል።

ምሁር በአንድ ነገር ዙርያ ዕውቀት አለው የሚባለው፤ ሰው በሙያው እጅግ የጠለቀ ዕውቀት፤ በተጓዳኝም በሌሎች ጉዳዮች ዙርያ ለመንገድ እንኳ የሚሆን ዕውቀት ያስፈልጋል። ለምሳሌ አንድ የሒሳብ ሊቅ የጤናም፣ የታሪክም፣ የፖለቲካም፣ የኢኮኖሚም፣ ..ወዘተ የተለያዩ መሠረታዊ ጉዳዮች ዕውቀት ያስፈልገዋል። እነዚህን ዕውቀቶች ደግሞ በልምድና በሕይወት ዘመን ንባብ ማዳበር የግድ ይሆናል። አስፈላጊም ባይሆን መወሰን ካለመወሰን ስለሚሻል፤ በጤና መኖርንም እንደ ምርጫ በመውሰድ፤ ሁልጊዜም በአንድ ጉዳይ ከመተከዝ፤ ዘመኑም የ‹ጊንጊልቻ› ዘመን ስለሆነ ማበጠር ስለሚያስፈልግ በከረረ የሐሳብ ልዩነት ምክንያት ከምትወዳቸውም ጭምር ልትነጠል ትችላለህ። ያ ልብ ይሰብራል።

እንደማሳያ ባነሳ፣ በሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሐይማኖተኛ ነው። የሐይማኖት ምዕራፍ አንድ መርህ ደግሞ ፍቅር ነው። ፍቅር ደግሞ የሁሉ ነገር ማሰርያ ነው። ፍቅር ከመውደድ ይመነጫል። የሰው ልጅ ማንንም እንዲጠላ አድርጎ ፈጣሪ አልፈጠረውም። መውደድ ባይችል እንኳ ራሱ መጎዳት የማይፈልገውን ያህል ሌላውን ለመጉዳት አያቅድም። ካለቀደ ደግሞ አያደርገውም። ሰው ሰሜታዊ ፍጡር መሆኑን አልዘነጋውም። ‹Human being is also an irrational being› እንዲሉ።

ታዲያ በዚህ ዘመን የምንሰማው እጅግ የሚሰቀጥጥ ጭካኔ በምድራቸን ከየት መጣ? ሐይማኖት ነው ወይስ ሐይማኖተኞቹ ናቸው? ፍቅር’ኮ ጨረር ነው። ኖሮህ የምታወጣው። ሊኖርህ ይገባል ማለት ነው፤ ከመስጠት በፊት። ፈክተህ የምትፈካበት፤ ሰጥተህ የምትደሰትበት፤ ኖረህ የምትወደስለት፤ ሞተህ የምትታወስበት፤ በሕይወትም ከሞትም ባሻገር ደረትህን ነፍተህ የምትኮራበት። ስናፈቅር ‹ከነፍሳችን› ነው እንደምንለው ነው። የሚያፈቅር ብሔር አይለይም፤ የሚያፈቅር እድሜ አይመርጥም፣ ያለክፍያ በፈጣሪ እንደተፈቀረ እንዲሁ ያፈቅራል።

በነገራችን ላይ ሰው መጀመርያ ፈጣሪውን ነው ማፍቀር ያለበት። ከዚያም ራሱን፤ ቤተሰብና ወዳጆቹን አልፎም አገሩን ላቅ ሲልም ዓለምን ማፍቀር ይጠበቅበታል። ያም ሰው ዜጋና ሀይማኖተኛ ይባላል። ያ ሰው የራሱም የዓለምም ሰላምና ዕረፍት ነው። መውደድ በፍቅር፤ ፍቅርም በእምነትና ተስፋ ያብባል። እምነት ያለው ትናንትንም፣ ዛሬንም፣ ነገንም አሻግሮ ያያል። አይፈራም። መከራው ሲበዛ፤ ፈተናው ሰማይ ሲነካ አይበረግግም። ትናንትን እንዳልበጠበጠ ሁሉ ነገንም አያደርገውም። እምነት በራሱ፤ እምነት በጓደኞቹ፤ እምነት በወገኑ፤ እምነት በአገሩ ሲጠቃለልም እምነት በፈጣሪው ላይ ያሳድራል። ዛሬን ቢከፋውም ተስፋ አይቆርጥም። ተስፋ ደግሞ ሌላ ተስፋን ይወልዳል። የእስከዛሬ እምነት ተስፋውን ይወልዳል።

የራሱ ተስፋ ያለው ሰው እንኳንና ደልቶትም ከፍቶትም ሌላ ሰው ቢጫን እንኳ ተስፋ እንዲሞት አይፈቅድም። ‹ተስፋ ባይኖር ሕዝብ መረን ይለቅ ነበር› እንዲል ታላቁ መጽሐፍ። ሙሉ ሰው ሦሰቱም ይኖሩታል። ሦስቱንም በሕይወቱ ይኖራቸዋል። ታድያ መረን የለቀቅነው ተስፋችንን ምን ቢውጠው ነው? ወንድሜ አንተ ለመኖር የምትጓጓለትን ሕይወትኮ ያም ሰው ማጣጣም ይፈልጋል።

አትንገረን እንጂ የሰውን ስጋ ስትበላኮ ያማህበት ምላስ ከትናጋህ ጋራ ተጣብቆ ቀርቷል። ስታሳድድ ዐይንህኮ ተሳዳጁን ተከትሎ ተተክሎ ቀርቷል። ስትገድል መግደያህን አገላብጠህ ባየህበት ቅጽበትኮ ነፍስህ በእጆችህ በኩል አምልጣ ወጥታለች። ይሄ ሰው ታድያ ማክበርም ማፍቀርም ባይኖረው፤ እምነትና ተስፋም ቢከዱት ምዕራፍ አንድ ቢገባውኮ ለራሱ ሰው የሚል ሰው ሆኖ ለእኛም ይተርፈን ነበር። የገባው ፍቅር እስከ መቃብርን ይኖረዋል። ዘላቂ እምነት፤ የዛሬና የነገ ተስፋ፤ የዘላለም ፍቅር፤ ከምዕራፍ አንድ ዕውቀት ጋራ ይስጠን። ምዕራፍ አንድ

ይለምልም! ሰላም!
በድሉ አበበ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ላይ ይገኛሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here