8 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ መድረሱ ተገለፀ

0
891

ዕረቡ ግንቦት 10 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ስምንት ነጥብ ኹለት ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ተጓጉዞ ጅቡቲ ወደብ መድረሱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በግብርና ሚኒስቴር የግብዓት አቅርቦትና ሥርጭት ዳይሬክተር መንግሥቱ ተስፋ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱና በተፈለገው መጠን ለአርሶ አደሩ ለማድረስ የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

ለዘንድሮው ዓመት ከሚያስፈልገውና ግዢ ከተፈጸመበት 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪ ውስጥ፤ 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታሉ አስፈላጊውን ሂደት አልፎ ጅቡቲ ወደብ ደርሷል። በመርከብ ተጓጉዞ ጂቡቲ የደረሰው ማዳበሪያ አጠቃላይ ግዢ ከተፈጸመበት ማዳበሪያ 64 በመቶው ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም 7 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች መሰራጨቱን የጠቆሙት መንግሥቱ፤ ኹለት ነጥብ አራት ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያም ለአርሶአደሮች መድረሱን ገልጸዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ከሆነ፤ የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዙ ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተጠቃሚው አርሶአደር ሙሉ ለሙሉ እንዲደርስ ይደረጋል። ማዳበሪያውም ለግብርና ሥራው ወሳኝ ለሆነው የዘር ወቅት እንዲደርስ በማድረግ የተሻለ ምርት ለማግኘት ታቅዷል።

የተጠቃሚውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መረጃ አሰባስቦ ጨረታ የማዘጋጀት፣ አጋር አካላትን የማስተባበር እንዲሁም ከአሁን በፊት የነበሩ ችግሮችን በመገምገም ችግሮቹ ደግመው እንዳይከሰቱ ከፍተኛ የሆነ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

በዘንድሮ ዓመት በነበሩ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ሁኔታዎች የአፈር ማዳበሪ ለማግኘት ከፍተኛ ችግር አጋጥሞ እንደነበር አስታውሰው፤ የግዢ ጨረታ ሲወጣ አቅራቢና አምራቾች ጨረታው ላይ ያለመሳተፍ፣ ጨረታ ካሸነፉ በኋላም ለማቅረብ ፍቃደኛ ያለመሆን ችግሮች ተስተውለው እንደነበር ገልጸዋል።

ችግሩን ለመፍታት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጀምሮ እስከ ግብርና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድረስ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ተሰርቷል። በዚህም የአፈር ማዳበሪያውን ለአርሶአደሩ በወቅቱ ለማድረስ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት አመቺ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።

በአቅርቦት እጥረትና በጥሬ እቃ መወደድ ምክንያት የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ጠቁመው፤ በቀጣይ ችግሮችን ለመቋቋም አርሶአደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀሙን መጨመርን እንደ አንድ አማራጭ መጠቀም እንዳለበት ዳይሬክተሩ ማሳሰባቸውን የኢፕድ ዘገባ አመላክቷል።

እንደ ግብርና ሚኒስቴር መረጃ ፤ ዘንድሮ አዲስ ግዢ የተፈጸመበት 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ እንዲሁም ካለፉት ጊዜያት የተገዛ ወደ ኹለት ነጥብ ሦስት ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ በአጠቃላይ 15 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ዘንድሮ ለአርሶ አደሩ እንዲቀርብ ይደረጋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here