ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በሀረሪ ክልል ከ30 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተከናወኑ ከነበሩ 17 ፕሮጀክቶች መካከል 8ቱ ተጠናቀው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በተገኙበት ሥራ ጀምረዋል።
ኦርዲን በድሪ በኹለተኛው የከተማ ውሃ አቅርቦት እና ንፅህና የተከናወኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶች የመስክ ጉብኝት በማድረግ የሥራ መመሪያ አሰተላልፈዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በ30 ሚሊየን ብር ወጪ እየተከናወኑ ካሉ ፕሮጀክቶች ውስጥ 8ቱን ሥራ ያስጀመሩ ሲሆን፤ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችንም በመጎብኘት፤ በአፋጣኝ ተጠናቀው ሥራ እንዲጀምሩም አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የክልሉ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ ዲኒ ረመዳን ፕሮጀክቶችን አስመልክተው እንደተናገሩት፤ በክልሉ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተከናወኑ ከነበሩ 17 ፕሮጀክቶች መካከል 8ቱ ተጠናቀው በዕለቱ ሥራ ጀምረዋል፤ ቀሪዎቹ ፕሮጀክቶችም ከ95 በመቶ በላይ ተጠናቀዋል ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ በተለይም የድሃ ድሃ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ከማድረግና ክልሉንም ፅዱ ከማድረግ አንፃር ጉልህ ሚና እንዳላቸው መጠቆማቸውን ከክልሉ መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
ከተከናወኑ ፕሮጀክቶችም የጋራ መፀዳጃ ቤቶች፣ የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች እና ሌሎች ፕሮጀክቶች መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም 409 የድሃ ድሃ እማወራዎችንና አባወራዎችን ተጠቃሚ ያደረገ የውሃ መሰረተ ልማት መከናወኑንም ተገልጿል።
____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n





