በሕገ ወጥ መንገድ 70 ቆጣሪዎችን የገጠሙ 15 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ

0
691

ከኅብረተሰብ በደረሰ ጥቆማ በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ 01 ቀበሌ በተለምዶ ገዋሳ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በሕገ ወጥ መንገድ ቆጣሪ የገጠሙ ግለሰቦች ከነተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እውቅና ውጪ ለአደጋ አጋላጭ በሆነ መንገድ 70 ቆጣሪዎችን የገጠሙና ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ያላቸው 15 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን የለገጣፎ ለገዳዲ ፖሊስ መምሪያ አሳውቋል።

ወንጀሉ በተፈፀመበት አካባቢ ምሰሶዎችን ጨምሮ በማይታወቁ ግለሰቦች የተዘረጉ የኤሌክትሪክ ገመዶች እንዲሁም ቆጣሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ በአንድ ግለሰብ ቤት የተጠቀለለና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ንብረትነት የሚጠረጠር የኤሌክትሪክ ገመድ መገኘቱም ተነግሯል።

በሕገ ወጥ ተግባሩ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ቆጣሪ በሚገጥሙበት ወቅት ከእያንዳንዳቸው ደንበኞቻቸው ከ20 እስከ 35 ሺሕ ብር እንደተቀበሉ መረጃ መገኘቱም ተጠቅሷል።

የለገጣፎ ለገዳዲ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ወርቁ በዳኔ እንደገለፁት፣ በወንጀሉ ተጠርጥረው ከተያዙት በተጨማሪ ሌሎች ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችም አሉ። የአካባቢው ኅብረተሰብ በሰጠው ጥቆማ በሕገ ወጥ ተግባሩ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችን ጨምሮ ሌሎች በቁጥጥር ስር ያልዋሉና በመሰል ተግባር ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችን በቀጣይ ከክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማድረግ እንደሚሠራ ተነግሯል።

ሕገወጥ ተግባሩ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ከዚህ ጋር በተገናኘ የሚሠራ ወንጀል ከ5 እስከ 15 ዓመት ፅኑ እስራት እና እስከ 50 ሺሕ ብር መቀጮ ያስከትላል ተብሏል። ኅብረተሰቡ ይህን አውቆ አገልግሎቱን ለማግኘት ሕጋዊ መንገድ ብቻ መከተል እንዳለበት የተነገረ ሲሆን፣ በሕገወጥ መንገድ የሚሳተፉ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተገኘው መረጃ አሳውቋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here