በደቡብ ኦሞ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ የተፈጠረው ችግር በአፋጣኝ እንዲቆም ኢሰመጉ ጥሪ አቀረበ

0
1236

ዕረቡ ሚያዝያ 5 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ የተፈጠረው ችግር በአፋጣኝ እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል።

ኢሰመጉ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ በሚገኙ በ ጋዘር (የደቡብ አሪ ከተማ) እንዲሁም በሌጠር፣ ሺሸር፣ ሆለታ፣ በርካማማ እና ቲቲ ቀበሌዎች ውስጥ ከመጋቢት 28 ቀን 2014 እስከ ሚያዚያ 01 ቀን 2014 ድረስ ቤቶችን በማቃጠል፣ ንብረት በማውደም እና ዘረፈ በመፈጸም “የአሪ ወጣት ነን” የሚሉ ሸኮን የሚባሉ የተደራጁ ቡድኖች ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን አስታውቋል፡፡

እንዲሁም ጂንካ ከተማ ላይ በሚያዝያ 01 ቀን 2014 እነዚሁ የተደራጁ ቡድኖች በመኖሪያ ቤቶች እና በተለያዩ ንብረቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ያለው ኢሰመጉ፤ በአሁን ሰዓት የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የጸጥታ ሀይል ወደ አካባቢው መግባቱን እና የማረጋጋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ካሰባሰብኳቸው የመረጃ ምንጮች ለመረዳት ችያለሁ ብሏል፡፡

ለዚህ ክስተት መነሻ ምክንያት ተደርጎ የቀረበው የአሪ ወረዳ የዞን አደረጃጀት ጥያቄ ለደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት ያቀረበ ቢሆንም፤ ምክር ቤቱ ጥያቄውን አይቶ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት አላስተላለፈም በሚል እንደሆነ ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት መቻሉን አስታውቋል፡፡

ይህንን ክስተት ተከትሎ ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን፤ በአሁን ሰዓት እነዚህ ተፈናቃዮች በኮልታ ቤተክርስቲያን፣ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ተጠልለው በችግር ላይ እንደሚገኙም ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በዛሬው መግለጫው፤ ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና አገር አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተያያዥ የህግ ግዴታዎች ያጣቀሰ ሲሆን፤ ይሁንና እነዚህን ህጎች መንግስት ሊያስከብር ባለመቻሉ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል ብሏል፡፡

በዚህም መሰረት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ የተፈጠረው ችግር በአፋጣኝ እንዲቆም ኢሰመጉ ጥሪ አቅርቧል።

በዚህም መሰረት:-
• በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን በህይወት የመኖር መብት እና የአካል ደህንነት መብቶችን የጣሱ፣ ቤቶች እና የተለያዩ ንብረቶችን ያወደሙ እና የዘረፉ አካላት ድርጊቱ የሰዎችን በህይወት የመኖር መብት፣ የአካል ደህንነት መብት እና ንብረት የማፍራት መብት ከህግ አግባብ ውጪ የሚገድብ በመሆኑ ይህንን ድርጊት በፈጸሙ አካላት ላይ መንግስት ህጋዊ አርምጃ እንዲወስድ፣

• የፌደራል መንግስት እንዲሁም የደቡብ ክልል መንግስት የዜጎችን በህይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነት፣ ንብረት የማፍራት መብትን እና ያፈሩትን ንብረት በዘፈቀደ ያለማጣት መብትን እንዲያስከብር እና እንዲያከብር፣ ለተፈናቀሉ ሰዎች መንግስት ተገቢውን ጥበቃ እና በቂ ድጋፍ በአፋጣኝ እንዲያቀርብ፣

• በዚህ ክስተት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ላይ ተገቢ የሆነ ህጋዊ እና አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ፣

• ተመሳሳይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊያስከትሉ የሚችሉ ክስተቶች ዳግም እንዳይፈጠሩ የፌደራል እና የክልል መንግስታት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የማሕበረሰብ አንቂዎች፣ ሲቪክ ማህበራት እና የሚመለከታቸው ኹሉ የበኩላቸውን እንዲወጡ ኢሰመጉ ጥሪውን አቅርቧል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here