ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካ የለም

Views: 389

መስፍን ወልደማርያም (ፕሮፌሰር) የአደባባይ ምሁር ተብለው ከሚጠሩ ጥቂት ምሁራን መካከል በግንባር ቀደምትነት ሥማቸው ይጠራል። ብዙ ወዳጆቻቸው የኔታ የሚሏቸው ፕሮፌሰር መስፍን፣ 90ኛ የልደት በዓላቸውን ትላንትና አርብ፣ ሚያዚያ 16/2012 አክብረዋል።

የኔታ መስፍን በረጅሙ የዕድሜ ዘመናቸው ሙያቸውን በተመለከተ እንዲሁም ያገባኛል ይመለከተኛል በሚሉት ማንኛውም ጉዳይ ላይ ከመሳተፍ፣ ሐሳብ ከማዋጣት፣ ከመሞገት ከፍ ሲልም የሰላ ሒስ ከመሰንዘር ሳያፈገፍጉ እነሆ እዚህኛው ዘመን ደርሰዋል።

በሙያቸው በአገር ውስጥና በውጪ አገራት በመማር የፕሮፌሰርነት ካባ የደረቡት የኔታ መስፍን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (በቀድሞ አጠራሩ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ) ለብዙ ዓመታት አስተምረዋል፤ ብዙ ደቀ መዘምራንንም አፍርተዋል። ከመምህርነት ጎን ለጎንም በምርምር ከፍተኛ አበርክቶ አላቸው። የምርምር ሥራቸውን በተለያዩ ታዋቂ የጥናት መጽሔቶች ላይ ከማሳተም በተጨማሪ በመጽሐፍ መልክ ለኅትመት ብርሃን አብቅተዋቸዋል። ‘An Atlas of Ethiopia’ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ከሆኑ ሕያው ሥራዎቻቸው መካከል ይመደባል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሰብኣዊ መብቶች መከበር ጉዳይ ሲያሳስባቸው የኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብቶች ጉባኤ የተባለ ተቋም በማቋቋም ሕዝብን በማንቃት፣ በመንግሥትም ይሁን በሌሎች አካላት የሚደርሱ ሰብኣዊ መብቶች ጥሰት በሪፖርት በማጠናቀርና በማጋለጥ ሠርተዋል፤ በብርቱም ተፈትነውበታል።

በሰብኣዊ መብቶች ጉባኤ ያደርጉ የነበሩትን እንቅስቃሴ በማቆም በቁጭት ቀጥታ የፖለቲካ ተሳትፎ በማድረግ ቅንጅት የተባለ የፓርቲዎች ስብስብን ከጓደኞቻቸው ጋር ዕውን አድርገዋል። ቅንጅት በ1997 አገር ዐቀፍ ምርጫ ላይ መሳተፉ አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ አካሄድን ለማስተካከል፣ የብዙኀኑን የፖለቲካ ግንዛቤ ለማዳበር በርካታ መጽሐፍትን በአማርኛ ቋንቋ በመጻፍ በሰፊው ያስነበቡት የኔታ መስፍን፣ አሁንም በረጅሙ ዕድሜያቸውና ሕመማቸው ሳያግዳቸው የሰላ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሒስ በመጻፍ ለብዙኀን በማጋራት ላይ ይገኛሉ።

የኔታ መስፍን በረጅሙ ዕድሜያቸው ብዙ መንግሥታትን አይተዋል፤ ተችተዋልም። በሚያደርጉት ተጽዕኖ ፈጣሪ እንቅስቃሴም በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርገዋል።
የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ የ90ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ምክንያት በማድረግ ከየኔታ መስፍን ወልደማርያም ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

እንኳን ለ90 ዓመት የልደት በዓልዎ አደረሰዎ። እንኳን ለዚህ ጸጋ አበቃዎ
አሜን እግዚአብሔር ይስጥልኝ፤ አመሰግናለሁ።

የ90 ዓመት ጉዞ ምን ይመስላል፤ ከረጅም በአጭሩ?
ሊያጥር አይችልም (ሳቅ)። እኔ ያለምንም ችግር ማለት አልችልም [ይሁንና] እግዚአብሔር ረድቶኝ እዚህ ደርሻለሁና እግዚአብሔር ይመስገን ነው የምለው።

የተለያየ የሕክምና ክትትል እያደረጉ እንደሆነ አውቃለሁ። አሁን ላይ ጊዜዎትን በምንድን ነው የሚያሳልፉት?
ያው በማንበብና በመጻፍ ነው፣ ሌላ ሥራ የለኝም። ማኅበረሰቡን፣ ኢትዮጵያን አልተለየሁም። እናም ባለኝ አቅም፣ በተቻለኝ መጠን ባለው ሁኔታ መሳተፍ እፈልጋለሁ።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህላችንን እንዴት ያዩታል?

እሱ [የፖለቲካ ባህል] የለምኮ! ወሬ ነው። ፖለቲካ የሚባል ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ነው። አገዛዝ እስካለ ድረስ ፖለቲካ የለም። አገዛዝ ሲጠፋ ነው ፖለቲካ የሚመጣው። አገዛዝ ጠፍቶ እያንዳንዱ ሰው ሰው ሆኖ፣ ዜጋ ሆኖ ለነጻነቱ ለመብቱ ሲቆም ነው ፖለቲካ የሚመጣው። እዛ ጋር ገና አልደረስንም። አሁን ያለው እንደው ዝም ብሎ የጎሳ ትርምስ ነው ፖለቲካ የሚባለው።

በቀደመው ጊዜ የራሳችን ባህል ሳንለቅ የሌላውን የማምጣት ነገር ነበረን። አጼ ኃይለሥላሴ እርስዎንና ከእርሶ ቀደም ያሉትን ውጪ አገር በመላክ የቀለም ትምህርት ቀስማችሁ እንድትመጡ አድርገዋል። በተዘዋዋሪ ይኸው ተምሮ የመጣው ወጣት ስርዓትና ባህል አጠፋ የሚባል ነገር ይነሳል። የኢትዮጵያውያን ማኅበረ ፖለቲካ መስተጋብራችን ተበላሸ የምንለው የቱ ጋር ነው?

ቀላል ጥያቄ ነው። እንዳልከው እኛን አስተምረውናል። እኔ ለአንዱ የአጼ ኃይለሥላሴ ሚኒስትር ያቀረብኩላቸው ጥያቄ ነበር። ‹አሜሪካ ተምራችሁ የመጣችሁ ልጆች ሁሉ ነገር ኳኳኳ እንዲል ነው የምትፈልጉት፣ ይሄ’ኮ አሜሪካ አይደለም› አሉኝ። ለምን አሜሪካ መሆን አይችልም አልኳቸው፣ አሜሪካውያን እንደ እኛ ሰው ናቸው፣ እኛን ምን ያግደናል አልኳቸው።

ችግሩን ልንገርዎት አልኳቸው። ተማሩ ብላችሁ ተማሪ ቤት አስገባችሁን፤ እዚህ ተምረን ጨረስን። ይህ አይበቃም ብላችሁ ፈረንጅ አገር ላካችሁን። ፈረንጅ አገር ሄደን ተምረን፣ ተለውጠን መጣን። እኛ ተምረን ተለውጠን ስንመጣ እናንተ ያው ሆናችሁ ቆያችሁን አልኳቸው። አየህ! ነገሩ ያለው እንደዛ ነው። ገባህ!

ስለዚህ ቅራኔ የመጣው ከዚህ በኋላ ነው፣ እኛን እንድንለወጥ ፈልገው ለወጡን። [ነገር ግን] የእነርሱ አሽከር እንድንሆን ነው የፈለጉት። ትምህርቱ ደግሞ ነጻነትና መብትን ነው ያስተማረን [ስለዚህ] አንዳንዶቻችን አሽከር መሆን አልፈለግንም። ያ ነው ልዩነቱን ያመጣው።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ የብሔር ለብሔር ጭቆና አለ ይባላል፤ እርስዎ የብሔር ጭቆና አለ ብለው ያምናሉ?

የቱ ብሔር የቱን ጨቆነ ብዬ መናገር ያስቸግረኛል። የብዙ ሰዎችን ዘር አናውቅም። አሁን አሁን አንዳንድ ነገር አወቅን። ለምሳሌ የአፄ ኃይለሥላሴን ብሔር አሁን ከለውጡ በኋላ ነው ያወቅነው፣ በፊት አናውቅም። ከእርሳቸው በኋላ የመጡትን ስንመለከት፣ የተፈሪ በንቲ ዘር ይሁኑ፣ የጄኔራል አማን አምዶም ዘር ወይስ የመለስ ዘር ነው [የጨቆነው] … ይህን ማሰብ ያስፈልጋል።

በኢትዮጵያ ከብሔር ተኮር ፖለቲካ አራማጆች እና ከዜግነት ተኮር ፖለቲካ ወይም የአንድነት ኃይል ከሚባሉት የትኛው የሚያሸንፍ ይመስልዎታል? ከማሸነፉ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያስ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል ብለው ያስባሉ?

ሲመጣ ነው የምናየው፤ እኔ ምን አውቃለሁ፤ ጠንቋይ አይደለሁም!

በጣም የሚያደንቁት ፖለቲከኛ አለ?
ፖለቲካ የለም አልኩኝ`ኮ። የጎሳ ነገር ፖለቲካ አይደለም። በአገዛዝ ውስጥ ያለ ለሥልጣን፣ ለወፍራም እንጀራ መቆራቆዝ ፖለቲካ አይደለም። አሜሪካና እንግሊዝ የሚደረገውን ነገር እያየን አይደለም እንዴ? እሱን አይተን እኛ ጋር እንምጣ። እኛ ጋር ፖለቲካ አልተጀመረም፣ ሥሙ ብቻ ነው የመጣው።

ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት በዓለማችን እንዲሁም በአገራችን ጉዳት እያደረሰ ነው። በዚህ ላይ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን እንዴት ታዝበዋል?

እስከ አሁን ድረስ እንደማየው አመራሩ ጥሩ ነው። የተባለውን እየተከተልን ከሄድን የምንፈጽም ከሆነ፣ ባለን ሀብትና ችሎታ አመራሩ ጥሩ ይመስለኛል፤ ተመሪውን ይህን ያህል ብቁ ነው ባልልም። አመራሩ ግን የገባውና ሊያስተካክል የሚሞክር ይመስለኛል።

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com