በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ድባጤና ቡለን ወረዳ ባሉ ሥፍራዎች የሚንቀሳቀሱ የኦነግና የጉምዝ ታጣቂዎች የዘረፉትን ንብረት ለመከፋፈል ሥምምነት ላይ ባለመድረሳቸው ከቀደመ ወዳጅነታቸው ወደለየለት ጥላቻ መሸጋገራቸውን በቦታው የሚገኙ ታማኝ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
አንድ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአዲስ ማለዳ ምንጭ እንደተናገሩት፣ ከዚህ በፊት በወዳጅነት አብረው ሲሠሩ የነበሩት የኹለቱ ቡድን ታጣቂዎች በዘረፉት የንብረት ክፍፍል ላይ ስምምነት ባለመድረሳቸው ነው ወደግጭት የገቡት። ታጣቂዎቹ ያልተስማሙት “ከሕብረተሰቡ የዘረፉትን ሃብት የኔ ነው የኔ ነው” በሚል መሆኑን ምንጩ አብራርተዋል።
ይህን ተከትሎም፣ የአካባቢው የጸጥታ ኹኔታ እንደተባባሰና ነዋሪዎች ጥቃት እንደደረሰባቸው ነው የተመላከተው። የአዲስ ማለዳ ምንጭ ስለጉዳዩ ሲናገሩ፣ “ቁጥራቸውን ባላውቅም የሞቱ ብዙ ሰዎች አሉ። ቆስለው በቡለን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የገቡ አሉ፤ ከዚህ ባለፈ ደግሞ ‹ሪፈር› ተጽፎላቸው በፓዌ ሆስፒታል የሚታከሙ አሉ” ነው ያሉት።
የጸጥታ ችግሩ አሁንም እንደቀጠለ ነው ያሉት የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ ችግሩ በስፋት የሚስተዋለው በቡለንና ድባጤ ወረዳ ባሉ ቦታዎች መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተያያዘም፣ ታጣቂዎቹ ጥቃት በሚሠነዝሩባቸው በድባጤ ወረዳ ውስጥ በጫቲ፣ በርበር፣ ዳልቻ እና ዲቦ፤ እንዲሁም ቡለን ወረዳ ውስጥ ሞራ፣ ዳን፣ ጊፍታ በተሰኙ ሥፍራዎች የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እየተፈናቀሉ መሆናቸው ነው የተገለጸው።
ዜጎች የሚፈናቀሉት ከፊልም ሠላም ወዳለባቸው የቡለን ወረዳ አካባቢዎችና በድባጤ ወረዳ ውስጥ በርብር ተብሎ ወደሚጠራው አካባቢ ነው።
የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ፣ የኦነግ ሸኔና የጉምዝ ታጣዎች ከዚህ በፊት በመካከላቸው በነበረ ስምምነት የቆዩ ቢሆንም፣ ከሦስት ሳምንት ወዲህ ግን በመካከላቸው አለመግባባት ተፈጥሯል።
በክልሉ ታጣቂዎች በሚሠነዝሩት ጥቃት ሳቢያ በዜጎች ላይ ችግር መከሰት ከጀመረ ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን አንጻራዊ ሠላም ሠፍኖ እንደቆየ ይነገራል። ከኹለትና ሦስት ሳምንት ወዲህ ግን መረጋጋቱ እየቀነሰ ጥቃቱ እንደ አዲስ ያገረሸ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የተፈናቀሉ ዜጎች መፍትሔ ሳይሠጣቸው ከላይ በተጠቀሱት ቦታዎች የነበሩ ነዋሪዎች በተጨማሪ በመፈናቀል ላይ ናቸው ተብሏል።
ሠሞኑን እየተፈናቀሉ ያሉትን ሳይጨምር በቡለን ወረዳ ብቻ ከዚህ በፊት 67 ሺሕ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጭ ያመላከቱ ሲሆን፣ አክለውም “ምንም ድጋፍ የለም። ከዚህ በፊት ሲመጣ የነበረው የሰብዓዊ ድጋፍ ቁሟል” ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ከደረሳት መረጃ ማወቅ የተቻለው፣ በቡለን ወረዳ የመከላከያ ሠራዊት ቢኖርም የሥጋት ቀጠና በሚባሉ ሥፍራዎች ግን ሠራዊቱ እንደሌለ ነው።
ችግሩ በስፋት የሚስተዋለው ድባጤ ወረዳ ቢሆንም፣ ወረዳው ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት እየሠራ አለመሆኑንም ምንጮች ጠቁመዋል። የአዲስ ማለዳ ምንጭ በመጨረሻም፣ማኅበረሰቡ ቀየውን ለቆ ወደ ሌላ ቦታ ሲፈናቀል ዝም ብሎ ከማየት እዛው እንዲረጋጋ አድርጎ በታጣቂዎቹ ላይ የማያዳግም ዕርምጃ መወሰድ ነበረበት ያሉ ሲሆን፣ የጸጥታ ኃይሉ ግን ቆራጥ ዕርምጃ ከመውስድ ይልቅ የቀዘቀዘና የለሰለሰ ወኔ ነው የሚስተዋልበት ብለዋል። ይህም ለችግሩ መከሠት ዋነኛ ክፍተትም ነው ሲሉ አክለዋል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የድባጤ ወረዳ አስተዳደር ሙሉዓለም ዋውያ የተከሰተውን ችግር ምላሽ እንዲሰጡበት ሲጠየቁ “ስብሰባ ላይ ነኝ። ስብሰባ እንደጨረስኩ ምልክት አደርጋለሁ” የሚል ምላሽ ሠጥተው የነበረ ቢሆንም፣ ከዚያ በኋላ በተደጋጋሚ ሲደወልላቸው ስልክ ለማንሳትም ፈቃደኛ አልሆኑም።
ከዚህ በተጨማሪም የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ መለስ በየነ በበኩላቸው ስለጉዳዩ መረጃ እንዲሠጡ ሲጠየቁ ስብስባ ላይ እንደሆኑ ነው የተናገሩት። ከቆይታ በኋላም ስልክ ማንሳት ባለመቻላቸው ያላቸውን ምላሽ ማካተት አልተቻለም።
ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014


