ለነዋሪዎቹ ገሀነም ሆኖ የኖረው ወልቃይት ጠገዴ

0
2287

የኢትዮጵያን የኻምሳ ዓመት ታሪክ የሚያወሱ የጽሑፍ መረጃዎች እንደሚሉት ወታደራዊው መንግሥት ደርግ የአገሪቱን ሥልጣን ተቆጣጠሮ ብዙም ሳይቆይ ታጣቂ ቡድኖች ተፈጥረው ሥርዓቱን ሲታገሉ ቆይተዋል።
በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠሩ የብሔር ፖለቲካ ቡድኖች የኋላ ኋላ የደርግ ሥርዓት ከሥልጣን እንዲወገድ ምክንያት ሆነዋል።

በ1968 ደደቢት በረሃ ላይ የተመሠረተው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይም (ሕወሓት) በሰሜን ኢትዮጵያ ከተመሠረቱ የትጥቀ ትግል ቡድኖች አንዱ ሲሆን፣ ከምሥረታው ጀምሮ እስከ ደርግ መንግሥት የሥልጣን ማብቂያ ድረስ በበረሃ ትግል መቆየቱ ይታወቃል።
የሕወሓት ቡድን ከአመሠራረቱ ጀምሮ በአማራ ሕዝብ ላይ የተዛባ አመለካከት እንደነበረው ይነገራል። ትግል ላይ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ባሉት ከ40 የሚልቁ ዓመታትም በዋናነት ለአማራ ሕዝብ ሞትና ሥቃይ ዋነኛ ተጠያቂ አድርገው የሚያነሱት ወገኖች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።

በአማራ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ በደል እንደፈጸመ የሚነገር ቢሆንም፣ በተለይ በትግራይ ክልል አቅራቢያ የሚገኙ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ዜጎች ላይ የፈጸመው ግፍና ሠቆቃ ደግሞ በየትኛውም ቦታ ካደረሰው ጉዳት የባሰ ሆኖ በብዙዎች ይነሳል።
ከ1972 ጀምሮ በጊዜው በበጌምድር አውራጃ ሥር ይተዳደር የነበረውን አሁን ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ተብሎ የሚታወቀው ዞን፣ ካለው ከፍተኛ ምርታማነት የተነሳ ቦታውን ለመቆጣጠር ሕወሓት እንቅስቃሴ እንደጀመረ ይነገራል። ተሳክቶለትም ከ1975 ጀምሮ ቦታውን የተቆጣጠረ ሲሆን፣ በአካባቢው የነበሩ በርካታ ንጹኃንን ያፍንና ይገድል እንደነበር ነው የሚነገረው።

ምሁራን እንደሚሉት፣ ወልቃይት በኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን በአማራ ሕዝብ ላይ ይደርስ የነበረው በደል ማሳያ ዕምብርት ነበር። ሕወሓት ከ1972 ጀምሮ ወደ ወልቃይት ለመግባቱ ዋነኛው ምክንያት አካባቢው ለም መሬትና ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያለበት መሆኑ ሲሆን፣ በዚህም ጎንደርን ማዳከም አማራን ለማዳከም ዋና ስልት ነው ብሎ በማሰቡ እንደሆነ ይነሳል።

ታሪክ እንደሚያሳየው በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን በበጌምድር አውራጃ ሥር የነበረው የአካባቢው አስተዳደር ወልቃይት፣ ጠገዴና ሑመራ በሚባሉ ሦስት ወረዳዎች የተከፈለ ሲሆን፣ የአውራጃው ሰሜን ጠቅላይ ግዛት ደግሞ ጠለምት ወረዳ ተብሎ ይተዳደር ነበር።
በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት አካባቢው ላይ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን በመጠቀም ሠፋፊ የግብርና ሥራዎች ይከናወኑበት እንደነበርና ከዚያ በፊትም የጎንደር ነገሥታት ከፍተኛውን ግብር የሚሰበስቡት ከዚሁ አካባቢ እንደነበር ነው የሚነገረው።
ወልቃይት በሰሜን የተከዜን ወንዝ ተከትሎ ከኤርትራ ጋር የሚዋሰን በመሆኑም፣ ከጥንት ጀምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች ባህረ ነጋሽን በማለፍ ቀይባህርን ተሻግረው ንግድ ይለዋወጡ እንደነበር ይወሳል።

አካባቢው በምሥራቅ በኩል ከትግራይ ክልል ጋር የሚዋሰን በመሆኑም ከ1971 ማብቂያ ክረምት ወራት ጀምሮ ሕወሓት በቦታው ሲንቀሳቀስ ቆይቶ በ1983 የአገሪቱን ሥልጣን ሲቆጣጠር ይህን እንደመልካም ዕድል በመጠቀም፣ ቡድኑ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲጠፉ ዕሥር እና ግድያን ሲጠቀም መኖሩን ነው መረጃዎች የሚገልጹት።

የተረፉትም ባህላቸውን የሚገልጽ አማርኛ ቋንቋን እንዳይጠቀሙ በይፋ ከመከልከል ጀምሮ፣ በሥርዓተ- ትምህርት ትግርኛ ቋንቋ በማዘጋጀት እንዲማሩ ሲያደርግ ቆይቷል ነው የሚባለው። ለሰርግ፣ ለቅሶና የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎችም ጭምር ነዋሪዎቹ አማርኛ ቋንቋን እንዳይጠቀሙ ከማድረግ አልፎ፣ የአካባቢውን ለም መሬቶች በስልታዊ ሠፈራ ከሱዳንና ከሌሎች ቦታዎች ለሚያመጣቸው የትግሬ ማንነት ያላቸው ወገኖቹ ሲያከፋፍል መኖሩን ታሪክ አዋቂዎች ይመሠክራሉ።

በዚህ ኹሉ ጊዜ ታዋቂ ሰዎችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ ባለሀብቶችንና ጀግኖችን በማሳደድ ሲገድል እና ሲሰወር እስከቅርብ ጊዜ ድረስ መኖሩ የሚነገር ሲሆን፣ እስካሁንም ድረስ ከ30 ዓመት በላይ መኖር መሞታቸው ሳይታወቅ የቆዩ በርካታ ንጹኃን መኖራቸው ነው የሚገለጸው። ይህን አስከፊ ጭቆና ለማስወገድም ማኅበረሰቡ ‹‹ከፋኝ›› የሚባል የትግል ቡድን መሥርቶ ሲታገል መኖሩ ይነገራል።

የጎንደር ዩንቨርስቲም የጥናት ቡድን አቋቁሞ፣ ሥውር ዕሥር ቤቶችና የጅምላ መቃብሮች ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ከተጠቆሙ ቦታዎች ውስጥ አምስቱ ላይ ጥናት ሲያካሒድ ቆይቶ በርካታ ንጹኃን የአካባቢው ሰዎች በጅምላ የተቀበሩባቸው የመቃብር ጉድጓዶችን በቅርቡ ይፋ አድርጓል።

በጥናቱ መሠረትም የሕወሓት ቡድን የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ንጹኃን አማራ ነዋሪዎችን በማንነታቸው ብቻ ከአርባ አመታት በላይ በማፈን ሲገድልና ሲሰውር ኖሯል ተብሏል።
የጅምላ መቃብር የተገኘበት አካባቢ ሰው የማይኖርበት፣ ዙሪያው በከፍተኛ ሰንሰለታማ ተራሮች የተከበበ በመሆኑ ቡድኑ ለማጎሪያነት እንደመረጠው ብሎም በኃይል ይዟቸው ከነበሩት የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት አካባቢዎች አማካኝ ቦታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከኹሉም አካባቢዎች ንጹኃንን እያፈነ ወስዶ ለማጎርና ለመጨፍጨፍ እንዳመቸው መረጃዎች ያሳያሉ።

የጎንደር ዩኒቨርስቲ ያሰባሰበው መረጃ፣ በአሰቃቂ ዕሥር ቤቱ ውስጥ የታሠሩ ንጹኃን በሚደርስባቸው ሰቆቃ ምክንያት ራሳቸውን ያጠፉ እንደነበር እና የቡድኑ ታጣቂዎችም በየቀኑ ታሳሪዎችን እየወሰዱ መግደል አድካሚ ተግባር ሆኖባቸው እንደቆየ የሚያሳይ ነው።
የብዙዎቹ አስከሬን በአካባቢው የሚገኝ ቃሌማ ወንዝ ላይ ይጣል እንደነበርና ድብቅ ዕሥር ቤቱ ውስጥ በበሽታ፣ በርሃብና በድብደባ ተሰቃይተው ለሚሞቱትም ሆነ የሕወሓት ታጣቂዎች ለሚገደሏቸው ዕሥረኞች ቀብር ይቆፍሩ የነበሩት ራሳው ታሳሪዎቹ እንደነበሩም የጥናት ቡድኑ አመላክቷል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹትም፣ በዕሥር ቤቶች ታጉረው የነበሩ ሰዎች በሺሕዎች የሚቆጠሩ እንደመሆናቸው መጠን አሁን የተገኘው ገና ጅማሮ ነው ብለዋል።
የአፅሙ መገኘት ለአካባቢው ማኅበረሰብ አዲስ ነገር እንዳልሆነ የጠቀሱት የአካባቢው ነዋሪ፣ ሰዎች ሲጠፉ ባዶ ስድስት ወይም ገሀነም ወስደዋቸው ነው ሲባል እየሠማን ነው ያደግነው ሲሉ ተናግረዋል።
የተወሰዱትን ሰዎች በሕይወት መኖር አለመኖር ማወቅ ትልቅ ነገር ነው፤ ሆኖም ግን ከ28 ዓመታት በላይ ወላጆቻቸው መኖር አለመኖራቸውን ሳያውቁ የሚኖሩ በርካታ ልጆችና ቤተሰቦች አሉ ነው ያሉት።

ሕወሓት በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ያላደረገው ነገር የለም። አሁን ላይ የጅምላ መቃብሮች መገኘት ምናልባት ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰቡ እንዲረዳው ሊያድርግ ስለሚችል ተግባሩ በጎ ጅማሮ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
እስካሁን ይህን ማድረግ አለመቻሉ ቁጭት የሚፈጥር ቢሆንም፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ወደ ቦታው መጠጋት የሚያስከትለው ሞት በመሆኑ ዕሥር ቤቶቹንና መቃብር ቦታዎቹን ማግኘት ሳይቻል እንደቆየ አመላክተዋል።

ለወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎች ብቻ ተብለው የተዘጋጁ ተመሳሳይ ዕሥር ቤቶችም በትግራይ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ የሚያነሱት የአካባቢው ነዋሪ፣ ደብዛቸው ጠፍተው ከቀሩ ብዙዎች ውስጥ አብዛኞቹ ወደዚያ የተወሠዱ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
ለጎንደር ዩኒቨርስቲ የጥናት ቡድንም አንድ ወረዳ ላይ በመረጃ ሰብሳቢነት በሠራሁበት ወቅት፣ ዳንሻ ከተማ ውስጥ አንድት ግለሰብ ባለቤቷንና የባለቤቷን ወንድሞች ጨምሮ ከ10 በላይ ቤተሰቦቿ ደብዛቸው ጠፍተው እንደቀሩ ለማወቅ ችለናል ያሉት ግለሰቡ፣ ማኅበረሰቡ ያለበት የማይሻር የውስጥ ሕመም ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም የሚል ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

የዩኒቨርስቲው የጥናት ቡድን መሪጌታ አስራደ (ረ/ፕ) ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ይህ በወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አካባቢዎች የተካሔደው ጥናት አንድ ዓመት ከሦስት ወር ገደማ እንደወሰደ ገልጸው፣ ጥናቱ ይህን ያህል ጊዜ ይወስዳል ተብሎ አልታሰበም ነበር ይላሉ። ይሁን እንጂ በማኅበረሰቡ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ሠፊና ውስብስብ ከመሆናቸው አንጻር የደረሰውን ግፍ ሙሉ ገጽታ ለማግኘት ረዥም ጊዜ ወስዷል ብለዋል።

ከተለያዩ የሙያ መስኮች የተወጣጡ ባለሙያዎች የተካተቱበት የጥናት ቡድኑ፣ የመስክ ምልክታ፣ የሰነድ ማስረጃ፣ ቃለ መጠይቅ፣ የቡድን ውይይትና ሌሎች የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን በመጠቀም በርካታ ለማመን የሚያስቸግሩና ልብ የሚነኩ ነገሮችን በጥናቱ አግኝቷል ነው ያሉት።

የሕወሓት ቡድን ከደደቢት በረሃ ተነስቶ ተከዜን አቋርጦ፣ ወልቃይት ጠገዴ ከገባ በኋላም ያለምንም ሕጋዊ አሠራርና የሕዝብ ውይይት፣ እስከ 1984 የጎንደር አካል የነበሩ ማኅበረሰቦችን ከነይዞታቸው ወደ ትግራይ እንዲካለሉ በማድረግ በርካታ ግፎችን ሲፈጽም ቆይቷል ሲሉ ገልጸዋል።

ከተፈጸሙ በርካታ በደሎች ውስጥ ሰብዓዊ የሆኑትን ብንመለከት እንኳን፣ ከ100 ሺሕ የሚልቁ ነዋሪዎችንና ባላባቶችን በግድያ፣ በማፈናቀልና በመሰወር ከአካባቢው እንዲጸዱ እና አካባቢው ትግራይ እንዲመስል አድርጓል ነው ያሉት።
ሕወሓት ሠፈራ አላደረገም፤ የፈፀመው ወረራ ነው የሚሉት የቡድን መሪው፣ ሠፈራ መስፈርት አለው። በእኛ ጥናትም ከትግራይ ወደ ወልቃይት መጥተው ድንግል መሬት ላይ የሠፈሩ ንጹኃን የሉም ብለዋል።

በዚህም፣ ሕወሓት ካድሬዎቹንና ታጣቂዎቹን፣ በሱዳን የነበሩ ወገኖቹን እንዲሁም ከማዕከላዊ ትግራይ ሰዎች በማምጣት፣ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎችን መሬት በመንጠቅ፣ ከብቶቻቸውን በመቀማትና ቤታቸውን በማቃጠል ከ1984 ጀምሮ በሕገ-ወጥ መልኩ አካባቢውን ወሯል ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚያ በኋላም፣ አንድም የጎንደር አማራ በአስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ እንዳይሳተፍ ከማድረግ ጀምሮ ሕዝቡ ባህሉንና ምንነቱን እንዳይገልጽ አፈና ሲደረግበት እንደኖረ ጠቁመዋል።

መቀሌ ላይ አማርኛ ማውራት የተከለከለ አይደለም የሚሉት የቡድን መሪው፣ ወልቃይት ላይ ግን በአማርኛ ማውራትም ሆነ መጻፍ ፈጽሞ የተከለከለ ነበር። ይህ የሚያሳየውም እነዚህ ሰዎች ትግሬ ቢሆኑ ኖሮ እንደ መቀሌና አድዋ ነዋሪ መብታቸው ይከበርላቸው ነበር ነው ያሉት።
አካባቢውን በግድ ትግራይ ለማስመሰል በሚደረጉ ሥራዎች ማኅበረሰቡ በቋንቋው ምንም እንዳይሠራ ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ወልቃይት ላይ እንኳን በአማርኛ መዝፈን በአማርኛ የሚተላለፍ የቴሌቪዥን መርሃግብር መክፈት እንደማይቻልና ለአምስት የወልቃይት ነዋሪ አንድ ሠላይ ተመድቦለት እንደኖረ አውስተዋል።

ሠሞኑን የተገኘው የጅምላ መቃብርም ገና የመጀመሪያ ዙር ሥራ መሆኑን አንስተው፣ ስንት ሰው እንደተቀበረባቸው የሚታወቁ ቦታዎች እንደተገኙ፣ 36 ሰዎች የተቀበሩበት ቦታ ያልተቆፈረ እንዳለም ገልጸዋል። እንዲሁም 12 የሚደርሱ ቦታዎችም በጥቆማ ተለይተው መያዛቸውን አንስተዋል።

ነዋሪዎቹ ከተገደሉ በኋላም ኢሰብዓዊ በሆነ መልኩ መቃብራቸው ላይ እሳት ይነድባቸውና ፍየል ይታረድባቸው ነበር ያሉት የቡድን መሪው፣ አሁንም ምን ያህል ዓመት እንደቆዩ፣ ዛፍ እንደበቀለባቸው፣ በምን መልኩ እንደተቀበሩና ምልክት እንዳይኖረው ተደርጎ መቃብራቸው እንዴት እንደተደለደለ በዝርዝር ይፋ ይደረጋል። ዘግይቶም ቢሆን ይህን የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ የሚሆኑበት መንገድ ይኖራል ነው ያሉት።

አክለውም፣ ይህ ጥናት የዘር ወይም የፖለቲካ ሳይሆን የሰብዓዊነት ጉዳይ ነው፤ በቀጣይ አገር ውስጥና ከአገር ውጭ ያሉ አጥኝዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና ባለሙያዎች ቦታው ድረስ ተገኝተው ማየትና ለኹሉም ማሳወቅ ይገባቸዋል ብለዋል።
የንጹኃን አፅም ሲወጣ፣ ‹‹ልጆቻቸው ጥርሱ የእኔን አባት ይመስላል ሲሉ መስማት ልብ ይሰብራል›› አሁን የወጣው አፅም በክብር ወደ ቤተክርስትያን ሔዶ እንዲያርፍ ቢደረግም፣ ወደፊት ዩኒቨርሲቲው እስከ ዘረ መል ጥናት በማድረግ ቤተሰቦቻቸው እንዲያውቁ ለማድረግ የማመቻቸት ሥራ ሊሠራ እንደሚችል አመላክተዋል።

ሕወሓት ባለፉት 40 ዓመታት ከ60 ሺሕ በላይ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አማራዎችን መጨፍጨፉን የጎንደር ዩኒቨርስቲ ያደረገው ጥናት የእስካሁን አጠቃላይ ውጤት አመላክቷል። በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አካባቢዎች ከ12 በላይ የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸው ነው በጥናቱ የተገለጸው።

ዩኒቨርስቲው በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ አደረኩት ባለው ጥናትና በሰበሰባቸው ሌሎች ማስረጃዎች መነሻነት እንደገለጸውም፣ ‹‹19 በመቶ የሚሆኑ አባወራዎች አድራሻቸው እንዲጠፋ፣ 25 በመቶው ሕዝብ እንዲገደልና 29 በመቶ የሚሆነው ነዋሪ ደግሞ አካባቢውን ለቆ እንዲሰደድ ተደርጓል።››

በዚህም፣ በአጠቃላይ 75 በመቶ የሚሆኑት የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አማራዎች እንዲገደሉ፣ እንዲፈናቀሉና አደራሻቸው እንዲጠፋ መደረጉ ዩኒቨርስቲው በጥናቱ ማረጋገጡን አመላክቷል።

በወልቃይት አድኖ፣ ገሃነም እና ተከዜ ውስጥ የጅምላ መቃብሮች የተገኙ ሲሆን፣ በተጨማሪም ትግራይ ክልል ውስጥ ደደቢትና ሌሎች ሦስት ቦታዎች ላይ፣ እንዲሁም ጠለምት ውስጥ ፍየል ውኃ እና ሰይጣን መጣያ በሚባሉ ቦታዎች የጅምላ መቃብር እንዳሉ የጥናት ቡድኑ ማረጋገጥ እንደቻለ ተሠምቷል።

የጅምላ መቃብሮቹ በተጠናና በምስጢር በተደራጀ መንገድ የወንዝ ተፋስስን መሠረት አድርገው የተቆፈሩና አስከሬኖች በዚያ መንገድ በመቀበራቸው በክረምት አጽሞች በጎርፍ እንዲወሰዱ ይደረግ እንደነበርና ይህም ወደፊት በታሪክ እንዳይገኝና የሟቾቹን ታሪክ ደብዛ ለማጥፋት ሕወሓት ያደረገው እንደሆነ ነው የሚገለጸው።

ሆኖም አሁን ላይ የጅምላ መቃብሮች መገኘት በሕወሓት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍ ያለ እንደሚሆን ይነገራል። በተለይም የቡድኑ ደጋፊ የሆኑ የአገር ውስጥና የውጭ ማኅበረሰቦችን ሳይቀር የሚያስደነግጥ ሊሆን እንደሚችልና ሕወሓትም ይህ በመጋለጡ መደንገጡ እንደማይቀር አስተያየታቸውን የሚሠነዝሩ አሉ።

የጅምላ መቃብሮችን መገኘት አስመልክቶ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ (አብን) ባወጣው መግለጫም፣ ‹‹አሸባሪውና ዘረኛው ትሕነግ የሽምቅ ተዋጊ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ወልቃይትና ጠገዴ አካባቢ ያለውን ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታና ሀብት በመገንዘብ አካባቢውን ለመቆጣጠር ወጣ ገባ ማለት ከጀመረበት 1972 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በተለይም አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረበት 1983 ዓ.ም. ጀምሮ በወልቃይት-ጠገዴ ሰቲት ሑመራ የአማራ ሕዝብ ላይ መጠነ ሠፊ ግድያ፣ ማፈናቀልና አፈና ሲፈጽም ቆይቷል›› ሲል ገልጿል::

ፓርቲው አክሎም፣ ‹‹አሸባሪው ቡድን ከወልቃይት፣ ጠገዴና ሑመራ አካባቢ ተመትቶ መልቀቁን ተከትሎ የሑመራ ኤርፖርት በቁጥጥር ሥር ሲውል በዙሪያው የጅምላ መቃብሮች የተገኙ ሲሆን፣ በዚሁ ቀጠና በተለያየ ጊዜ የተለያየ ቦታ ላይም በርካታ የጀምላ መቃብሮች ተገኝተዋል:: ከሠሞኑ በወልቃይት-ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አካባቢ ለአሥራ ስድስት ወራት ጥናት ሲሠራ የቆየው የጎንደር ዩኒቨርስቲ የጥናት ቡድን የአካባቢው ማኅበረሰብ “ገሃነም” እያለ በሚጠራው የትሕነግ ድብቅ የማሰቃያ፣ መግደያና ማሰሪያ ቦታ እጅግ አስደንጋጭ የሆነ የጅምላ መቃብር አገኝቷል:: ትህነግ በሐሰት ትርክት ከቆመበት ተፈጥሯዊ የጭካኔ ባህሪውና በአካባቢው ሲፈጽማቸው ከኖሩ ዓለም ዐቀፍ ወንጀሎች አኳያ ተጨማሪ ምርመራ ቢደረግ አያሌ የጅምላ መቃብሮች እንደሚገኙ አያጠራጥርም›› ነው ያለው::

‹‹ስለሆነም፣ የፌዴራል መንግሥቱ ይኸን መዋቅራዊ ሆኖ ለሦስት ዐሥርት ዓመታት የዘለቀ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲጣራ እንዲያደርግና፣ ዓለም ዐቀፍ የሆነውን ወንጀል የፈፀሙ የሕወሓት ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮች ላይ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ኹሉን ዐቀፍ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ›› ሲል በጥብቅ ጠይቋል።

‹‹የአማራ ሕዝብ አሁንም ቢሆን በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ (ወለጋና አካባቢው) የጅምላ ፍጅት ሰለባ ሆኖ የቀጠለ ስለሆነ መንግሥት የጅምላ ፍጅቱን እንዲያስቆም እየጠየቅን፣ የወንጀሉ ተባባሪና አቀናባሪ የሆኑ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎችን ጨምሮ ወንጀል ፈፃሚዎችን ተገቢውን ምርመራ በማድረግ ለሕግ እንዲያቀርብም›› ፓርቲው አሳስቧል::

በቀጣይም፣ ብዙ ድብቅ ዕሥር ቤቶች ቢገኙና የጅምላ መቃብሮች ቢቆፈሩ የበርካታ ንጹኃን አጽም እንደሚገኝ ነው የሚነገረው።

የጎንደር ዩኒቨርስቲም በቀጣይ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ምርመራ በማድረግ ዝርዝር ጥናት በቋሚነት እንደሚሠራ (center for genocide study) ወይም የጅምላ ጭፍጨፋ የጥናት ማዕከል በማቋቋም ሊሠራ እንደሚችል ተመላክቷል።
አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ማብራሪያ ለማግኘት ሙከራ ብታደርግም፣ ተቋሙ መግለጫ ሳያወጣ በፊት የተናጠል መረጃ ሊሰጥ እንደማይችል በመግለጹ ለጊዜው የተቋሙን አስተያያት ማካተት አልቻለችም።


ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here