አዋጅ ነጋሪ ሚዲያዎች ከ2 ሺሕ ዓመት በኋላም!?

0
1005

በኢትዮጵያ አንፃራዊ አዎንታዊ የፖለቲካ ለውጥ አለ በሚባልበት በአሁኑ ወቅት መገናኛ ብዙኀን አሁንም ከ2 ሺሕ ዓመታት በፊት ያለፈውን የነገሥታት ዕለታዊ ተግባራት ከሚዘግበው ‘አዋጅ ነጋሪ’ነት ያለፈ ሥራ እየሠሩ አይደለም ሲሉ ናርዶስ ዮሴፍ የተወሰኑ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኀንን የአገር ውስጥ ዜናዎቻቸውን በናሙናነት ውስደው በመተንተን ይከራከራሉ።

 

በ131 ዓመተ ዓለም ጀምሮ በሮማን ሪፐብሊክ የተጀመረ በላቲን ቋንቋ ‘አክታ ዲዩርና’ (The Daily Acts) የተባለ ዕለታዊ ለሕዝብ የነገሥታቱ ሥራ የሚታወጅበት ጋዜጣ መሰል የማሳወቂያ ጽሁፍ ነበር።

እነዚህ የማሳወቂያ ጽሑፎች በድንጋይ አልያም በብረት ላይ ተቀርጸው እንደ ሮማን ፎረም ያለ ሕዝቡ የሚሰበሰብበት ቦታዎች ላይ ያስቀምጡት ነበር።

ይህ ጋዜጣ መሰል ጽሁፍ ሲጀመር የፍርድ ቤት ሒደቶችን እና የክስ ውጤቶች ይገለጹበት የነበረ ሲሆን በቀጣይ በአገሪቱ ፓርላማ፤ ነገሥታት እና አጠቃላይ በአገዛዙ ለሕዝቡ እንዲገለጹ የሚፈለጉ ጉዳዩች ይጻፉበት ነበር።
‘አክታ ዲዩርና’ ወይም ‘አክታ’ በሚል ብቻ የሚታወቀው ጥንታዊ የነገሥታት መዝገብ በአውሮፓ በተለይም በጣሊያን በእንግሊዝ እና በተወሰኑ የግሪክ ግዛቶች ተተግብሮ ማለፉን ድርሳናት ያወሳሉ።

በኢትዮጵያ ደግሞ መሰል ጥንታዊ የነገሥታት ዕለታዊ ክንውን የሚዘገብበት ማሳወቂያ ‘አዋጅ ነጋሪ’ ይባል እንደነበረ ይታወሳል።

አዋጅ ነጋሪ ልክ እንደአውሮፓውያኑ ሁሉ ኢትዮጵያውያኑ ነገሥታት ሕዝቡ እንዲያውቁ የሚፈልጓቸውን ጉዳዩች የሚያውጁበት መንገድ ነው።

እንደ ዛሬው የሰለጠነ የምንለው ዓለም ሬዲዩ፣ ጋዜጣ፣ ቴሌቪዥን ያሉ የመገናኛ ብዙኀንን ተጠቅሞ ለሕዝቡ መረጃ የሚደርስበት አማራጭ፤ አልያም ደግሞ የዜጋ ጋዜጠኝነት (Citizen Journalism) የሚተገበርባቸው ሚሊዩኖች የሚጠቀሙባቸው የማኅበረሰብ ትስስር ገጾች ሳይፈበረኩ በፊት፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው እና ሥራቸው የሕዝብን ንብረት ምን ላይ አዋሉ ብሎ የሚያጣራልን የሥራ ኃላፊነቱ እና ግዴታው ምን እንደሆነ በግልጽ የተደነገገለት ጋዜጠኛ የምንለው ጠያቂ አካል ሳናበጅ በፊት ኢትዮጵያ የነበራት ነገሥታቱ ሕዝቡ እንዲያውቅ የፈለጉትን ብቻ የሚነግሩበት፤ መረጃውን የሚከትበው ጸሐፊም ይህ እውነት ነው ወይ? ብሎ ሳያጠራ የሚጽፍበት እና ለፋፊውም ያለምንም ጥያቄ የነገሥታቱን ሐሳብ የሚያንበለብልበት ‘አዋጅ ነጋሪ’ ነበር።

አሁንስ? ‘አዋጅ ነጋሪ’ ተወልዶ ኖሮ ከሞተ ከ2 ሺሕ ዓመታት በላይ ካለፉት በኋላ የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ከሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና ሕግ ተርጓሚ በኋላ አራተኛው የመንግሥት ገምጋሚ ጠያቂ አካል ሆኖ ለሕዝቡ ቆሟል? የኢትዮጵያ መንግሥትስ ጋዜጠኝነት በሙሉ አቅሙ እንዲተገበር እያደረገ ነው ብለን በድፍረት መናገር የምንችልበትን ሁኔታ አሳይቶናል?

ለዚህ ጽሁፍ የአራት መገናኛ ብዙሀንን የአንድ ሳምንት የአገር ውስጥ ዜናዎች ብቻ ለናሙና ተጠቅሜያለሁ።

ለግምገማ ጥሩ ማሳያ ይሆናሉ ለውክልናም ይመቻሉ በሚል በኢትዮጵያ ብቸኛ የአክሲዩን ማኅበር መገናኛ ብዙኀን የሆነውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን የሆነውን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት-ኢቲቪ ዜና ጣቢያን፣ በኢትዮጵያ የግል ሬዲዩ ጣቢያ የሆኑትንና ከተመሰረቱ 10 ዓመታት ያለፋቸውን የዛሚ 90 ነጥብ 7 ኤፍ ኤም እና የሸገር ኤፍ ኤም 102 ነጥብ 1 ን መርጫለሁ።

እነዚህ አራት መገናኛ ብዙሀን ከየካቲት 5-7/2011 ድረስ የዘገቧቸውን እና በድረ ገጾቻቸው እና በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ፌስቡክ ላይ ከለጠፏቸው ዜናዎች እና ሌሎች መረጃዎች ሁሉንም የአገር ውስጥ ዜናዎቻቸውን ብቻ በመውሰድ እውነት የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ከአዋጅ ነጋሪነት ተሻግሯል የሚለውን ቃኝቻለሁ።

የመገናኛ ብዙኀኑ ዜናዎች ከመሪ እና መንግሥት (ነገሥታት) መዝገብነት ያለፉ መሆናቸውን ለማየት ለመመዘኛነት የተጠቀምኩት የዜናዎቻቸውን ብዛት፤ የመንግሥት ሥራ የሚያትቱ ዜናዎች ማለትም መንግሥት ይህን አደረገ ይህ ሊደረግ ነው የሚሉ ዜናዎች ብዛት፤ በግሉ ዘርፍ እና ሌሎች ማኅበረሰቡ ትኩረት የጠየቀባቸው ጉዳዩች ዘገባ ዜና ብዛት እና የዜናዎቹ ዘገባ ዘርፍ፤ በቀጥታ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም መሪው ስላደረጉት ንግግር እና ተግባር ያለ ምንም የጋዜጠኛ መጠየቅ የሚያትቱ ዜናዎች ብዛት እንዲሁም ከተለያዩ የመንግሥት አካላት በተሰጡ መግለጫዎች ብቻ ላይ ተባለ እና ተገለጸ በሚል የተሠሩ ዜናዎች ናቸው።

ይህን ይዘን የወቅቱ ጋዜጠኝነት በአንዱ በኩል የተደፋበትን ውሃ በሌላ በኩል የሚተፋ ‘ትቦ’ ዓይነት የመንግሥት ዕለታዊ መዝገብ ነው? አልያም የሕዝብ ዘብ ጠያቂ ጋዜጠኝነት ነው እየተተገበረ ያለው የሚለውን እንመልከት።
ከየካቲት 5 እስከ የካቲተ 11/2011 ባለው በድረ-ገጽ እና በማኅበራዊ ትስሰር ፌስቡክ ገጹ ላይ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 121 የአገር ውስጥ ዜናዎችን ሲለጥፍ፤ ከእነዚህ ውስጥ የመንግሥት ሥራ የሚያትቱ ዜናዎች ማለትም መንግሥት ይህን አደረገ ይህ ሊደረግ ነው የሚሉ 82 ዜናዎች ናቸው።

በግሉ ዘርፍ እና ሌሎች ማኅበረሰቡ ትኩረት የጠየቀባቸው ጉዳዩች ዘገባ 23 ዜናዎች ሲያወጣ ከእነዚህም ውስጥ ሦስቱ ብቻ ፖለቲካ ነክ ዜና ናቸው። በማኅበራዊ ዘርፍ 11 ዜናዎች፣ ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዩች 9 እና 3 የስፖርት ዜናዎች አውጥቷል።
በቀጥታ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ስላደረጉት ንግግር እና ተግባር ያለ ምንም ጋዜጠኛዊ መጠየቅ የሚያትቱ 13 ዜናዎች የዘገበ ሲሆን በአጠቃላይ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በ5 ቀናት የአገር ውስጥ ዜና ዘገባዎቹ 78 ነጥብ 51 በመቶ የሚሆነውን ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባር እና ንግግር እንዲሁም ከመንግሥት የተሰጡ መግለጫዎችን ዘግቧል።

ወደ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት-ኢቲቪ ዜና ስንመጣ በአምስት ቀናት የአገር ውስጥ ዘገባው 105 ዜናዎችን ዘግቧል።

የመንግሥት ሥራ የሚያትቱ ዜናዎች ማለትም መንግሥት ይህን አደረገ ይህ ሊደረግ ነው የሚሉ 79 ዜናዎችን በድረ ገጹ እና በፌስቡክ ገጹ ለጥፏል፤ ዜናዎቹ ከመንግስት አካላት በተሰጡ መግለጫዎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው።
በቀጥታ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወይም ስላደረጉት ንግግር እና ተግባር ያለ ምንም የጋዜጠኛ መጠየቅ የሚያትቱ 9 ዜናዎች አውጥቷል።

በግሉ ዘርፍ እና ሌሎች ማኅበረሰቡ ትኩረት የጠየቀባቸው ጉዳዩች ዘገባ 17 ዜናዎች ሲለጥፍ ከእነዚህ መካከል ምንም ዓይነት ፖለቲካ ነክ ዜና የሌለ ሲሆን፤ 4ቱ ምጣኔ ሀብተወ ነክ፤ 9ኙ ማኅበራዊ ነክ እና 4ቱ ደግሞ ስፖርታዊ ጉዳዩች ናቸው።
ኢቲቪ ዜና በ5 ቀናት ከዘገባቸው ዜናዎች 83 ነጥብ 8 በመቶው ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባር እና ንግግር እንዲሁም ከመንግሥት የተሰጡ መግለጫዎችን ዘግቧል።

ወደ ግሉ መገናኛ ብዙኀን ስናልፍ ዛሚ 90 ነጥብ 7 ኤፍ ኤም ራዲዩ ጣቢያ ከላይ በተጠቀሰው የ5 ቀናት ጊዜ 27 ዜናዎችን ያወጣ ሲሆን የመንግሥት ሥራ የሚያትቱ ዜናዎች ማለትም መንግሥት ይህን አደረገ ይህ ሊደረግ ነው የሚሉ 19 ዜናዎችን ከእነዚህን ውስጥ 15ቱ በተለያዩ የመንግሥት አካላት በተሰጡ መግለጫዎች የተሠሩ ዜናዎች ሲሆኑ 2ቱ ብቻ በቀጥታ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ስላደረጉት ንግግር እና ተግባር ያለ ምንም የጋዜጠኛ መጠየቅ የተሠራ ነው።

በግሉ ዘርፍ እና ሌሎች ማኅበረሰቡ ትኩረት የጠየቀባቸው ጉዳዩች 8 ዘገባዎች ያወጣ ሲሆን ሦስቱ ኢኮኖሚያዊ፤ ሦስት ማኅበራዊ እና ሁለቱ የፖለቲካ ዘገባዎች ሲሆኑ ምንም ዓይነት ስፖርት ዘገባዎች አልነበረውም።

እንደ ዛሚ ላለ ለዐሥርት ዓመታት የቆየ እና የመንግሥትን ሥራዎች መሆን ካለበት መርህ አንጻር ለዓመታት ሲዘግብ ለቆየ መገናኛ ብዙኀን ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባራት አንድ ዘገባ ብቻ መዘገቡ እና አሁን በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ አሳሳቢነት እየተመለከተ ለኅብረተሰቡ የሚመለከተው ምልከታ የሚያሻው የጉዳዩች ዕይታ አለመስጠቱ መገናኛ ብዙኀኑ በፍርሀት አልያም በሌሎች ምክንያቶች እንደቀድሞው ከመዘገብ አቅቦታል የሚል ምልከታ አለኝ።

ዛሚ 90 ነጥብ 7 በ5 ቀናት ከዘገበው ዘገባ 70 ነጥብ 37 በመቶው በመንግሥት መሥሪያ ቤት የተሰጡ መግለጫዎች እና ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሠሩ ዜናዎች ናቸው።

በሌላ በኩል ወደ ሌላው ዐሥርት ዓመታትን ወዳስቆጠረው ራዲዮ ሸገር ኤፍ ኤም 102 ነጥብ 1 ስናልፍ ከላይ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ በ5 ቀናት 44 የአገር ውስጥ ዜናዎችን ሲለጥፍ ከእነዚህ ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ላይ ያተኮሩ እና የጋዜጠኝነት አመክንዩ ያልነበራቸው ተባለ እና ተገለጸ የሚሉ 34 ዜናዎች ሲሆኑ በግሉ ዘርፍ እና ሌሎች ማኅበረሰቡ ትኩረት የጠየቀባቸው ጉዳዩች 10 ዘገባዎችን ሰርቷል።

ከእነዚህ ውስጥ 2ቱ ፖለቲካዊ፤ 3ቱ ምጣኔ ሀብታዊ እና 5ቱ ማኅበራዊ ዘገባዎች ናቸው። በአጠቃላይ ሸገር 77 ነጥብ 27 በመቶው ዘገባው በመንግሥት መሥሪያ ቤት የተሰጡ መግለጫዎች እና ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሠሩ ዜናዎች ናቸው።

በአራቱም መገናኛ ብዙኀን እንደተመለከትነው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን በሰለጠነ የግንኙነት መንገድ ቢጠቀሙም አሁንም ከ2 ሺሕ ዓመታት በላይ ያለፈውን የነገሥታት ዕለታዊ ተግባራት ከሚዘግበው ‘አዋጅ ነጋሪ’ነት ያለፈ ሥራ እየሠሩ አይደለም። ይልቁንስ መንግሥት ሊነግረን የሚፈልገውን ሐተታ እያስተጋቡልን ነው።

ለዚህ ደግሞ በአሁን ወቅት ያለው የኢሕአዴግ መንግሥት የጣለው ድብቅ ወይም የአደባባይ ሽሽግ ገደብ ምክንያቱ ነው።
ለምሳሌ ኢ ኤን ኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ ከመዘጋቱ በፊት ከብሮድካስት ባለስልጣን ለጣቢያው የላከው ደብዳቤ በግርድፉ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይን የአዲስ አበባ የድጋፍ ሰልፍ በቀጥታ ስርጭት ለምን አላስተላለፋችሁም ማብራሪያ አቅርቡ ይላል።

እንደ እውነቱ ከሆነ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29፣ በፕሬስ ሕጉ መሰረት በብሮድካስት አዋጁ እንዲሁም በጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ መሰረት በየትኛውም ኢ ኤን ኤን እንደ አንድ ነጻ ሚዲያ አንድ ጉዳይ በቀጥታ ስላላስተላለፈ የሚዘጋበት ሕጋዊ አግባብ የለም፤ ነገር ግን ተዘግቷል። ይህ ደግሞ ለሌሎቹ ወይ አዋጅ ነጋሪ ሁኑ አልያም ዕጣ ፈንታው ይደርሳችኋል መልዕክት አስተላልፏል።

በጋዜጠኝነት ሳንሱር ኹለት ዓይነት ነው። ተቀዳሚው መንግሥት በመገናኛ ብዙኀን ላይ የሚጥለው ሳንሱር ሲሆን ይህ በአሁኑ ሕገ መንግሥት መሰረት የተከለከለ ነው።

ኹለተኛው ሳንሱር ጋዜጠኛው ወይም መገናኛ ብዙኀኑ በራሱ ላይ የሚያደርገው ሳንሱር ነው። ይህ ዓይነቱ ሳንሱር ሊደረግ ከሚችልባቸው ምክንያቶች የሚዲያው ኤዲቶሪያል ፖሊሲ፤ ጋዜጠኛው ሥራዬን አጣለሁ ሚዲያው እዘጋለሁ የሚል ፍርሀት፤ በሚዲያው ውስጥም ሆነ ውጪ ባለ አሉታዊ ግፊት ምክንያት፤ አስተዋዋቂዎችን የሚጎዳ ዘገባ ላለመሥራት ያለ የገቢ እጦት ፍርሀት፤ የስም ማጥፋት እና የግለሰብ ነጻነት ሕጎችን ተጋፍታችኋል በሚል የሚመጡ ክሶችን ላለመጋፈጥ፤ የተለያዩ የክስ ሒደቶች ውስጥ ላለመግባት እና አለቃቸውን ለማስደሰት ጋዜጠኛ ወይ ሚዲያ ራሱን ሳንሱር ከሚያደርግበት ምክንያች ተጠቃሾቹ ናቸው።

እዚህ ውስጥ በተጠቀሱት በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት በአሁን ወቅት መገናኛ ብዙኀኖቻችን የመንግሥት አፍ፤ የፕሮፓጋንዳ ማስተላለፊያ ትቦዎች ሆነዋል። በአንድ በኩል የተደፋባቸውን በሌላ መገልበጥ የጋዜጠኛ ሞራላቸው ያልፈቀደላቸው ደግሞ ሽሽት በሚመስል መልኩ ስለ መንግሥት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ትንፍሽ ከማለት ተቆጥበዋል።

ይህ የአሁኑ ኢሕአዴግ ተግባር ደግሞ ከደርግ እና ከአፄ ኃይለ ሥላሴ በጊዜያቸው በነበረው ጋዜጠኝነት ላይ ከጣሉት እገዳ ጋር የሚጋራው ብዙ ነገር አለ። የኹለቱንም የቀድሞ መንግሥታት እገዳዎች መመልከት እንችላለን።

አፄ ኃይለ ሥላሴ በዘመናቸው ካስቀመጡት እገዳ የአሁኑ መንግሥት ድብቅ እገዳዎች ጋር የሚመሳሰሉትን ብንመለከት ተቀዳሚው ንጉሠ ነገሥቱን እና ሕገ መንግሥታቸውን የሚቃረን ዘገባ ተከልክሎ እንደነበረ እናያለን።

አሁን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ተግባር የሚነቅፍ ዘገባ መጻፍ ወይም መዘገብ እንደ ሰላም እና ፍቅር፣ የአገር አንድነት ጠላት የሆነ ሚዲያ እንደሆነ በዘመቻ እንደሚያስነቅፈው ማለት ነው። ሕገ መንግሥቱን ይጣረሳል ብሎ አንድ አካል (ልክ እንደ ብሮድካስት ባለሥልጣን ኢ ኤን ኤን ቴሌቪዥን ጣቢያን መዝጋት ያለ ተግባር ) በወሰነው የዘገባ ጥፋት ሚዲያ እንደሚቀጣው ያለ ተግባር ማለት ነው።

በአጼው ዘመን ንጉሰ ነገስቱን እና አገዛዛቸውን ተቃውሞ የወጡ ሰልፎችን መዘገብ ክልክል ነበር። አሁንም ሚዲያዎቻችን የተከለከሉ ይመስል ግላጭ የሆኑ ተቃውሞዎችን እና ብጥብጦችን እንዳላዩ ሆነው እያለፉ ነው።

የመጨረሻ የንጉሱን እና የአሁኑን ዴሞክራሲያዊ መንግስት ተብዬ የሚያመሳስላቸው አንድ እገዳ ስናነሳ በአጼው ዘመን የሌሎች ውጪ ሀገራትን ፖሊሲ መንቀፍ የተከለከለ ነበር።

ታዲያ አሁንስ የትኛው መገናኛ ብዙሀን ነው በኢትዩጲያ የአሜሪካን አልያም የተባበሩት አረብ ኢምሬትስን መዘውር ፖሊሲያቸው ሀገራችንን ሊያጠፋ ነው ብሎ በዜና የነገረን?

ይህ መንግስት በጋዜጠኝነት ላይ የጣለውን ድብቅ ገደብ ከደርግ ይፋዊ ገደብም ጋር ልናነጻጽረው አንችላለን።
የደርግ ዘመን ጋዜጠኝነት የግል ሚዲያ የተፈቀደበት ስላልነበረ ዘገባዎች ዘግይተው ይወጡ የነበረ ሲሆን ሳንሱር ስለሚደረጉ ዜናዎቻቸው መንግስት ለህዝቡ ይህን አደረገ ይህን ፈጸመ የሚሉ መንግስትን የሚክቡ ነበሩ።

አሁን ሚዲያዎች በፍርሀት አልያም ምንነቱን ግልጽ ባላደረጉት ምክንያት ራሳቸውን ሳንሱር እያደረጉ ቀደም ሲል እንዳሳየሁትም ሚዛናዊ ያልሆነ መንግስት ይህን አለ ይህን አደረገ የሚል ዜናዎች እየሰበኩን ነው።

እንግዲህ ስንጀምር ስለ አውሮፓውያኑ ‹‹አክታ ዲዩርና›› የነገስታት እለታዊ ስራ መዝገብ እንዲሁም ‹‹አዋጅ ነጋሪ›› የኢትዩጲያ ነገስታት ህዝቡን እንዲያውቅ የሚፈልጉትን ነገር ብቻ ስለሚዘግቡበት ጥንታዊ ኋላቀር አመክንዩ እና መጠይቅ የሌለው ጋዜጠኝነት አንስተናል።

የአሁኑ የኢትዩጲያ ጋዜጠኝነት ምን ይመስላል ብለን ጠይቀናል። ያለው እውነታ እንደሚያሳየን ከሆነ የአሁኑ ጋዜጠኝነት አራተኛው የመንግስት ጠያቂ አካል ሳይሆን የመንግስት የህዝብ ግንኙነት እንደሆነ ነው።

ጽሁፌን በአንድ የአልበርት አንስታይን አባባል ልዝጋ‹‹ …አለማችን አደገኛ ቦታ ላይ የሆነችው ክፋትን እና ጥፋትን በሚፈበርኩት ምክንያት ብቻ ሳይሆን ይልቁንስ ጥፋቱን እየታዘቡ ዝምታን በመረጡት እና ምንም ለማድረግ ፈቃደኛ ባልሆኑትም ምክንያት ነው።››

ናርዶስ ዮሴፍ

በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በጋዜጠኝነት ሠርተዋል። በኢሜል አድራሻቸው nardosyoseph@gmail.com ሊገኙ ይቻላል።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here