ለኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን ይጠቅማታል?

0
876

የውስጥ ወይስ የውጭ ገበያ ነው የአንድ አገር የዕድገት መሰረት?

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን አለባት ወይም መሆን የለባትም በሚል የምጣኔ ሀብት ምሁራን የሐሳብ ሙግት እንደሚያደርጉ ይታወቃል። ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር) አንድ አገር የዓለም ዐቀፍ ድርጅት አባል ከመሆኑ በፊት ማሟላት የሚገባውን መስፈርቶች በመንተራስና የኢትየጵያን የምጣኔ ሀብት የዕድገት ደረጃን በመተንተን በባለፈው ሳምንት ጽሑፋቸው መከራከሪያ ነጥባቸውን ማስቀመጣቸው ይታወሳል። በዚህ ጽሑፋቸው የቀደመ አቋማቸውን በማጠናከር ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ከመሆኗ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ እራሷን ከውስጥ ማጠናከር አለባት፤ ወደ ውስጥ ያተኮረና ሕዝቡን ሊያሰባስብ የሚያስችልና ጥንካሬም የሚሰጠው የምጠኔ ሀብትና የማኅበራዊ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጉ ሊታለፍ የማይችል ጉዳይ ሲሉ ይሞግታሉ።

በአጠቃላይ ሲታይ የኅብረተሰብን ዕድገትና የሰውን ልጅ ሥልጣኔ በሚመለከት ከሦስት ሺሕ ዓመት ጀምሮ የዕውቀትን ምንጭ በተለያየ መልክ በተረጎሙና በሚተረጉሙ ፈላስፋዎች ዘንድ የጦፈ ክርክር ተካሒዷል። ይህ የተለያየ ፍልስፍናዊ አመለካከት ለተከታታዩ ተመራማሪ መሰረት በመሆን አንድ ኅብረተሰብ በምን መልክ ቢዋቀር ሰላምና መረጋጋት፣ እንዲሁም ብልጽግና ሊመጣ ይችላል በሚለው ላይ የጦፈ ክርክር በመካሔድ የኋላ ኋላ ለአውሮፓው ሕዝብ የኅብረ-ብሔር መመስረቻ ዘዴ መመሪያ ሊሆን ችሏል።

በዛሬው ወቅት በአገራችንም ሆነ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች አንድን ኅብረተሰብ ለመገንባት የሚደረገው ክርክር የተለያየ ዝንባሌ ባላቸው የየአገሩ ምሁራን ሳይሆን፣ የየአገሮች መንግሥታት ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፖሊሲዎች በሙሉ ከውጭ የመጡና በሕዝቡ ትከሻ ላይ የሚጫኑ ናቸው። በዚህም ምክንያት የተነሳ በእኛ ኢትዮጵያውያንም ሆነ በአብዛኛዎቹ አፍሪካ መንግሥታት ዘንድ ካላንዳች ክርክርና ምርምር ከውጭ የመጣን ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ እንደባሕል ተወስዷል። ከውስጥ በአንዳንድ ‘ክሪቲካል’ አመለካከት ባላቸው ምሁራን የተሻለ አስተያየት በሚቀርብበት ጊዜ የቀረበውን ሐሳብ እንዳልሰሙ በመጣል በዓለም ዐቀፍ ኮሙኒቲው የተደነገገው ፖሊሲ ተግባራዊ ይሆናል። እንደምናየው ውጤቱ የተወሳሰቡና በቀላሉ መፍትሔ ሊያገኙ የማይችሉ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊ፣ የሥነ-ልቦናና የባሕል ውድቀት ውስጥ ከቶናል።

በአውሮፓው ምድር የተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ወደ ኅብረ-ብሔር ከመሸጋገራቸው በፊት በመጀመሪያ ደረጃ ያካሒዱ የነበረው ትግል የማሰብ ኃይልን ወይም ንቃተ ህሊናን ማዳበር ነበር። ይህም ማለት በየአገሩ ያለው ሕዝብ ከባሕላዊና ለዕድገት ጠንቅ ከሆኑ አስተሳሰቦች በመላቀቅ ተፈጥሮን ለመቃኘትና በተፈጥሮ ውስጥ ያሉትን ነገሮች ለመለወጥ የሚያስችሉትን ዕውቀት ማግኘትና ንቃተ ህሊናውን ማዳበር ነበር። በዚህም መሰረት እያንዳንዱ ዜጋ ሰው መሆኑን በመገንዘብ ዕውነተኛ ነፃነቱን የሚያገኝበትንና ውስጣዊ ፍላጎቱን ተግባራዊ የሚያደርግበትን ሁኔታ ማዘጋጀት ነበር። በመሆኑም የምጣኔ ሀብት ጉዳይ ከፍተኛ አትኩሮ የተሰጠው ስለነበር አገርን በጸና መሰረት ላይ የመገንባቱ ጉዳይ ተቀዳሚውን ቦታ የያዘ ነበር። ስለሆነም አገሮች ወደ ህብረ ብሔር ሲሸጋገሩ መንግሥታት ምን ምን ነገሮች በቅደም ተከተል ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው በምሁራኑ ዘንድ የጦፈ ክርክር ይካሔድ ነበር።

የኋላ ኋላ ‘መርከንታሊዝም’ ወይም የውስጥ ገበያን ማሳደግና ኅብረተሰብን ማስተሳሰር ያስፈልጋል የሚለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተቀባይነት በማግኘት በተለያየ ጊዜያት በየአገሮች ውስጥ ይህ ፖሊሲ ተግባራዊ በመሆን አገሮች ቀስ በቀስ ግን ደግሞ በእርግጠኝነት ወደ ኅብረ ብሔር እንዲሸጋገር አስችሏቸዋል። ይሁንና የአውሮፓ አገሮችን ዕድገት ስንመለከት ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ በአንድ ጊዜ በሁሉም አገሮች በተመሳሳይ ደረጃ ተግባራዊ የሆነ አይደለም። በተለይም እስከ 19ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ እንግሊዝ በኢንዱስትሪና በውስጥ ገበያ ቀድማ የሔደች ስለነበረች ሌሎች አገሮች የእሷን ፈለግ እንዳይከተሉና በተለይም በውጭ ንግድና በተወሰኑ ምርቶች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ግፊት ታደርግ ነበር። በአዳም ስሚዝና በሬካርዶ የፈለቀው የነፃ ገበያ ቲዎሪና ዓለም ዐቀፋዊ የሥራ ክፍፍል ዋናው የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ መመሪያ እንዲሆንና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች እንዲቀበሉት ከፍተኛ ግፊት ይደረግ ነበር።

በፍልስፍናና በሳይንሳዊ ንድፈ ሐሳብ የገፉ አገሮች፣ ግን ደግሞ በቁስ አካላቸው (‘ማቴሪያል’) ሁኔታቸው ወደ ኋላ የቀሩ እንደ ጀርመን የመሳሰሉ አገሮች የእንግሊዝን የነፃ ንግድ ንድፈ ሐሳብ አሽቀንጥረው በመጣል ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተል ሁለት ትውልድ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። ለዚህ ዐይነቱ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ካበረከቱት ውስጥ ፍሪድሪሽ ሊስት የሚባለው ሁለገብ አዋቂ መጠቀስ የሚገባው ነው። በእሱ ትምህርት መሰረት አንድ በኢኮኖሚ ወደ ኋላ የቀረች አገር የእንግሊዝ ኢኮኖሚስቶች ያዳባሩትን የነፃ ንግድና የነፃ ገበያ ፖሊሲ ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነች ፖሊሲው እንግሊዝን ብቻ የሚጠቅም ነው። አንድ አገር በጥሬ ሀብት ማውጣትና በእርሻ ምርት ላይ ብቻ የምታተኩር ከሆነ በዚያው ቀጭጫ ትቀራለች። በተለያየ መልክ የሚገለጽ ምሁራዊ ኃይል ለመፍለቅ ስለማይችል ብሔራዊ ነፃነቷ ይገፈፋል። ስለሆነም ይላል ፍሪድሪሽ ሊስት፣ አንድ አገር የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን ከፈለገችና የውስጥ ገበያ እንዲያድግ የግዴታ ወደ ውስጥ ያተኮረ ፖሊሲ መከተል አለባት። ለዚህ ደግሞ ንቁ ኅብረተሰብ ክፍሎችን በማገዝና በኢንዱስትሪ ግንባታ እንዲሳተፉ በማድረግ የውስጥ ገበያን ማሳደግ ሊታለፍ የማይችል ጉዳይ ነው።

 

የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ከመሆኗ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ እራሷን ከውስጥ ማጠናከር አለባት

 

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይም በማደግ ያሉ ኢንዱስትሪዎች (Infant Industries) ከውጭ በሚመጣ ተመሳሳይ ምርት እንዳይጠቁና እንዳይፈራርሱ ከተፈለገ መንግሥት የግዴታ የእገዳ ፖሊሲ መከተል አለበት። በዚህ መልክ የኢንዱስትሪዎችን ዕድገት ማፋጠን ብቻ ሳይሆን ለፈጠራ ሥራ የሚያመች ሁኔታም ማዘጋጀት ይቻላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንግሥት ዋናው ተግባር የባቡር ሃዲዶችን፣ የ‘ካናል ሲሰትምን’፣ መንገዶችንና ከተማዎችን፣ እንዲሁም መንደሮችን በመገንባት ሕዝቡ እንደ ማኅበረሰብ በመሰባሰብ ውስጣዊ ኃይሉ እንዲጠነክር ማድረግ የኅብረ-ብሔር ግንባታ ዋናው መሰረተ ሐሳብ እንደሆነ በተለያዩ ምሁራን በመሰበክ ከንድፈ ሐሳብ አልፎ ተግባራዊ የሆነ ጉዳይ ነው። ይህንን መንገድ ያልተከተሉና የእንግሊዝን የነፃ ንግድ ምክር የተቀበሉ እንደ ፖርቹጋል የመሳሰሉ አገሮች ተግባራዊ ባደረጉት ፖሊሲ አማካይነት የተጠበቀውን ውጤት ባለማግኘታቸው በተለይም ገበሬው በረሃብ ሊጠቃ ችሏል። ምክንያቱም ገበሬው የእርሻ ምርቱን በመተው በወይን ምርት ላይ ብቻ እንዲረባረብ በመደረጉና፣ በጊዜው በዓለም ገበያ ላይ የወይን ምርት ጥያቄ እየደከመና የፖርቹጋል የውጭ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ በመናጋቱ ነው።

የውስጥ ገበያን ጥናካሬና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የመመስረትን ጉዳይ የኋላ ኋላ አሜሪካ፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ፣ በኋላ ደግሞ ቻይና የተከተሉትና ከፍተኛ ውጤትም ያገኙበት በመሆኑ ዛሬ የደረሱበት ደረጃ ያረጋግጣል። የቻይናን ጉዳይ ብንወሰድ በመጀመሪያ የውስጥ አደረጃጀት ጉዳይና ኅብረተሰብኣዊ ጥንካሬ መሰረቱ የተጣለው እ.አ.አ ከ1949 እስከ 1978 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። ከብዙ ውዝግብ በኋላ እነ ዴንግ ሲያዎፒንግ ባሸናፊነት ሲወጡና የገበያ ኢኮኖሚ የጥገና ለውጥ ሲያካሒዱ ዝም ብለው ገበያውን ለውጭ ተዋንያን ክፍት በማድረግ አልነበረም ዛሬ የደረሱበት ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት። በተለይም የኢንዱስትሪው፣ የእርሻውና የሚሊታሪው መስክ መሻሻል እንዳለበት በማመን በአንድ በኩል በዚህ ላይ ሲረባረቡ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከውጭ ቴክኖሎጂ ለማግኘት ሲሉ ለውጭ ኢንቬስተሮች ልዩ የመዋዕለ ነዋይ ቦታ በማዘጋጀት ቴክኖሎጂዎችን መቅዳትና የራሳቸው ማድረግ ነበር። በዚህ መሰረት ሰላሳ ዓመት ያህል ሙከራ ካደረጉና አንድ የዕድገት ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ እ.አ.አ በ2005 ቻይና የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በቃች። አሜሪካም ሆነ የአውሮፓው አንድነት ቻይና በቴክኖሎጂ ዕድገት መንጥቃ በመሄዷ በጣም ፈርተዋል። የሚያደርጉትን ሁሉ በማጣት ቻይና አምርታ ወደ አውሮፓው አንድነትና የአሜሪካ ገበያ ላይ በምትልከውና ከእነሱ ምርት ጋር በሚወዳደሩ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ለመጨመር እየጣሩ ነው። በአጭሩ እነዚህ ሁሉ አገሮች ከውስጥ ገበያቸውን በደንብ ሳያደራጁና ኅብረተሰባቸውን በፀና መሰረት ላይ ሳያቆሙ የግዴታ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንሁን ብለው በፍጹም አልተጣደፉም።

ከዚህ አጭር ሀተታና ኢምፔሪካል ማስረጃ ስንነሳ አገራችን የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ከመሆኗ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ እራሷን ከውስጥ ማጠናከር አለባት። ወደ ውስጥ ያተኮረና ሕዝቡን ሊያሰባስብ የሚያስችልና ጥንካሬም የሚሰጠው የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጉ ሊታለፍ የማይችል ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው አንድ ቦክሰኛምም ሆነ አንድ አገር ተፎካካሪዎቻቸውንና ጠላቶቻቸውን በደንብ ሊቋቋሙና በአሸናፊነት ሊወጡ የሚችሉት በመጀመሪይ ራሳቸውን ሲያዘጋጁና ጥንካሬ ሲያገኙ ብቻ ነው። ቦክሰኛው ካለአቅሙ በክብደትም ሆነ በጥንካሬ ከሚበልጠው ጋር ዝም ብሎ የውድድር መረብ ውስጥ ገብተን እንታገል አይልም። አቅሙን ማወቅ አለበት። አንድ አገርም እንዳትወረር ከተፈለገ በደንብ የተደራጀና የተማረ የወታደር ኃይል ያስፈልጋታል። ለዚህ ደግሞ የግዴታ ሰፋ ያለ ምጣኔ ሀብታዊ መሰረት በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ከመሆኑ በፊት ትግል እናድርግ ማለት ራስን ለጠላት አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል።

ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር) የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው fekadubekele@gmx.de ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here