የገናሌ ዳዋ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ከስምንት ወር በላይ አገልግሎት መስጠት አቁሟል
በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ በዳዋ ወንዝ ላይ የተገነባውና በየካቲት 2012 ተመርቆ ኃይል ማመንጨት የጀመረው የገናሌ ዳዋ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ (Genale Dawa III Hydropower Dam) አገልግሎት መስጠት ካቆመ ከስምንት ወራት በላይ እንደሆነው ተጠቆመ።
ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ በኃላፊነት እሠራለሁ ያሉና ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ግድቡ 254 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፣ ከገናሌ ዳዋ ይርጋለም ድረስ ያለው ከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር የካሳ ክፍያ ሙሉ በሙሉ ተከፍሎ ስላልተጠናቀቀ ኃይል ማመንጨት አቁሟል ነው ያሉት።
ከነሐሴ 2013 ጀምሮ አገልግሎቱ የተቋረጠ ሲሆን፣ የካሳ ክፍያ ካልተፈጸመላቸው አንዱ የሆኑ አርሶ አደር ዛፍ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ላይ በመውደቁ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ኃይል እንደተቋረጠ ተናግረዋል። ኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ እንዲገናኝ የተደረገው ቀደም ብሎ ለአርሶ አደሮቹ ከፍተኛ መጠን ያለው የካሳ ክፍያ እንደሚፈጸም ቃል ተገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ክፍያው ተጠንቶ ሊከፈላቸው ሲል ሰዎቹ ካሳውን አንቀበልም ማለታቸውን ገልጸዋል።
ማስተላለፊያ መስመሮችም ዛፍ ከወደቀባቸው ኃይል ማስተላለፍ ስለሚያቋርጡ በየጊዜው ጥገና ይደረጋል ያሉት ግለሰቡ፣ በዚህ መስመር ላይ ግን ለሰዎች ካሳ ስላልተከፈለ ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት እንደማይቻል ነው ያመላከቱት። ሠራተኞች እዚያ ሔደው አይሠሩም፤ እንዲሔዱም አይገደዱም፤ ቢሔዱም ይገድሏቸውና ሸኔ ገደላቸው ይላሉ በማለት ተናግረዋል።
የግድቡ ሠራተኞች አሁን ላይ ምንም ሥራ እንደማይሠሩና እነሱ ያጠፉት ጥፋት ባለመኖሩም ያለሥራ ደሞዝ እየተከፈላቸው መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ግድቡ ሥራ ካቆመበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ያመነጭ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል በገንዘብ ቢሰላ፣ እንኳን ካሳውን ሌላም ይከፍላል የሚል ሐሳባቸውንም ሠንዝረዋል።
የካሳ ክፍያ ችግሩ ያለው ከክብረ መንግሥት (አዶላ) አንስቶ እስከ ቦሬ ድረስ ባሉ ወደ አራት በሚደርሱ ወረዳዎች እንደሆነ ገልጸው፣ ግድቡ ይህን ያህል ጊዜ ኃይል ማመንጨት ማቆሙ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን፣ ኃይል ማመንጫ ጣቢያው ችግር የለበትም፤ ነገር ግን በኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ አካባቢ በበቀሉ ተክሎች የተነሳ ኃይል ማስተላለፍ የማይቻልበት ኹኔታ ስለተፈጠረና የካሳ ክፍያ ስላልተፈጸመ ጣቢያው ከበጀት ዓመቱ መጀመሪያ አካባቢ ጀምሮ አገልገሎት መስጠት ማቆሙን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ችግሩ የተከሠተው በሲዳማ እና ኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች መሆኑንም ጠቅሰው፣ የካሳ ግምት የሚሠራው በወረዳ ስለሆነ፣ ወረዳዎች ለፍራፍሬና እንደ ባህር ዛፍ ላሉ ተክሎች ግልጽ ግምት ሠርተው እንዲያመጡና ሕጉ በሚፈቅደው ካሳው ተፈጽሞ ሥራው እንዲቀጥል የሚል አቋም ይዘን እየሠራን ነው ብለዋል።
ለዚህም ከኹለቱም ክልሎች ጋር እየተነጋገርን ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ገማች ኮሚቴው ትክክለኛ የካሳ ግምቱን ሲያቀርብልን በሕጉ መሠረት ክፍያ ፈጽመን ተክሎች ከተጸዱ በኋላ ጣቢያው አገልግሎት መስጠቱን ይቀጥላል ነው ያሉት።
የገናሌ ዳዋ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ 451 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደተደረገበትና 110 ሜትር ከፍታና 426 ርዝመት እንዳለው መረጃዎች ያሳያሉ። 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውኃ የመያዝ አቅምም አለው።
ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014



