በሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኘው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ 20 ሄክታር ደን መጨፍጨፉን የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።
የፓርኩ ኃላፊ አበባው አዛናው፣ የፓርኩ ዋና ዋና ስጋቶች ከፍተኛ የሆነ ልቅ ግጦሽ፣ ወደ ፓርኩ ተጠግቶ የሚደረግ ሕገ ወጥ የቤት ግንባታ እና ሕገ ወጥ የእርሻ መስፋፋት መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የደን መጨፍጨፍም እንዲሁ ፓርኩን ለአደጋ እንዳጋለጠው ገልጸዋል።
በዚህም ፓርኩን ከሚያዋስኑት አምስት ወረዳዎች አንዱ በሆነው በአዳርቃይ ወረዳ በኩል ከፍተኛ የሆነ የደን ምንጣሮ መኖሩን አስረድተዋል። በዚህም 20 ሄክታር የሚጠጋ ደን መጨፍጨፉን ነው የጠቀሱት። በዚህ የተነሳም 20 የሚደርሱ ሰዎች ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም ፓርኩን ከሚያዋስኑት ወረዳዎች ጠለምት በከፊልና አዳርቃይ ወረዳ በከፊል በአሸባሪው ሕወሓት ቁጥጥር ውስጥ በመሆናቸው፣ ያለው የመንግሥት መዋቅር ተረጋግቶ አስተዳደራዊ ሥራውን መሥራት ባለመቻሉ ፓርኩ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላትን መያዝና ለሕግ ማቅረብ እንዳልተቻለ አንስተዋል።
በደባርቅ ወረዳ በኩልም እንዲሁ የከፋ ባይሆንም ለከብቶች መንቀሳቀሻ በሚል ፓርኩ ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው ብለዋል።
በፓርኩና በገበሬዎች መሬት መካከል ያለውን ቦታ (የፓርኩ ደጀን) በሕገ ወጥ መልኩ በመውረር፣ ለሕገ ወጥ ቤት ግንባታና የእርሻ ሥራ በማዋል ፓርኩን ያለ ደጀን እንዲቀርና በኋላም የማኅበረሰቡ ከብት ፓርኩ ውስጥ ገብቶ እንዲግጥ እየተደረገ ነው ሲሉም አክለዋል።
ዞኑ ካለበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር አመራሩ ፓርኩ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ እንደበፊቱ ትኩረት ሰጥቶ አለመሥራቱ ፓርኩ ጉዳት እንዲደርስበት አድርጓል በማለትም ተናግረዋል።
በዓለም የተፈጥሮ ቅርስ መዝገብ ውስጥ ተካትቶ የሚገኘው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ ከዚህ ቀደም አደጋ መዝገብ ውስጥ ገብቶ በብዙ ጥረት መሰረዙን አስታውሰው፣ አሁን እያስተናገደው ያለው ጉዳትም ተመልሶ አደጋ መዝገብ ውስጥ እንዲካተት ሊያደርግ የሚችል ተጽዕኖ ነው ብለዋል። ፓርኩ እየደረሰበት ያለው ችግር ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ የመጣ እንደሆነም አስምረውበታል።
ፓርኩ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስም ከቀበሌ እስከ ክልል በየደረጃው ካሉ የፓርክ አማካሪ ኮሚቴ ጋር እቅድ ወጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የቱሪዝም ፍሰቱን በተመለከተ ኃላፊው ሲገልጹ፣ ቀድሞ በኮሮና ወረርሽኝ መከሰት፣ በኋላም ጦርነቱ ወደ ፓርኩ አካባቢ የተጠጋ ስለነበር የቱሪዝም እንቅስቃሴው ጨርሶ ቆሞ ነበር። አሁን ላይ በተለይ ከመጋቢት ወር ወዲህ የተወሰነ እንቅስቃሴ አለ። ሆኖም ደርሶ መልስ እንጂ እንደ በፊቱ ለረዥም ጊዜ ቆይታ የሚመጣ ጎብኚ የለም ነው ያሉት።
የቱሪዝም እንቅስቃሴው በመቆሙም፣ ኑሮአቸውን ከዚህ ጋር ያስተሳሰሩ በርካታ አካላት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቀው ይገኛሉ ብለዋል። በዚህም አስጎብኚ ማኅበራት፣ ምግብ አብሳይ እና ድንኳን ተካይ የነበሩ ሰዎች፣ አጃቢ ሚሊሻዎች እንዲሁም ኢኮ ቱሪዝም ማኅበራት ችግር ውስጥ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር የሚገኝ የበርካታ ተራራዎች ሰንሰለት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ረዥሙ ተራራ ራስ ዳሽን እንዲሁም በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እንደ ዋልያና ቀይ ቀበሮ ያሉ ብርቅዬ የዱር እንስሳት መገኛ መሆኑ ይታወቃል።
ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014



