መነሻ ገጽዜናትንታኔየተንሰራፋው የስርቆት ወንጀል

የተንሰራፋው የስርቆት ወንጀል

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች የስርቆት እና የዝርፊያ ወንጀሎች ተበራክቷል። ከዛም ልቆና ተበራክቷልም ከማለት ባለፈ ዐይን ባወጣ መልኩ በእኩለ ቀን ሳይቀር እየተፈፀመ ይገኛል።
በተደራጁ ቡድኖች ጭምር የሚደረጉ ዝርፊያዎች ከእለት እለት እየጨመሩ ሲሆን፣ የእጅ ስልክ፣ ቦርሳ እና ጥሬ ገንዘብን ጨምሮ ሌሎች ዝርፊያዎችም እየተፈጸሙ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተለያየ ጊዜ በሚያሰሙት ቅሬታና ከከተማው ፖሊስ ዘገባዎችም መረዳት ይቻላለ።

ከዚህ ባሻገር ትራፊክ መብራት ላይ ከቆሙ መኪኖችም ላይ ጭምር የስፖኪዮ የዝርፊያ ወንጀሎችም በብዛት እየተፈፀሙ መሆናቸውን ምስክር የማይጠየቅለት እውነት እየሆነ ይመስላል።

በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚፈፀሙ የወንጀል ዓይነቶችን ለመቀነስ ያስችላል ተብሎ የተዘጋጀ አገር ዐቀፍ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ አለ። ይህም ከኹለት ዓመት በፊት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦና ፀድቆ፣ ወደ ተግባር እንዲገባ ወደ ፍትህ ሚኒስቴር መላኩ አይዘነጋም።

የፌዴራል መንግሥት ወንጀልን የመከላከሉ ሥራ የወንጀል መንስኤዎች እና ተስማሚ የመከላከያ እርምጃዎችን ለይቶ በሚያስቀምጥ መንገድ ሊተገበርና ሊመዘን በሚችል ስትራቴጂ መመራት ስላለበት ስትራቴጂውን ለማዘጋጀት እንደተገደደም ጠቁሟል።

ምን ታቀደ?
ከስትራቴጂው ዝርዝር ዓላማዎች ለወንጀል ድርጊቶች መፈጸም ምቹ የሆኑ ሁኔታዎችን በማስወገድ እና የወንጀል መከላከል ሥራን ሊያግዙ የሚችሉ አሰራሮችን በመዘርጋት የወንጀል መከላከል ሥራ ማከናወን አንዱ ነው። በዚህም ለኅብረተሰቡ ዋና ስጋት የሆኑ፣ ልዩ ትኩረት የሚሹና ተጽዕኖ የሚፈጥሩ የወንጀል ድርጊቶችን ዓይነትና መንስኤዎቻቸውን በመለየት ድርጊቶቹን ለመከላከል የሚያስችል መሆናቸውንም የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።

እንዲሁም በመረጃና ምርጥ ተሞክሮዎች ላይ የተመሠረቱ ስልቶችን መንደፍ የሚለውን ሚኒስትሩ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ተጨማሪ የስትራቴጂው ዓላማዎችንም በዝርዝር አስቀምጧል። ይህም በድምሩ በወንጀል መከላከል ሥራ የባለድርሻና አጋር አካላትን ተግባርና ኃላፊነት በማስቀመጥ ውጤታማ የሆኑ የወንጀል መከላከል ተግባራትን ማከናወንና መከታተል የሚያስችል ነው ብሏል።

በተጨማሪ የተቀናጀ አሠራር በመካከላቸው እንዲኖር የሚያግዝ ሥርዓት መዘርጋት፣ ወንጀል ጠል የሆነ ማኅበረሰብ በመፍጠር እና በሕዝቦች ንቁ ተሳትፎ የዳበረ ጠንካራ የወንጀል መከላከል ሥርዓት በመዘርጋት የሕግ ማስከበር ተግባርን ማጠናከር እንደሚገባም ሚኒስትሩ አሳስቧል።

ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የወንጀል መከላከል ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል አቅም መፍጠርና የስትራቴጂውን አፈጻጸም የሚያስተባብር አካል፣ ተግባርና ኃላፊነት በማስቀመጥ ወንጀልን ከመካለከል አንፃር ውጤታማ የሆነ የክትትልና ግምገማ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑንም አክሏል።

ስትራቴጂዉ ሲዘጋጅም ጠቅላላ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ እና የተለዩ የወንጀል ዓይነቶች በሚል በኹለት ዋና ዋና ዓይነቶች ተመስርቶ ተዘጋጅቶ ነበር።

በተለይም በመሠረተ ልማት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ ከባድ የኢኮኖሚና ከገንዘብ ጋር ተያይዘው የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር ማሻገር፣ በሰላምና ፀጥታ፣ በሴቶችና ሕጻናት እንዲሁም መሰል ከ10 በላይ የወንጀል ዓይነቶች ላይ በመመሥረትና በእነዚህ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ተግባራት ውስጥ ምን ምን ተግባራት ይከናወናሉ ማንስ ምን ይሠራል፣ ማን ያስተባብራል የሚሉት ጉዳዮችም በዝርዝር ተቀምጠዋል።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂዎች ወደ ተግባር ገብተው በመዲናዋ ያለውን የስርቆት ወንጀል ለመቆጣጠር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከፌዴራል ፖሊስ እና ከደንብ አስከባሪ አካላት ጋር በጋራ እየሠሩ መሆኑን ሚኒስቴሩ ቢናገርም፣ በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ግን በኅብረተሰቡ ላይ የሚፈፀሙ ቅሚያ እና ዝርፊያ እንዳልቀነሰ የሚናገሩ አሉ።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ያሬድ ሀይለመስቀል በበኩላቸው በመዲናዋ ሞባይልን ጨምሮ የተለያዩ የስርቆት ወንጀሎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን እንደታዘቡ እና እርሳቸውም ይህ ጥንቅር ከተዘጋጀበት የተወሰኑ ቀናት በፊት የሞባይል ስርቆት እንደተፈፀመባቸው ጠቁመዋል።
ይህ ዓይነቱ የስርቆት ወንጀል በየወቅቱ በኅብረተሰቡ ላይ በሚፈፀምበት ወቅት ስርአት አልበኝነት እየሰፋ ይሄዳል። እንዲሁም ስርቆት ፈፅሞ ‹ገቢ የማግኘት› ወንጀል ወደ ሌሎች ሥራ አጥ ወጣቶችም የሚስፋፋበት እድል ቀላል አይደለም ሲሉ አሳስበዋል።
እንደዚህ ዓይነት የስርቆት ወንጀሎች ማስቆም ካልተቻለ፣ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር እና ኢንቨስትመንቱን ሳይቀር ለማሳደግ እንደሚያሰጋም ገልፀዋል።

የስርቆት ወንጀሉ የተፈፀመባቸው ግለሰቦች ለሕግ የማያሳውቁ እና የሚያሳውቁ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ አጠናክረው ሊቀጥሉበት ይገባል ያሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ የሕግ አካላትም አንድ ወንጀል ፈፃሚ ተገቢው የቅጣት እርምጃ ካልተወሰደበት ወንጀል ፈፃሚ አካላት ሊበራከቱ ስለሚችሉ ጉዳዩ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል።

ኅብረተሰቡም የፀጥታ አስከባሪ አካላትና የፖሊስ አባላት ጋር በመሆን ወንጀል ሲፈፅሙ የሚታዩ እና እጅ ከፍንጅ የሚያዙ ግለሰቦችን ለሕግ በማቅረብ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ባለሙያው መክረዋል።
የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ ደሳለኝ በበኩላቸው በመዲናዋ የስርቆት ወንጀል እየተበራከተ መምጣቱን እና ፖሊስ ወንጀል ፈፃሚ አካላትን ዐይቶ እንዳላየ የሚያልፍበት ሂደት መኖሩን ታዝቢያለሁ ባይ ናቸው።
የሕግ ባለሙያው አክለውም በወንጀል ሕጉ መሠረት ወንጀለኞችን ተከታትሎ ማስፈፀም ያለባቸው መርማሪ ፖሊስ እና ዐቃቢ ሕግ ናቸው ይላሉ።

በከተማዋ የሚፈፀመውን ወንጀል ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ መግታት ባይቻል እንኳ፣ ለመቆጣጠር የፀጥታ አስከባሪ እና የፖሊስ አባላት ኅብረተሰቡን ተሳታፊ ባደረገ መልኩ በጥምረት መሥራት አለባቸው ባይ ናቸው።
የፀጥታ አስከባሪ የፖሊስ አባላት ማናቸውንም ወንጀል የሚፈፅሙ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ተገቢውን ምርመራ አድርጎ የወንጀል ድርጊቱን ለዐቃቢ ሕግ ማስተላለፍ አለበት ይላሉ።
የፍትህ ሚኒስትር እንዲሁ ከፖሊስ የተቀበለውን እና ወንጀል ፈፃሚውን አካል በሕጉ መሠረት በፍርድ ቤት በኩል ተጠያቂ ማድረግ አለበት ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ ወንጀል እንዲሁም ቀላል እና ከባድ ስርቆት የሚፈፅሙ አካላትን ላይ ተገቢው ምርመራ ሳይደረግ ለዐቃቢ ሕግ የሚያልፍበት ሂደት ያለ ሲሆን፣ ይህን ጉዳይ በትኩረት ማጥራት እንደሚያስፈልግ እና የወንጀሉን ዓይነት ግልፅ በሆነ መንገድ ማጥራት ወይም መግለፅ እንደሚገባ የሕግ ባለሙያው አመልክተዋል።

- ይከተሉን -Social Media

የህግ ባለሙያው አስከትለውም በተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሠራር መኖርና ያም መናበብ እንዳለበት እና የወንጀል መከላከል ሥራው ኅብረተሰቡን ባማከለ መልኩ ወይም የማኅበረሰብ ዐቀፍ ፖሊስ በማቋቋም ወንጀል የሚፈፅሙ ግለሰቦች ላይ ክትትል ከማድረግ ባሻገር ክስ መሥርቶ ተጠያቂ የማድረግ ሥራን መሥራት ተገቢ ነው ደግሞም ያስፈልጋል ይላሉ።

ከላይ የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ወንጀል ፈፃሚ አካላትን የተጠረጠሩበትን ጉዳይ ሳይጣራ ተጠርጣሪ አካላትን በቁጥጥር ስር አውሎ ሦስት እና አራት ቀናት አስሮ መልቀቁ ፋይዳ የለውም ያሉት የሕግ ባለሙያው፣ ወንጀል ፈፅመሀል ተብሎ የተያዘው አካል ላይ የተጠናከረ ምርመራ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ግን አመላክተዋል።

በዋናነት የፖሊስ አካላት ከኅብረተሰቡ ጋር የቅኝት፣ የዘመቻ እና የቁጥጥር ሥራ መሥራት ከቻለ የወንጀል ድርጊቶች የሚቀንሱበት እድል ሰፊ መሆኑንም ተናግረዋል።
በፍትህ አካላትም በኩል ምንም እንኳ የቅጣት ውሳኔ ሊያስተላልፉበት ለዳኞች የተሰጠ ኃላፊነት ቢሆንም፣ ተገቢውን ቅጣት ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

ለዚህ ደግሞ የስርቆት ወንጀል የሚፈፅሙ አካላትን ሦስት እና አምስት ዓመት ሊያስቀጣቸው የሚችል ወንጀል ፈፅመው የቅጣት ማቅለያዎችን አስቀምጦ ሕጉን ያልተከተለ ውሳኔ ማሳለፍ ተገቢ አይደለም ብለዋል።
ወንጀል የማኅበረሰቡ ጠንቅ፣ የእድገት ፀር እና የህልውና ችግር መሆኑን የፍትህ አካላት ተገንዝበው ወንጀል የሚፈፅሙ አካላትን ሊያስተምር የሚችል የቅጣት ውሳኔ ማስተላለፋቸው ጠቃሚና ተገቢ መሆኑን የሕግ ባለሙያው ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በየወቅቱ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ከመከላከል ጎን ለጎን ለኅብረተሰቡ ስጋት የሆኑ 10 የሆኑ ወንጀሎችን በመለየት እና እቅድ በማውጣት እየተሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ ተናግረዋል። 10ሩንም ከባድ ወንጀሎች በእኩል ትኩረት በመስጠት ወንጀሎቹን የመከላከል ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከወንጀሎቹ መካከል ለአብነትም የግድያ ወንጀል፣ የመግደል ሙከራ፣ ማንኛውም የሌብነት ወንጀል ተጠቃሽ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

ከሐምሌ 30/2013 እስከ ጥር 30/2014፣ ባለፉት 6 ወራት ወንጀል በመከላከል ረገድ ብቻ ትኩረት ተደርጎ በመሠራቱ ወንጀልን አምስት በመቶ መቀነስ መቻሉን ገልፀዋል። ኅብረተሰቡ የትኛዉንም የወንጀል ድርጊት በሚመለከትበት ወቅት እና አጠራጣሪ ነገሮችን ካስተዋል ለፖሊስ በመጠቆም የሁልጊዜ ትብብሩን እንዲያደርግም ኮሚሽኑ አደራ ብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች