አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል – በፋሽን

Views: 505

ዓለም በተለያየ ጊዜ ከባድ የሚባሉ ወረርሽኞችን ያስተናገደች ሲሆን፣ በቶሎ መከላከያውን ባለማግኘት እንዲሁም በፍጥነት መድኃኒቱን ለማድረስ ባለመቻል ብዙ ሰዎችን ተነጥቃለች። እንዲህ ያለ ክስተት በ19ኛው ወይም በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ብቻ የሆነ አይደለም፣ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን፣ ዓለም በሁሉም ዘርፍ ዳር ላይ ደርሻለሁ ባለችበት ጊዜም ሆኖ ታይቷል/ እየታየም ነው።

እንዲህ አድርጎ የዓለምን አቅምና ደረጃዋን ያሳያት የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ነው። ከኃያላኑ አገራት ደሃ እስከተባሉት ድረስ ሁሉን በእኩል ሚዛን አስቀምጦ አሳይቷል። ታድያ ቫይረሱን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመቀነስ ለጊዜው ያለው አማራጭ ንጽህናን እንዲሁም ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎች መጠቀም ብቻ ነው።

አዲስ ማለዳ ትኩረቷን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ላይ አድርጋለች። የዚህ ጭንብል አጠቃቀም በወረርሽኙ መጀመሪያ ሰሞን ለጤና ባለሞያዎች ብቻ የሚመከር ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ በኋላ ግን ሰዎች በበዙበት አካባቢና ለመራቅ አማራጭ በማይገኝበት ጊዜ መጠቀም የግድ እንደሆነ ተባለ።

ይህንንም ተከትሎ ሰዎች ለአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ያላቸው ፍላጎት ሲጨምር በተለያየ አቅጣጫም ምርቱን በተለያየ ዋጋ የሚያቀርቡ በሌላው ዘርፍ የቀዘቀዘውን ንግድ ሞቅ አደረጉት። አልፎም መሸፈኛዎቹ በዲዛይንና በተለያየ መልክ ተሠርተው ቀረቡ። ይህም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አገራትም የታየ ነው።

የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ታሪክ
የአፍና የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም የተዋወቁት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ነበር። ጆን ስፑነር የተባለ ሰው ‹History of Surgical Face Masks: The myths, the masks, and the men and women behind them› በሚል ርዕስ ከጻፈው መጽሐፍ አገኘሁት ያለውን ኒውዮርክ ታይምስ በአንድ ዘገባው አጣቅሷል። በዚህም ጭንብሉን የጤና ባለሞያዎች የቀዶ ጥገና ሕክምና በሚሰጡ ጊዜ ነው መጀመሪያ የተጠቀሙበት። ይህም ቀጥሎ በ1910 በቻይናውያን ተወርሶ በወቅቱ የነበረውን በትንፋሽ የሚተላለፍ በሽታ ለመቆጣጠር ረድቷቸዋል።

ያኔም አፍና አፍንጫ መሸፈኛው ከዛሬ ይልቅ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን፣ በስዕሎች ሳይቀር ጭንብሉን ያደረጉ ሰዎች ምስል እየተለመደ መጣ። ይሁንና የማስክ አጠቃቀም ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ በእጅጉ ቀንሶ ታይቷል። በእስያ ይልቁንም በቻይና ግን የጭንብሉ ዝነኝነትና ተቀባይነት ቀጠለ። በነዛ አገራትም ጭንብሎችን ማድረግ ለማኅበረሰብ የመጨነቅና እንደዜጋ ማስተዋል ያለው ሰው የመሆን ምሳሌ ወይም መገለጫ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።

ያም ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ሀብት መመናመን ግንዛቤ ውስጥ የገባ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአየር ብክለት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በዚህም ጭንብሎች የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል። በተለይም በካይ ጭስ ባለባቸው እንዲሁም እንደ ሰደድ እሳት ያለ የተፈጥሮ አደጋ በሚያስቸግራቸው፣ ብዙ ሕዝብም በሚንቀሳቀስባቸው ስፍራዎችም ሁሉ፣ ጭንብል መጠቀም የተለመደ ሆነ። ታድያ በቻይና እና እስያ ይህ ባህል የተለመደ ይሆን እንጂ፣ በቀረው ዓለም ልምዱ አነስተኛ ነበር።

ከፋሽን ጋር ያለውን ነጥብ ስንቃኝ ደግሞ፣ በአሜሪካ እንዲህ ሆነ። አይሊዮ እና ማቲዮ የተባሉ የሂፖፕ አቀንቃኞች፣ ሙዚቃ ሲጫወቱ እንዲሁም ውዝዋዜ ሲያቀርቡ በሚያሳዩት የፊት ገጽታቸው ሰዎች እየቀለዱባቸው መቸገራቸውን የሙዚቃና ፊልም ሰንጠረዥን ለሚቆጣጠረው ቢልቦርድ አሳወቁ። እባም መፍትሔ ይሆናል ያሉት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን መጠቀም ጀመሩ። ይሁንና ለዚህ ዓላማ የጀመሩት የፊት ጭምብል መታወቂያ ምልክታቸው ሆኖ ቀረ።

ይህንንም በተለያየ መልክና አሠራር እንዲሁም ቀለም አስተዋወቁት። እንደ እነርሱ ሁሉ በተመሳሳይ ጭንብልን በፋሽን መልክ የሚጠቀሙ ጥቂት አልነበሩም። ባለፉት ሦስት ዓመታትም በተለያየ ዲዛይን እና ፋሽን የተሠሩ ጭንብሎች ተዋውቀዋል። በፋሽን ማሳያ መድረኮች ላይ ሳይቀር ጭንብሎች ተደርገው ለእይታ ይቀርቡ ነበር።

ይኸው ጭንብል ከፋሽን ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካም ጋር ተዛምዷል። ኒውዮርክ ታይምስ አስታውሶ እንደዘገበው፣ በቻይናዋ ሆንግ ኮንግ ጥቁር ጭንብል በማጥለቅ የፖለቲካ አቋምና ተቃውሞም ተገልጧል። ይህም ጭንብሎችን የተቃውሞ ተምሳሌት እያደረገ ነው በሚል የቻይና መንግሥት ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን እንዳያደርጉ ለማገድ ጥረት ሁሉ አድርጓል። ነገር ግን በእስያ ጭንብሎች ከሕዝቡ ጋር ፍጹም የተዋሐዱ ስለነበሩ አልሆነም።

የማስክ ጥቅም
ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ በያዛቸው ሰዎች ላይ ምልክቶችን ማሳየት የሚጀምረው ቢያንስ በ14 ቀናት ውስጥ ነው። ይሁንና ጥቂት በማይባል ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ምልክቱ ላይታይ ይችላል፣ እንደ ሕክምና ባለሞያዎች አገላለጽ። እናም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል የማድረግ ጥቅምም በዚህ አጋጣሚ እንደሆነ ያስረዳሉ።

ያም ብቻ አይደለም። በአውሮፓውያን አቆጣጠር መጋቢት 24 ወይም ከወር ገደማ በፊት ነበር፣ ወሳኝ የሆኑና ለጤና ባለሞያዎች የሚውሉ ጭንብሎች እጥረት እንዳለ በይፋ የታወቀው። ይህንንም ተከትሎ ለሕክምና ባለሞያዎች የሚሆኑትን ጭንብሎች ማኅበረሰቡ እንዳይጠቀምና አካላዊ ርቀትን አማራጭ እንዲያደርግ ሐሳብ ሰጡ። ለዚህም ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም እንዲቻል ከቀረቡ አማራጮች ውስጥ አንደኛው ሰዎች ለየራሳቸው ቤት ውስጥ የተሠራ ማስክን መጠቀም ሲሆን፣ ይህም ስካርፍን ይጨምራል።

የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶክተር ብሩክ ዓለማየሁ ‹የጤና ወግ› በተሰኘ ወቅታዊና አጠቃላይ የጤና ጉዳዮች ላይ የሐኪሞችን መልእክት በሚያስተላልፈው ድረ ገጽ ባሰፈሩት ጽሑፍ ይህን ጉዳይ አብረርተውታል። ምንም እንኳ በወረርሽኙ የመጀመሪያ ሰሞን ጤነኛ ሰው ጭንብል እንዲያደረግ ባይመከርም፣ እያደረግ ግርታ ተፈጥሯል ብለዋል። ነገር ግን እንደተባለው ቫይረሱ ራሱን የሚደብቅና ምልክቶችን በቶሎ የማያሳይ ሰው ስለሚኖር፣ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ፣ ጭንብሉን ካለማድረግ ማድረግ የተሻለ እንደሆነ ተነግሯል።

ታድያ ጭንብሉን በማድረግ ጊዜ ቀድሞ ከሚደረገው ንጽህናን የሚመለከት ጥንቃቄ ጎን ለጎን፣ ጭንብሉ ያልተቀደደ ወይም ያልተበሳ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ እንዲሁም አፍና አፍንጫን በሚገባና በደንብ መሸፈኑ መዘንጋት እንደሌለበት ተጠቅሷል። ሰውን ለማናገር ዝቅ የሚደረግ ከሆነ ታድያ ምንም ዋጋ የለውም ይላሉ።

ጭንብሎች ግን የተለያዩ ዓይነት ናቸው። ብሩክ እንደገለጹት ደግሞ ኹለት የጭንብል አይነቶች በዋናነት በዚህ ጊዜ ይነሳሉ። እነዚህም ‹ሰርጂካል ማስክ› እና N95 የሚል ሥያሜ ያላቸው የጭንብል ዓይነቶች ናቸው። ሰርጂካል የሚባለው ከአድራጊው ሰው የሚወጡ ፈሳሾችን ወይም ቅንጣቶችን ለመከላከል ሲሆን፣ በአየር ላይ የሚንሳፈፉ ቅንጣቶችንም ለማጣራት ይጠቅማል። ይህም ታድያ በተመሳሳይ ልኬት የሚመጣና ከአገጭ ጀምሮ እስከ አፍንጫ ድረስ ልክክ የሚል እንደሆነ አስፍረወል።

ሌላውና N95 የሚባለው የጭንብል ዓጥነት ደግሞ በጤና ባለሞያ ብቻ የሚደረግ ነው። ይህም በመጠን ከፍ ካሉ ቅንጣቶች በተጨማሪ ደቃቅ የሆኑትን ቫይረሶች ጨምሮ ትንንሾቹን የማጣራት አቅም ያለው ነው።በአየር የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል እንደሚጠቅምም ባለሞያው ያስረዳሉ።

ታድያ በዚህ መካከል ደግሞ ቤት ውስጥ የሚሠራ ወይም በባለሙያ የሚዘጋጅ ጭንብል አለ። ይህም እንዲዘጋጅ ያስፈለገው በተከሰተው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እጥረት ምክንያት ነው። ይህንንም ለመቅረፍ፣ እንደተባለው ያለምንም ከመሆን ማድረግ ተመራጭ ስለሆነ፣ ቤት ውስጥ በጨርቅ የተሰፉ ጭንብሎችን መጠቀም የሚል አማራጭ ቀርቧል። ይህን ታድያ ማኅበረሰቡ አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ ፈጽሞ በማያስችል አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ እንዲጠቀምባቸው እንጂ፣ የጤና ባለሞያዎች እንዳይጠቀሙ ይመከራል ብለዋል። ደግሞም የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ተከታትለው እንደዘገቡት፣ ቤት ውስጥ የሚሠራን ጭንብል በሆስፒታልና ሰው በበዛበት ጥቅም ላይ ይዋል አይዋል የሚለው ብዙ አከራክሯል።

የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማእከል ሲዲሲ እነዚህን ጭንብሎች መጠቀም የማኅበረሰብ ደኅንነትን ለመጠበቅ በፈቃደኝነት የሚደረግ የጤና መጠበቂያ እርምጃ ነው ብሏል። በሕክምና ተቋማት ውስጥ አይሁን እንጂ በቤት ውስጥ ባሉ ጨርቆች የተሠሩትን የፊትና የአፍ መሸፈኛ ማስኮች ተጠቀሙ ሲሉም ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በተመሳሳይ አሳስበዋል።

ፋሽን በጭንብል
በዓለማችን ዝነኛ የተባሉ የንግድ ምልክት ወይም ብራንድ ያላቸው ልብስ አምራች የተባሉ እንደ ጉቺ፣ ፕራዳ ብሩክስ ብራዘርስ የመሳሰሉት ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራች ፋብሪካቸው በተወሰነ ደረጃ ጭንብሎችን እና ለሐኪሞች በሆስፒታል ውስጥ የሚያገለግሉ ጋውኖችን እንደሚያመርቱ ይፋ አድርገዋል። ይህን የዘገበው ኒውዮርክ ታይምስ፣ እንደውም ይህን ተከትለው ጭንብሎች በዓለም ዐቀፍ ደረጃ መፈለጋቸው አይቀርምና እነዚህ ብራንዳቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ አምራቾች የፋሽን ሥራቸውን በጭንብል ላይ ሳይገልጡ አይቀርም ሲል አስነብቧል።

ፎርብስ በተመሳሳይ በዚህ ጉዳይ ላይ ባስነበበው ዘገባ፣ ቀድሞ ዘናጭ ቦርሳና ቁሳቁሶችን ያቀርቡ የነበሩ አምራቾች አሁን በአካል ባይሆንም በኦንላይን ገበያውን በጭንብል ሽያጭ ሳይቆጣጠሩት አይቀሩም ብሏል። ይህም ታድያ እንደው ለገበያ ብቻ ሳይሆን፣ ለሕክምና ተቋማት በልገሳ የተሰጠው የሚበዛ ነው። አንዳንዶቹ ‹በዚህ ጊዜ እነዚህን አስፈላጊ ጭንብሎች መሸጥ አግባብ አይደለም› ብለው፣ አቅም ለሌላቸው ሁሉ ሲያድሉ አቅም ያላቸው ደግሞ የሚገዙበትን አጋጣሚዎች ፈጥረዋል።

ማህሌት አፈወርቅ (ማፊ) አሁን ላይ ጭንብሎችን እየሠሩ ካሉ ዲዛይነሮች መካከል ናት። ‹ማፊ-ማፊ› የተሰኘ ብራንድ ያላት ሲሆን፣ ይህም በ2011 ሥራውን የጀመረ ነው። ማሕሌት ‹ፋሽኖሚክስ› ከተባለውና በአፍሪካ በፋሽን ዙሪያ ባሉ እንቅስቃሴዎች ላይ መረጃዎችን ከሚያቀብለው አውታር ጋር ቆይታ አድርጋለች። በዛም ላይ በሙያዋና በምትወደው የፋሽን ሥራ ሰዎችን ማገለግል የሚሰጣትን ደስታ ጠቅሳለች። ግንዛቤ ከመፍጠር ጎን ለጎን ቫይረሱን በሚመለከት ጥቃቄዎችን ማድረግ ተገቢ ነውና፣ ከዚህም መካከል ሰው በበዛበት የጭንብል አስፈላጊነት ግልጽ ስለሆነ፣ ያለው ምርት አነስተኛ ከሆነ ያንን ለማገዝ ነው እየሠራሁ ያለሁት ብላለችም።

መጀመሪያ ምርቶቹን ማምረት የጀመረችበትን ቀን እንዲሁም ገበያው መቼ እንደጨመረ ጥያቄ ቀርቦላት ነበር። እርሷም የሆነውን ስታስታውስ እንዲህ አለች፣ ‹‹የዓለም ጤና ድርጅት ቫይረሱ ለዓለም ስጋት ነው ብሎ ይፋ ሲያደርግ ገበያችን በአንድ ጊዜ ቀዝቅዞ ነበር። ሠራተኞችን ማቆየትና በሥራው መቆየትም አስጨናቂ ሆነብን። ሠራተኛ ወደ መበተንና ወደ መዝጋት ተቃርበንም ነበር። እናም ሚድያውን እከታተል ስለነበር የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ/ጭንብል እጥረት እንዳለ ሲነገር ሰማሁ፣ እናም በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ጭንብሎችን መሥራት ጀመርን› ብላለች።

መጀመሪያ ጥቂት ስታመርት የነበረ ሲሆን፣ ይህም ለድርጅቱ ሠራተኞች፣ ለቤተሰብና ለጓደኛ ብቻ የተረፈ ነበር ትላለች። ይሁንና በቀን እስከ ሦስት ሺሕ ማምረት ቻሉ። ይህም የሆነው ድርጅቶች ጭንብሎች ለሠራተኞቻቸው እንዲቀርብላቸው በማዘዛቸው ነው። መንግሥት የጭንብልን አስፈላጊነት ይፋ በማድረጉና እንዲደረግ በማዘዙም የበለጠ ተፈላጊ እየሆነ በመሄዱ ምርታቸው ጨመረ። የቫይረሱ ስርጭት መጨመሩን ተከትሎም ማሕሌት አንድ ሺሕ ማስኮችን ለበጎ አድራጎት እንደሰጠች ገልጻለች።

ታድያ ጭንብሎቹን ፋሽንን የተከተሉ እንዲሆኑ አድርጎ ማምረትና በውድ ዋጋ ለመሸጥ ሳይሆን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ላይ በማተኮራቸው፣ ጭንብሎቹን በተመሳሳይ መልክ በሚገባው አግባብ እየሠሩ መሆኑን ጠቅሳለች።

ታድያ በተመሳሳይ በተለይም ባህር ማዶ የተለያየ ዲዛይንና ጨርቅን የተጠቀሙ ጭንብሎች ተሠርተው ታይተዋል። በተለይም የአገር ባህል ልብስ የሆኑ ጥለቶችን በመጠቀም እነዚህ አዳዲስ የጭንብል አይነቶች ተዘጋጅተዋል። የፋሽኑ ዘርፍ እንደ አውሮፓውያኑ ስላልሆነ እንዲሁም ጉዳዩ የዝነጣና የፋሽን ሳይሆን የጤና ጉዳይ በመሆኑ፣ ቢቻል በቤት ውስጥ በተገኘ ጨርቅ ሰፍቶ ማዘጋጀቱን እንጂ አሠራርና ውበቱ የሚየስጨንቃቸው ጥቂቶች ሳይሆኑ አይቀሩም።

‹ዘ ከት› የተባለ የፋሽን ዜናዎችን የሚያስነብብ መገናኛ ብዙኀን ታድያ በአንጻሩ በውጪ አገራት በተለይም ዝነኞች በሚበዙባቸው ያለውን ልምድ አንስቷል። በዚህም የፋሽን ተንታኝ እና ዲዛይነር ጄኒ ዋልተን ጭንብሎችን ከአለባበስ ጋር የሚሄዱና በተለያየ ዲዛይን ሠርተው ካቀረቡ መካከል ናት ይላል። ታድያ የሠራቸው ጭንብል ተቀባይነትንም አግኝቷል። እርሷም ታድያ ዓላማዋ ፋሽን ሳይሆን ጤና እና ደኅንነት እንደሆነ ደጋግማ ስትጠቅስ ነበር። አያይዛ ግን የሰዎችን ሐሳብ ማግኘት እንዲሁም ተከታዮቿን ለጥሩ ነገር ለማነቃቃትና የፈጠራ ሥራ እንዲሠሩም ለማነሳሳት ዓልማ እንደሆነ ጠቅሳለች ለ‹ዘ ከት› ጠቅሳለች።

ሺርሊ ራይንስ የ‹Beauty2theStreetz› መሥራች ናት። ድርጅቷ ለትርፍ ያልተቋቋመ ሲሆን በአሜሪካ ሎሳንጀለስ ቤት አልባ ለሆኑ ምግብ፣ መታጠቢያ፣ ጸጉር እጥበት፣ ውበት መጠበቂያና መሰል በማሟላት ያገለግላል። እርሷ ታድያ በወረርሽኙ መጀመሪያ ሰሞን ስትናገር፣ ‹‹በወረርሽኝ መካከል እንደሆንን አውቃለሁ። ብዙ ነገሮቻችንን እንድንቀይርም ይጠበቃል። ያም ቢሆን መልካችንን መቀየር አለብን ብዬ አላስብም።›› አለች።

ዘ ከት ይህን እንዲህ ባለ መንገድ ዘገበው። ‹እንደ ወትሮው ቢሆን ራይነስ ስትመጣ ገና ከርቀት ታስታውቃለች። ልብሷ እና የምትጠቀመው የውበት መጠበቂያ ባለቀለም ቅባት ደማቅ ነው። አሁን ታድያ ጭንብል ማድረግ እንዳለባት ብታውቅምና እሷን እሷ እንዳደረጋት የምታምነው ውበቷን ቢደብቀውም፣ አማራጭ አልነበራትም። በዛም ደስተኛ አልነበረችም።

ታድያ ይህቺ ሴት የልቧ የሞላላት ፔሪ ሜክ ከተባለችው የኤሚ አዋርድ አሸናፊ የአልባሳት ዲዛይነር ነው። የልቧን ያደረሰውም በዛች ዲዛይነር የተሠራው ከመደበኛው ለየት ያለና ፋሽንን የተከተለ ጭንብል ሲሆን፣ ‹አሁንም እንደበፊቱ የተቸገሩትን እየረዳንና አገልግሎት እየሰጠን ነው። ግን ለምን በልዩ መልክና ዘናጭ በሆነ መንገድ ውበት አንሰጠውም ብለን ነው። ራሴን በምፈልገው መንገድ መግለጤ እጅግ ጨለማ በሆነው የሕይወቴ ክፍል ረድቶኛል። አሁንም ምንም ቢፈጠር፣ ያ ነገር የሚለወጥ አይሆንም›› ብላለች፣ መፍትሔ እንዳገኘች የተሰማት ሺርሊ።

ነዋሪነቷ በአዲስ አበባ የሆነ ሔዋን አበራ ለአዲስ ማለዳ በሰጠችው አስተያየት ታድያ ይህን ጉዳይ አንስታለች። ከገበያ ላይ በተመጣጣኝ ዋጋ ጭንብሎችን እንደገዛች አስታውሳ፣ አዳዲስ ፋሽንን መከተል እንደምትወድም ጠቅሳለች። ታድያ አሁንም እንዳይቀርባት የተለያየ ቀለም ያላቸውን ጭንብሎች እንምትጠቀምና በአለባበሷ መሠረት እንደምትቀይርም ትጠቅሳለች።

‹‹አሁን ቅድሚያ የምንሰጠው ለጤናችን ነው። በዚህ ጊዜ ፋሽንን ማሰቡ ቅንጦት የሚመስለው ይኖራል። ግን ካደረግን አይቀርና ለፋሽን ፍቅሩ ካለን፣ አቅማችንም ከፈቀደ የሚያማምሩ ጭንብሎችን በየቤታችን ሰፍተን አልያም የተሠራውን ገዝተን ብናደርግ ችግር የለውም። እንደውም አዲስ መልክ ስለሚፈጥር ተጠቃሚው ሊጨምር ይችላል›› ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com