“የዓመቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በአማካይ በ6 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት እንደሚኖረው ይጠበቃል“:-የብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት

0
845
ማክሰኞ ግንቦት 2 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የዓመቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በአማካይ በ6 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት እንደሚኖረው የሚጠበቅ ሲሆን፥ ይኽ ዕድገት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ጭማሬ እንዳለው የብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት አስታወቀ።
ምክር ቤቱ የ2014 የበጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የኢኮኖሚ አፈጻጸምን በማስመልከት መግለጫ አውጥቷል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-
የተከበራችሁ የአገራችን ሕዝቦች፣
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአገራችን ኢኮኖሚ እንደ ፖለቲካው ኹሉ በተለያዩ ምክንያቶች ለተደጋጋሚ ፈተናዎች ሲዳረግ ቆይቷል።
ያልተጠበቁ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የፈጠሯቸው ጫናዎች እጅግ ፈታኝ መሆናቸው አይካድም። የሰሜኑ ጦርነት ያስከተለው የንግድና የቢዝነስ እንቅስቃሴ መስተጓጎል እንዳለ ሆኖ የፈጠረው የመሰረተ ልማቶች ውድመትና የዜጎች መፈናቀል፣ እንዲሁም የዲፕሎማሲ ቀውስ በኢኮኖሚያችን ላይ ያሳደረው ጫና ቀላል የሚባል አይደለም።
በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ያጋጠመው ድርቅ እና እሱን ተከትሎ ባጋጠመው የሕዝብ ርሃብና የእንስሳት ሞት ኢትዮጵያን ብዙ አሳጥቷታል። ያም ሆኖ ግን የአገራችን ኢኮኖሚ የአገር ውስጥና የውጭ ጫናዎችን ተቋቁሞ በተሻለ ኹኔታ በመጓዝ ላይ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል። የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤቱም የበጀት ዓመቱን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሁኔታዎች በገመገመበት ወቅት ያረጋገጠው ይሄንን ነው።
በመጀመሪያዎቹ ኹለት ሩብ ዓመታት ላይ የተመዘገበው ዕድገት ላይ በመንተራስ የዓመቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በአማካይ በ6 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት እንደሚኖረው የሚጠበቅ ሲሆን፥ ይኽ ዕድገት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ጭማሬ አለው። ለዚህ ዕድገት መመዝገብ በዋነኝነት በግብርናው ዘርፍ በተለይም በሰብል ምርት ላይ የታየው እመርታ ተጠቃሸ ነው።
የመኸር ምርት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የበጋ ስንዴን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ርብርብ መደረጉን ተከትሎ 613 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከ25 ሚልዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል።
ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ ቀስ በቀስ እያገገመ የሚገኘው የአገልገሎት ዘርፉ ላይ ተስፋ ሰጪ ዕድገት እየታየ ነው። በተመሳሳይ መጠነኛ የዕድገት መቀነስ የተመዘገበበት የኢንዱስትሪው ዘርፍ እንደገና እንዲያንሠራራ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ይገኛል። በጦርነቱ ተቀዛቅዞ የቆየውን የሀገር ውስጥና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ድርሻ ለማሳደግ የተደረጉ ርብርቦች ውጤት ማምጣት ጀምረዋል።
ከኢንቨስትመንት ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያላቸው የብድርና ቁጠባ መጠንም ላይ ጭማሪዎች የተመዘገቡበት ወቅት ነበር፡፡ የባንኮች አጠቃላይ የቁጠባ መጠን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ25 በመቶ በማደግ 1 ነጥብ 6 ትሪልዮን ብር ደርሷል፤ ይህም ከፍተኛ ብድርን ለግሉ ዘርፍ ማቅረብ እንድንችል አድርጎናል።
ከውጭ ንግድ 2 ነጥብ 95 ቢሊየን ዶላር የተገኘ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 05 ቢሊየን ዶላር በሆነ ድርሻ አሁንም ግብርናው የወጪ ንግዱ የጀርባ አጥንት ሆኖ ቀጥሏል። ከግብርናው በመቀጠል የማዕድን ዘርፉ 453 ሚልዮን ዶላር እና አምራች ኢንደስትሪው በ378 ነጥብ 5 ሚልዮን ዶላር ገቢ የተገኘባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡
የዘጠኝ ወራቱ ውጭ ምንዛሬ ግኝቱ ከእቅዳችን አንጻር በመጠኑ ዝቅ ያለ ቢሆንም አገራችን ላይ ካጋጠሙ ችግሮች አንጻር እና ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ጭማሬ የታየበት መሆኑ አይካድም፡፡ ምንም እንኳን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ፍላጎት ቢኖርም በበጀት ዓመቱ የሚጠበቅብንን የውጭ ዕዳ ክፍያ በአግባቡ ለመክፈል ችለናል።
በየጊዜው እያደገ የመጣውን የሥራ አጥነት ለመቀነስ የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተነድፈው ሲሰራባቸው የቆዩ ሲሆን፣ ባለፉት 9 ወራት ውስጥ 1.4 ሚልዮን ገደማ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። ከዚህ ውስጥ የሀገር ውስጥ የተፈጠረው የሥራ ዕድል ሰፊውን ቁጥር ቢሸፍንም፣ ሞያዊ ሥልጠና ወስደው በውጭ ሀገራት ማለትም በኳታር፣ በዮርዳኖስና በተባበሩት የዓረብ ኤምሬቶች የሥራ እድል የተመቻቸላቸው ዜጎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።
ውድ ኢትዮጵያውያን፣
አሁንም በኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ፈተና እየገጠመን ያለው ከዋጋ ግሽበት ጋር በተገናኘ ሲሆን፥ ከአምናው የሚያዚያ ወር ጋር ሲነጻጸር የዋጋ ግሽበቱ 36 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል። ነገሩን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየተመዘገበ ያለው የምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ መሆኑ ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አሐዝ ለማውረድ በርካታ ርምጃዎች የተወሰዱ ቢሆንም በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ምክንያት ጥረታችን በቂ ውጤት ሳያመጣ ቀርቷል፡፡
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ያጋጠሙ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የጥሬ ዕቃዎች መናር፣ በአገራችን ያጋጠሙ ግጭቶች እና በቅርብ ወራት ደግሞ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የፈጠረው ዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት የሀገራችንን የዋጋ ግሽበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያሻቅብ ምክንያት ከሆኑት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በመንግሥት በኩል አሁንም የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት የተለያዩ ርምጃዎችን ከመውሰድ አልተቆጠበም። የስንዴ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው። በርካታ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል። ተጨባጭ ተግባራትና አስተዳደራዊ ርምጃዎችም እየተወሰዱ ናቸው።
ያልተመጣጠነውን የመንግሥት ገቢና የወጪ ለማስተካከል በቀጣይ የመንግስት ወጪን ከሀገር ውስጥ ገቢ በተገቢው መልኩ ለመሸፈን፣ የታክስ ሥርዓቱን ማዘመን እና በሂደት ላይ ያሉትን እንደ ንብረት ታክስ፣ የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻዎያችን በአፋጣኝ ወደ ሥራ ማስገባት ያስፈልጋል።
የተጨማሪ ዕሴት ታክስ ሕጉን ለማሻሻልም እየተሠራ ይገኛል። ከወጪ አንፃር መከናወን የሌለባቸውን ፕሮጀክቶች ሀብት ሳይባክን ወደ ቀጣይ ሂደት እንዳያልፉ በማድረግና ፕሮጀክቶችን ቅደም ተከተል በማስያዝ፣ መሸጋገር የሚችሉትን ወደሚቀጥለው ጊዜ በማሸጋገር ወጪን ለመቀነስ ጥረት ተደርጓል።
በቀጣይ ጊዜያት በኢኮኖሚያችን ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ጫናዎችን ለመቀነስ የተለያዩ አንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ።
መሠረታዊነታቸው የታመነባቸው እንደ ስንዴ፣ ዘይት፣ የሕጻናት ምግብ እና ስኳር የመሳሰሉ የፍጆታ ዕቃዎች አስመጪዎች በፍራንኮ ቫሉታ አሠራር የራሳቸውን የውጭ ምንዛሪ በመጠቀም እንዲያስገቡ ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል። የመድኃኒት፣ ነዳጅ፣ ማዳበርያ፣ ዘይት፣ እና ሌሎችም መሠረታዊ ሸቀጦች ግዥን በተገቢው ሁኔታ እንዲካሄድ፣ በእነዚህ ሸቀጦች አቅርቦት ላይ መንዛዛት እንዳይኖር በግዥ ሥርዓቱ ላይ አስፈላጊው ማስተካከያ ይወሰዳል።
ከዚህ በተጫማሪ ከአንዳንድ አስመጭዎች ጋር በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል በተደረገ ውል አሁን ላይ መክፍል ሳያስፈልግ በ“deferred letter of credit” አማካይነት እንደ ዘይት፣ ስንዴ እና ስኳር ያሉ መሠረታዊ ዕቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡቡት ሁኔታ እየተመቻቸ ይገኛል።
ነዳጅን በተመለከተ የዋጋ ንረቱን ተከትሎ የሚኖርውን የበጀት ጫና መቀነስ ይቻል ዘንድ፣ ወጥ ከሆነው የመንግሥት የነዳጅ ድጎማ ቀስ በቀስ በመውጣት በተጠና መንገድ ድጎማው ለሚያስፈልጋቸው አካላት ብቻ እንዲሆን በዕቅድ እየተሠራ ነው።
በበጋ ስንዴ ምርት ላይ የታየውን አበረታች ውጤት በማጎልበት፣ የስንዴ ምርትን መሉ በመሉ ከውጪ ማስገባት ለማስቀረት የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን የምርቱ መጨመር በራሱ ገበያውን ለማረጋጋት ጉልህ ሚና አንደሚኖረው ይጠበቃል። ይህ ክሥተት የራሳችንን ውስጣዊ ዐቅም በደንብ እንድንፈትሽ ዕድል በመፍጠሩ ክሥተቱን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በዘላቂነት በመሠረታዊ ሸቀጦች ራስን ለመቻል በምንወስዳቸው ርምጃዎች እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ርብርብ ሊያደርግ ይገባል፡፡
ጥረታችን ኢኮኖሚው ተግዳሮቶችን ከመቋቋም አልፎ ተግዳሮቶችን ወደማሸነፍ የሚያሸጋግር መሆን አለበት። መንግሥት፣ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ፣ ምሁራንና ሕዝቡ፣ ኹሉም የየድርሻቸውን መወጣት ከቻለ በእርግጥም ጥረታችን ፍሬ ማፍራቱ አይቀርም። በእስካሁኑ ጉዞአችን የገጠሙን ፈተናዎች ጥንካሬአችንን የተገዳደሩ ቢሆኑም በቀላሉ ስላልወደቅን አጠንክረውን አልፈዋል፡፡ ፈተናዎቻችንን በጽናት ተቋቁመን ባለፍን ቁጥር አንድ ደረጃ ወደ ላይ ከፍ ማለታችን አይቀርም፤ የምናስመዘግባቸው ድሎች በሚፈጥሩልን ወኔ ተበረታትተን አሻግረን የብልጽግና ተስፋችንን እንደምናይ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ተስፋችን ተሳክቶ ለትውልዱ የበለጸገች ኢትዮጵያን ማውረስ እንድንችል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ትብብር እንዲያደርግ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
የብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት
ግንቦት 2፣ 2014
አዲስ አበባ
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here