ሀናን አሕመድ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው። በዲዛይኒንግ ሙያ ላይ የተሰማራች ሲሆን የእስልምና እምነት ተከታይ ሴቶች የሚለብሷቸውን አልባሳት፣ ሂጃብ እንዲሁም አባያ የመሳሰሉትን ጥለት አክላባቸው ኢትዮጵያዊ ባህልን ከአልባሳቱ፣ እንዲሁም ሞደስት ከሚባለው ፋሽን ጋር አዋህዳ እየሠራች ነው። በተለያየ አጋጣሚ የፋሽን ትርዒቶች ላይ የሠራቻቸው ልብሶች ለዕይታ የቀረቡላት ሲሆን፣ በንግድ ባዛሮች ላይም ሥራዎቿን ለሕዝብ አድርሳለች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ (ሞዴስ/ፓድ) ላይ በትኩረት እየሠራች ትገኛለች። በኢትዮጵያ በተለይ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኋላ እንዲሁም ያንን ቀጥሎ በተከሰተው ጦርነት ሳቢያ ብዙ ሥራዎች መስተጓጎላቸው ግልጽ ነው። የሀናን የፋሽንና የዲዛይን ሥራም አሁን ላይ ወትሮ የሚሰጠውን ትኩረት እያገኘ አይደለም። ‹ይህ ችግር እስኪያልፍ፣ አገራችን ሰላም እስክትሆን ባለን መተጋገዝ ነው› የምትለው ሀናን፣ ትኩረቷን የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ላይ በማድረግ፣ ከተለያዩ ድርጅቶች፣ ከወዳጅ ጓደኞቿ ጋር በመተጋገዝ ምርቶቿን ወደተለያዩ ድጋፍ ወደሚያስፈልጋቸው ቦታዎች እየላከች ትገኛለች። እንዲሁም ይህ ደረጃውንና ጥራቱን ጠብቆ በእጅ የሚዘጋጀው የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ላይ በሰፊው መሥራትና ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባም ትገልጻለች።
ይህንን እና ሌሎች ሥራዎቿን በሚመለከትም ዲዛይነር ሀናን አሕመድ ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።
ወቅታዊ አገራችን ሁኔታ አስቸጋሪ እንደሆነ ይታወቃል። የፋሽን እና የዲዛይኑ ሥራ እንዴት ነው?
አሁን ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታ ሁሉም ላይ ተጽእኖ ፈጥሯል። በእኛ በዲዛይኒንግ ሙያም ሥራ በጣም የቀዘቀዘበት ወቅት ነው። ነገር ግን እዚህ ላይ መቆም የለብኝም በማለት ባለኝ ሙያ፣ አገር ውስጥ ባለው ነገር ምን ማድረግ እችላለሁ በሚለው እሳቤ በመነሳት፣ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ላይ ሙሉ ትኩረቴን ወደዛ አድርጌአለሁ። ደግሞም የሴቶች ብቻ ሳይሆን የሴቶችና አረጋውያን የንጽህና መጠበቂያ በማምረት ላይ እገኛለሁ።
ታድያ ከፋሽን ዲዛይን ጋር በተገናኘ ቀድሞ የነበሩ አውደ ርዕዮችና መሰል ክዋኔዎችም የሉም?
በፋሽኑ በኩል ከኮሮናውም በኋላ፣ በኢኮኖሚውም የተነሳ ቀዝቅዟል። ምክንያቱም የሰዉም ኢኮኖሚና የመግዛት አቅም ስለተነካ፣ መሠረታዊ ጉዳዮች ነገር ላይ ነው እያረፈ ያለው። ሰዉን እረዳዋለሁ። ምክንያቱም በሁሉም ላይ የደረሰ ነው። ኢኮኖሚውም ተጽዕኖ ስለፈጠረበት ነው። እኛ ደግሞ እንደ ባለሞያ ሥራ ቀዘቀዘ ብለሽ ከምትቀመጪ ሌላውን ማገልገል የምትችይበት ነገር ላይ ብታተኩሪ፣ ችግርን መቅረፍ ይቻላል።
ፋሽን ለእኔ አንዳንዴ እንደ ቅንጦት ነው። ምክንያቱም ካለንበት ሁኔታ አንጻር ብዙ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። እሱ ሲሟላና ኢከኖሚው ሲረጋጋ አንድ ላይ አድርገሽ ትሄጃለሽ። አገራችንን ሰላም ያድርግልንና በዓለማቀፍ ደረጃ አገርሽን የምትወክይበት ዘርፍ ነው፣ የፋሽን ሙያ። በአሁኑ ሰዓት ግን ቀዝቅዟል።
እንዴት አሰብሽውና በጥልቀት ወደ ሥራው ለመግባት ወሰንሽ፣ መነሻ የሆነሽስ ምን ነበር?
ወደዚህ ሥራ ከመግባቴ በፊት፣ በአጋጣሚ የወንድሜ ባለቤት ዶክተር ናት። እና ስደተኞችና ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታና እንደሚያስፈልጋቸው [የንጽህና መጠበቂያ] ነገረችኝ። ያኔ ገና ዲዛይኒንግ ሙያ ትምህርት ላይ ነበርኩኝ። እና ዩትዩብ ላይ ዐይቼ የሚታጠብ ሞዴስ በእናቴ የስፌት ማሽን ነው መጀመሪያ የሠራሁት። በዛ ሰዓት ላይ ማሽንም የለኝም፣ ገና ተማሪም ነበርኩኝ። ስለዚህ አነስተኛ እና ጥቃቅን ሄጄ እንዲሰፉልኝ አደረግኩኝ። ከዛ ምርቶቹን መጀመሪያ ያቀርብኩት ለጋምቤላ ተማሪዎች ነው፤ በወርልድ ቪዥን በኩል።
ያለው እርካታ ውስጥሽ የሚቀር ነው። እናም ይህን ነገር አንድ ቀን እሠራለሁ ብዬ ነበር። ውስጥሽ የምታስቀምጪው ቀናት የምትጠብቂለት ነገር አለ። ቀኑ ሲደርስ ሙሉ ትኩረቴን ወደዛ አደረግኩኝ።
ደግሞ ሴት ልጅ በዚህ የተፈጥሮ ጉዳይ ምክንያት ከትምህርቷ መቅረት የለባትም። እኔም ራሴ የዚህ ሰለባ ነበርኩ ልልሽ እችላለሁ። ሃይስኩል ላይ ልብሴ ላይ ታይቶ ሳምንት ከትምህርት ቤት እቀር ነበር። ቦሌ ሃይስኩል ነውና የተማርኩት፣ ዴስክ ሁሉ ይታሰር ነበር። እናም የሚሰማውን ስሜትና እፍረቱን አውቀዋለሁ። ያንን ስሜት ሌላም ሴት ይሰማታል፤ ሊሰማትም ይችላል። የእኔ ምርት የእርሷን ጭንቀት ማቅለል ከቻለ፣ ለምን ሁሌም ትኩረቴን ወደዛ አላደርግም ብዬ ነው የቀጠልኩት።
በፊት በወር አበባ ወቅት እናቶቻችን ጨርቅ ይጠቀሙ ነበር። በኋላ ላይ ከውጪ የሚመጣውና በተለያየ ኬሚካል የሚሠራው መጥቷል። አሁን ወደ ቀደመው እንመለስ ማለት አያስቸግርም? ገበያስ መፍጠሩስ አያስቸግርም?
ይህ የግንዛቤ ማጣት ይመስለኛል። ምክንያቱም እንደውም በሳይንሱም ላይ አሁን ያለውን የበሽታ ሪፖርት ስንመለከት፣ ኖርማል ፕላስቲክ (የሚጣለውንና አካባቢም የሚበክለውን) መጠቀም ከጀመርን በኋላ፣ የሴቶች በካንሰር ሕመም የመያዝ ደረጃ መጨመርና ተያያዥ ብዙ የምንሰማቸው ተጽእኖዎች አሉ።
ያ የሚመጣው፣ ፓድ የሚሠራበትን ኬሚካል የያዘውን ነገር አናውቅም፣ ደሙ እንዴት ሊረጋ እንደሚችል አናውቅም፤ ምን ተጽእኖ እንዳለውም እንደዛው አናውቅም። ሰው መቅለሉን ነው የሚያየው። ግን እየቆየ ውስጥን መጉዳቱ አይቀርም።
ወደኋላ ሄደን ስናይ፣ የነጠላ ጨርቅ ይደረግ ነበር። ያኔ ይህን ያህል የተጋነነ ዓይነት የበሽታ ነገር አይሰማበትም። ሰዉ የግንዛቤ ችግር ስላለው ነው። ሁሉንም ሄደሽ አስረድተሽ ነው የሚሆነው። አንዳንዴ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ለማድረስ ምርቱን በሚወስዱበት ቦታ ላይ፣ አብረን ሄደን አጠቃቀምና ጥቅሙን አስረድተን ነው።
እነዛ [በኬሚካል የሚዘጋጁ የንጽህና መጠበቂያዎች] በደንብ ሚድያ ላይ ተሠርቶላቸዋል፣ ማስታወቂያ አላቸው። ሕዝቡ እውቀቱ አለው። ይህኛው ደግሞ ገና እንደጀማሪነታችን ጊዜ ይፈጃል፤ እንጂ ሰዉ ወደዚህ መመለሱ አይቀርም ባይ ነኝ፣ ከኢኮኖሚውም አንጻር ስናየው።
ጊዜ ይፈጃል እንዳልሽው። ጊዜውን ለማሳጠር ምንድን ነው መደረግ ያለበት፣ ግንዛቤ መፍጠር ላይስ ማን ሊሠራ ይገባል ትያለሽ?
ሥራው ላይ ገብቼ የሚመለከተው ይሄ ነው የምልሽ ነገር የለም። ምክንያቱም እኔ እንደ ግለሰብ ነው እየሠራሁ ያለሁት። እገዛ ግን ትጠብቂያለሽ። ምክንያቱም ይህንን ራሱ ሂደቱን ለማለፍ መድኃኒትና ቁጥጥር ላይ የምትሄጂባቸው ደረጃዎች አሉ። እሱን ሁሉ አልፈሽ ለመሄድ አንድ ሰው ብቻውን ምንም ማድረግ አይችልም። ግን መንግሥት ቢያግዝ፣ አዳዲስ ወደ ሥራ እየገባን ያለነውን ቢደግፍና የመንግሥት እገዛ ቢኖረው በጣም ጥሩ ይሆናል ብዬ አምናለሁ።
አሁን ግንቦት 27/2014 ላይ አይኬር፣ ጀግኒት ኢትዮጵያ፣ አደይ ፓድ (በዚህ ሥራ ላይ ነው የተሠማራች) እነሱ ደውለውልኝ ተገናኝተን፤ አንድ ላይ ምርቶቻችንን ሚኒስትሮች በሚገኙበት ትልቅ ክዋኔ ላይ እናቀርባለን። እዛ ላይ የሚዲያ ሽፋንም ይኖራል ብዬ እገምታለሁ።
ሰዉ እንዲህም ዓይነት አለ እንዴ ብሎ ግንዛቤ እንዲኖር፣ እናንተ (ሚድያው) ትልቅ አስተዋጽኦ አላችሁ። ሰዉ እርግጠኛ ነኝ ወደዛ ነው የሚመለሰው። ምክንያቱም ሦስት ሴት ልጅ ያለው አንድ ቤተሰብ የወር ወጪውን አስቢው፤ አንዳንዴ ውስጧ የምትይዘው [8/10 ፍሬ] ራሱ አንድ ዙር (ፉል ሳይክል) ላታስጨርስ ትችላለች። ያንን ለመቆጠብ ረጅም ሰዓት ሲያደርጉት ደግሞ ለዘላቂው የሚፈጥረው ችግር አለ። ይህ ግን ታጥቦ ከ2 ዓመት በላይ መጠቀም የምትችይው ነው።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ሚድያው፣ ሌላውም ጋር እንደሚረባረበው ይህኛው ምን ያህል ለጤና አስፈላጊ እንደሆነ በማሳወቅ ድጋፉ ቢታከልበት አንድ ደረጃ መድረስ ይቻላል ነው የምለው። እንዳልኩሽ የሴቶች ብቻ ሳይሆን ለአረጋውያንም እያመረትን ነው። ስለሴቶች እየተባለ፣ እየተነገረ ነው። አረጋውያን ሲባል፣ ሁሉም በየቤቱ ታማሚ፣ አልጋ ላይ የወደቀ አለ፣ ብዙ አለ። እነሱም የተረሱ አንድ ማኅበረሰብ ክፍል ናቸው። ለዛ ነው የሴቶችና አረጋውያን ማምረቻ ብዬ እየሠራሁ ያለሁት። የአረጋውያንን ዳይፐር መጠቀሚያ ብታይ በጣም ውድ ነው። አሁን ታርጌት አድርጌ እየሠራሁ ያለሁት በስፖንሰሮች እገዛ መቄዶንያ የአረጋውያን እና የአእምሮ ሕሙማን ማዕከል ለሚገኙት ለመድረስ ነው። ዳይፐሩ የሚታጠብ ነው፣ ከዛ ቢያልፈ ተብሎ አልጋ መጠበቂያም የሚሠራ አለ።
ከሴቶች ጋር በተገናኘ ከንጽህና መጠበቂያ ውጪ የፌስቱላም እሠራለሁ። በፌስቱላ የተጠቁ ሴቶችም አሉ። እነሱ በየእለቱ ነው የሚያስፈልጋቸው እንጂ እንደ መደበኛው አይደለም። ረጅም የሆነ ተጽእኖ ነው ሕይወታቸው ላይ ያለው። እና ምንም ሳይሳቀቁ የሚያደርጉት ፓንት (ዋተር ፕሩፍ ነው) በደንብ የተሠራ ሆኖ እንደ ፓንት መታጠቅ የሚችሉት ነው። እነሱም ምርቶችም አሉ። እና የሚድያ እገዛ ቢጨመርት ለሁሉም ተደራሽ እንሆናለን እላለሁ።
በተጨማሪ ሁላችንም እንደ እኔ ላሉ ሴቶች፣ ለጀማሪዎች እገዛ ቢኖር። ከወረዳ ጀምሮ ክፍለ ከተማ ድረስ እኔ ሄጄ ጠይቄአለሁ፣ ድጋፍ እንዲሰጠኝ፤ ቦታ አስፋፍቶ ለመሥራት። እኔ በደንብ አስፋፍቼ መሥራት እፈልጋለሁ፣ ግን ቦታ እጥረት ይይዘኛል። ማሽን ጨምሮ ለመሥራት ቦታ ፈታኝ ይሆንብኛል። ይህ ቢስተካከል ኢኮኖሚውንም መጥቀም ይቻላል። እኛ አገር ውስጥ ባለው ምርት ነውና የምንሠራው። ስለዚህ የአገርን ኢኮኖሚ ማሳደግ ስለሆነ በጣም መታገዝ አለብን ነው የምለው።
ይህን የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ምርት ለማምረት ፈቃድ የማውጣት ሂደቱ ምን ይመስል ነበር?
ቀላል መንገድ ሆኖ አላየሁትም። ኹለት ዓመት አካባቢ ነው የፈጀብኝ። ምክንያቱም የሚጠይቁሽ መስፈርት እና አንቺ ማድረግ የምትችይው የተለያየ ነው። ያኔ ደግሞ አቅሙም አልነበረኝም። መስፈርታቸው ወደ 10 ገጽ ነው። ቀላል አልነበረም። ግን ስለጀምረኩት እጨርሰዋለሁ በማለት ነው የቀጠልኩት። ከጠየቁት መካከል 90 በመቶ በላይ አሟልቼ ነው። ፈቃዱን ለማለፍ ራሱ ምርትሽ ተስማሚነት ሄዶ ተመርምሮ ነው። ቀላል ሂደት ነው አልልም፤ እውነት ለመናገር። ከባድ መንገድ ሄደሽ ነው ያንን የምታደርጊው።
ግን ከእድሳት ጋር በተገናኘ ሥራው ላይ እንደገባሁ፣ እነርሱም እርዳታ በጠየቁ ሰዓት ተደራሽ ስለነበርኩኝ፤ ኹለተኛውን ማደስ ላይ በደንብ ነው የተባበሩኝ። ያው ጅማሬው ነው የሚከብደው።
እነዚህ ምርቶች አሁን የት ነው የሚገኙት? ገበያ ላይስ አሉ ወይ?
እያመረትን ያለነው አራት ኪሎ በሚገኘው ወርክሾፕ ላይ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ምርቴን የሚወስዱት ከወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ለተፈናቃዮች፣ በስደት ላሉትና ተደራሽነት ለሌለባቸው ብሎም ማግኘት ላልቻሉት፣ በተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የታገዙ ሆኖ ለትምህርት ቤትም ለዩኒቨርሲቲም በብዛት የሚወሰዱ አሉ። አሁን ባለኝ አቅም ለእነርሱ ነው እያመረትን ያለነው።
ግንዛቤው ሕዝቡ ጋር ሲደርስና ሕዝብ ይን ነገር በተረዳ ሰዓት እኔ ሕልሜም የሚሆነው ማንም ሰው ሱቅ ላይ ወይም ሱፐር ማርኬት ሄዶ መግዘት የሚችለው እንዲሆን ነው። ምክንያቱም እስከ ኹለት ዓመት ተኩል የሚያሳርፍና በየወሩ የማያሳስብ ነው። እና አሁን በወርክሾፕ ደረጃ እያመረትን ለሚጠይቁ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ነው እያቀረብን ያለነው።
ምን ያህል ድጋፍ ማድረግ ተችሏል?
መጀመሪያ መድኃኒትና ቁጥጥር ደብረብርሀን ላሉ ተፈናቃዮች ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ጓደኞቼን፣ ቤተሰብና ታዬ የሚባል በጣም ትልቅ በጎ አድራጎት ሥራ ላይ የተሰማራ አለ፤ እርሱም ሰብስቦ፤ እኔም ውጪ ያሉ ቤተሰቦቼን የቻላችሁትን ለአገራችሁ ብዬ፣ ሰዉ እንደ አቅሙ ከአንድ ሴት ፓድ ጀምሮ ነበር እያዋጣ የነበረው። በዛ መሠረት መጀመሪያ ለደብረብርሃን ነው ያቀረብነው።
ኹለተኛውም በቤተክርስትያን መጥተው በጠየቁት መሠረት፣ የተሰበሰበው በቂ ስለነበር ኹለተኛውን ዙር በዛ አድርገናል። ከዛ ለትምህርት ቤትም አቅርበናል። እንዲህ እያለ ነው የቀጠለው፤ በዚህም ከ1500 በላይ ፓዶችን ተደራሽ አድርገናል።
ወደኋላ ልመልስሽ፤ ወደፋሽን እና ዲዛይን ሙያው። ወደዚህ ሙያ ለመግባት አረአያ የሆነሽ ወይም የተከተልሽው ሰው ማን ነበር?
ባህሉን እንድወድ ያደረገችኝ እናቴ ናት። እኔ የመጣሁት ከኹለቱም ሐይማኖት ነው። እናቴ በክርስትናው ካቶሊክ ናት፣ አባቴ ደግሞ የእስልምና እምነት ተከታይ ነው። ያደኩበት በኹለቱም ማኅበረሰብ ውስጥ ነው። ባህሉን ከአባያ ጋር እንድዳፈር ያደረገኝ እኔው ጋር ይመላለስ የነበረ ሐሳብ ይመስለኛል። ጥለቱ አባያ ላይ ቢሆን ምን ችግር አለ ብዬ ነው። የምንለብሰው ከአረብ አገርና ከሳውዲ ተገዝቶ የሚመጣ።
ኢድም ሲሆን የሚለበሱት የውጪ ልብሶች ናቸው። ግን የተለያዩ ብሔረሰቦች ላይ ስትሄጂ፣ አበሻ ቀሚስ ለብሶ በተመሳሳይ ሃይማኖቱን የሚከተል አለ። አባያን ለሚወደው አባያው ላይ ለምን ጥለት አይሆንም/አይደረግም ብዬ ነው የጀመርኩት። እናም አረአያ የሆነችኝ እናቴ ናት።
የምትሠሪያቸው ልብሶች የተለየ ኹነት ተጠብቆ የሚለበሱ ናቸው ወይስ በማንኛውም ወቅትና ሁኔታ ሊለበሱ ይችላሉ?
ዘወትር ልታደርጊ የምትችይው ነው። ኹነት ጠብቆ የሚደረግና ብልጭልጭ የበዛበት አይደለም። ጥለቶች አሉበት፣ ማንም ሊለብሰው ይችላል። ዱባይ አገር ያሉት እንደውም በመጀመሪያ ባዛር በጣም ብዙ ነው የገዙት። ከአፋር የመጡና እናቶችና አባቶች ብዙ መርቀውኝ ነው የሄዱት። ‹እኛ ማለት ይሄ ነን› ነው ያሉት። የአረብን ስለለበስን አይደለም። እንደውም እነሱን ስንመስል እነሱን መወራረስ አለ። ገና ላይ በግሮቭ ጋርደን በነበረን ባዛርም የምናገኘው አስተያየት ደስ የሚል ነው፣ ጥሩ ምላሽ አግኝተናል።
አሁን ለደረስሽበት ደረጃና ለጥንካሬሽ ያሳለፍሽ ሕይወት መሠረት እንደሚሆን እሙን ነው። መለስ ብለሽ አስተዳደግና ልጅነትሽን አጫውቺን?
አባቴ የሀረር ሰው ነው፤ እናቴ ከጅማ ናት። እናቴ እኔን ነፍሰጡር ሆና ነው እዚህ [አዲስ አበባ] የመጣነው። በኹለቱ መካከል ማደጌ እንዳልኩት ኹለቱንም ሐይማኖት ታያለሽና፣ ይህ እኔን ‹ኦፕን ማይንድድ› እንዲሁም ሊበራል አድርጎኛል። የእኔ መንገድ ብቻ ነው ትክል እኔ ጋር አይሠራም፤ ለእኔ ሰውነት ይበቃል።
ተወልጄ ያደግኩት ባምቢስ አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን አጼ ቴዎድሮስ ነው የተማርኩት፣ ኹለተኛ ደረጃ ደግሞ ቦሌ ሃይስኩል ነው የጨረስኩት። ያሳደገችኝ አክስቴ የበረራ አስተናጋጅ (ሆስተስ) ነበረችናና እሷን እያየሁ እኔም ሆስተስ መሆን እፈልግ ነበር።
በኋላ አዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ወይም ኮሜርስ ትምህርቴን ጨረስኩ። ያኔ ሕልሜን ለማሳካት ለሆስተስነት ስወዳደር ኪሎሽ አይሞላም ተብሎ ሦስት ጊዜ ወድቄ ነበር። በጊዜው የአገልግሎት ዘርፍ ላይ ምንም ልምድ አልነበረኝም። ቤተሰብ ልጄ ተምሮ ይህን ይሆንልኛል ነው የሚለውና፣ እኔም ያንን እሆናለሁ ነበር የምለው።
ቀጥሎ ውጪ ያሉ አየር መንገዶች ለመወዳደር ሄድኩኝ። መጀመሪያ የሄድኩት አቡዳቢ ነው፤ የአክስቴ ባለቤት እዛ አብራሪ ነበር። እዛም ገልፍ ኤር (Gulf Air – Airlines) ነበር የተወዳደርኩት፤ በመጀመሪያ ዙር ነው በደንብ ነው የወደቅኩት። ዐይናፋር ነበርኩ፤ ሰው ፊት ቆሞ ማውራት ላይ በራስ መተማመኑ አልነበረኝም። እናም ለምን እንደወደቅኩ ተረዳሁ።
እናም የአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ መግባት አለብኝ ብዬ በ750 ዱርሃም እዛው በአንድ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ተቀጠርኩኝ። የማጣት ጉዳይ ሳይሆን ፍላጎቴና ሕልሜን እየተከተልኩኝ ነበር።
ያኔ አንድ ክፍል ውስጥ ለአራት ተከራይተን ነበር የምንኖረው፤ ከተለያየ አገር ሰው ጋር። የሌሊት ተረኛ ከፋች ነበርኩ፤ በጊዜው ኻያ ዓመቴ ነበር። ሁሉንም እችላለሁ ብዬ ገባሁ። እዛ እያለሁ ኢትሀድ (Etihad Airways) የበረራ አስተናጋጅነት ሥራ እድል እንዳለ ሰማሁ። በዛም ተወዳደርኩ፣ በዚህኛው የመጀመሪያዎቹ 13 ውስጥ ገባሁ ግን አላለፍኩም። ግን የሠራሁበት ሆቴል በደንብ እሠራ ስለነበርና የአገልግሎት ልምድ ስለሚሰጥ ብዙ ልምድ ሰብስቤ ነበር።
ከዛ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ዩኒቲ እየተማርኩኝ ነበርና መጥቼ ዲግሪ ለመያዝ ነበር። ከዛ ስመጣ ትንሽ ልምድ ስላገኘሁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀበለኝ። እናም ገልፍ ኤር እንዲሁም ኢትሀድ ስወድቅ፤ በኋላ ኤምሬትስ ልወዳደር ሳመለከት የሳቀብኝ ሰው አለ። ኹለቱ ላይ ወድቀሽ እንዴት ኤምሬትስ ትመኛለሽ ብሎ። እኔ ሰው ያሰበው ነገር ካለ ጥጉ ሰማይ ነው። ዋናው በትልቁ ማለም ነው። ሌላው እንደሆነው መሆን እችላለሁ፣ ምንም አያንሰኝም። ሕይወትን እየተማርሽበት ነው የምትሄጂው።



