15 ኢትዮጵያዊ የቴክኖሎጂ አበልፃጊዎች ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በማሸነፍ እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ተሸለሙ

0
555

ማክሰኞ ሚያዝያ 11 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአለም አቀር ውድድሮች ተወዳድረው በማሸነፍ እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ያገኙ 15 ወጣት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎች በዛሬው ዕለት እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

ለእኚህ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎችና ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ሽልማቱን የሰጠው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ነው።

መድረኩ የቴክኖሎጂ አፍላቂዎች እና ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች የእርስ በርስ ትስስር እንዲፈጥሩ ታልሞ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ አሸናፊዎች ከኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ የምስክር ወረቀት እና የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ባይሳ በዳዳ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶቹ የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ እድገት ለማፋጠን አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኮርያ አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ሚኒስትር ዴኤታው፤ መንግስት ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች የሚደገፉበትን ሥርዓት ለመዘርጋት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ዳይሬክተር ሊ ቢዮንግ ኋ ኢትዮጵያ ለኢኖቬሽን ዘርፍ ሥራ ፈጠራ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት ኢጀንሲው እንደሚደግፍ ተናግረዋል።

ከአይ ሲ ቲ፣ ከግብርና፣ ከማምረቻ ዘርፍ፣ ከቱሪዝም፣ ከማዕድን እና ከዲጂታል ዘርፎች የተውጣጡ 15 የቴክኖሎጂ አበልፃጊ ተሸላሚዎች በንግድ እና ቴክኒካል ጉዳይ ስልጠና ሲሰጣቸው ቆይቷል።

በተሰጣቸው ስልጠና መሰረት አለም አቀፍ ውድድሮችን ተወዳድረው በማሸነፍ ከ25 ሺህ እስከ 2 ነጥብ 5 ሚልየን ዶላር ሽልማት ያገኙ ሲሆን፤ በአገር ውስጥም ከ200 በላይ የሥራ እድሎች፣ ከ100 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር ድረስ ሀብት ማግኘታቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

  

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here