ማክሰኞ ሚያዚያ 18 (አዲስ ማለዳ) ዳሽን ባንክ “ዱቤ ፔይ ቴክኖሎጂ” የተሰኘ አዲስ የሞባይል መተግበሪያ ለደንበኞች ማቅረብ የሚያስችለውን የመግባቢያ ሥምምነት ከኤግልላየን ሲስተም ቴክኖሎጂ ጋር በዛሬው ዕለት ተፈራርሟል።
መተግበሪያው ለነጋዴዎች፣ ለአምራቾችና ለአገልግሎት አቅራቢዎች ተጨማሪ የግብይት እድልን እንደሚፈጥር የተገለፀ ሲሆን፤ የተለመደውን ባህላዊ የዱቤ አገልግሎት በማስቀረት በዘመናዊ የአገልግሎት ማቅረብ እንደሚያስችል ተገልጿል።
“ዱቤፔይ” አሁን ይግዙ በኋላ ይክፈሉ (Buy Now Pay later) መርህን የሚከተል ቴክኖሎጂ ሲሆን፤ በባንኮችን ወይም የፋይናንስ ተቋማት ግብይት በሚያከናውኑ ደንበኞቻቸው፣ ነጋዴዎች፣ ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦች ወይንም ተቋሞች መሃል እንደ ዋስትና ሆኖ ያገለግላል ተብሏል።
“ዱቤፔይ” የሞባይል መተግበሪያ ኹሉን በአንድ የያዘ ማለትም፤ ከደንበኝነት መዝገባ፣ የመለያ ፈጠራን፣ የደንበኛ መገለጫን፣ የግብይት ሂደትን እና የዱቤ ክፍያ መጠየቂያን ከሌሎች ግልጋሎቶች ጋር አጥምሮ የያዘ መሆኑን የኤግልላየን ሲስተም ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስኪያጅ በእርሱፍቃድ ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዎል።
የንግድ ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን ለሸማቾች በዱቤ ማቅረብ ይችሉበታል በተባለለት በዚህ መተግበሪያ፤ የምርትና አገልግሎት አቅራቢዎች ሽያጫቸውን የሚያሳድጉበት መተግበሪ እንደሚሆንም ገልፀዋል።
ሸማቾችም በጊዜያዊ የገንዘብ እጥረት ምክንያት ወቅታዊ ፍላጎታቸውን ከማሳካት እንዳያግዳቸው እና ያሉባቸውን ክፍያዎች፤ በቴክኖሎጅ በመታገዝ በተራዘመ ጊዜ ለመፈጸም እንደሚያስችላቸውም በእርሱፍቃድ ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ገልጸዋል።
ዱቤ ፔይ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላና ደህንነቱ አስተማማኝ ዘመናዊ መተግበሪያ መሆኑም በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ተነግሯል።
መተበሪያውን ለመጠቀም ደንበኞች በቅድሚያ መተግበሪያውን ከአፕ ስቶር ላይ ማውረድ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ በማስከተለም በባንኩ ቅርንጫፎች በመሄድ መመዝገብ እንደሚገባቸው እንዲሁም ከሚሰሩበት መ/ቤት የደሞዝ መጠን ማሳወቂያ ደብዳቤ ማፃፍ እንደሚጠበቅባቸው የዳሽን ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ መኮንን ዮሃንስ ሚሊየን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
ዱቤ ፔይ ቴክኖሎጂ መተግበሪያ ላይ ለነጋዴዎች፣ ለአምራቾችና ለአገልግሎት አቅራቢዎች ምርት እና አገልግሎታቸውን በመጫን እንደሚያጋሩ የገለፁት ዮሃንስ፤ ሸማቾችም መተግበሪያውን በመጠቀም ባንኩ እስካስቀመጠላቸው የዱቤ ጣራ ድረስ መገበያየት ይችላሉ ብለዋል።
መተግበሪያ በአራት አገር በቀል ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግረኛና ሶማሊኛ የቀረበ ሲሆን እንዲሁም እንግሊዘኛ ቋንቋም ጭምር አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል።
በቀጣይም ባንኩ በተናጠል እንዲሁም ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር ይፋ የሚያደርጋቸው ፕሮጀክቶች መኖራቸውም በመድረኩ ተጠቁሟል።
_____
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n






