ትኩረት የተነፈጋቸው ቅርሶቻችን

0
1756

ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ሀብቶች መገኛ እንደሆነች ይታወቃል። ሆኖም እነዚህ ሀብቶቿን ተንከባክባ እና ለቀጣይ ትውልድ እንዲሻገር ከማድረግ አኳያ ብዙ ሥራዎች ይጠበቁባታል። በተለያዩ አካባቢዎች ቅርሶቿ ላይ የተጋረጡትን አደጋዎች በትኩረት መመልከት እንደሚያስፈልግም ብዙዎች ሲያነሱ ይደመጣሉ።

በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት የሚንቀሳቀስበትን ‘ጭስ አልባው’ የሚባለውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማጎልበት አገራት ጥረት ያደርጋሉ። በተለያዩ ዝግጅቶችም ሁሉም እንደየአቅሙ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ ተፈጥሯዊና መሰል ቅርሶች በመንከባከብ ጎብኚዎችን ሊስቡ የሚችሉ ሀብቶቻቸውን በማስተዋወቅ ከዘርፉ ተጠቃሚነታቸውን ለማጉላት ይጥራሉ።

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ካሏት የሚዳሰሱ ቁሳዊና የማይዳሰሱ መንፈሳዊ ሀብቶቿ አኳያ በተለያዩ ዘርፎች ቅርሶቿን አስመዝግባ እያስጎበኘች ትገኛለች። በተፈጥሮም የታደለች ከመሆኗ አንፃር በርካታ የቱሪስት መስህቦችን በዓለም ደረጃ ለማስመዝገብ እንደምትጥር የቱሪዝም ሚኒስቴር (የቀድሞ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር) ሲያወሳ ይደመጣል።

ከሚዳሰሱ ቅርሶቿ መካከል ከአክሱም ሐውልቶች እስከ ኦሞ ሸለቆ ድረስ እንዲሁም ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የሚታዩባቸው በርካታ ክዋኔዎች አሏት። አስደናቂ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የአየር ንብረት፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ እንዲሁም የሰው ዘር መገኛ ስፍራዎች ኢትዮጵያን ለቱሪስት መዳረሻነት ከሚያበቋት መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።

በዚህ መሠረት ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርሶች መዝገብ ከ13 ያላነሱ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ሀብቶቿን በዓለም ቅርስነት አስመዝግባለች። በዚህም ከአፍሪካ ቀዳሚ አገር ናት።

እነዚህ ቅርሶች ታድያ በእድሜ አንጋፋ በመሆናቸው ሰው ሠራሽም ይሁን ተፈጥሮአዊ ጉዳትን ያስተናግዳሉ። ያንን ተከትሎም ይዘታቸውን ሳይለቁ ጥገና እንዲደረግላቸው ለማስቻል ከፍተኛ ወጪን መጠየቃቸው አልቀረም።

አክሱም

አክሱም ሰው ሠራሽ የኪነ ሕንጻ ጥበብ (አርኪዮሎጂ) የሚታይበት ስፍራ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ1980 በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። በትግራይ ክልል ከአዲስ አበባ በ1080 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ቅርስ፤ ከፍተኛ የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት እንዲሁም ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍን የሚወክል በመሆኑ ክብካቤ እንዲደረግለት ይጠበቃል። በዚህም መሠረት የፌዴራል መንግሥት ለቅርሱ ጥገና ለማድረግ የጀመራቸው እንቅስቃሴዎች ነበሩ።
24 ሜትር ርዝመት ያለውና “ሦስት ሐውልት” ተብሎ የሚጠራውን የአክሱም ዋናውን ሐውልት ለማደስ የሚያስችል ስምምነት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከሦስት ዓመት በፊት አድርጎ ነበረ።

በዚህ መሰረት ሐውልቱ የተገጠመለት የንዝረት መቆጣጠሪያ በጊዜ ብዛት፣ በፀሀይና በዝናብ ምክንያት ብልሽት ስለገጠመው እድሳት አስፈልጎት ነበር። ይህንን ተከትሎም የሐውልቱ እድሳት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ የጊዜ ገደብ ተያዘለት። ይህ የእድሳት ሥራም ‹ኤም.ኤች. ኢንጂነሪንግ› በተባለ አገር በቀል ድርጅት እና ከጣሊያን የተመለሰውን ሐውልት የዳግም ተከላ ሥራ ባከናወነው ‹ስቱዲዮ ክሮቺ› በተባለ የጣሊያን አማካሪ ድርጅት በኩል እንዲጀመር ተወሰነ። ይሁንና በ2012 ታህሳስ ወር ኮቪዲ 19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ እድሳቱ ተቋርጧል።

ወረርሽኙ የተወሰነ ለውጦች በሚያሳይበት ወቅት በድጋሚ ወደ እድሳት ሥራው እንደሚገባ የፌዴራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ቢያሳውቅም፣ ሌላ ተደራቢ ችግር የሆነው የሰሜኑ ጦርነት በመጀመሩ ምንም ዓይነት ጥገና ሥራ አልተካሄደም። በአሁን ወቅትም በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ እንደማይታወቅ ባለሥልጣኑ አስታውቋል።

ላሊበላ
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ከአንድ ወጥ ድንጋይ በመፈልፈል የተሠሩ፣ ድንቅ የሰው ልጅ የኪነ ሕንጻ ጥበብ የሚስተዋልባቸው ሀብቶች ናቸው። 11 የተለያየ መጠሪያ ያላቸውና የተለያየ የኪነ ሕንጻ ጥበብ የሚታይባቸው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት፣ በጊዜ ሂደት ሰው ሠራሽ እንዲሁም ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተደቅኖባቸዋል።

ከዐስራ አንዱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት መካከል ቤተ-ማርያም እና ቤተ-መድኃኒዓለም የመሰነጣጠቅ አደጋ እንደደረሰባቸው የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤትን በመጥቀስ አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም መዘገቧ ይታወሳል።
በዘገባውም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን ላሊበላ ከተማን ተቆጣጥሮ በቆየባቸው ወራት፣ በቀጥተኛ መንገድ ባይሆንም በአብያተ ክርስትያናቱ ውስጥ የሚገኙ የድንጋይ ፍልፍል ቅርሶች የላይኛው ክፍላቸውን ለመትረይስ እና ለሌሎች ከባድ የጦር መሣሪያ መደገፊያ አውሎ ለመተኮሻነት እንደተጠቀማቸው መገለጹ ይታወሳል። በዚህም የተነሳ የመሰነጣጠቅ አደጋ እንደገጠማቸው የላሊበላ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መልካሙ ዓለሙ ለአዲስ ማለዳ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

በዛው ዘገባ ላይ ከኹለት ዓመት በፊት ጀምሮ ከዐስራ አንዱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ቤተ-ማርያም እና ቤተ-መድኃኒዓለም አደጋ ተጋርጦባቸው እንደነበር የተናገሩት ኃላፊው፣ እነዚህ ቅርሶች ለጦር መሣሪያ መተኮሻ እንደድጋፍ መዋላቸው የጉዳት መጠኑን ከማስፋቱ ባሻገር አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ እንዲገኙ ማድረጉን ተናግረዋል።

አያይዘውም፣ በኹለተኛው ምድብ የተቀመጡት ቤተ-አማኑኤል፣ ቤተ-ገብርኤል፣ ቤተ-መርቆርዮስ፣ ቤተ-አባ ሊባኖስ፣ ቤተ- ሚካኤል እና ቤተ-ጊዮርጊስም ላይ አደጋው እንዳለ ገልጸዋል።
በድምሩም ከፌዴራል መንግሥት በኩል ተገቢውን ትኩረት አለማግኘት እንዲሁም የፈረንሳይ መንግሥትም በሙሉ አቅሙ ወደ ጥገና መግባት ባለመቻሉ በቅርሶች ላይ የተጋረጠው አደጋ ጨምሯል ብለዋል።

በፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እና በላሊበላ ከተማ አስተዳደር በኩል በየዓመቱ ራሱን የቻለ በጀት በየስድስት ወሩ በመመደብ፣ ከኹለት መቶ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎችን በመመልመል በአብያተ ክርስትያናቱ ውስጥ የሚገኙ ቅርሶችን በየጊዜው የማፅዳት ዘመቻ ይከናወን ነበር። ይህም በ2013 በመጀመሪያው ሩብ ዓመት አልተከናወነም።

የፌዴራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ እንክብካቤና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው በጊዜው በጉዳዩ ላይ በሰጡት ሐሳብ፣ በሕወሓት ቡድን ተግባር ሳቢያ ቤተ-ማርያም እና ቤተ-መድኃኒዓለም አብያተ ክርስትያናት ላይ የመሰነጣጠቅ አደጋ እንደደረሰባቸው የሚጠቁም መረጃ አልደረሰንም፤ ባለሥልጣኑም ራሱን በቻለ ጥናት አላረጋገጠም ብለዋል።

ያም ሆነ ይህ ግን ባለሥልጣኑ ከጦርነቱ በፊት ለቅርሱ የሚገባውን በጀት መድቦ ከመሥራት እንዳልተቆጠበ እና አሁን ባለው ሁኔታ ባለሥልጣኑ ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር ተነጋግሮ ታቅዶ የነበረውን የጥገና ሥራ ለማስጀመር እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ይህን የዓለም ቅርስ ለመታደግ ከመጋቢት 12 ቀን 2014 ጀምሮ የፈረንሳይ መንግሥት ለላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት ጥገና የገባውን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊ ግብዓቶችን ወደ አገር ውስጥ እያስገባ መሆኑን የላሊበላ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ መልካሙ፣ ለውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ 24 የተለዩ ቦታዎች ላይ የቅድመ ጥገና ሥራ ለመሥራት አስፈላጊ ቁሳቁሶች እየገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሚደረገው ጥገና ዙሪያ ከማኅበረሰቡ ጋር ምክክር መደረጉን የተናገሩት ኃላፊው፣ የቀድሞ ይዘቱን ሳይለቅ በአገር በቀል ቁሳቁሶችና ግብዓቶች እንዲጠገን ሥምምነት ላይ መድረሱንም ገልጸዋል።

በቅድመ ጥገናው ለአንገብጋቢ ችግሮች ቅድሚያ መፍትሄ በመስጠት የሚጀመር ሲሆን፤ ዋናው የጥገና ሥራም ጎን ለጎን ተግባራዊ ይደረጋል። በአሁኑ ጊዜም ከውጪና ከአገር ውስጥ የተውጣጡ አዲስ የሙያው አማካሪዎች ተቋቁመው አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ እንቅስቃሴው መጀመሩን ተናግረዋል።

በላሊበላ ከተማ ማኅበረሰቡ አሁን ላይ ሰላማዊ እንቅስቃሴውን የመጀመረ ቢሆንም የውሀ፤ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት እንዲሁም የኑሮ ውድነት ፈተና መሆኑን መልካሙ ጠቅሰዋል። በከተማው ለሚደረገው የቅርስ ጥገናም ሆነ የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት የክልልና የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የጀጎል ግንብ
በጀጎል ግንብ የታጠረው የሐረር ታሪካዊ ከተማ በጥንታዊ በሮችና ታሪካዊ የሕንጻ ሥራዎች ቁሳዊና ባህላዊ ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ ተመዝግቧል። ይህ ቅርስ በዓለም የቅርስ መዝገብ ላይ እ.ኤ.አ. በ2006 የተመዘገበ ነው።
በጀጎል ግንብ የተከበበችው ሐረር ከተማ አምስት በሮች አሏት። ሐረር ለዘመናት ከፍተኛ የንግድ ማዕከል ሆና ከመሃል አገር፣ ከአፍሪካ ቀንድ እና ከአረብ አገራት ጋር በንግድ መንገዶች ስትገናኝ ከቀሪው ዓለም ጋር ደግሞ በቀይ ባሕር ወደቦች አማካኝነት ትተሳሰር እንደነበር የሐረሪ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን በድረገጹ አስፍሯል።

ይሁን እንጂ በሐረሪ ክልል የሚገኘው የጀጎል ግንብ እና በውስጡ ያሉ በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶች ላይ አደጋ እንደተጋረጠ የክልሉ የባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
አምስት መቶ ዓመት ገደማ ዕድሜ ያስቆጠረው ይኸው የጀጎል ግንብ እና በዙሪያው የሚገኙ ቤቶች፣ በክረምት ወራት፣ በየወቅቱ በሚጥል ዝናብ ሳቢያ እንዲሁም በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በሚያደርሱት ጉዳት ምክንያት ቅርሶቹ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ይህንንም ክስተት አዲስ ማለዳ የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ተወለዳ ሀዱሽን ጠቅሳ መዘገቧ ይታወሳል።

ቅርሶቹ በክልሉ በኩል በየዓመቱ ራሱን የቻለ በጀት ተመድቦ የጥገና ሥራ ቢደረግላቸውም፣ ከሚያጋጥማቸው ችግር መላቀቅ እንዳልቻሉ በዘገባው ተጠቅሷል። በተያያዘም፣ ለቅርሱ ጥገና እንዲከናወን ለማስቻል ቅድሚያ የጥናት ሥራ ለማድረግ ከክልሉ ቤቶች ልማት ጋር በጥምረት የጥናት ሥራ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ የጥናት ሥራው ሙሉ ለሙሉ ባለመጠናቀቁ እና በወቅቱ በአካባቢው በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ጥገናው ሳይከናወን ቀርቷል ተብሏል።

ክልሉ በቻለው አቅም የጥገና ሥራውን እያከናወነ መሆኑን የተጠቀሰ ሲሆን፣ ከደረሰበት አደጋ መከላከል ግን እንዳልተቻለ ነው የተገለጸው። የሐረሪ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ በተያዘው ዓመትም ለኹለተኛ ጊዜ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን የቢሮው ኃላፊ ተወለዳ አስታውሰዋል።

ቅርሱን ለመታደግ የሚደረገው ጥረትና ርብርብ ባይቆምም፣ ጉዳዩ በቂ ትኩረት እንዲያገኝና የሚመለከታቸውም ጉዳዩን ቸል እንዳይሉ ኃላፊው አሳስበዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ ስለ ጉዳዩ የጠየቀቻቸው እና ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በፌዴራል ቅርስና ጥበቃ ሚኒስቴር ውስጥ ያሉ ባለሙያ፣ በጀጎል ግንብና በዙሪያው የሚገኙ ቅርሶች ላይ አደጋ መጋረጡ እንደማይሸሸግ አንስተዋል።
ባለፈው ዓመት ከዓለም ዐቀፍ የቅርስ ጥበቃ ኮሚቴ ጋር በመተባበር ለቅርሱ ጥገና የሚውል ራሱን የቻለ በጀት ተመድቦ የነበረ ቢሆንም፣ በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ቅርሱን መጠገን አልተቻለም ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በ2013 የበጀት ዓመት ለቅርሱ ጥገና ተይዞ የነበረው በጀት ለሌላ ሥራ እንደዋለ ተናግረዋል። በተያዘው 2014 በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ወራት ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ እስከ አሁን ባለው መረጃ ምንም ዓይነት የተጀመረ ሥራ እንደሌለ ገልጸዋል።

የፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን አሁን ላይ ለቅርሱ ጥገና ለማድረግ ከዓለም ዐቀፍ የቅርስ ጥበቃ ኮሚቴ እና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

የሐረሪ ክልል የባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ በከተማዋ ያለውን ቅርስ ለመታደግ ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን፣ በሐረር ከተማ ዙሪያ የሚገኝ ‹አወር ሄሌ› የሚል ሥያሜ የተሰጠውን የሚዳሰስ ቅርስ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ኃላፊው ተወልዳ ተናግረዋል።

ተስፋና የወደፊት መንገድ
የፌዴራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ነጃት ጀማል በበኩላቸው፣ ባለሥልጣኑ በተያዘው ዓመት ከላይ የተጠቀሱትን እና በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢ የሚገኙ ሌሎች ቅርሶችም እድሳትና ጥገና የሚያስፈልጋቸውን በመለየት ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል።

ለቅርሶች እንክብካቤ የመንግሥት አካላትም ሆኑ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ ያሳሰቡት ዳይሬክተራ፣ በተለይም ጦርነትና ግጭት በሚፈጠርበት ወቅት እንዲሁም የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በሚሠሩ ጊዜ ቅርሶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ከተሠሩ በጎ ሥራዎች መካከል ጢያ ትክል ድንጋይን በተመለከተ ጥሩ ውጤት እንደተገኘ ተጠቅሷል። የተለያየ ስፋት፣ ርዝመት (ከ1 እስከ 5 ሜትር) እና ውፍረት ያላቸው የ36 የሚሆኑ ትክል ድንጋዮች በ 2012 አደጋ ተጋርጦባቸው ነበር። ሆኖም ባለፈው በጀት ዓመት ጥገና ተደርጎላቸው ከተደቀነባቸው አደጋ መታደግ መቻሉን ባለሥልጣኑ አውስቷል።

ቅርሶች ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ ከሚደርስባቸው አደጋ በተጓዳኝ፣ ባለፉት ጊዜያት ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ወደ ሥልጣን በሚመጡ መንግሥታት ትኩረት ማነስ፣ ለበርካታ ዓመታት ተገቢውን መጠለያ ማግኘት ባለመቻልና በመሳሰለው ምክንያት ለችግር ሲጋለጡ ይስተዋላል።

ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት ከመንግሥት ጋር ውል ተዋውለው ወደ ሥራ የሚገቡ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ተገቢውን ጥገና ባለማድረጋቸው እና ድርጅቶችን የሚቆጣጠራቸው አካላት ትኩረት አናሳ መሆን፣ ከዛም ባለፈ ዘላቂ ወይም አስተማማኝ ጥገና በመነፈጋቸው የጉዳቱ መጠን አሳሳቢ ወደሚባል ደረጃ እንዲደርስ ማድረጉን በተለያየ አጋጣሚ መዘገቡ አይዘነጋም።


ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here