ዕረቡ ግንቦት 10 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በወላይታ ዞን የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነዉ እና ኢ ቲ አር ኤስ1 ኬ ኤም ተብሎ የሚጠራ ሮኬት መስራት የቻለዉን ታዳጊ ሳሙኤል ዘካሪያስ በአስተዳደሩ የኢትዮ-ሳይበር ታለንት ማዕከል እንዲታቀፍ መደረጉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ።
የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛዉ እንደገለጹት÷ የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነዉ እና ETR S1KM ተብሎ የሚጠራ ሮኬት መስራት የቻለዉን ታዳጊ ሳሙኤል ዘካሪያስን የፈጠራ ሥራዎቹን ወደተሻለ ደረጃ እንዲያደርስ በአስተዳደሩ የኢትዮ-ሳይበር ታለንት ማዕከል እንዲታቀፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርም ለተማሪ ሳሙኤል ዘካሪያስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግና በዚህም የአቅም ግንባታ፣ የቁሳቁስ እና የሥልጠና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የተማሪ ሳሙኤልን ተሰጥኦ ለማሳደግ በሚረዱት ጉዳዮች ላይም ዉይይት መደረጉን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
በውይይቱ ተማሪው የፈጠራ ዉጤት ለአገር የሚያበረክተዉ አስተዋጽዎ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ሹመቴ፤ እንደ ሳሙኤል አይነት ታዳጊ የፈጠራ ባለቤቶችን አቅም በማጎልበት ለአገር በሚጠቅም መልኩ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
አስተዳደሩ በሳይበር ደህንነት እና ተያያዥ ዘርፎች ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊ ወጣት ኢትዮጵያውያንን የመደገፍና የማብቃት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡





