ድህረ-ዘመናዊነት፡ ቀጣዩ የሃይማኖቶች ጉባኤ የቤት ሥራ

Views: 222

ያለፉት ኹለት ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወገን በፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች በሚሰጡ አጥፊ አጀንዳዎች ሕይወቱን ያጣባቸው፣ ደህንነቱን የተነጠቀባቸው እና ያፈራውን ንብረት ያጣባቸው ነበሩ። ባለፈው አንድ ዓመት የታየው አዲስ ጉዳይ ደግሞ ግጭቶች ኃይማኖታዊ መልክ እንዲይዙ እየተደረጉ መሄዳቸው ነው።

አብዛኛውን ሕዝብም በግጭቶቹ ተሳታፊ ለማድረግ በሚመስል መልኩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቤተ ክርስቲያኖች እና መስጊዶች በእሳት እንዲወድሙ ተደርገዋል። እነዚህ ከቦታ ቦታ እየተደጋገሙ ሲፈፀሙ የቆዩ ኃይማኖታዊ ጥቃቶች በሕዝቦች መካከል ያለመተማመንን፣ ልዩነትን እና የጠላትነት ስሜትን ለማዳበር ታስበው የተደረጉ እንደሆኑም መገመት ይቻላል። የኃይማኖች አባቶች በሰከነ መንፈስ ጉዳዩን በተናጠልም ሆነ በጋራ ሆነው ሲያወግዙ መቆየታቸውም ይህ ሙከራ የተሳካ እንዳይሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ግን እነዚህ ሁሉ የፖለቲካ እና የኃይማኖት የግጭት መንስኤዎች ረገብ ያሉ ይመስላል። በሽታው ዓለም አቀፋዊ መሆኑ እና ባደጉት አገሮች ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ሺዎችን እየገደለ የሚገኝ መሆኑ ዓለምም ሆነ አገራችን ላይ ሲታዩ በቆዩት ዘግናኝ ነገሮች ፈጣሪ ተበሳጭቶ ሊቀጣን ያመጣው መቅሰፍት መሆኑን አማኞች ሙሉ በሙሉ እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢአማኒያንም እየተስማሙ ይገኛሉ። በመሆኑም የዓለም አገራትን ሁሉ ያዳረሰው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሰው ልጆች ስለአኗኗራቸው ቆም ብለው እንዲያስቡ እያደረገ ይገኛል።

በአገራችን እያየን እንዳለውም እንቅስቃሴን መግታት የመፍትሔው አንድ አካል መሆኑን ተከትሎ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር የሚይዘው የአገሪቱ ሕዝብ በኃይማኖት መሪዎቹ እየተመራ ፈጣሪው የመጣውን ችግር እንዲያሳልፍለት እየለመነ ይገኛል። ሁሉም ኃይማኖቶች በተለየ መንገድ ወደ ፈጣሪ ፀሎት የሚደረግበት ስርዓትም አበጅተዋል።
በኃይማኖት ተቋማትም መካከል ያለው አብሮ የመሥራት እና የመተባበር መንፈስ ከፍ እያለ እንደመጣ የሰሞኑ ሒደቶች ማሳያ ናቸው። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ የሆኑት ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ይህ የተቋማቱ ትብብር አሁን የመጣ ሳይሆን ቀደም ብሎም የነበር ነው ይላሉ። በርግጥ ጉባኤው ከተቋቋመ ዐስር ዓመታት ሆነውታል። ጉባኤው ከዐስር ዓመታት በፊት ይታዩ የነበሩ የኃይማኖት አክራሪነት ተግባራትን ለመከላከል እና የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮችን ማጥቃት በየትኛውም የእምነት ተቋም ሃይማኖታዊ መሠረት የሌለው መሆኑን ለማሳየት እንደተቋቋመ አስረድተዋል። “የሃይማኖት መሠረት የሆኑት ቅዱስ ቁርዓን እና መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰዎች እንዲገዳደሉ እና እንዲጋጩ የሚጋብዝ ምንም ትዕዛዝ የለም” ብለዋል ዋና ፀሐፊው። በመሆኑም ሰዎች በግል እና በቡድን ፍላጎት ይህንን እንደ ሰበብ አድርገው አማኞችን ሲያርዱ እና ቤተ እምነቶችን ሲያቃጥሉ ሁኔታውን በመቃወም እና በጋራ በመቆም በሰላም እና በአብሮነት መሻገር አለብን በሚል ነው ጉባኤው የተቋቋመው ብለዋል፡፡

እንደ እርሳቸው አባባል አሁን ከሚካሔደው የተቋማቱ አማኞችን በፀሎት የማትጋት እና ይቅርታን ከፈጣሪ የመለመን ተግባር ጎን ለጎን ከተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን ሕዝብ በወረርሽኙ ላይ ያለው ግንዛቤ እንዲጨምር እየሠሩ ነው። የንጽህና ግብዓቶችን (ሳኒታይዘር እና ሳሙና) እንዲሁም ሌሎች የቫይረሱን ስርጭት ሊከላከሉ የሚችሉ ነገሮችን የሚያቀርብ ግብረ ኃይል ተሰማርቶ አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ ዋና ፀሐፊው ገልፀዋል።

ከወረርሽኙ በኋላም ቢሆን ገባኤው በዘላቂነት ከሚሠራባቸው ጉዳዮች አንዱ አክራሪነትን መከላከል መሆኑን ጠቅሰዋል። ጉባኤው ከሚሰራቸው ሥራዎች ውስጥ ሌላ በዋናነት የሚጠቀሰው ሥራ ደግሞ ሰላምን መገንባት እንደሆነ ቀሲስ አስረድተዋል። ሰላም ወዳድ የሆነው አብዛኛው ሕዝብ ተሳስቦ ችግሮችን የሚያልፍ ቢሆንም ፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች የሚኖራቸው ሚና ይህንን ሲያዛባ መታየቱ ጉባኤው ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ግጭትን የመቆጣጠር፣ ሰላምን የመገንባት እንዲሁም የግጭት ጊዜ እና ድህረ ግጭት ተግባራትን እንዲያከናውን እንዳደረገው ቀሲስ አስረድተዋል። ወረርሽኙም ካለፈ በኋላ ይህ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአዲስ ማለዳ ምንጭ የጉባኤው ክፍተቶች ብለው ከጠቀሷቸው ጉዳዮች አንዱ የድህረ-ዘመናዊነት (ፖስት ሞደርኒዝም) አስተሳሰቦችን ለመከላከል ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረገ ያለመሆኑን ነው። ድህረ-ዘመናዊነት ከ17ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በሰፊው ተቀባይነት አግኝተው የቆዩትን የምዕራባውያን ፍልስፍና አስተሳሰቦች የሚጠራጠር፣ ብሎም ውድቅ የሚያደርግ እንቅስቃሴ ነው። ድህረ-ዘመናዊያን ፍፁም የሆነ እውነት የለም፤ እውነት የምንለው የተስማማንበት ተለዋዋጭ ጉዳይ እንጂ ከሰዎች ግንዛቤ ውጪ ያለ የማይለዋወጥ ነገር አይደለም ብለው ያምናሉ።

ይህም አስተሳሰብ በዓለም ዙሪያ ባሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ከመሆኑ የተነሳ በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች ይህንን ሀሳብ የማይቀበሉ መምህራን ከፍተኛ ጫና እንደሚደረግባቸው አለፍ ሲልም እንደሚባረሩ አንዳንድ ምንጮች ያሳያሉ። በእኛ አገር አስተሳሰቡ በዩኒቨርስቲ መምህራን ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ሲሆን ከፍልስፍና ውጭ ባሉ የትምህርት ዓይነቶች ላይም ጉዳዩ የካተታል። ርዕዩተ ዓለሙ በቀጥታ የትምህርት አካል ባይሆን እንኳን “ክሪቲካል ቲንኪንግ” የሚባለው አስተሳሰቡ በተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች ውስጥ ተካቷል። በዚህም አካሔድ መሠረት አስተሳሰቡ እየሰፋ ነው ማለት ይቻላል።

ሃይማኖቶች ደግሞ በመሠረታዊነት ዓለምን የፈጠረ የማይቀያየር እውነት የሆነ ነው ብለው የሚያምኑበትን አምላክ የሚያምኑ በመሆናቸው ዕውነት ተቀያያሪ እና የሰዎች ስምምነት ውጤት ነው የሚለው የድህረ-ዘመናዊ አስተሳሰብ አምላክን የሚክድ ሆኖ ያገኙታል። በመሆኑም ድህረ-ዘመናዊነት ከሃይማኖት አስተሳሰብ ጋር ይጋጫል። እስልምናም ሆነ ክርስትና ለውጥ በሌለው መልኩ የፈጣሪን የማይቀያየር እውነት መሆን ያምናሉ። ድህረ-ዘመናዊነትም በቀጥታ ይህንን መጣረስ ዕውቅና ይሰጣል። በአስተሳሰቡ እንደሚገለፀውም የአብርሆት ፍልስፍናዎች እና ሃይማኖቶች ቦታ የላቸውም።

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያኑ መምህር ታደሰ ወርቁ ይህንን አስመልክተው ሲያብራሩ የነገሮች ተለዋዋጭነት የግንዛቤ ወይም አንድን ነገር የምናይበት መንገድ መቀያየር ጉዳይ ነው ይላሉ። ይህንን በቀላሉ ለመረዳት በአንድ ጠረጴዛ ማዶ የተቀመጡ ኹለት ሰዎች ስድስት ቁጥርን በአንድነት ስድስት ነች ብለው አያዩም። ይልቁንም ለአንዱ ዘጠኝ ሆና ትታያለች። መምህር ታደሰ ሃይማኖት ግን እንደዚህ አይደለም ይላሉ። ሃይማኖት በውስጡ ኹለት መሠረታዊ እሳቤዎች አሉት ይላሉ፤ እነሱም ማመን እና መታመን ናቸው። ማመን ያላየኸውን ፈጣሪን እንዳየኸው፣ ያልዳሰስከውን ፈጣሪን እንደዳሰስከው መቀበል ነው ሲሉ ያስረዳሉ። መታመን ደግሞ ካመንክ በኋላ አድርግ የተባልከውን ትዕዛዛት በእርሱ ስም ዋጋውን ይከፍለኛል ብሎ አምልኮ መፈፀም፣ መስገድ፣ ለደሆች መመፅወት ነው። እንደእርሳቸው አባባል ይሄ ሊቀየር የማይችል እውነት ነው፤ ከሆነ ግንዛቤ ተነስተህ ልትበይነው የምትችለው ሳይሆን የተሰመረ አንድ መስመር ነው።

በሰው እይታ እና አስተሳሰብ እውነት አንጻራዊ ነው። ለምሳሌም አሉ መምህሩ ልጆች ኬክ እንዲገዛላቸው ሲፈልጉ እናታቸውን ካላደረግሽልኝ ወንዝ ወስጥ ገብቼ እሞትልሻለሁ ሊሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን በሱርማ (ደቡብ ኦሞ) አካባቢ ህፃን ልጅ እናቱ እንድትገዛለት የሚፈልገው ትልቅ ነገር ጨው ነው። ይህንን ማድረግ አልችልም ገንዘብ የለኝም ስትል ልጁ እናቱን የሚያስፈራራት ካልገዛሽልኝ ልብስ እለብሳለሁ ብሎ ነው ሲሉ ተነጻጻሪነቱን ያሳያሉ። በከተማው ሕዝብ አመለካከት ራቁት መሔድ የእብደት ምልክት ሲሆን በሱርማዎች አመለካከት ልብስ መልበስ ነውር ነው። በሰዎች አስተሳሰብ የሚታየው አንጻራዊነት ግን በሃይማኖት ውስጥ የሚታይ አይደለም ሲሉ መምህሩ አስረድተዋል።

መምህር ታደሰ ለሃይማኖት ተግዳሮት የሆኑ አስተሳሰቦች ድሮም ነበሩ ወደፊትም ይቀጥላሉ። በተለያዩ አስተሳሰቦች መፈተን የሃይማኖት ባሕሪይ ነውም ይላሉ። ከዚህ በፊትም ብዙ ፈላስፎች ተነስተው ሃይማኖትን የፈተኑ ቢሆንም ሃይማኖት ግን እየዘየደ አልፏቸዋል ሲሉም የሁኔታውን ታሪካዊ ድግግሞሽ ያሳያሉ። ሃይማኖቶች ዘመኑን መዋጀት አለባቸው ሲሉም ካለው አኗኗር ጋር የተጣጣሙ እንጂ የድሮውን ብቻ አሳይተው ካለው ጋር የማይሔዱ መሆን እንደሌለባቸው ይጠቁማሉ። ያለው ዋነኛ መፍትሔ ሃይማኖት ከተነሳው አስተሳሰብ የተሻለ መሆኑን በሚያሳይ መንገድ ልዕለ ሃሳብ አድርጎ ማውጣት ነው ይላሉ። የሃይማኖት ተቋማት ሕዝባቸውን ማዳን ከፈለጉ ከተለመደው ዲስኩር ወጥተው ወደ ሃይማኖታዊ ጥናት እና ፍልስፍና ከፍ ሊሉ ይገባል ሲሉም ይመክራሉ።

መምህር ታደሰ የሃይማኖት ተቋማት በአስተምህሮ የሚለያዩ ቢሆኑም የጋራ ችግሮቻቸው ላይ በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው ያምናሉ። ድህረ-ዘመናዊነትም ሌላ በእምነት ላይ የሚነሳ ፈተና አንድ ሃይማኖት ላይ ለይቶ የመጣ እስካልሆነ ድረስ የሃይማኖት ተቋማት አማኞቻችን የዚህ ሀሳብ ሰለባ እንዳይሆኑ ምን ማድረግ አለብን ብለው ቁጭ ብለው መምከር እንዳለባቸው ያሳስባሉ።

የሃይማኖት ተቋማት ግን በተናጠል ድህረ-ዘመናዊነትን እንደ ተግዳሮት ቆጥረው እንደሚወያዩበት መምህሩ ጨምረው ገልፀዋል። በእስልምናውም ሆነ በተለያዩ የክርስትና ቤተ እምነቶች ውስጥ ድህረ-ዘመናዊነት ላይ ብቻ ሳይሆን ሶሻሊዝም፣ ኮሚኒዝም፣ ሊብራሊዝም እና ኒዮሊብራሊዝም ሁሉ ላይ ጥናቶች እየቀረቡ ለእምነቶቹ ያላቸው ተግዳሮትነት ለውይይት እንደሚቀርብም ገልፀዋል።

ነገር ግን የሃይማኖት ተቋማቱ በጋራ ሆነው ይህንን አስተሳሰብ እንደ ተግዳሮት በጋራ ልንወጣው ይገባል የተባባሉበት ጊዜ እንደሌለ መምህር ታደሰ ያስረዳሉ። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለም የመምህሩን አስተያየት ይቀበላሉ። በየእምነት ተቋማት ድህረ-ዘመናዊነት እንደእምነቶቹ ተግዳሮትነት የሚነሳ እና አስተምህሮውም ያለ ሲሆን በጉባኤው ደረጃ ግን በጋራ የተያዘ አጀንዳ እስከአሁን አልሆነም ብለዋል።

በመሆኑም ጊዜ የማይሰጠው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጉዳይን አጠናክሮ መጨረስ ሙሉ ትኩረት የሚጠይቅ ስለሆነ ጉዳዩን በትጋት መጨረሱ ከሃይማኖት ተቋማቱ ህብረት የሚጠበቅ ነው። ይህ ወረርሽን ሲያልፍ ግን በጋራ ትኩረት ሊያደርጉባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል የድህረ-ዘመናዊነት መስፋፋትን መከላከል አንዱ አንደሆነ እሙን ነው፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com