<ከድጥ ወደ ማጥ> የሆነው የአፋሮች ሕይወት

0
1597

በሰሜኑ ክልል የነበረውና አሁንም በአፋፍ ላይ ያለው ጦርነት ዘለግ ላለ ጊዜ የሚቆዩና መልሶ ለመገንባት ብዙ አቅም የሚፈልጉ ጥፋቶችንና ውድመቶችን አድርሷል። አፋር እንዲህ ያለውን ውድመት ካስተናገዱ ክልሎች መካከል ናት። ተፈጥሮአዊ አቀማመጧ እና የአየር ጠባይዋ ተደራርቦ ከሰው ሠራሽ ክስተቱ ጋር ለነዋሪዋ እጅግ ፈታኝ አድርጎባታል። ለወትሮ የቀኑን ከፍተኛ የአየር ሙቀት ለመቋቋም እንዲቻል ይውለበለቡ የነበሩ የአየር ማቀዝቀዣዎች አሁን በኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያት እንቅስቃሴአቸው ተገትቷል። በዚህም የተነሳ ሙቀቱ ከፍ በሚልባቸው አካባቢዎች ላይ ሕጻናት እየሞቱ፣ አዋቂዎችም እየተንገላቱ፣ የቻሉ ደግሞ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አለበት እንዲሁም የአየር ሁኔታው ሻል ያለ ነው ወደሚባልበት የክልሉ አካባቢ እየሄዱ ይገኛሉ።
የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ወደ አፋር አቅንቶ ነበር። በክልሉ ያለውን የመሠረተ ልማት ችግርና ማኅበረሰቡ እንዴት እየኖረ እንደሆነ፣ ያየውን እና የሰማውን አጠናቅሮ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

‹የመሬቱ እውነት›
አይሻ ሀሰን በአፋር ክልል ዞን ኹለት የአፍዴራ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። አይሻ በሚኖሩበት አፍዴራ ወረዳ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተቋረጠ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ሆኖታል። ላለፉት 18 ወራት አይሻ የዕለት ከዕለት ሕይወታቸውን ያለ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የመሩት አይሻ፣ ከዚህ ቀደም በኤሌክትሪክ ያገኙ የነበሩትን አገልግሎቶች ማጣታቸውን ተከትሎ የመኖሪያ አካባቢያቸውን ለቀው ሰመራ ከተማ ወደሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው ለመጠጋት ተገደዋል።

ኤሌክትሪክ አይሻ ይኖሩበት ለነበረው የአፍዴራ ወረዳ ነዋሪዎች ከመብራት፣ ከባንክ፣ ከቴሌና ሕክምና አገልግሎቶች በላይ በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ ሙቀት ለመከላከል በአየር ማቀዥቀዣ ሕይወታቸው ለማስቀጠል የሚጠቀሙበት ብቸኛ አማራጭ ነበር። ታዲያ ምን ያደርጋል! የዕለት ከዕለት ሕይወታቸውን የሚያቀልላቸው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተቋረጠ ላለፉት 18 ወራት ተመልሶ ሊመጣ አልቻልም።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ውኃ ሽታ ሆኖ በመቅረቱ ሙቀቱን መቋቋም አቅቷቸው መኖሪያቸውን ወደ ሰማራ ከተማ የቀየሩት አይሻ እንደሚሉት፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሕይወት ነው። ይሁን እንጂ የዕለት ከዕለት ሕይወትን ለመግፋትና ጤናማ አየር ለማግኘት ብቸኛ አማራጭ የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማጣትን ተከትሎ የቻለ ወደ ሌላ ቦታ መኖሪያ እየቀየረ ያልቻለ ደግሞ ሕይወቱን ‹በጨለማ ውስጥ› እየመራ ነው ይላሉ፤ አይሻ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ።

በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተቋረጠባቸው አካባቢዎች መካከል ከፍተኛ ሙቀት የሚያስተናግዱት ዳሎል እና አፍዴራ ወረዳዎች የሚገኙበት ዞን ኹለትና ዞን አራት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ ኃይል ጥገኛ የሆኑ አገልግሎቶችን አጥተዋል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸው አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ሰዎች በሰላሙ ጊዜ የኤሌክትሪክ ኃይል በሚለግሳቸውን ጤናማ አየር እየቀሰሙ በማንኛውም ስዓት ከቤታቸው ሆነው ምግብ ማብሰል ይችሉ ነበር። የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተቋረጠ በኋላ ግን በተለይ የእናቶች ሕይወት ከብርሃን ወደ ጨለማ ገጽ ተዘዋውሯል።

ከብርሃን ወደ ጨለማ ገጽ የተቀየረው የአፋር እናቶች ሕይወት፣ በኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት ሙቀቱን የሚያስታግስ የአየር ማቀዝቀዣ ማግኘት ስላልተቻለ ‹በእሳት ላይ እሳት› የሚሉትን ችግር ፈርተው የየዕለት መደበኛ ሥራ የሆነውን ምግብ ማብሰል ከቀን ወደ ሌሊት መቀየራቸውን አዲስ ማለዳ ታዝባለች። እናቶች ምግብ የሚያበስሉት በእሳት ሲሆን፣ የእሳቱ ሙቀት ካለው የተፈጥሮ ሙቀት ጋር ተዳምሮ የሚፈጥረውን ቃጠሎ ለመሸሽ በየዕለቱ ሌሊት ተነስተው ሙቀቱ ሳይጨምር በማለዳ መጨረስ ይጠበቅባቸዋል።

አይሻ ከአፍዴራ ወረዳ ወደ ሰማራ ከተማ የተዘዋወሩት ባለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ አካባቢ ሲሆን፣ በአካባቢው በነበሩበት ወቅት ከአጎራባች ወረዳዎች ተፈናቅለው ወደ አፍዴራ ወረዳ የመጡ ተፈናቃዮች ሙቀቱን መቋቋም አቅቷቸው በተለይ ሕጻናት ለሞትና ለሕመም እየተጋለጡ ነው ይላሉ። ‹‹እኛ ጋር የመጡት ሰዎች ሙቀቱን አልቻሉትም። ብዙ ሕጻናት ይሞታሉ፣ ማንም አያድናቸውም›› የሚሉት አይሻ፣ የሕክምና ተቋማት ቢኖሩም በኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጡ ሕክምናዎችን እየሰጡ ባለመሆኑ ለሕጻናቱ የሙቀት ማቀዝቀዣ አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ ይገልጻሉ።

የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት ከግማሽ ያስቆጠረ ሲሆን፣ ጦርነቱ በተካሄደባቸው በአፋር፣ በትግራይና በአማራ ክልሎች በተለይም ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ላይ በሚኖረው የማኅበረሰብ ክፍል ላይ ያሳደረው ችግር አሁንም እንደቀጠለ ነው። ጦርነቱ ከተጀመረበት ከጥቅምት 24/2013 ጀምሮ በአፋር የተወሰኑ አካባቢዎችና በትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡን ተከትሎ አንድ ዓመት ከግማሽ ያህል ያለ ኤሌክትሪክ ኑሯቸውን የሚገፉ ዜጎች ችግር አሁንም መፍትሔ አላገኘም።

በኢትዮጵያ በተፈጠረው ጦርነት ቀጥተኛ ሰላባ የሆኑት ትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ ከሰብዓዊ እስከ ቁሳዊ ኪሳራ አስተናግደዋል። መነሻውን በትግራይ ክልል ያደረገው ጦርነት ለስምንት ወራት በትግራይ ክልል ተገድቦ ቢቆይም፣ በ2013 ሐምሌ ወር ላይ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ተሸጋግሮ ከአምስት ወራት በላይ ጦርነቱ በኹለቱ ክልሎች ውስጥ ቆይቷል።

በእነዚህ ወራት የጦርነቱ ሰላባ የሆኑ የክልሎቹ ነዋሪዎች በርካታ የሰብአዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ አስተናግደዋል። ሰብአዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ያስተናገዱት የኹለቱ ክልል ነዋሪዎች ባለፈው ታኅሣሥ ወር ላይ ነበር ከሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ወረራ ‹ነጻ ወጡ› ብሎ የፌዴራል መንግሥት የገለጸው።

በወቅቱ አማራ እና አፋር ክልሎች ከሕወሓት ነጻ መውጣታቸው ቢገለጽም፣ በኹለቱም ክልሎች የትግራይ አዋሳኝ በሆኑ አከባቢዎች ላይ ውጊያ እንደነበር፣ እንዲሁም በርካታ አዋሳኝ አካባቢዎች ነጻ አለመውጣታቸው ሲገለጽ ነበር። በወቅቱ ሕወሓት ከኹለቱ ክልሎች ወጣ በመባሉ የጦርነቱ ቀጥተኛ ተጎጂ ከሆኑት ዜጎች በተጨማሪ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጦርነት ውስጥ የነበሩ አካባቢዎች ከጦርነት ነጻ በመሆናቸው ደስታውን የገለጸበት ጊዜ ነበር።

በአፋር ክልል ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች አካባቢያቸው ከጦርነት ነጻ መሆኑን ተከትሎ ወደየመጡበት ተመልሰው ኑሯቸውን መግፋት ከጀመሩ ወራት ቢቆጠሩም፣ እንደ ኤሌክትሪክ፣ ባንክ፣ ውኃ፣ ቴሌ፣ ጤና እና ትምህርት የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶችን እንዳላገኙ አዲስ ማለዳ በክልሉ ተገኝታ ተመልክታለች። በአፋር ክልል ከሚገኙ አምስት ዞኖችና 32 ወረዳዎች መካከል አሁን ላይ ከጦርነት ነጻ ያልሆነውን የዞን ኹለትን ወረዳዎች ጨምሮ ከ25 በላይ የሚሆኑት ወረዳዎች በጦርነቱ ምክንያት የመሠረተ ልማት ውድምት እንዳጋጠማቸው የክልሉ መንግሥት አደረግኩት ባለው ጥናት መግለጹ የሚታወስ ነው።

አዲስ ማለዳ በአፋር ክልል ተገኝታ ቀደም ብሎ ጦርነት የተካሄደባቸው አካባቢዎች ያጋጠመውን የመሠረተ ልማት ውድመት ተከትሎ በማኅበረሰቡ ላይ የተፈጠረውን ችግር ተመልክታለች። በጦርነቱ ምክንያት የመሠረት ልማቶች ውድመት ቢያጋጥምም ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸው አልቀረም። ይሁን እንጂ ከጦርነት በኋላ ወደቀያቸው የተመለሱ ሰዎች፣ የእለት ከእለት ሕይወታቸውን ለመምራት በተለይም ሙቀትን የሚከላከሉበትና ውሀ ለማግኘት የሚጠቀሙበት ኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡ ሕይወታቸውን በከፍተኛ ችግር እንዲገፉ እንዳስገደዳቸው ይናገራሉ።

የአፋር ክልል ከአየር ጸባይና ከተፈጥሮ አንጻር ዜጎች ከፍተኛ ሙቀት በሚያጋጥምበት ወቅት ሙቀትን ለመከላከል ወይም ሙቀት ከሚያስከትለው የጤና ችግር ራሳቸውን ለመጠበቅ ውሀ ለማግኘት የኤሌክትሪክ አገልግሎት የግድ ማግኘት ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠው የኤሌክትሪክ አገልግሎት በአንዳንድ ነጻ በውጡ አካባቢዎች ወደ አገልግሎት የተመለሰ ቢሆንም በኪልበቲ ረሱ (ዞን-2) እና ፈንቲ ረሱ ( ዞን-4) ውስጥ የሚገኙ ወረዳዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እያገኙ አይደለም።
በዞን አራት ውስጥ አምስት ወረዳዎች የሚገኙ ሲሆን፣ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ወረዳዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እያገኙ አይደለም። በዞን ኹለትም በተመሳሳይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደተቋረጠ ነው።

በክልሉ በጦርነቱ የወደሙ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎቶች ሲያገኙ ለእነዚህ ኹለት ዞኖች የኤሌክትሪክ አገልግሎታቸውን መመለስ ያልተቻለው የስርጭት ማዕከላቸው ከወልዲያና ከአላማጣ መሆኑን ተከትሎ ማስተካከል ስላልተቻለ መሆኑን የአፋር ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ብርሃኑ አዳነ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። እንደ ብርሃኑ ገለጻ ከአላማጣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኝ የነበረው ዞን ኹለት የሰሜኑ ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከተቋረጠው የትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ ኃይል ጋር አብሮ የተቋረጠ ነው። በዚህም የዞኑ ነዋሪዎች በጦርነቱ ምክንያት ኤሌክትሪክ ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ በኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት የሚችሉትን አገልግሎት ሳያገኙ ሕይወታቸውን እየገፉ ነው ይላሉ።

ዞን ኹለት ከሚገኙት ስምንት ወረዳዎች መካከል በሰላሙ ጊዜም የኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያገኝ ወረዳ ያለበት አካባቢ ያለ ሲሆን፣ ‹ቢዱ› የሚባለው ይኸው ወረዳ ከጦርነቱ በፊትም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ አልነበረም። ወትሮውንም በቂ የሚባል የመሠረተ ልማት አገልግሎት ተጠቃሚ ያልሆነው የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ይባስ ብሎ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ሕይወቱ ‹ከድጥ ወደ ማጥ› ይሉትን መሆኑን በሙቀቱ ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን የክልሉ ዋና ከተማ ወደሆነችው ሰመራ ከተማ ለማምጣት የተገደዱት መሐመድ እንድሪስ ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ።

ዞኑ በክልሉ ከሚገኙ አካባቢዎች አንጻር ከፍተኛ በረሃ መሆኑን ተከትሎ በተለይም አፍዴራና ዳሎል ወረዳዎች ከፍተኛ ሙቀት ያስተናግዳሉ። በዚህ ወቀት የዞኑ ወረዳዎች ከሆኑት መካከል የዳሎል ወረዳ አካባቢ ሙቀት 45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሲሆን፣ አፍዴራ አካባቢ ደግሞ 43 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል። ምንም እንኳን የአየር ጸባይ በየእለቱ እና በየሰዓቱ የሚለዋወጥ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ በአካባቢው ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ የሙቀት መጠኑ ይጨምራል።

የአየር ትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ አየር ሙቀት ለሰው ልጅ እንቅስቃሴ ጤናማ አይደለም። አፋሮች ሙቀትን ለመከላከል በዋናነት የሚጠቀሙት ‘ኤር ኮንዲሽነር’ ወይም አየር ማቀዝቀዣ ሲሆን፣ ይህም ያለኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መስጠት የማይችል በመሆኑ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያገኙ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ሰዎች ለችግር መጋላጣቸውን መሐመድ ይናገራሉ።

በዳሎልና አፍዴራ ወረዳዎች የሚኖረው ማኅበረሰብ በዚህ በተለይ ከሚያዚያ ወር መጨረሻ ጀምሮ በግንቦት ወር የሚጨምረውን ሙቀት ለመቋቋም የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያስፈልገው ቢሆንም፣ ማግኘት ባለመቻሉ መኖሪያውን ለቅቆ ወደ ሌላ አካባቢ ለመዘዋወር የቻለው ወደ ሌላ ከተማ እየተንቀሳቀሰ፣ መንቀሳቀስ ያልቻለው ደግሞ ሙቀቱ የሚያስከትለውን የጤና ችግር ችሎ እየኖረ መሆኑን መሐመድ ይገልጻሉ።

መሐመድ ቤተሰቦቻቸውን ከአፍዴራ ወረዳ ለማውጣት ወደ ቦታው ባቀኑበት ወቅት የታዘቡትን ለአዲስ ማለዳ ሲያስረዱ፤ ‹‹ግንቦት ሲደርስ ሙቀቱ ስለሚጨምር ሕጻናትና አዛውንቶች ስለማይቋቋሙት ሙቀቱ እስከሚያልፍ ሰባት ቤተሰቦቼን ከእኔ ጋር እያኖርኩ ነው።›› ይላሉ። አክለውም በተለይ በዳሎልና አፍዴራ አካባቢ ሙቀቱ ስለሚጨምር አቅሙ የቻለ እና የተሻለ ቦታ ቤተሰብ ያለው ወደ ሌላ ቦታ ለጊዜው መኖሪያ እንደሚቀይር ይናገራሉ።

‹‹መብራት ቢኖር በኤሲ ወቅቱን ማለፍ ይቻል ነበር። አሁን እሱን ማድረግ አልተቻለም። አፍዴራ ላይ ከአጎራባች ወረዳዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ሙቀቱ በመጨመሩ ሕጻናቶች እየሞቱ ነው። የአፋር ማኅበረሰቡ የመተባበር ባህሉ ጠንካራ ስለሆነ ዐስርም አስራምስትም ቤተሰብ ይይዛል። እዚያ ተፈናቃዮች ግን በሙቀት እየሞቱ ነው።›› የሚሉት መሐመድ፣ ከበርሃሌና መጋሌ ወረዳ አሁን ባለው ጦርነት ተፈናቅለው አፍዴራ ወረዳ የሚገኙ ተፈናቃዮች ሙቀቱን መቋቋም እንዳቃታቸው ይናገራሉ።

ሙቀት መጨመሩን ተከትሎ ወደ ሰመራ ካቀኑት የመሐመድ ቤተሰቦች መካከል አንዷ የሆኑት አይሻ ሀሰን፣ ‹‹እኛ ሙቀት ሽሽት ወደዚህ ስንመጣ በጦርነት የተፈናቀሉት ሰዎች ተሰብስበው መጡ። ምን የለ ምን የለ! እሜዳ ላይ ነው ያሉት። ሕጻናት በሙቀት ምክንያት እየሞቱ ናቸው።›› ሲሉ ሁኔታውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አይሻ እንደሚሉት ከበርሀሌ የተፈናቀሉ ሰዎች ሙቀቱን ለመቋቋም ከመቸገራቸው በተጨማሪ የሚታመሙ ሕጻናት ሕክምና የሚያገኙበት እድል እንደሌለ ይናገራሉ።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከአላማጣ ያገኝ የነበረው ዞን አራት የትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሲቋረጥ አብሮ የተቋረጠ ሲሆን፣ የዞኑ ወረዳዎች አንድ ዓመት ከስድስት ወር መጠጥም አየርም የሆነውን ኤሌክትሪክ አገልግሎት አጥተው ኑሯቸውን እየገፉ ነው። የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸው አካባቢዎች ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የተገናኙ እንደ መብራት፣ ቴሌ፣ ባንክ፣ ውሀ፣ በአየር ማቀዝቀዣ የሚገኝ አየርንና በኤሌክትሪክ ኃይል የሚፈልጉ የሕክምና አገልግሎቶችን ማግኘት እየቻሉ አይደለም።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በአማራና አፋር ክልሎች በሚገኙ አካባቢዎች በጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረግ ሰብአዊ ድጋፍ፣ መሠረታዊ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ እና መልሶ የማቋቋም ሥራ ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ዳሰሳዊ ቁጥጥር አካሂዶ ይፋ አድርጓል። በዚህ መሰረት በአፋር ክልል በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው ወደ መኖርያ ቀያቸው የተመለሱ ሰዎች 308 ሺሕ 936 ናቸው።

ተቋሙ ቀደም ሲል ጦርነት የተካሄደባቸውና በክልሉ በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ መሠረተ ልማት (የትምህርት ተቋማት፣ የጤና ተቋማት፣ የወረዳ ሴክተር መሥርያ ቤት ሕንፃዎች፣ የግለሰብ ቤቶችና የእምነት ተቋማትን ጨምሮ) በድምሩ 833 ሚሊዮን 918 ሺሕ 532 መሆኑን በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ባሰባሰብኩት መረጃ አረጋግጫለሁ ብሏል።

ማኅበረሰቡ እንዴት እየኖረ ነው?
ኡመር እንሃባ የዞን አራት ያሎ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ፣ በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠው አሌክትሪክ አገልግሎት ኑሯቸውን እንዳከበደባቸው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ይገልጻሉ። በዞን አራት በጦርነት ምክንያት የተቋረጠው ኤሌክትሪክ አገልግሎት የዞኑ ነዋሪ የውሀ፣ የባንክ፣ አየር ማቀዝቀዣና ሌሎችም ተያያዥ አገልግሎቶችን እንዳያገኝ እንቅፋት መሆኑን ይናገራሉ።

‹‹የእኛ ኑሮ የሚያሳዝን ነው።›› የሚሉት ኡመር፣ ዞኑ በጦርነቱ ምክንያት ከመውደሙ በፊት ለአምስቱም ወረዳ አገልግሎት የሚሰጥ የዞኑ መቀመጫ በሆነችው ከለዋን ከተማ አንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደነበር ይናገራሉ። ‹‹ከጦርነት በኋላ ግን መብራት ስለተቋረጠ በዞኑ ላይ ምንም የባንክ አገልግሎት የለም›› የሚሉት ኡመር፣ የዞኑ ነዋሪ የባንክ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ክልሉ ዋና ከተማ ሰማራ በመቶዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትር አቋርጦ መሄድ የግድ ብሎታል ይላሉ።

በክልሉ በጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የነበሩ፣ ሕወሓት ወደ ትግራይ መመለሱን ተከትሎ ወደ አካባቢያቸው ቢመለሱም፣ በጦርነቱ ምክንያት የመሠረተ ልማት ውድመት ማጋጠሙን ተከትሎ ኑሯቸውን እንደቀድሞው መምራት አልቻሉም። የመሠረተ ልማት ውድመቱ በተለይም የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸው አካባቢዎች ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የተገናኙ አገልግሎቶችን ማግኘት አልቻሉም።

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፣ ‹‹በጦርነቱ የደረሱ የተለያዩ ዓይነት ጉዳቶችና ውድመቶች በዝርዝር መረጃ ተደራጅቶ ለሚመለከታቸው አካላት ቢቀርብም እስከ አሁን መረጃውን ተንተርሶ በፌዴራልና በክልል ደረጃ በእቅድና በበጀት የተደገፈ ምላሽ ያልተሰጠ በመሆኑ፤ የመንግሥት ተቋማትና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በተሟላ ሁኔታና ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አገልግሎት መስጠት አልተቻላቸውም።›› ብሏል። ተቋሙ እንደ አብነት ያነሳቸው ከተቋረጡ ወይም በአግባቡ አገልግሎት ከማይሰጡት መካከል ጤና፣ ትምህርት፣ ቴሌ፣ መብራት፣ ውሀና ባንክ ዋና ዋናዎቹ መሆናቸው አረጋግጫለሁ ብሏል።

ተቋሙ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ‹‹ባንኮች በተለይም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጦርነት ስጋት ምክንያት በዞን አራት በሁሉም ወረዳዎች የባንክ አገልግሎት ባለመጀመሩ ኅብረተሰቡና የመንግሥት ተቋማት ለከፍተኛ እንግልትና ወጪ እየዳረጉ ነው።›› ብሏል። አዲስ ማለዳ በክልሉ በተገኘችበት ወቅት የባንክ አገልግሎት ከተቋረጠባቸው አካባቢዎች ወደ ሰማራ ተጉዘው ብር ለማውጣት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየቀኑ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰመራ ቅርንጫፍ ተሰልፈው ተመልክታለች።

ከተለያዩ አካባቢዎች የባንክ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሰማራ የሚያቀኑ ሰዎች ከፍተኛ መሆናቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰማራ ቅርንጫፍ ከፍተኛ መጨናነቅ እንዳለበት አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ ተመልክታለች። ከባንኩ ገንዘብ ለማውጣት ወይም ገቢ ለማድረግ በሰዓታት ወረፋ መያዝ ከሚጠበቅባቸው ደንበኞች መካከል ረጅም ሰዓት መጠበቅ ያልፈለገ ሰው፣ ከሰመራ በቅርብ ርቀት ላይ ወደምትገኘው ሎጊያ ከተማ ተጉዞ በተሻለ ወረፋ ማውጣት እንደሚችል አዲስ ማለዳ ታዝባለች።

የባንክ አገልግሎት ለማግኘት ከተለያዩ አካባቢዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ወደ ሰማራ ወይም ወደ ሎጊያ ከተማ የሚያቀኑ ሰዎች እድለኛ ሆነው የትራንስፖርት አገልግሎት ካገኙ ነው። በጦርነቱ ምክንያት ከተቋረጡ አገልግሎቶች መካከል የትራንስፖርት አገልግሎት ይገኝበታል። የመንገድ፣ መብራት፣ ውሃ፣ ባንክና ቴሌ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ችግር መኖሩን ተከትሎ፣ የሸቀጦች ዋጋ መናር በመፈጠሩ በማኀበረሰቡ ላይ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል ተብሏል።

ጨለማ እስከመቼ ?
‹‹መብራት ለዚህ አካባቢ ሕይወት ነው›› የሚሉት የአፋር ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ ‹‹ማኅበረሰቡ ሕይወቱን ነው ያጣው›› ይላሉ። ያለኤሌክትሪክ አቅርቦት የባንክ፣ የቴሌ፣ የውሀና የአየር ማቀዝቀዣ የሚገኙ አይደሉም የሚሉት ኃላፊው፣ ማኅበረሰቡ እነዚህን አገልግሎቶች አጥቶ እየኖረ ነው ብለዋል።

ኃላፊው አያይዘው ተቋማቸው ችግሩን ለመፍታት ባደረገው ጥረት በክልሉ ከነበሩት 18 የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማሰራጫ ማዕከላት መካከል አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት 12ቱ መሆናቸውን ይገልጻሉ። በጦርነቱ በኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጫ መሠረተ ልማት ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን የሚገልጹት ኃላፊው፣ ችግሩን ለማስተካከል እስከ አሁን 31 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሥራ መሠራቱን ይጠቅሳሉ። ይሁን እንጂ ሥራው ገና መሆኑን ተከትሎ 101 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለማልማት እየተሠራ መሆኑንም ነው ያነሱት።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸውን ዞን ኹለትና ዞን አራት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ በጦርነቱ ወቅት የወደመው የወልዲያ ማከፋፈያ ጣቢያ መገንባት እንዳለበት ይገልጻሉ። ከዚህ ውጪ አማራጭ የለም የሚሉት ኃላፊው፣ የወልዲያ ማከፋፈያ ጣቢያ የኹለቱን ዞኖች የኤሌከትሪክ ኃይል አቅርቦት ማግኘት አለማግኘት በወልዲያ ማከፋፈያ ጣቢያ አገልግሎት መስጠት ላይ ጥገኛ ነው ብለዋል።

ከዚህ ከቀም ከአላማጣ ኤሌክትሪክ ያገኝ የነበረው ዞን አራት ከወልዲያ ማከፋፋያ ጣቢያ ኤሌክትሪክ እንዲያገኝ አዲስ የመስመር ዝርጋታ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ነው ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ የጠቆሙት።

በጦርነቱ ወቅት የወደመው የወልድያ ተንቀሳቃሽ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ/ማከፋፈያ ጣቢያን በአዲስ ጣቢያ ለመተካት የሚያስችል ፕሮጀክት ከየካቲት 15/2014 ጀምሮ እየተሠራ ነው። ይሁን እንጂ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለተቋረጠባቸው አፋር ክልል አካባቢዎች የመድረስ አለመድረሱ ጉዳይ በፕሮጀክቱ ግንባታ መጠናቀቅ ላይ የተመሠረተ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው፣ የወልዲያ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንደማይጠናቀቅ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ከአንድ ዓመት ያላነሰ ጊዜ ይፈጃል የሚሉት ሞገስ፣ ‹‹በአጭር ጊዜ ምንም አማራጭ የለም።›› ብለዋል። ከወልዲያ የሚያገኙትን በሌላ አማራጭ ለመተካት ረዥም ጊዜ ስለሚፈጅ፣ ያለው ብቸኛ አማራጭ እየተገነባ ያለው ማከፋፈያ እስከሚጠናቀቅ መጠበቅ መሆኑን ሞገስ ገልጸዋል።

በኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት የባንክ፣ የቴሌና ተያያዝ አገልግሎቶቹን ያጡ ዞን ኹለትና ዞን አራት አንድ ዓመት ከስድስት ወር በቆዩበት ሁኔታ ሆነው ለሚቀጥለው አንድ ዓመት በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚቀጥሉ የኃላፊዎቹ ምላሽ ያስረዳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here