የማኅበራዊ ሕይወት ምስቅልቅሎሽና ኮቪድ 19

Views: 300

የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ካመሳቀላቸው የሰው ልጅ ምድራዊ ስርዓቶች መካከል ቫይረሱ በማኅበራዊ ሕይወት የሚፈጥረውና የፈጠረው ማኅበራዊ ምስቅልቅሎሽ አንዱና ተጠቃሹ ነው። ይህም በአንድ ጀንበር የሚገለጥ ሳይሆን እያደር የሚታይ ሲሆን፣ ከምጣኔ ሀብት ድቀት ጋርም ዝምድናው የጠነከረ ነው። በተለይም የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል የሚደረጉ ከቤት ያለመውጣትና የእንቅስቃሴ ገደብ መመሪያዎች የብዙዎችን ሕይወት እንዳልነበር አድርገዋል።

አብርሐም ፀሐዬ ይህን ጉዳይ መነሻ በማድረግ በኡጋንዳ ካምፓላ የአንዲትን በወሲብ ንግድ የምትተዳደር ሴት ሕይወት በማሳያነት ያስቃኛሉ። እንዲህ ባለ ቀድሞም በተገለለ ሥራ እንዲሁም ከፍተኛ ድህነት ውስጥ ያሉ ሰዎች ላይ ወረርሽኙ በተለየ የሚያደርሰውን ተጽእኖም ያስረዳሉ።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ የወሲብ ንግዳችን በመቆሙ የረሃብ ስጋት ውስጥ ወድቀናል – ሞሬና (ካምፓላ – ኡጋንዳ)
በ2018 በፊዚዮሎጂና በሜዲሲን ዘርፍ ከጄምስ ፒ. አሊሰን (James P. Allison) ጋር በጥምረት በመሆን የኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ጃፓናዊው ፕሮፌሰር ታሱኩ ሆንጆ (Tasuku Honjo) ስለኮሮና ቫይረስ የተናገሩት መረጃ የዓለምን ትኩረት ስቧል። ‹‹ይህ ኮሮና ቫይረስ ከሌሊት ወፍ መጣ የምትሉትን ቀልድ አቁሙ፤ በጭራሽ በባህሪው ተፈጥሯዊ አይደለም። ሆነ ተብሎ በቤተ ሙከራ የተፈበረከ ነው። ተፈጥሯዊ ቢሆን ኖሮ ቻይና ውስጥ እንደመከሰቱ የሚያስከትለው ጉዳትም እንደ ቻይና ተመሳሳይ የአየር ጸባይ ባላቸው አገራት ላይ ብቻ በተገደበ ነበር። ነገር ግን ከስዊዘርላንድ ጀምሮ እስከ በረሃማ አካባቢ ያሉ የዓለም ሕዝቦችን ሁሉ እያጠቃና እየገደለ የሚገሰግስ ሁሉን ገዳይ ቫይረስ ነው። ይህ ደግሞ የተፈጥሯዊ ቫይረስ ባህሪ ሊሆን አይችልም።›› ብለዋል።

ሐሳባቸውን ሲያጠናክሩ ‹‹በእንስሳትና ቫይረስ ዘርፍ ከአርባ በላይ ዓመታትን በተመራማሪነት ሠርቻለሁ። በቻይና ዉሃን ግዛት ባለው የምርምር ጣቢያም ለአራት ዓመታት አገልግያለሁ። በዚያ ተቋም ያሉትን ባለሙያዎች ስለማውቃቸው የቫይረሱ ወረረሽኝ ከተከሰተ በኋላ በስልክ ለማግኘት ስደውልላቸው የሁሉም ስልክ ከአገልግሎት ውጪ ሆኗል። ይህ ግጥምጥሞሽ ሳይሆን ቴክኒሻኖቹ እንደሞቱ ያመላክታል” ብለዋል።

ፕሮፌሰር ታሱኩ ‹ሰው ሠራሽ ቫይረስ ስለመሆኑ የተናገርኩት ውሸት ከሆነ ከምላሴ ጸጉር ይብቀል። በሕይወትም አልፌ ቢሆን እንኳን የሰጣችሁኝን የኖቤል ሽልማት አንሱት› ብለው ቫይረሱ የቻይና ሰው ሠራሽ ውጤት መሆኑን እንዲያምኗቸው አበክረው ተናግረዋል ።

ኮሮና ቫይረስ የዓለምን መልክ ቀይሯል። ከቀድሞ በባሰ አለመተማመኑን አጉልቶታል። ፊታውራሪው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕም ኮሮና ቫይረስ ከማለት ይልቅ የ’ቻይና ቫይረስ’ እስከማለት ደርሰዋል። ከዓለም ጤና ጥበቃው አለቃ ከቴዎድሮስ አድኃኖም (ዶ/ር) ጋር የነበረው ውዝግብም በይፋ ሆነ ውስጥ ውስጡን አልበረደም። በተለይም ቴዎድሮስ ‹በጥቁርነቴ ‘ኔግሮ’ ተብዬ እስከመሰደብና የግድያ ዛቻ ሁሉ ተደርጎብኛል።› ብለው ይፋዊ መግለጫ ከሰጡ በኋላ፣ የጥቁሮችን እና የነጮችን ልሂቃን ለኹለት የከፈለ ሆኖ ታይቷል። ነገሩ ከጤና እና ሰብዓዊ ጉዳይነቱ ባሻገር የፖለቲካ አጀንዳ ማራገቢያ ወደመሆንም ተሸጋገሯል።

ቤጂንግም ለጉዳዩ አጸፋዊ ምላሽ እየሰጠች በዛውም ቫይረሱን ስለመቆጣጠሯ እየገለጸች ብትገኝም፣ ኮሮና ቫይረስ ግን ያለማንም ከልካይ በየቀኑ የመግደያ ሰይፉን ወደአፎቱ ሳይመልስ አራት ወራትን አስቆጥሯል። ሚሊዮኖችን በማጥቃት ከኹለት መቶ ሺሕ በላይ ንጹሀንን ቀጥፎ አሁንም እየገሠገሠ ነው።
ኮቪድ 19 የበለጸጉ አገራትን የጤና ስርዓት ጉድለት አጋልጧል። ኃያሏ አሜሪካ እንደምጣኔ ሀብቱና ፖለቲካው በአዎንታዊ መልኩ ሳይሆን በተቃራኒው መንገድ ዜጎቿን በሞት መዝገብ በማስፈር ግንባር ቀደም ሆናለች። በአጠቃላይ ዓለም ልኳን አውቃለች። ገዳዩ ቫይረስ ሆን ተብሎ ተፈጥሯል ቢባልም ለዚህ ዓይነት ሰው ጨራሽ ክስተት ዓለማችን ለጊዜውም ቢሆን እጇን የሰጠች ይመስላል። የረቀቁ ቴክኖሎጂዎቿና የሳይንስ ምርምሮቿ አላስጣሏትም። በጎን ደሞ የክትባት/የመድኃኒት ግኝት ላይ ለመድረስ ፉክክሩ ተጧጡፏል።

የምጣኔ ሀብት ቀውስ
በኹለቱ የዓለም ጦርነቶች ማግስት እንደተከሰተው ሁሉ የምጣኔ ሀብት ቀውሱ ከበሽታው በላይ አስጊ እየሆነ ይመስላል። የዚህ የሦስተኛ የዓለም ጦርነት የሚመስለው ዝምተኛው የቫይረስ ቀውስ ትሪሊዮን ዶላሮችን አስወጥቷል ወይም አክስሯል። ከፍተኛ የነፍስ ዋጋ እየተከፈለበትም ነው። ምንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆንም ሀብት ያላቸው አገራት ከተማቸውን ዘግተውና ሕዝባቸውን በቤት ሸሽገው የቫይረሱን ቀውስ ለማለፍ እየሞከሩ ነው።

የአሜሪካ የነዳጅ ገበያ ከዜሮ በታች ወርዷል። ከሰማንያ በመቶ በላይ የዓለም አገራት የተባበሩት መንግሥታትን ገንዘብ ስጠን ብለውታል። የቱሪዝም ኢንዱስትሪዎች ቆመዋል፣ የሁሉም ዘርፍ ትራንስፖርት ተገትቷል። በአሜሪካ ወደ 26 ሚሊዮን ሕዝብ በአንድ ወር ተኩል ውስጥ ሥራ ዕጥ ሆኗል። ወደሥራችን እንመለስ የሚሉ የግፊት ጥያቄዎች እየበረቱ ነው።

የአገራችን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ተቋም ጥናት እንዳመለከተው ደግሞ የዘንድሮ ዕድገታችን ከሦስት በመቶ እንደማይበልጥ ነግሮናል። ብዙ አገራት ዘግቶ የመቀመጥን ሕግ ተግብረው ለዜጎቻቸው ሕይወት ቅድሚያ ሰጥተዋል። የምጣኔ ሀብቱ ቀውስ ግን በጎን ሌላ በሽታ ሆኖ እየመጣ ነው።

አፍሪካና ‘ሎክ ዳውን’
የአፍሪካን ምጣኔ ሀብት በአንዲት ሴት መነጽር እንመልከተው። ከሳምንታት በፊት ሮይተርስ ባስነበበው መረጃ በኡጋንዳ ካምፓላ በወሲብ ንግድ የተሰማራችን ሴት ሕይወት ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር አያይዞ ገልጾት ነበር። ጽሑፉ ‘Who is going to stand up for us?’ ‹ለእኛስ ማን ይደርስልናል?› በማለት በወሲብ ንግድ ውስጥ ያለችውን ሴት ንግግር በርዕስነት መርጦታል። አና ትዌት ሞሬና (Anna Xwexx Morena) ትባላለች።
እንደሚታወቀው ካምፓላ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ዜጎችንና ተቋማትን ከእንቅስቃሴ የሚገድብ ሕግ አውጥታ ነበር። ሞሬና ይህ ችግር ያስከተለባትን የሕይወት ምስቅልቅል ለጠየቃት ጋዜጠኛ ገልጻለታለች።

‹‹ነገና ከዚያ ቀጥለው ባሉት ቀናት ሌላው ቀርቶ ምን እንደምበላ እንኳን እርግጠኛ አይደለሁም። መንግሥት ያወጣውን አዋጅ ተከትሎ፣ የወሲብ ደንበኞቻችን የነበሩት ከኛ ጋር መገናኘቱን እያቋረጡ መጥተዋል። ይህ ደግሞ ለኑሯችን ትልቅ ፈተና ሆኗል።›› ብላለች።

መንግሥት የሰዎችን የእንቅስቃሴ ለሳምንት ያህል በዘጋበትና ገደብ በጣለበት ወቅት የተጠየቀችው ሞሬና፣ ይህ ሕግ ምናልባትም ለወር ከዘለቀ እንደሷ በተመሳሳይ ሥራ ላይ የተሰማሩና የእርሷን ዓይነት ሕይወትና ኑሮ እየገፉ ያሉ ሰዎች ዕጣ ፈንታ በረሃብ መሞት እንደሆነ አስረድታለች። በተለይም የማኅበራዊ መገለል የደረሰባቸውና ራሳቸውን በተለያየ የኑሮ ጥላ ውስጥ ለደበቁ ሰዎች እንዲሁ በእለት ከእለት ገቢ የሚተዳደሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ኮሮና ቫይረስ ሌላ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል።

የካምፓላዋን ሴት ሁኔታ ወደአገራችን ብንመልሰው ኑሮን ለማሸነፍ ከቤተሰባቸውና ከሚያውቃቸው ሰው ርቀው በተለያየ የገቢ ምንጭ የተሰማሩ ወገኖቻችን አሉ። በየጊዜው አሃዙ እየጨመረ ያለው የልመና፣ የጎዳና እና የወሲብ ንግድ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ነዋሪዎችን ካየን፣ የምጣኔ ሀብትን እያሽመደመደ ከመጣው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ውጤቱ በልተው ማደር እስከማይችሉ ድረስ አደጋው በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ መገመት ይቻላል።

አንድ ሰበዝ መዘን ብናይ እንኳን ሆቴሎች ሥራቸው እየቀነሰ በመጣ ቁጥር ተረፈ ምግቡን የሚጠቀሙት የጎዳና ሕይወት ላይ ያሉ ወገኖቻችን የቀናትን ዕድሜ በማይሰጠው ረሃብ መጎዳታቸውን ለማሰብ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው። መደበኛው የምጣኔ ሀብት ቀመራችን እምብዛም ትኩረት የማይሰጠው የተሳሰረ አኗኗራችን ብዙዎችን በስሩ ያቀፈ ነው። ከቫይረሱ የሞት ስጋት ይልቅ የረሃብ ስጋቱ ሊገዝፍ ይችላል። ይህንኑ ስጋት ተከትሎ የሚመጣው ምስቅልቅል ከባድ ስለመሆኑ ባለሙያዎች ከአሁኑ ግምታቸውን እያስቀመጡ ነው።

በኹለት አሃዝ አደገ ተብሎም የእያንዳንዱን ጓዳ መሙላት ያልቻለው ምጣኔ ሀብታችን እስከ 2.3 እንደሚወርድ ተነግሯል። እዚህ ላይ ከወዲሁ ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለና እንደሚጠይቅ ማመላከቻ ነው። ችግራችን የዋዛ አይደለም። ይህንኑ ማስረገጫ የሚነግረን የረሃብ ስጋት ካለባቸው ጥቂት የዓለም ሀገራት ተርታ መቀመጣችን ነው።

የየዕለት ኑሮ በስጋት ውስጥ
ወደ ጀመርነው የኡጋንዳዋ ካምፓላ ስንመለስ በወሲብ ንግድ ውስጥ ያለችው የሞሬና ስጋት ጥሩ ማሳያ ይሆናል። ዕድገቷን ጨረፍ አድርገን እንለፍ። ገና ስትወለድ ወንድ እንደነበረችና በሂደት ግን እንግዳ የሆነ የጾታ፣ ሥነ ባህሪና የስርዓተ – ጾታ ምስቅልቅል በራሷ ላይ ተመለከተች። እናቷን በሕጻንነቷ አጥታ ከእንጀራ እናቷና ወላጅ አባቷ ጋር ለመኖር የተገደደችው ሞሬና ለጓደኞቿ ሁኔታውን ብትነግራቸውም እንኳን ሊረዷት እንዳልቻሉ ትናገራለች።
በመጨረሻም በተለያዩ የጾታዊ፣ የስርዓተ ጾታ ጉዳዮች ላይ የሚሠራ ተቋም ጋር በመሄድ ያለባትን የጾታ መፋለስ ለማወቅ ችላለች። ቤተሰቦቿ ግን ይህንን ከሰሙበት ዕለት ጀምሮ በማግለላቸው የተነሳ እሷም ሴትነቷን መርጣ በመሰል ሕይወት ውስጥ ካሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር የወሲብ ንግዱ ጎራ ውስጥ ተቀላቅላለች።

ይህ ሕይወቷ በኮሮና ቫይረስም ሰለባ ከመሆን አልዳነም። ስለካምፓላ የእንቅስቃሴ ገደብና የገቢ ምንጯ መድረቅ ስታብራራ ‹‹የሕክምና ማእከላት ሥራቸው በመስተጓጎሉ በሆስፒታል ውስጥ የማገኘውን የኤች አይቪ ኤድስ ክትትል እንኳን ማግኘት አልቻልኩም፤ ገቢዬ ቆሟል። ሥራ ባለኝ ጊዜ በወር እስከ 160 ሺሕ ሽልንግ (42 ዶላር) አገኝ ነበር። ከዚህ ላይ 130 ሺሕ ለቤት ኪራይ፣ የተረፈውን ደሞ ለሌሎች ወጪዎች አብቃቃ ነበር። ይህ የእንቅስቃሴ ገደብ ሕግ ለአንድ ወር እየገፋ ከሄደ የመኖር ህልውናዬ አደጋ ውስጥ ነው›› ስትል ገልጻለች።

የሸቀጥ ዋጋ ጭማሬና የደኅንነት ጉዳይ
ከኮሮና ጋር ተያይዞ የኑሮ ውድነቱን የተናገረችው ሞሬና ካምፓላ ላይ ያለውን የሸቀጥ ዋጋ ስትገልጽ ከዚህ በፊት አንድ ኪሎ ስኳርን በ4500 ሽልንግ ትገዛ እንደነበርና አሁን ላይ ግን የሃምሳ በመቶ ጭማሪ አሳይቶ 6500 ሽልንግ ስለመድረሱ ተናግራለች። ‹‹በጥቅሉ በፈጣሪ ዕርዳታ እስከ አሁኗ ቀን ያለችውን ኑሮዬን እየገፋሁ ነው። ነገ ላይ ግን እንጃ…›› በማለት የመነመነ ተስፋዋን ለጋዜጠኛው አጋርታዋለች።

ተጨማሪ ስጋቷን ስትገልጽም ‹‹እኛ እንድንወጣ ቢፈቀድልን እንኳን የተገለልን የማኅበረሰብ ክፍል ከመሆናችን ጋር ተያይዞ ሊያጠቁን የሚችሉ ቡድኖች ይኖራሉ።›› ብላለች። መንግሥት ደግሞ ወረርሽኙ ላይ እንጂ ተያያዥ ጉዳዮችን ትኩረት ሊሰጥ አይችልም የሚል ፍራቻ አላት። የተለያዩ ምሁራን በአንድም ይሁን በሌላ ከዚህ ጋር ተመሣሣይነት ያላቸው የማኅበረሰብ ቀውሶች ይፈጠራሉ ባይ ናቸው። እንደዝርፊያና ከፍ ያሉ የውንብድና ችግሮች የምጣኔ ሀብት ቀውሱ የሚወልዳቸው ስጋቶች እንደሚሆኑም ከወዲሁ እየተተነበየ ነው።

መፍትሔ
ሞሬና ከዚህ ጋር ተያይዞ እንደኛ ያሉ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች በቂ የሆነ የሥነ ልቦና እና የኑሮ ድጎማ እስካልተደረገላቸው ድረስ ራስን እስከማጥፋት የሚደርስ ውሳኔ ላይ እንደሚገቡ ግምቷን አስቀምጣለች።

ይህ አንዲት ተነጣይ ታሪክ እንደሚነግረን በአገራችንም ይሁን እንደኛ ባሉ ደሃ አገራት ውስጥ ሌሎች ሳይነገሩ ራሳቸውን በየቀዳዳው የደበቁ ነገር ግን ጊዜያቸውን እየጠበቁ ተከታትለው የሚፈነዱ የማኅበራዊ፣ የምጣኔ ሀብትና ፖለቲካዊ ቦንቦች አይኖሩም ማለት ሞኝነት ነው። የኮሮና ሻይረስ ምስቅልቅል በብልሃት የሚያዝ እንጂ እንዲሁ በደመነፍስ የሚፈታ ችግር ባለመሆኑ ትልቅ የመውጫ ቀመር ከልሂቃኑ የሚጠበቅ ይሆናል። ቸር ያሰማን!!!

አብርሐም ፀሐዬ የቢዝነስ አማካሪና ጋዜጠኛ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው geraramc@gmail.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com